www.maledatimes.com በውኑ የቤተክርስቲያኔ ጉዳይ እኔንስ አያገባኝ ይሆን?የተማፅኖ ደብዳቤ(፪) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

በውኑ የቤተክርስቲያኔ ጉዳይ እኔንስ አያገባኝ ይሆን?የተማፅኖ ደብዳቤ(፪)

By   /   January 6, 2013  /   Comments Off on በውኑ የቤተክርስቲያኔ ጉዳይ እኔንስ አያገባኝ ይሆን?የተማፅኖ ደብዳቤ(፪)

    Print       Email
0 0
Read Time:19 Minute, 30 Second

የተማፅኖ ደብዳቤ(፪)

ለብፁዕ አቡነ ሳሙዔል፣ ለብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ ለብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ ለብፁዕ አቡነ ቀለሜንጦስ፣ ለብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ለብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ እንዲሁም ለሚመለከታችሁ ሁሉ፤

አዲስ አበባ/ ኢትዮጵያ

በውኑ የቤተክርስቲያኔ ጉዳይ እኔንስ አያገባኝ ይሆን?

ከሁሉም አስቀድሜ ልጁ እንድሆን ፀጋውን ያደለኝና ለነገሮቼ ሁሉ መትባት ያለዋጋ የፈቀደውን ቸሩ ፈጣሪዬ፣ ኃያሉ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ እንዲሁም እናቱና እናቴን ተወዳጇን ድንግል ማርያምን አመሰግናለሁ፡፡ ያለ እርሷ በከንቱ የምባዝን መፃተኛ መሆኔን በተረዳ ነገር አውቄዋለሁና፡፡

ብጹዓን አባቶቼ!

እኔ እጅግ ባልገባኝና ባልተገባኝ ነገር ውስጥ ገብቼ በከንቱ የምናውዝ ነገርግን እግዚአብሔር ባወቀ በልቤ የተረዳሁትን ነገር ሳልናገረው ብቀር ለፀፀት እንዳይዳርገኝ የፈራሁት ከንቱ ሃሳቤ አስጨንቆኛልና እነሆ ዛሬ ለእናንተ ልናዘዘው የተዳፈርኩ የምድር ድውይ የሆንኩ ልጃችሁ ወልደአረጋዊ የጣፍኩላችሁን መልዕክት የገደፍኩትን አሟልታችሁ፣ ያወላገድኩትን አቃንታችሁ፣ ያቆረፈድኩትን አለስልሳችሁ ትረዱልኝ ዘንድ በህያው በእግዚአብሔር ስም እጫማቹህ ስር ወድቄ እማጠናለሁ፡፡

እግዚአብሔር ባወቀ እውነተኛውን የልቤን ሃሳብ ያመላክትልኝ፡፡ አሜን!

፩ኛ እርቀ ሰላሙን በተመለከተ

ብጹዓን አባቶቼ!

አባታችን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ (ነብሳቸውን ይማርና) በህይዎተ ስጋ በነበሩበት ዘመን ቤተክርስቲያናችን ተዳከመች፣ እግዚአብሔር ተረስቶ ዘርና ገንዘብ ተመለከ፣ እምነታችን ተበረዘ፣ መንጋው ተበተነ፣ ተኩላው በረታ፣ ወዘተ በማለት ስትጋደሉ በነበረበት በእነዚያ የጭንቅ ዓመታት ለእናንተ የነበረን አክብሮትና አድናቆት ወደር አልነበረውም፡፡ እኛም ልጆቻችሁ ቤተክርስቲያናችን እውነተኛ አባቶች ደረሱላት በማለት ከጎናችሁ በመቆም በተለይም ከወደ “አንጋሹ” ይመጣ የነበረው እንግልትና ጉሸማ እንዳያናውፅብን በመስጋት በውስጥም በውጭም የምንገኝ ልጆቻችሁ በአንድነት ድጋፋችንን ለማድረግ ሞክረናል፡፡ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይድረሰውና እነሆ እስከ ዛሬ በዚያ መልካም ተጋድሏቹህ እኛ ልጆቻችሁ በእውነት ኮርተናል፡፡

እነሆ ዛሬ ደግሞ ከእርሳቸው ህልፈት በኃላ ሌላ ታሪካዊ ፈተና በቤተክርስቲያናችን ላይ አንዣብቧል፡፡ ይህን ፈተና በድል ከተወጣን የከረመውን መለያየት የሚያርምና መጭውንም ትውልዶች ጭምር የሚያኮራ ሲሆን፤ በአንፃሩ ከተጓዝን ደግሞ ወደ ከፋ መለያየት የሚወስደንና መጪውን ዘመን እንድንፈራው የሚያደርግ፣ ትውልዱንም የሚያስጨንቅ ክፉ ዘመን ይሆናል ብዬ እሰጋለሁ፡፡

ታዲያ ከሰሞኑ ወደ እናንተ መንደር የሚሰማው “ነገር” ሁሉ አሁን ለገጠመን ታሪካዊ ፈተና የሚመጥን አልመስልህ ቢለኝ ነው “አቤት” ማለቴ፡፡ እኮ ዛሬ ምን ተገኘና ነው ያ መልካም ስማችሁ የተገላቢጦሽ ያሳቅቀን የጀመረው? ትላንት በአቡነ ጳውሎስ ዘመን “ቅድሚያ ለእርቅ” ባዮች እናንተ እንዳልነበራችሁ ሁሉ ዛሬ ላይ “ቅድሚያ ለምርጫ” ማለትን ምን አመጣው? ጉዳዩን የሌላ አያስመስልባችሁም ትላላችሁ? ያን የቀደመውን አኩሪ ተጋድሏችሁን ጥላሸት ባትቀቡት አይሻልም? እኛም ልጆቻችሁን ባታሳፍሩንና ባትለያዩን አይሻልም?

መቸም ቢሆን ያ ወንበር የመንፈስ ቅዱስ ነውና ድልድሉን ለእርሱ ተዉለት፡፡ እናንተ አማናዊውን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሆነውን መንጋችሁን ሰብስቡን፤ እኛን አንድ አድርጉን፣ የጥል ግድግዳውን ናዱልን፤ ቅድሚያ ለሰላም፣ ቅድሚያ ለፍቅር፣ ቅድሚያ ለአንድነትና፣ ለእርቅ አድርጉልን ከዚያም ሌላው …

ስለገጠመን ፈተና እናንት አባቶቻችን ከእኛ ከምዕመናን የተሻለ መረጃ ይኖራችሁ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እናንተ በአቡነ ጳውሎስ የፕትርክና ዘመን የተሾማችሁ ከመሆናችሁ አንፃር በወቅቱ አቡነ መርቆሪዎስ በምን ሁኔታ እንደወረዱ በጉባኤ ተገኝታችሁ ያያችሁ የአይን እማኞች ልትሆኑ የምትችሉ አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም በወቅቱ የነበሩት አባቶች “እውነቱን” ያውቃሉና ቢያሻቸው ተወቃቅሰው፣ ከቻሉም ተላቅሰው ሰላምና እርቅ ያወርዱ ዘንድ እርዷቸው እንጂ “ቅድሚያ ለምርጫ” እያለችሁ ፈተና አትሁኑባቸው፡፡ ቢቻላችሁስ ሁሉም አባቶች በዚያ ክፉ ዘመን በጋራ ለሰሩት በደል በጋራ ኃላፊነት እንዲወስዱና የጥል ግድግዳውን ለአንዴና ለመጨረሻ ይንዱት ዘንድ እድሉን አመቻቹላቸው፡፡ ያኔ የተባባሉትን እነርሱና እግዚአብሔር ያውቃሉና!

“ቅድሚያ ለምርጫ” የሚለው ጩሃት በእናንተ መንደር እንዲህ የበረከተው ምን አልባትም ከ“አንጋሹ” ክፍል መንበሩን እነሆኝ ተብላችሁ ይሆናል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስን ከመንበራቸው ለማውረድና ችግሩ ስር ሳይሰድ ወደቦታቸው ላለመመለስ እጅግ የተጉት የገዛ ወንድሞቻቸው እንደነበሩና “መንበሩም” በ“አንጋሹ” “ቃል” ተገብቶላቸው እንደነበር ዛሬ ዛሬ ፀሐይ የሞቀው እውነት ሆኗል፡፡ በዚህም የአባቶቻችን ድርጊትና ብሎም በቅዱስነታቸው መሰደድ ገፈቱ የተረፈን ልጆቻቸው እጅግ አዝነናል አፍረናልም፡፡ “አንጋሹ” ግን የሚበጀውን ያውቅ ኖሯልና እነርሱን እንደህፃን አቁለጭልጮና ከድቶ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን “ጉብ” አደረገባቸው፡፡ እነሱም በተራቸው ተሳደዱ፡፡ ይባስ ብሎ ከመካከላቸውም በወጡበት የቀሩም የሚቀሩም አይጠፉም፡፡ እናም እኔ መፃተኛው ልጃችሁ ግን በፍፁም እንዳትስቱ አደራ ተጠንቀቁ እላለሁ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔርን እንጂ “አንጋሹ”ን ማመን ከንቱ ነውና፡፡ ይልቁንስ እንደ አምና ካቻምናው ዛሬም “ቅድሚያ ለእርቅ”!

ምን አልባት ብዙዎቻችሁ እዚህ በነበራችሁበት ጊዜ ውጭ ሃገር ባለው የቤተክርስቲያን አስተዳደርና ስርዓት ተስፋ እንደ ቆርጣችሁ እና እዚህም ያለው መወነጋገር የማይስተካከከል እንደሚመስላችሁ በወቅቱ ለልጆቻችሁ እንዳጫወታችሁን እናስታውሳለን፡፡ በዚህም የተነሳ እዚህ በስደት ያለችውን የቤተክርስቲያናችሁን ጉዳይ “በይደር” እንድትይዙትና ወደ “ምርጫው” እንድታደሉ ገፍቷችሁ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይህ ውንግርግር በአስተዳደራዊ ጥበብ የሚፈታና ወቅቱም ሲደርስ ለምዕመኑ የምታሸክሙት እዳ ይመስለኛል፡፡ አብዛኛው ችግሮች በሙያው በተሰማሩ አካላት በኩል የሚፈቱ በመሆናቸው “እዳው ገብስ ነው” ብለን ለዛሬ እንለፈው፡፡ አሁን እናንተ አባቶቻችን  በቅድሚያ የአንድነታችንን ጉዳይ፣ የሰላሙን ጉዳይ፣ የፍቅሩን ጉዳይ፣ የእርቁን ጉዳይ  አብጁልን፡፡ አሁንም “እርቁ ይቅደም!”

፪ኛ የ“ምርጫ” ህጉን በተመለከተ

ብጹዓን አባቶቼ!

ሀ) አበው መነኮሳትን በፓትርያርክ ምርጫ ውስጥ በዕጩነት ስለማካተት

ዛሬ ምን አልባት የዓለማዊውን ትምህርትና የአስተዳደር ዘርፉን በከፍተኛ ደረጃ የተማሩና የተረዱ መነኮሳት በገዳም አይኖርም ብላችሁ  ይሆናል፡፡ ወይም እነዚህ አባቶች የየዘመኑን ቢሮክራሲ ላይረዱት ይችሉ ይሆናል በማለትም ይሆናል፡፡ ነገር ግን ዛሬ እስከ ፒ.ኤች.ዲ  ድረስ የተማሩና እየተማሩ የሚገኙ መነኮሳት በውጭ ሃገራትና በየከተማው እንዳሉን ይታወቃል፡፡ የየገዳማቱንስ አቅም ማን ይውቃል? የነገይቱንስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መነኮሳት አቅምና ችሎታ እንዴት አሻግረን አንመለከትም? ወይስ ዛሬ ማስተካከል ሲቻል ለዚህ ተብሎ ነገ ደግሞ አዲስ የ“ምርጫ ህግ” ሊወጣ ይሆን? አርቆ ማስተዋል የጎደለው የሚመስልና አሁን በተለይም ጥቂቶቹን ለማስመረጥ የተዘጋጀ ይመስላልና በቅርቡ ተዘጋጀ የተባለው የ“ምርጫ ህግ” “መነኮሳትን ጭምር እንዲያካትት” ሆኖ ቢዘጋጅና ባይሆን ትጋታችሁ ምን አይነት መነኮሳት ለምርጫ ይቅረቡ? በሚለው ላይ ቢሆን የሚበጅ ይመስለኛል፡፡

ለ) የሚመራንን አባት በ“ዕጣ” ስለመለየት

እኛ ልጆቻችሁ እስከዛሬ ከእግራችሁ ስር እየዳህን ከተማርናቸው ታላላቅ ቁምነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ነገር በህይዎታችንና በውሳኔውቻችን ሁሉ ቅዱሱን የእግዚአብሔር መንፈስ ስራ እንዲሰራልን ከሁሉ አስቀድመን እድል መስጠትን ነው፡፡ ይህንንም እውነት በህይዎታችሁ ተርጉማችሁ ስታሳዩን ኖራችኃል፡፡ ታዲያ ስለምን ታላቁን አባት ለማግኘት የሚደረገውን ምርጫ በደካማው የሰው ልጅ ስጋና ደም ላይ እንዲደገፍ ፈረዳችሁበት? ለምንስ የመንፈስ ቅዱስን ዳኝነት ቸል አላችሁት? እንዴትስ በሰሞኑ የግብፆች ምርጫ ላይ ተከሰተ የተባለውን የአፈፃፀም ጉድለት እንደ አመንክዮ ማንሳትን ወደዳችሁ? ይህ በአናንት ዘንድ ሊደረግ አይገባምና ፍፁም አለማዊ የሆነውን ለተለያዩ ትችቶች፣ ጥርጣሬዎችና፣ ውዝግቦች እድል የሚከፍተውን “በስጋና በደም” ለይ የተንጠለጠለውን የምርጫ መንገድ ከወዲሁ ብትከሉትና የመጨረሻውን የመለያ መንገድ በ“ዕጣ” ብታደርጉት መልካም ይመስለኛል፡፡

ሐ) በስደት የሚገኙ አባቶችን በ“ምርጫው” ስለማካተት

በስደት የሚገኙት አባቶች ሃሳብና ስምምነት በምርጫ ህጉ ውስጥ እንዲካተት ቢደረግ እጅግ ማስተዋል የታከለበት ይመስለኛል፡፡ ማን ያውቃል? ቀጣዩ ምርጫ ሁላችሁም በአንድነት ለአንድ አላማ የምትሳተፍበት ይሆናልና ነው፡፡

በመጨረሻም እኔ ደካማና አላዋቂ ነኝ፡፡ የተሰማኝን፣ እውነት ነው ያልኩትንና፣ ያመንኩበትን ሁሉ በቅንነትና በእውነት በዝርዝር ለማስፈር ሞክሪያለሁ፡፡ እናም በዚህ ተማፅኖ ውስጥ ያለዕውቀት በስህተት ካጠፍሁና ካስቀየምኩ ሁሉችሁንም ከወዲሁ በህያው በእግዚአብሔር ስም በደሌን ሁሉ ይቅር ትሉኝ ዘንድ እኔ ወልደአረጋዊ ተማፅኛቹሃለሁ፡፡

እግዚአብሔር አምላክ የምህረት ፊቱን ከተቅባዝባዥ ልጆቹ ላይ አይመልስብን!

እግዚአብሔር ይስጥልኝ! (ታህሳስ 29, 2005 ዓ.ም)

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on January 6, 2013
  • By:
  • Last Modified: January 6, 2013 @ 11:00 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar