www.maledatimes.com የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ የተቃወሙት ዋና ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ አቀረቡ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ የተቃወሙት ዋና ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ አቀረቡ

By   /   January 18, 2013  /   Comments Off on የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ የተቃወሙት ዋና ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ አቀረቡ

    Print       Email
0 0
Read Time:17 Minute, 15 Second
  • ‹‹ማንንም አሿሿሚ አይደለሁም፤ የሥልጣን ጥመኞችን አላገለግልም››Ab Hizkiel

የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ከሐላፊነት የመልቀቂያ ደብዳቤ ለዐቃቤ መንበሩ ማቅረባቸው ተሰማ፡፡ ብፁዕ ዋና ጸሐፊው ከሓላፊነታቸው ለመልቀቅ የወሰኑትና ከሐላፊነት የመልቀቂያ ደብዳቤ ያቀረቡት ከጥር 6 – 8 ቀን የቆየው የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንደተጠናቀቀ መኾኑ ተገልጧል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ከሐላፊነታቸው እንዲለቁ ለውሳኔ ያበቋቸው ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች እንዳሉ የዜናው ምንጮች አስረድተዋል፡፡ የመጀመሪያው÷ ቅዱስ ሲኖዶሱ በዐራተኛው ፓትርያሪክ ላይ ስላለው አቋም፣ ዕርቀ ሰላሙንና የፓትርያሪክ ምርጫውን አስመልክቶ በትላንትናው ዕለት ያሳለፈው ባለሦሰት ነጥብ ውሳኔና ውሳኔውን ተከትሎ ጋዜጣዊ መግለጫ የተሰጠበት መንገድ ነው፡፡

ውሳኔውን አስመልክቶ ዋና ጸሐፊው ያላቸው ልዩነት፣ ‹‹በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙት አባቶች ጋራ የተጀመረው የዕርቅና የሰላም ሂደት የጊዜ ገደብ ተሰጥቶት፣ ፍጻሜውን አይተን በውጭ በስደት የሚገኙት አባቶች ወደ አገራቸው ተመልሰው ምርጫውን በሰላም እናካሂድ›› የሚል ነው፡፡ ይህ አቋም የዕርቀ ሰላም ልኡካኑ በተለይም ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ከእርሳቸውም ጋራ ብፁዕ አቡነ ሉቃስም በከፍተኛ ደረጃ የተሟገቱለት እንደነበር ነው የተገለጸው፡፡

በመጨረሻም ‹‹ጥሪ አድርገንና የጊዜ ገደብ ሰጥተን ምላሻቸውን እንጠባበቅ፤ አዎንታዊ መልስ ከተገኘ እሰየኹ፤ የሰላም ጉባኤው ተካሂዶ ዕርቁ ተፈጽሞ አብረን እንመርጣለን፤ ካልተገኘ ደግሞ በመልሱ ቅ/ሲኖዶስ ይነጋገርበት›› በሚል መንፈስ በረቂቅ የቀረበው መግለጫ እንዲታረም ስምምነት ተደርሶ የነበረ ቢኾንም መግለጫው አድሮ ሲመጣ ከቀድሞው ይዘቱ ብዙ ሳይለወጥና እርማቱን ሳያካትት ነበር የቀረበው፡፡ አካሄዱ ክፉኛ ያስቆጣቸው ብፁዕ ዋና ጸሐፊው÷ ከስብሰባው መጠናቀቅ አንድ ቀን በፊት ስብሰባውን ትተው የወጡ ሲኾን መግለጫው በተሰጠበት ቀንም ‹‹አሁን ባለው የአሠራር ኹኔታ ለመቀጠል ያስቸግረኛል፤ ማንንም አሿሿሚ አይደለሁም፤ የሥልጣን ጥመኞችን አላገለግልም፤›› በማለት በአቋማቸው ከመጽናታቸውም በላይ ከዋና ጸሐፊነት ሓላፊነታቸው ለመልቀቅ መወሰናቸው ታውቋል፡፡

ሌላው ጋዜጠኞች የተጠሩበትና ጋዜጣዊ መግለጫ የተሰጠበት መንገድ በሕገ ቤተ  ክርስቲያን ለብፁዕ ዋና ጸሐፊው ከተሰጠው ሥልጣንና ከተለመደው አሠራር መለየቱ ነው፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 25 ንኡስ አንቀጽ 3 መሠረት÷ ቅ/ሲኖዶስ የሚሰጠውን ትእዛዝና ውሳኔ ለጠቅላይ ቤተ ክህነትና ለሚመለከተው ሁሉ የማስተላለፍ ሥልጣንና ተግባር የብፁዕ ዋና ጸሐፊው ነው፡፡ የቅ/ሲኖዶሱን ማኅተምና ልዩ ልዩ ሰነዶች የሚይዙትም ብፁዕ ዋና ጸሐፊው ናቸው፡፡ በተለመደው አሠራር መሠረት ደግሞ መግለጫ የሚያነቡት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ወይም ብፁዕ ዋና ጸሐፊው ናቸው፡፡

በትላንትናው መግለጫ ላይ እንደታየው አንባቢው ብፁዕ አቡነ አብርሃም ናቸው፡፡ ይህም ብፁዕነታቸው የመግለጫ አርቃቂ ኮሚቴው አባል ስለኾኑ ነው በሚል ቢገለጽም በሦስቱ አርቃቂ ኮሚቴ አባላት ውስጥ ልዩነት እንደነበር (ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕና ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በአንድ ወገን ናቸው)፣ የመግለጫው የጽሑፍ ሥራ ከቅ/ሲኖዶሱ ጽ/ቤት እና አባላቱ ውጭ የኾኑ ግለሰቦች ጉልሕ ሚና የተጫወቱበት እንደ ኾነ የሚገልጹ መረጃዎች፣ ስሞችን በመጥቀስ ጭምር በመውጣት ላይ ናቸው፡፡

በቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤቱ የፕሮቶኮል ደብዳቤ የወጣው መግለጫ ሌላው ቀርቶ ማኅተም እንኳ ሊኖረው ይገባ እንደነበር ተመልክቷል፡፡ በሌላ በኩል ብፁዕ ዋና ጸሐፊው ጋዜጣዊ መግለጫው እንዲጠራ ትእዛዝ ያስተላለፉት ለዛሬ፣ ጥር 9 ቀን 2005 ዓ.ም 5፡00 ላይ እንደነበር ጥሪው የደረሳቸው ጋዜጠኞች የተናገሩ ሲኾን በእነብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የተላለፈ ነው በተባለ ትእዛዝ ግን ጋዜጣዊ መግለጫው የተሰጠው ትላንት፣ ጥር 8 ቀን 2005 ዓ.ም፣ በ9፡00 ነበር፡፡ ‹‹ነገሩ ቀላል መስሎ ቢታይም በአቡነ ጳውሎስ ጊዜ የነበረው የተደገመበት (እርሳቸውም የቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ ሳያልቅ ለብቻቸው መግለጫ ለመስጠት ይሞክሩ ነበር) እና ጠቅላላ ሂደቱን ከወዲሁ ለመቆጣጠር የናረ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች መደራጀታቸውን ያሳያል፤›› ይላሉ ታዛቢዎች፡፡

ሁለተኛው የብፁዕ ዋና ጸሐፊው ከሓላፊነታቸው የመልቀቂያ ምክንያት÷ የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሚካሄድበት ወቅትና ከዚያ በፊት ባሉት ቀናት ብፁዕነታቸው ወይም ጽ/ቤቱ ሳያውቋቸው የሚወጡ ደብዳቤዎች መበራከታቸው ነው፡፡ ከደብዳቤዎቹ መካከል÷ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የጻፉት ደብዳቤ አንዱ ነው፡፡

በዚህ ደብዳቤ ዐቃቤ መንበሩ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከፍተኛ ሓላፊዎች ሥራቸውን እንዳይሠሩ ከፍተኛ ዕንቅፋት እየፈጠሩባቸው በመኾኑ የሚኒስቴሩን እገዛ ጠይቀዋል፡፡ የመንበረ ፓትርያሪኩ ምንጮች እንደሚያስረዱት÷ ዐቃቤ መንበሩ በዚህ ደብዳቤ ከከሰሷቸው ውስጥ ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ይገኙበታል፡፡ የሁለቱ አባቶች ውዝግብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስብሰባዎች ላይ ጭምር እየተካረረ የመጣ ሲኾን በግልጽ የታወቀው ያለመግባባታቸው መንሥኤ÷ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅነት ከተነሡ በኋላ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ያለቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ዕውቅና የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመንፈሳዊ ዘርፍ ም/ሥራ አስኪያጅ ኾነው መሾማቸው ነው፡፡

በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የሚመራው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ማኔጅመንት ኮሚቴ የንቡረ እዱ ሹመት አንድም፣ በቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ያልታየ፤ በሌላም በኩል ‹‹መንፈሳዊ ዘርፍ የሚባል መዋቅር የለንም›› በሚል ለቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ በጻፈው ደብዳቤ የዐቃቤ መንበሩን ርምጃ ተቃውሞታል፡፡ ንቡረ እዱ ለዕርቀ ሰላም ተልእኮ በአሜሪካ ሳሉ በሌለ መዋቅር የተሰጣቸው ይህ ሹመት ከዕርቀ ሰላሙና ከፓትርያሪክ ሹመቱ ጋራ ተያይዞ ‹‹የውስጥ ግዳጆችን ለማስፈጸም እንዲያመቻቸው ነው›› በሚል ሲነገር ቆይቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ንቡረ እዱ በአስተዳደር ሕንጻ ውስጥ ከዋና ሥራ አስኪያጁ ጋራ ሳይኾን በጽርሐ መንበረ ፓትርያሪኩ ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ጋራ በተሰጣቸው ቢሮ እንደሚሠሩ ተገልጧል፡፡ ከብፁዕ ዋና ሥ/አስኪያጁ ጋራ የንቡረ እዱን ሹመት ከተቃወሙት የማኔጅመንት ኮሚቴ አባላት መካከል እንደ አቶ ተስፋዬ ውብሸት (ምክትል ሥራ አስኪያጅ) ያሉት በዐቃቤ መንበሩና በዙሪያቸው ባሉ ሰዎች ጥርስ ውስጥ መግባታቸውም ተነግሯል፡፡

በዐቃቤ መንበሩ ዙሪያ የተሰለፉ ግለሰቦችን በሕገ ወጥ መንገድ የማስቀጠሩንና እስከ መመሪያ ሓላፊነት ድረስ ሹመት የማሰጠቱን ትእዛዝ ብፁዕ ዋና ሥ/አስኪያጁ አለመቀበላቸውም ሌላው የውዝግቡ መንሥኤ ነው ተብሏል፡፡ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ራሳቸው በርካታ ቀራቢዎቻቸውን በተለያዩ መምሪያዎች ውስጥ ቦታ በማስያዝ ቢተቹም በዐቃቤ መንበሩ ዙሪያ ካሉት ግለሰቦች ውስጥ እንደ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ሁሉ በወቅታዊ አጀንዳዎች ዙሪያ ተደራጅተው ከሚፈጽሙት ተግባር ጋራ እንደማይደራረስ ነው የሚነገረው፡፡

ሌላው ብፁዕ ዋና ጸሐፊውን ያሳዘነው ተግባር÷ ዐቃቤ መንበሩ በቀጥታ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የጥበቃ አገልግሎት በመጻፍ ያስተላለፉት ትእዛዝ ነው፡፡ ይህ ትእዛዝ የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር ሥራ አመራር አባል የነበረውና ለዕርቀ ሰላሙ ሂደት መሳካት ሌት ተቀን በመሥራት ላይ የሚገኘው ዲ/ን ማንያዘዋል አበበ÷ ከጥር 3 ቀን ጀምሮ ላልታወቀ ጊዜ ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ እንዳይገባ ማሳገዳቸው ነው፡፡ ይኸው ደብዳቤ በአድራሻ ለጥበቃ አገልግሎቱ ሲጻፍ ብፁዕ ዋና ጸሐፊው ይኹኑ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ እንኳ እንዲያውቁት አለመደረጉ ነው የተነገረው፡፡ ቁም ነገሩ ግን፣ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ቅድሚያ እንዲሰጠው ገንዘባቸውን፣ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ሰጥተው የሚቃተሉ ወገኖች በቀና አስተሳሰብና አሠራር ሳይኾን በባለጊዜዎች ተጽዕኖ በመደፈቅ ላይ እንዳሉ ዐይነተኛ ማሳያ መኾኑ ነው፡፡

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ከዋና ጸሐፊነት የመልቀቂያ ጥያቄያቸውን በጽሑፍ ለዐቃቤ መንበሩ ከማቅረባቸው በፊት በምልዐተ ጉባኤው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ‹‹እንደበቃቸው›› በቃል ማሳወቃቸው ተነግሯል፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 24 ንኡስ አንቀጽ 4 መሠረት የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የአገልግሎት ዘመን ሦስት ዓመት ነው፡፡ በዚሁ ንኡስ አንቀጽ መሠረት አስፈላጊ ኾኖ ከተገኘም ለአንድ የምርጫ ዘመን እንደገና ሊመረጥ ይችላል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on January 18, 2013
  • By:
  • Last Modified: January 18, 2013 @ 10:46 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar