www.maledatimes.com ይድረስ ለቅድስት ድንግል ማርያም (ክፍል ሁለት) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ይድረስ ለቅድስት ድንግል ማርያም (ክፍል ሁለት)

By   /   January 20, 2013  /   Comments Off on ይድረስ ለቅድስት ድንግል ማርያም (ክፍል ሁለት)

    Print       Email
0 0
Read Time:18 Minute, 6 Second

click here for pdf

ድንግል ማርያም ሆይ
ባለፈው እንደሰማሽኝ ዛሬም ትሰሚኛለሽ ብዬ ነገሬን እቀጥላለሁ፡፡
አንቺ በቤተልሔም ከተማ ማደርያ አጥተሽ እንደተንከራተትሽው ሁሉ ነፍሰ ጡር ሆኖ ቤት መከራየትማ የማይታሰብ ነው፡፡ አከራዮቹ የልጁን የሽንት ጨርቅ ማጠቢያ፣ የገንፎውን ማብሰያ፣ የጡጦውን መቀቀያ፣ የእንግዳውን ማስተናገጃ ሁሉ አስበው የቤት መሥሪያ ያስከፍሉሻል፤ ያለበለዚያም አንቺን እንዳሉሽ ‹ማደርያ የለም› ይላሉ፡፡
እኔማ ሳስበው አሁን አሁን ሕዝቡ መጥኖ መውለድ የጀመረው የቤተሰብ ምጣኔ ትምህርት ገብቶት አይመስለኝም፡፡ አከራዮች ናቸው የሕዝባችንን ቁጥር እየቀነሱት የመጡት፡፡ ልጅ ካለሽ፣ ያውም ከሦስት በላይ ከሆኑ፣ ማን ያከራይሻል፡፡ ብትከራይም ልጆችሽን እንደ ጥጃ ስትጠብቂ መኖርሽ ነው፡፡ ‹ይህንን ነኩ፣ ያንን ሰበሩ፣ ይህንን ቆረጡ፣ ያንን አበላሹ፣ እዚህ ገቡ፣ እዚያ ወጡ› እየተባለ በየቀኑ ሮሮ ነው፡፡ ልጅ ደግሞ በተገዛና በተከራየ ቤት መካከል ያለው ልዩነት አይገባውም፡፡ እና በዚህ ምክንያት ቤት ሳይሠራ ላለመውለድ፣ ከወለደም ከሁለት በላይ ላለመውለድ ስንቱ ወስኗል፡፡
ድንግል ሆይ
‹‹ምነው ለድኻ ኮንዶሚኒየም እየተሠራ አይደለም ወይ?›› ትይኝ ይሆናል፡፡ እውነት ነው ተሠርቷል፡፡ ምን ምን የመሳሰለ ኮንዶሚኒየም ተሠርቷል፡፡ እንዲያውም ሪል ስቴት ገብተሽ በገዛ ገንዘብሽ ከማረር ኮንዶሚኒየም ተመዝግበሽ አንድ ቀን ቢደርስሽ ይሻላል፡፡ አንዳንድ ሪል ስቴት ማለትኮ ገንዘብ ሰጥቶ የጨጓራ በሽታ መግዛት ማለት ነው፡፡ ሪል ስቴት ማለትኮ በገዛ ገንዘብሽ ቤትሽ ያልተሠራበትን ምክንያት የሚገልጠውን ሪፖርት ሲቀበሉ መኖር ማለት ነው፡፡ ሪል ስቴት ማለትኮ ባለቤት የሌለው ኮንዶሚንየም ማለት ነው፡፡ ኮንዶሚኒየምስ መንግሥት የሚባል ባለቤት ስላለው ከቀበሌ እስከ ክልል፣ ከባሰም እስከ ፓርላማ አቤት ይባልበታል፡፡ ይኼ ምርጫ የሚባል ነገር ሲመጣም በእግር በእጅ ተብሎ ቢያንስ ግምሹ ይታደላል፡፡ ከዚያም ከባሰ ግምገማ ሲመጣ ተጣድፈውም ቢሆን ጋዜጣ ያወጣሉ፡፡
አቤት የሚባልበት ቦታ የሌለበት፣ ምርጫ የማይነካው፣ ግምገማ የማይፈራ ሪል ስቴት አለልሽ አይደል እንዴ፡፡ እዚህ ሀገርኮ ሀብታምንም ድኻንም የሚያስተካክሏቸው ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ የቤት ችግርና ሞት፡፡ ይኼ ቀን ቀን ምን በመሰለ መኪና ሽር ብትን የሚለው ዘናጭ ሁሉ መኪና መግዛት ሳይሆን መኪና ማሳደር ነው የቸገረው፡፡ መኪና እንጂ መኪናውን የሚያህል መሬት እንኳን የለውም፡፡ ባይሆን እርሱ አከራዩ ውጣ ቢሉት ዕቃውን በገዛ መኪናው ጭኖ ይወጣልና ከኛ ከኛ ይሻላል፡፡
እስኪ ኮንዶሚኒየም ግቢ ውስጥ ማታ ማታ ተመልከች፡፡ ግቢውኮ የሞኢንኮ ወይም የፎርድ ግቢ ነው የሚመስለው፡፡ የኮንዶሚኒየሙን ውበት የሚያስንቁ መኪኖች ጎን ለጎን ቆመው ግቢውን ሲፎትቱ ታያለሽ፡፡ ኮንዶሚኒየምን ‹ድኻ ይደርሰዋል፣ ሀብታም ይከራየዋል› የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ እዚያም ቢሆን የሠፈሩ ደላሎች በተኛሽበት ነው ለሌላ አከራይተው የሚጠብቁሽ፡፡ አንቺ ኮንዶሚኒየም መከራየትሽን ለጓደኞችሽ በስልክ እየነገርሽ ባለሽበት ሰዓት ደላላና አከራይ ተስማምተው ለሌላ አከራይተው ይጠብቁሻል፡፡ ከዚያስ? ከዚያማ አንቺ በቤተልሔም እንደገጠመሽ ማደርያ ፍለጋ መንከራተት ነዋ፡፡
ይኼው አንቺ ቤት ብታጭ ጌታን በረት ውስጥ አይደል የወለድሽው? ዛሬምኮ መንገድ ላይ፣ የሰው ቤት ማድቤት ውስጥ፣ ላስቲክ ቤት ውስጥ፣ የሚወልዱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይኼው ለባለኮንዶሚኒየሞቹ በጋራ መጠቀሚያ ተብለው የተሠሩት ቤቶች እንደ ቤተልሔሟ በረት የድኾች ማደርያ ሆነዋልኮ፡፡
ድኻ ቤት ብቻ አይደለምኮ መቃብርም እያጣ ነው፡፡ ይኼው ለመቃብር እንኳን ሀብታምና ድኻ ተለይቶበት የመቃብር ሪል ስቴት መጥቷል አሉ፡፡ ታድያ ስሙን ቀይሮ ‹ፉካ› ተብሎ ይጠራል፡፡ እዚያ ሀብታም ነው የሚቀበረው፡፡ ኮንዶሚኒየምስ በዕጣ አንድ ቀን ይደርሰን ይሆናል፡፡ ይኼ መቃብር ግን ዕጣ ያለውም አይመስለኝም፡፡ እንግዲህ ሲኖር አንጀቱ የተቃጠለ ድኻ ሲሞትም አስከሬኑ ካልተቃጠለ በቀር የት ይቀበራል፡፡ ሲኖር ተንከራትቶ፣ ሲሞት ተንከራትቶ ድኻ እንዴት ይችለዋል? ለዚህ ነው ከሌላው ሁሉ የገና በዓል የሚገባኝ፡፡
ተከራይ ርካሽ ቤት ፍለጋ ወደ ከተማ ጥግ ሲሄድ፣ የከተማ ጥግ እያደግ የከተማ መሐል ሲሆን፤ ተከራይ ርካሽ ቤት ፍለጋ የድኻ ሠፈር ሲሰደድ፤ የድኻ ሠፈር እየተሸጠ የሀብታም ሠፈር ሲሆን፤ ይሄው መጨረሻችን ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡
ምነው ግን በቤተልሔም ከተማ የተከራይ አከራይ የለም እንዴ፡፡ የዚያ ሀገር ሰዎች ከኛም ሀገር የባሱ መሆን አለባቸው፡፡ የኛዎቹ እንኳን በርካሽ ተከራዩትን የመንግሥት ቤት፣ ለሌላው በማዘን›› ዋጋ ጨምረው ቆርሰው ያከራዩታል፡፡ በኋላ ዘመን ታድያ ‹የተከራይ አከራይ› ተብለው ሕግ ወጣባቸው፡፡ እኔን የገረመኝ ግን መንግሥት ራሱ ‹የወራሽ አከራይ› ሆኖ የተከራይ አከራዮችን መከልከሉ ነው፡፡ ይኼ አሁን መንግሥት የሚያከራየው ቤት አብዛኛው በቀድሞው መንግሥት የተወረሰ ቤት ነው፡፡ ወርሶ ማከራየት ወንጀል ካልሆነ ተከራይቶ ማከራየት እንዴት ወንጀል እንደሆነ መጠየቅ ቤት አጥቶ ከመንከራተት ስለማያድን ትቼዋለሁ፡፡
እመቤቴ ሆይ
ይህንን ሁሉ ብሶት የምነግርሽ መቼም ትሰሚኛለሽ ብዬ ነው፡፡ በዚህ ዘመንኮ የሚናገር እንጂ የሚሰማ ባለ ሥልጣን ማግኘት ከባድ ነው፡፡ እንቺ ግን የምትችይውን ታደርጊኛለሽ ያለበለዚም ሁሉ ለማይሳነው ልጅሽ ትነግሪልኛለሽ፡፡ ‹ወይ ግበርሎ፣ ወይ ንገርሎ› ይባላል በትግርኛ፡፡ ወይ አድርግለት፣ ያለበለዚያም ለሚያደርግ ንገርለት ማለት ነው፡፡
ለዚህ ነው እመቤቴ እኔ ያንቺ መንከራተት የሚገባኝ፤ የገና በዓልም የኔ በዓል የሚመስለኝ፡፡
በእውነቱ በዚህ ደብዳቤ እነዚያ እረኞችን ሳያመሰግኑ ማለፍ በራስ ላይ ርግማን ማምጣት ነው፡፡ ምንም እንኳን ቤት ባይኖራቸው በረታቸውን ግን ላንቺ ሰጥተውሻል፡፡ የሀገሬ ሰው ‹ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም› ይላል፡፡ እኔስ ‹ያለውን የሰጠ ታሪክ ያያል› ቢባል ነበር የምመርጠው፡፡ እነዚያ እረኞች የዓለምን ታሪክ ሲለወጥ ለማየት አልነበረም በረቱን የሰጡሽ፡፡ እንዴው ደግ ስለሆኑ ነው፡፡ ደግ ሰው ማለት እንደ ቀላል ነገር የሠራው ደግነት ተአምር ሲሠራ የሚያይ ነው፡፡
ዛሬኮ እመቤቴ እረኞቹ እንደዚያ ዘመን ለሌሎች በረታቸውን አይሰጡም፡፡ እንዲያውም የዛሬ ዘመን እረኞች ኢንቨስተሮችና ቤት ሠሪዎች፣ ቤት አከራዮች ሆነዋል፡፡ ምእመናንኮ ከአባቶቻቸው ከእረኞች ቤት እየተከራዩ ነው፡፡ እረኞች ዛሬ ቤት ላጡ ቤት እየሰጡ አይደለም፡፡ እንዲያውም ቤት ይገዛሉ፣ ቤት ይሸጣሉ፣ ቤት ይሠራሉ ቤት ያከራያሉ፡፡ አንቺ ደጎቹን እረኞች አግኝተሻቸው ነው፡፡
አቤት ያች የታደለች በረት፡፡ የሰማይ መላእክት ከምድራዊ ሰዎች፣ የሩቅ ሀገር የጥበብ ሰዎች ከእሥራኤላውያን እረኞች የተስማሙባት ቦታ፡፡ ምናለ ይህችኛዋ በረት ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ሁላችን የምንስማማባት ቦታ እንድትሆን ብታማልጅን፡፡ እንኳን የሰማዩ ከምድሩ፣ እንኳን የሩቁ ከቅርቡ የአንድ ቦታ ሰዎች እንኳን መስማማት አቅቶናል፡፡ ለዚህ ሳይሆን ይቀራል የጎንደሩ ባለቅኔ ክፍለ ዮሐንስ
እምነ ከዊነ ካህን ይኄይስ ከዊነ ኖላዊ
ወጎለ እንስሳ ይትበደር እም ቤተ መቅደስ ዐባይ
እስመ ቤተ መቅደስ ኮነ ቤተ ፈያታይ
ወበላዕለ ኖሎት ኢሀለወ ላዕለ ካህናት ዘሀሎ እከይ
ትእምርተ ዝኒ ክመ ንርአይ
በጎለ እንስሳ ሠረቀ ዘየአርብ ፀሐይ
ያለው ለዚህ ነበር፡፡
ይኼውልሽ አንቺ በስደትሽ ወቅት በመልካም ሁኔታ ያስተናገዱሽ ኢትዮጵያውያን እንኳን ወገናቸውን የሰው ሀገር ሰው የሚያለምዱ  ነበሩ፡፡ ‹እኔስ በሀገሬ እንኳን ሰው ወፍ አለምዳለሁ› ብለው ያንጎራጎሩትኮ ወደው አልነበረም፡፡ ስንቱ ከውጭ መጥቶ እዚሁ ለምዶ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ዐረቡ፣ እሥራኤላዊው፣ ግብጻዊው፣ አርመኑ፣ ግሪኩ፣ እንግሊዛዊው፣ ፈረንሳዊው፣ ፖርቹጊዙ፣ የመናዊው፣ ሕንዳዊው፣ ሶርያዊው፣ ኧረ ስንቱ፡፡ እንኳን ሰው በ15ኛው መክዘ ከሜክሲኮ የመጣው በርበሬ እንኳን ‹ፒርፒሬ› የሚለውን ስሙን በርበሬ አድርጎ ፍጹም ኢትዮጵያዊ ሆኖ፣ የኢትዮጵያውያን የሞያ መለኪያ ለመሆን በቅቶ የለም እንዴ፡፡
አሁንማ እንኳን የሰው ሀገር መቀበል ሰው ከጎረቤቱ ጋር በሰላም መኖር እየተሳነው ነው፡፡ አንድ ወንዝ የጠጣን የአንዲት ሀገር ሰዎች በሃይማኖትና በዘር ተቧድነን አትየኝ እየተባባልን ነው፡፡ እንኳን አልተማረም የሚባለው ትምህርት ገባው የተባለው ወገን እንኳን ኮሌጅ ውስጥ በዕውቀት መከራከሩን ትቶ በዘር ይቧቀስልሻል፡፡
መቼም የቸገረው ሰው ነገሩ ረዥም ነው፡፡ ባለጠጋማ ነገሩ አጭር ነው ፡፡ እንዲያውም የድኻ ፍታትና የባለጠጋ ጸሎት አጭር ነው ይባላል፡፡ ድኻ ብዙ ማመልከቻ አለው፡፡ ሀብታምማ ‹ያለኝን ጠብቅልኝ› ካለ በቃው፡፡ የቀረኝን ደግሞ ሳምንት ነግሬሽ ጉዳዬን እጨርሳለሁ፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on January 20, 2013
  • By:
  • Last Modified: January 20, 2013 @ 9:00 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar