www.maledatimes.com እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኀኒት ተወልዶላችኋል ሉቃ.2፥11 (መጋቤ ብሉይ አእምሮ ዘውዴ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኀኒት ተወልዶላችኋል ሉቃ.2፥11 (መጋቤ ብሉይ አእምሮ ዘውዴ)

By   /   January 7, 2013  /   Comments Off on እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኀኒት ተወልዶላችኋል ሉቃ.2፥11 (መጋቤ ብሉይ አእምሮ ዘውዴ)

    Print       Email
0 0
Read Time:16 Minute, 47 Second
እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኀኒት ተወልዶላችኋል ሉቃ.2፥11 ማለዳ ታይምስ መረጃ ማእከል ለክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ይላል ፡፡
ታኅሣሥ 27 ቀን 2005 ዓ.ም.

መጋቤ ብሉይ አእምሮ ዘውዴ

እንኳን ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡

 

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ  አይደለም፡፡ ከጥንት ከመሠረት ጀምሮ በመላእክት፤ በነቢያት  ሲነገር፤ ሲሰበክ የመጣ ነው እንጂ፡፡ ማቴ.1፥18፡፡

 

ሰው የመሆኑን ምሥጢር ለመጀመሪያ ጊዜ በማእከለ ገነት የተናገረ እርሱ እግዚአብሔር ነው፡፡

yeledeteአባታችን አዳም ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ወጥቶ ዕፀ በለስን በልቶ ከጸጋ እግዚአብሔር በተራቆተ ጊዜ /አዳም ኮነ ከመ አሐዱ እምኔነ/ አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ ዘፍ.3፥22 ብሎ ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው እንደሚሆን ተናግሯል፡፡ በዚህ ቃል መሠረት /መሪነት/ ቅዱሳን መላእክት ምሥጢረ ትንቢት ተገልጾላቸዋል፡፡ እነሱም የተገለጸላቸውን ምሥጢረ ትንቢት ኀላፍያትንና መጻእያትን ለሚናገሩ ነቢያት ነግረዋቸዋል፡፡ ቅዱሳን ነቢያትም ከእግዚአብሔር ያገኙትን ከመላእክት የሰሙትን መነሻ አድርገው በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ምሳሌያት በተለያዩ ዘመናት የወልደ እግዚአብሔርን ሥጋዌ ሰብከዋል /ገልጸዋል/ ዕብ.1፥1፡፡ ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፡፡

የጌታችን ልደት በትንቢተ ነቢያት

ከዓበይት ነቢያት መካከል አንዱ የሆነው ነብየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ የሚከተለውን ትንቢት ተናግሯል፡፡

እነሆ ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች ኢሳ.7፥14፣ ሕዝ.44፥1/ ፡፡ በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና የተወልደው አማኑኤል ጌታ ነው፡፡ ትርጉሙም  እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ ማለት ነው፡፡ነቢዩ  በጎላና በተረዳ ነገር “ሕፃን ተወልዶልናል ወልድም ተሰጥቶናል አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፡ ስሙም ድንቅ መካር ኀያል አምላክ የዘለዓለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል“ በማለት የሚወለደው ሕፃን የባሕርይ አምላክ የዘለዓለም አባት የሰላም አለቃ ሥልጣን የባሕርይ ገንዘቡ እንደሆነ እና ለሥልጣኑም ወሰን ድንበር እንደሌለው ተናግሯል፡፡

 

ከደቂቀ ነቢያት መካከል አንዱ ሚክያስም በቤተልሔም ስለመወለዱ፡-

  • የኤፍራታ ምድር አንቺ ቤተልሔም ከይሁዳ አለቆች ከቶ አታንሽም ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ ንጉሥ ከአንቺ ይወጣልና ሚክ.5፥2፣ ማቴ.2፥6/ ብሏል፡፡
  • ነቢየ እግዚብሔር ቅዱስ ዳዊትም እነሆ በኤፍራታ ሰማነው ዛፍ በበዛበትም ቦታ አገኘነው እንግዲህስ ወደ እግዚአብሔር ማደሪዎች እንገባለን ብሎ የወመለዱን ምሥጢር ተናግሯል መዝ.131፥6
  • ነቢዩ ዕንባቆምም አቤቱ ድምፅህን ሰምቼ ፈራሁ ሥራህንም ዐይቼ አደነቅሁ በሁለት እንስሶች መካከል አየሁህ ዘመኑ እንደደረሰ አድርጌ አውቅህአለሁ ዘመኑም በደረሰ ጊዜ ተገለጥክ ብሎ በቤተልሔም በረት በተወለደ ጊዜ አድግና ላኅም እስትንፋሳቸውን እንደሚገብሩለት ዕንባቆም 3፥1 ተናግሯል፡፡

 

christmas 1ከዚህ በኋላ የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስ እግዚአብሔር መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ወደ ድንግል ማርያም በመላክ አብሥሯታል፡፡ “ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ።እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል” በማለት፡፡ ሉቃ. 1፡32

 

እመቤታችንም በብዙ ኅብረ አምሳል ትንቢት ሲነገርለት፤ ምሳሌ ሲመሰልለት፤ ሱባኤ ሲቆጠርለት የነበረውን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በቤተልሔም ግርግም /ዋሻ/ ወለደችው፡፡

 

ይህንንም ብስራት በቤተልሔም ዋሻ መንጋቸውን ነቅተውና ተግተው ይጠብቁ ለነበሩ እረኞች መጋቤ ሐዲስ አብሣሬ ትስብዕት ቅዱስ ገብርኤል ፤ እነሆ ዛሬ መድኀኒት በዳዊት ከተማ ተወልዶላችኋል ይኸውም ቡሩክ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሚያርቅ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚያድል ከዓለም በፊት ንጉሥ የነበረ ዛሬም ከዳዊት ባሕርይ /ዘር/ በቤተልሔም ዋሻ ዓለምን ለማዳን የተወለደ የዳዊት ልጅ ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ተወለደ ሲል አበሰራቸው፡፡ መዝ.73፥12

 

የጌታችንን ልደት ስናነሣ ሁለት ልደታት እንዳሉት እናምናለን፡፡ እኒሁም ልደታት /ልደት ቀደሚዊና/ /ልደት ደኃራዊ/ ናቸው፡፡

ልደት ቀዳማዊ፡ ቅድመ ዓለም ከአብ አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእም ባሕርይ ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት የተወለደው ልደት ሲሆን /ነቢዩ ዳዊት እንዲህ ይገልጸዋል፡፡ ወለድኩከ እምከርሥ እምቅድመ ኮከበ ጽ    ባህ መዝ.109፥3 ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ወለድኩህ ፤አንተ ልጄ ነህ እኔም ዛሬ ወለድኩህ መዝ.2፥7

 

ልደት ደኃራዊ ፤ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈፀም በሀሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ እንዲል ቃሉ፡፡ ቅድስት ድንግል ከምትሆን ከእመቤታችን እንበለ ዘርዓ ብዕሲ ያለ አባት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም የተወለደው ልደት ነው፡፡

 

ቀዳማዊ ልደቱ ጥንትና ፍጻሜ የሌለው የማይመረመር ስለሆነ ቀዳማዊ ልደቱን ለመግለፅ ቅድመ ዓለም ያለ እናት ከአብ እንደ ተወለደ ድኅረ ዓለምም ከእመቤታችን /እንበለ ዘርዓ ብዕሲ/ ያለ አባት ተወለደ፡፡ እሱም እመቤታችን ያለ አባት የወለደችው ፤ እግዚአብሔርም ያለ እናት የወለደው ወልድ ዋሕድ ኢየሱስ ክርስቶስ

 

በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ሰባቱ መስተጻርራን /ተቃራኒ ነገሮች አንድ ሆነዋል

ሕዝብና አሕዛብ፤ በጠብና በክርክር ይፈላለጉ የነበሩ ሕዝብና አሕዛብ በጌታችን ልደት ታርቀዋል፡፡ ይኸውም ሊታወቅ ከዚህ አስቀድሞ ቤተ መቅደሱን ለማፍረስ ንዋየ ቅድሳቱን ለመዝረፍ ሕዝቡን ለመማረክ ምታ ነገሪት ብለው ይመጡ የነበሩ  የሩቅ ምስራቅ /የፋርስ የባቢሎን ሰዎች በጌታችን ልደት ምክንያት ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ አይቴ ሀሎ ዘተወልደ ንጉሠ አይሁድ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው ማቴ.2፥4 እያሉ መጥተው ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤ ገብረውለታል፡፡

 

ነፍስና ሥጋ፡- በሲዖልና በመቃብር ተለያይተው የነበሩ ነፍስና ሥጋ ከእመቤታችን ከነፍሷ ነፍስ ከሥጋዋ ሥጋ ነሥቶ በተዋሕዶ ሰው በሆነ ጊዜ ነፍስና ሥጋን አስታርቋል፡፡

 

ሰውና እግዚአብሔር፡- አባታችን አዳም አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስ በልቶ የሰውና የእግዚአብሔር የፍቅር ግንኙነት ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ተቋርጦ ነበርና ጌታችን የሰውን ሥጋ ተዋሕዶ በተወለደ ጊዜ እርቀ ሰላም ተገኝቷል፡፡

 

ሰውና መላእክት፡- አባታችን አዳም ከእግዚአብሔር ጋር በተጣላ ጊዜ ቅዱሳን መላእክትም ስለተጣሉት በምትገለባበጥ ሰይፈ እሳት አስፈራርተው ከገነት ከአስወጡት በኋላ ወደ ገነትም እንዳይገባ ገነትን ይጠብቁ ነበር፡፡ ጌታችን በተወለደ ጊዜ አንድ ሆነው ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ ይኸውም ዮም አሐደ መርኤተ ኮኑ መላእክት ወሰብእ ከመ ይሰብህዎ ለክርስቶስ እንዲል፡፡ ሰውና መላእክት ክርስቶስን ለማመስገን አንድ ሆኑ  እንዳለ ሊቁ፡፡

 

ቤተ ክርስቲያን፤ ጌታችን የተወለደባት እና ሰባቱ መስተጻርራን አንድ የሆኑባት፤ ሰውና መላእክት የዘመሩባት የብርሃን ጎርፍ የጎረፈባት እንስሳት እስትንፋሳቸውን የገበሩባት ቤተልሔም በቤተ ክርስቲያን ትመሰላለች፡፡

 

ቤተልሔም፡- ተለያይተው የነበሩ ሕዝብና አሕዛብ ፤ሰውና እግዚአብሔር፤ ነፍስና ሥጋ ፤ሰውና መላእክት አንድ ሆነው በቤተልሔም እንደዘመሩ ዛሬም የፍቅር ተምሳሌትና የአማኞች ሁሉ እናት በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በዘር፣ በጎሣ፣ በጥቅም፣ በሥልጣን ሳንከፋፈል አንዲት ቤተ ክርስቲያንን በፍቅር እንድናገለግል በቤተልሔም የተደረገው የልደቱ ምሥጢር ይህን ያስተምረናል፡፡

ክርስቲያኖች የጌታን መወለድ የምናስበው በዚህ መንፈስ ነው፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on January 7, 2013
  • By:
  • Last Modified: January 7, 2013 @ 12:02 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar