www.maledatimes.com የኢትዮጵያ እግር ኳስና የደደሩት ችግሮቹ! በሰሎሞን ተሰማ ጂ. - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የኢትዮጵያ እግር ኳስና የደደሩት ችግሮቹ! በሰሎሞን ተሰማ ጂ.

By   /   January 29, 2013  /   Comments Off on የኢትዮጵያ እግር ኳስና የደደሩት ችግሮቹ! በሰሎሞን ተሰማ ጂ.

    Print       Email
0 0
Read Time:33 Minute, 46 Second

 (semnaworeq.)

 
የኢትዮጵያን አግር ኳስ በዋናነት የሚፈታተኑት ችግሮች ቁጥር ስፍር የላቸውም፡፡ ዋና ዋናዎቹን የስፖርቱን እንቅፋቶች ለማውሳትም ያህል እንሞክራለን፡፡ ችግሮቹን በሦስት ረድፍ ደርድሮ ማየቱ ይበጃል፡፡ የመጀመሪያውና ዋናው የፖለቲካውና የፖለቲከኞቹ ብልጣብልጥነት ስሜት ነው፡፡ ይህም ብልጣ ብልጥነት በአንደኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወቅት ተንፀባርቆ ነበር፡፡ ሁለተኛው ችግር ደግሞ፣ የፌዴሬሽኑና የተጫዋቾቹ የብሔራዊ ስሜት የማጣት ችግር ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃም ተጠቃሽ የሚሆነው የስፖርት ጋዜጠኞቹና የሕዝቡ ድጋፉን በተገቢው ኹኔታ አለመስጠቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ችግሮች እርስ በርሳቸው የተያያዙ በመሆናቸው፣ ስለአንዱ ስናነሣ ስለሌላኛውም እያወሳን እንደሆነ ትገነዘባለችሁ፡፡ በመጽሔታችን ገጽና ዐምዶች ሙሉ ለሙሉ ተሸፍኖ የማያልቅም ስለሆነ (ራሱን ችሎ ጥናትና ምርምር ያስፈልገዋል)፣ ቀሪዎቹን ነጥቦች እናንተ አንባቢያኑ በጎደለ እንድትሞሉልን በትህትና እንጠይለን፡፡
ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ፣ አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ባለፈው ቅዳሜ በሚሌኒየም አዳራሽ የተናገረው ሃይለ ቃል ነው፡፡ ሰውነት አለ፤ “በመጀመሪያዎቹ ሁለት የማጣሪያ ጨዋታዎች ከሶማሊያ ጋር ባደረግንበት ወቅት ባይሳካልንም፤ ፌዴሬሽኑ ቡድኑንና አሠልጣኙን ታግሦ ወደፊት እንድንገፋ ስለፈቀደልን ላመሰግነው እወዳለሁ!” ያለ መሠለኝ፡፡ ቀጠል አርጎም፣ “እስከመጨረሻው ድረስ በውድድሩ ለመቆየትና ለመፎካከርም እንሠራለን፡፡ ማጣሪያውንም ለማለፍ የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለነም!” ሲል ሰማሁት፡፡ ግሩም ነው፡፡ እንዳፉ ያድርግለት፡፡ አሠልጣኙ እንዳለው/ እንደተመኘው ሆኖ ኢትዮጵያ ቢቀናት ደስታውንም አንችለው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ተሣትፎ ታሪክ ይኼንን አያሳይም፡፡ (ስለሆነም፣ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቡድን ያደረጋቸውን የአፍሪካ ዋንጫ ተሣትፎዎችና በዙሪያው ያሉትን ችግሮች ለመነካካት ጥረት እናደርጋለን፡፡
 
********************************
በ1950ዓ.ም የአፍሪካ ዋንጫ ሲጀመር መስራቾቹ አራት አገራት ነበሩ፤ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ግብፅና ደቡብ አፍሪካ ናቸው፡፡ መነሻውም ሆነ መድረሻው አፍሪካዊና ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን የተንተተራሰ ነበር፡፡ ይህም፣ በዓላው ላይ በጉልኅ ሰፍሮ ነበር፡፡ መሠረታዊ ዓላመውም፣ “የወንድማማችነትን መንፈስ በአፍሪካውያን መካከል ለማጠናከርና የፀረ-ቅኝ ግዛት ትግሉን ለማበረታታት” ያለመ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ፣ ፀንሣሽዋም ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ ገና ብሔራዊ ቡድን ካቋቋመች ሁለት አመቷ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ዓለም-ዓቀፍ ግጥሚያዋንም ከሱማሌ-ላንድ ጋር ነበር ያደረገችው፡፡ ሱዳንም ብትሆን አስር አመታት አልደፈነችም ነበር፡፡ የግብፅ ግን ይለያል፤ ብሔራዊ ቡድኗ ከተመሠረተ ሠላሳ ስድስት ዓመታት አልፎት ነበር፡፡ በዚያም ላይ የዓለም-ዓቀፍ ውድድር ልምዶችም ነበሩት፡፡ ለሦስት ዓመታትም ያህል በነዚሁ መስራች አገሮች አባልነት ብቻ ተወስኖ ቆየ፡፡ ከዚያም ከቀኝ ግዛት ነፃ የወጡት ኬንያ፣ ዑጋንዳ፣ ቱኒዚያ፣ ጋናና ሞሮኮን ጨምሮ በ1954ዓ.ም የአባላቱ ቁጥር ዘጠኝ ደርሶ ነበር(አዲስ ዘመን፣ ጥር 15/1954፣ ገጽ 4)፡፡
የመጀመሪያዋም አዘጋጅ አገር ሱዳን እንድትሆን በመስራች አገሮቹ ጉባኤ ተወሰነ፡፡ ለዋንጫ ለማለፍም ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ጋር መጋጠም ነበረባት፡፡ ሱዳንም ከግብፅ ጋር ተጋጥማ፣ ግብፅ 2-ለ-1 አሸነፈች፡፡ (ኢትዮጵያን ወክለው የተሣተፉት የሉዑካን ቡድን አባላት መካከል የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ሌ/ኮ ታምራት ይገዙና ፀሐፊው ይድነቃቸው ተሰማ ነበሩ፡፡) በወርኃ የካቲት 1950ዓ.ም ጨዋታው ሊጀመር ሦስት ቀናት ሲቀረው፣ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የደቡብ አፍሪካን ቡድን በሚመለከት የውሳኔ ሃሳብ/ሞሽን/ አቀረቡ፡፡ “የነጭ ደቡብ አፍሪካውያን መንግሥት በጥቁር አፍሪካውያን ላይ የሚያራምደውን የዘር መድሎ አገዛዝ ካላቆመ በስተቀር በአፍሪካ ዋንጫ ላይ መሳተፍ አይገባውም” አሉ፡፡ እርግጡን ለመናገር፣ ወደካርቱም መጥቶ የነበረው የደቡብ አፍሪካ ቡድን አንድም የአፍሪካነር/ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊ/ አላሣተፈም ነበር፡፡ ስለዚህም ሐሳቡ ተቀባይነት አግኝቶ፣ ደቡብ አፍሪካ ከዋንጫው በእግድ ተሠናበተች፡፡ (የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ፖለቲካዊ አጀንዳውን በእግር ኳስ አማካኝነት ለማስፈፀም እንደሚጥር ገና ከጅምሩ አመላካች ሆነ፡፡) ኢትዮጵያም (በካርቱም ማዘጋጃ/Municipality ስታዲየም) በቀጥታ/ያለማጣሪያ ለዋንጫው ከግብጽ ጋር ተጋጥማ፣ 4-ለ-0 ተሸንፋ ሁለተኛ ሆነች፡፡ አንደኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለኢትዮጵያ የተገኘ ብራማ ዕድል ኾኖ፣ ኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ አገኘች፡፡ ሱዳንም ያለተጋጣሚ ሦስተኛ ሆነች፡፡ (አስገራሚው፣ የአንደኛው የአፍሪካ ዋንጫ በዚህ መልኩ ተጠናቀቀ፡፡)
ሁለተኛውም የአፍሪካ ዋንጫ ከሁለት ዓመታት በኋላ በግብፅ-ካይሮ ተደርጎ፤ ግብፅ ለሁለተኛ ጊዜ ዋንጫውን አነሳች፡፡ ሱዳንም ሁለተኛ ስትሆን፣ ኢትዮጵያ ሦስተኛ ሆነች፡፡ (ከሦስት ቡድኖች ውስጥ ሦስተኛ መኾን ያስደንቃል እንዴ?! ብቻ ሆነች!)… ከሁለት ዓመታትም በኋላ፣ ሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫም በጥር 6/1954á‹“.ም በዛሬው አዲስ አበባ ስታዲየም (ያኔ ቀ.ኃ.ሥ ስታዲየም) ተጀመረ፡፡ መክፈቻው የእግር ኳስ ጨዋታ ብቻ አልነበረም፡፡ በመቶ፣ በአራት መቶና በአሥር ሺ ሜትር ሩጫ ውድድሮችም እንዲታጀብ ተደርጎ ነበር፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ኤርትራ ጠቅላይ ግዛት የሥራ ጉብኝት ላይ ስለነበሩ፣ በመክፈቻው ላይ ፀኃፊ ትዕዛዙ/ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተ ወልድ ነበሩ የተገኙት፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን ከቱኒዚያ ጋር ተጫውቶ 4-ለ-2 አሸነፈ፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን በመጀመሪያዎቹ አሥር ደቂቃዎች ውስጥ በተከታታይ ሁለት ግቦች ተቆጥረውበት ነበር፡፡ የተመልካቹን ድንጋጤና ተስፋ መቁረጥ ማስታሱ ይከብዳል፡፡ ከዚያም፣ በሠላሳኛው ደቂቃ ላይ 9-ቁጥሩ ሉቺያኖ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጠረ፡፡ ከዚያም በ45ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው 7-ቁጥሩ ግርማ ባገባት ግብ ኢትዮጵያን አቻ  ሆነች፡፡
ከረፍትም መልስ፣ በሦስተኛው ደቂቃ ላይ፣ 8-ቁጥሩ መንግሥቱ ወርቁ ያሻገራትን ኳስ፣ 11-ቁጥሩ ጌታቸው ወልዴ መረብ አስነካት፡፡ የመጨረሻውም ጎል፣ በባከነ ሠዓት 10-ቁጥሩ ኢታሎ አስቆጥሯት የኢትዮጵያ ቡድን ለዋንጫ ሽሚያ ደረሰ (አዲስ ዘመን፣ ጥር 7/1954፣ ገጽ 4)፡፡… ከሁለት ቀናት በኋላም፣ በጥር 8/1954á‹“.ም ግብጽና ዑጋንዳ ተጫውተው፣ ግብፅ 2-ለ-1 አሸንፎ ስለነበር(አዲስ ዘመን፣ ጥር 9/1954፣ ገጽ 4)፤ በጥር 13 ቀን 1954á‹“.ም ከኢትዮጵያ ቡድን ጋር ለዋንጫ ተፋለሙ፡፡ ግብፅ ለሦስተኛ ጊዜ ዋንጫውን ለመውሰድ ተፋለሙ፡፡ የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው የግብፁ 10-ቁጥር ነበር፡፡ በ27ኛው ደቂቃ ላይ ግብፅ 1-ለ-0 መራች፡፡ አፍታም ሳይቆይ፣ ኢትዮጵያም በ28ኛው ደቂቃ ላይ አቻ የሚያደርጋትን ግብ በ7-ቁጥሩ ተክሌ አማካኝነት አስቆጠረች፡፡ ከረፍት መልስም የግብፅ ቡድን ተራሩጦ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥረች፡፡ ኢትዮጵያ ያበቃላት መሰለች፡፡ ነገር ግን፣ በ81ኛውም ደቂቃ፣ ሉቺያኖ ኢትዮጵያን አቻ አደረጋት፡፡ ጨዋታው፣ ተጨማሪ ሠላሳ ደቂቃዎች አስፈለጉት፡፡ በጭማሪው ሰዓት ልክ በ12ኛው ደቂቃ ላይ ገባ፡፡ ከዚያም ጨዋታው ሊጠናቀቅ 5-ደቂቃ ሲቀረው አራተኛው ግብ ተቆጠረ፡፡ ኳሶቹን አመቻችቶ ያቀበለው መንግሥቱ ወርቁ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በተጨማሪ ሰዓት አሸንፋ፣ የ3ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ አነሳች(አዲስ ዘመን፣ ጥር 15/1954፣ ገጽ 4)፡፡ ጨዋታውን ንጉሠ ነገሥቱና 50ሺ ኢትዮጵያውያን በቀጥታ ተመልተውታል፡፡
ሆኖም ፌዴሬሽኑ፣ 175ሺ ብር ወጪ አቅዶ ሳለ፣ ሞሮኮና ጋና ስላልመጡ፣ ወጪው ወደ 110ሺህ ብር ዝቅ አለ፡፡ ከስታዲየም ትኬት ሽያጭና ከለጋሾች የተገኘው ገቢ 85ሺህ ብር ብቻ ስለሆነ፣ ፌዴሬሽኑ በጥር 16/1954ዓ.ም በወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ “ከ40ሺህ ብር በላይ ስለከሰርኩ፣ የድረሱልኝ ጥሪ!” አሰማ፡፡ መጠነኛ እርዳታና ልገሳንም ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከኤሌክትሪክ ኃይል መሥሪያ ቤት አግኝቶ ማገገም ቻለ፡፡ ብዙም የሚያላውስ እንዳልነበረ፣ በሚያዝያ 1954ዓ.ም የወጣው የፌዴረሽኑ ኃላፊዎች መግለጫ ይገልጻል፡፡ (ሁለተኛው የፌዴሬሽኑ ችግር ዛሬም ድረስ ያለ ይመስላል፡፡)

 

አራተኛውንም የአፍሪካ ዋንጫ፣ በ1956ዓ.ም ጋና አዘጋጅታ ዋንጫውን አክራ ላይ አስቀረች፡፡ አምስተኛውንም፣ ጋና አዘጋጅዋን አገር ተኒዚያን 3-ለ-2 በተጨማሪ ሰዓት አሸንፋ ለሁለተኛ ጊዜ ወሰደች፡፡ ከግብፅም ጋር፣ በተከታታይ ሁለት ጊዜ የማሸነፉን ክብር ተጋራች፡፡ በዚህ የአፍሪካ ዋንጫም ላይ የተሣታፊ አገሮች ቁጥር አይቮሪኮስትን፣ ኮንጎ-ኪንሻሳንና ሴኔጋልን ጨምሮ አስራ ሁለት ደርሶ ነበር፡፡ አይቮሪኮስት ሴኔጋልን አሸንፋ ሦስተኛ ሆነች፡፡ ሌላው የዚህ ዘመን መለያ፣ የኢትዮጵያ ቡድን አደገኛ ተቀናቃኞች እየመጡበት እንደሆነ ማሳያ መሆኑ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ፣ምድቧን እንኳን ሳታልፍ ቀርታ ከመጀመሪያው መሰናበቷ የግድ ሆነ፡፡ (“ሳይደግስ አይጣላም!” እንደሚባለው፣ ኢትዮጵያ 6ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ጥያቄ አቅርባ፣ በአፍሪካ የእግር-ኳስ ፌዴሬሽን ተፈቀደላት(የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ኅዳር 18/1958፣ ገጽ 8)፡፡

 

የ1960ዓመተ ምህረቱም የ6ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በጥር 2/1960ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ በተገኙበት በቀ.ኃ.ሥ ስታዲዮም ተጀመረ፡፡ (የዛሬን አያርገውና) ጨዋታዎቹ በሁለት ምድብ አዲስ አበባና አስመራ ስታዲዮሞች ላይ ተደረጉ፡፡ አዲስ አበባ ላይ ኢትዮጵያ፣ ዑጋንዳ፣ አይቮሪኮስትና አልጄሪያ ተመደቡ፤ በተመሳሳይ መልኩም፣ አስመራ ላይ ጋና፣ ሴኔጋል፣ ኮንጎ ኪንሻሳና ኮንኮ ብራዛቪል ተደለደሉ፡፡ በመክፈቻው ላይም፣ ኢትዮጵያና ዑጋንዳ ተጋጥመው፣ ኢትዮጵያ 30ሺ ተመልካቿን አሰልፋ፣ በግርማ አስመሮምና በሉቺያኖ ቫሳሎ ግቦች 2-ለ-1 አሸነፈች፡፡ በዚያኑ ዕለት የተጫወቱት አይቮሪኮስትና አልጄሪያ ሲሆኑ፣ አይቮሪኮስት 3-ለ-0 አሸነፈች፡፡ በአጠቃላይ፣ በአዲስ አበባው ምድብ ተጫውተው አልጄሪያ ዑጋንዳን 4-ለ-0፤ ኢትዮጵያ አይቮሪኮስትን 1-ለ-0፤ አና ዑጋንዳ አይቮሪኮስትን 2-ለ-1 በማስቆጠር ስለተሸናነፉ፤ ኢትዮጵያ ከምድቧ አንደኛ ሆና ስታጠናቅቅ አይቮሪኮስትም 2ኛ ሆና ነበር (የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ጥር 18/1960፣ ገጽ 6)፡፡
በአስመራውም ምድብ፣ ጋናና ሴኔጋል 2-ለ-2፤ ኮንጎ ኪንሻሳ ኮንጎ ብራዛቪልን 3-ለ-0፤ ሴኔጋል ኮንጎ ብራዛቪልን 2-ለ-1፤ ጋና ኮንጎ ኪንሻሻን 2-ለ-1፤ እና ጋና ኮንጎ ብራዛቪልን 3-ለ-1 ተሸናንፈው፤ ከምድቧ ጋና አንደኛ፣ ኮንጎ ኪንሻሳም ሁለተኛ ሆኑ፡፡ ኢትዮጵያም ከኮንኮ ኪንሻሳ ጋር አዲስ አበባ ላይ ተጋጥማ ተሸነፈች፡፡ (ውድ አንባቢያን በውጤቱ የተናደዱት የስፖርት ጋዜጠኞቻችን ስንት ለስንት እንደተሸናነፉ እንኳን ስላልዘገቡት፣ እኛም ውጤቱን መግለፅ አልቻልንም፡፡) ከዚህ ይልቅ፣ ጋዜጠኞቹ “11-ቁጥሩ ሸዋንግዛውና 10-ቁጥሩ ኢታሎ ከኮንጎ ኪንሻሳ ጋር በነበረው ጨዋታ ባለመሰለፋቸው ቡድኑ ተጎዳ!” የሚል አስተያየት ነበር ያሰፈሩት፡፡ “ሸዋንግዛውን የተካው በረከት ልምድ ያልነበረው ሲሆን፣ ኢታሎንም የተካው ጌታቸው ወልዴ ጥሩ አልተጫወተም ነበር፤” ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ የነበሩት ይድነቃቸው ተሰማ እንዲህ አሉ፤ “ቡድናችን በአምስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሦስተኛ ወጥቶ የነበረውን የአይቮሪኮስት ቡድን አሸንፎ ስለነበረ፣ የልብ-ልብ ተሰምቶት ነበር፡፡ በተጨማሪም፣ የኮንጎ ኪንሻሳን ቡድን አጨዋወት የሚሰልልና የጨዋታውን አካኼድ የሚያጤን የብሔራዊ ቡድናችን አመራር በመጥፋቱ፣ በጨዋታውን ልንሸነፍ ችለናል፤” ነበር ያሉት(የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ጥር 18/1960፣ ገጽ 6)፡፡
የሆነው ሆኖ፣ 9-ቁጥሩ ሊቺያኖ ቫሳሎ፣ ጨዋታውን በቀጥታ ከተከታተሉት 35 የአፍሪካ ጋዜጠኞች መካከል በ32ቱ ተርጦ ኮከብ ተጫዋች ሲሆን፣ የኮንጎ ኪንሻሳው ግብ ጠባቂ ከዛዲ ሮበርትስ ሁለተኛ ሆኖ ተመርጧል፡፡…. ከዚህኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ የኢትዮጵያ እግር ኳስና የብሔራዊ ቡድናችን የቁልቁለቱን መንገድ መያያዝ ጀመረ፡፡ በሰባተኛው፣ በስምንተኛውና በዘጠነኛውም የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ እዚህ ግባ የሚባል ተሣትፎ እንኳን አላደረገም፡፡ የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ትኩሳትና ነውጦች፣ እግር ኳሱንም እግር-ተወርች አሰሩት፡፡ በተለይም በበጀት እጥረት የክለቦች አቋም መዋዠቅና ተጫዋቾችም ሞራል መላሸቅ ብሔራዊ ቡድኑን እጅጉን ጎዳው፡፡
የ10ኛው የአፍሪካ ዋንጫም ኢትዮጵያ ውስጥ እስኪደረግ ድረስ፣ የእግር ኳሳችን እንደሌሎች ዘርፎች ሁሉ ባለመረጋጋትና በወጀብ ውስጥ ገባ፡፡ በየካቲት 1968ዓ.ም አዲስ አበባና ድሬዳዋ ስታዲዮሞች ላይ በሁለት ምድቦች ተከፍሎ የተጀመረው 10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ፣ በቂ ትምህርት ጥሎ አለፈ፡፡ (ማንም የተማረበት አመራርም ሆነ ስፖርተኛ አልተገኘም እንጂ!) በየካቲት 27 ቀን 1968ዓ.ም የወጣው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እንደዘገበው ከሆነ፣ “10ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ፣ የደርግ ዋናው ሊቀ መንበር ብ/ጄኔራል ተፈሪ በንቴ መርቀው ከፈቱት፡፡ በመክፈቻውም ላይ ኢትዮጵያና ዑጋንዳ ተጫውተው፣ ካሳሁን ተካ በሦስተኛው ደቂቃ፣ በ88ኛውም ደቂቃም ተስፋዬ ያቀበላትን ኳስ፣ ሰበታ አስቆጥሯት ኢትዮጵያ 2-ለ-0 አሸነፈች፡፡ ሆኖም፣ ቀሪዎቹን ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ ተስኗቸው (ማጣሪያውንም ማለፍ ስላልቻለች)-የብሔራዊ ቡድናችን ተጨዋቾች የሞሮኮንና የጊኒን ዋንጫ ሽሚያ በተመልካች ወንበር ላይ ሆነው ተከታተሉት፡፡ (የትኬት ሽያጭ ዋጋም የትየለሌ ስላቆለቆለ ኪሳራው ብዙ ነበር፡፡)
ስለሽንፈቱና ስለዝርዝር የጨዋታው ኹኔታ በመፃፍ ፈንታ፣ ስሜታዊዎቹ የስፖርት ጋዜጠኞቻችን የተለመደ ሮሯቸውን ፃፉ፡፡ “የሸዋንግዛውና የገረመው በቡድኑ ውስጥ አለመካተት፣ አጎደለ!” እያሉ ተነጫነጩ፡፡ እውነታው ግን ያ አልነበረም፡፡ በደርግ ሰዎች፣ ትኩረትና ድጋፍ የተነፈገው የኢትዮጵያ ቡድን፣ ምስጥ እንደበላው ብሳና ሞሰሰ፡፡ ማጣሪያውን እንኳን ለማለፍ ተሳነው፡፡ እግር ኳስ የፖለቲካና የኤኮኖሚውም ማሳያ ነፀብራቅ ነውና፣ በአኅጉራዊው መድረክ ላይ እርቃኑን ወጣ፡፡ ይህንን ሀቅና እውነታ ነው፣ ጋዜጠኞቹ ሊያስተባብሉት የሞከሩት፡፡ ይባስ ብለው፣ “አድኃሪያን አይሳካም፤ አይፈፀምም ብለው ያሟረቱበት 10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ፣ በተሳካ ኹኔታ ተፈፀመ!” የሚል ፕሮፓጋንዳ ደሰኮሩ (አዲስ ዘመን፣ ሚያዝያ 10/1968ዓ.ም)፡፡
11ኛውንና 12ኛውም የአፍሪካ ዋንጫዎች መሣተፍ ሳይችል የቀረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ሊቢያ ትሪፖሊና ቤንጋዚ ላይ ተደርጎ በነበረው በ13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያ በምድብ-2 ቤንጋዚ ላይ ከናይጄሪያ፣ ከአልጄሪያና ከዛምቢያ ጋር ነበር የተመደበችው፡፡ ጨዋታው ለመጀመሪያ ጊዜ በሣተላይት ቴሌቪዥን ስርጭት ተላልፎ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያንም፣ የኢትዮጵያንና የናይጄሪያን ጨዋታ እየተከታተሉት ነበር፡፡ ናይጄሪያ ኢትዮጵያን 3-ለ-0 ቀጣ፡፡ ከዛምቢያም ጋር ተጋጥሞ የነበረው ብሔራዊ ቡድናችን በ59ኛው ደቂቃ በተቆጠረበት ግብ 1-ለ-0 ተረትቶ፣ ከአልጄሪያም ጋር ተጫውቶ 0-ለ-0 በመውጣቱ፣ ማጣሪያውንም ሳያልፍ ቀረ፡፡ በቡድኑ ላይ የተቆጠሩት አራቱም ግቦች በዋናነት የተካላዮቹና የግብ ጠባቂው የለማ ክብረት ስሕተቶች እንደነበሩ አዲስ ዘመን ጽፏል(መጋቢት 5/1974ዓ.ም፣ ገጽ 6)፡፡ የመንግሥት ስፖርት ጋዜጠኞች፣ ቤንጋዚ ሄደው ስለጠፉት የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾቻችን እንድም ቃል ሳይተነፍሱ ቀሩ፡፡ ከነዚያ፣ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ከሄዱት የቡድኑ አባላት መካከል ሠላሳ በመቶ የሚሆኑት “እንደወጡ ቀሩ!”
በዚህ የ13ኛው የአፍሪካ ዋንጫም ላይ፣ ጋናና ሊቢያ ለዋንጫ ደርሰው 120 ደቂቃዎችን 1-ለ-1 ሆነው ስለፈጸሙ፤ በፍጹም ቅጣት ምት ጋና ቀንቶት፣ 8-ለ-7 አሸንፎ ለአራተኛ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ባለድል ሆነ፡፡ የኢትዮጵያ ቡድንም በመስራችነት ከቆረቆረው ውድድር፣ ከ1974á‹“.ም ጀምሮ፣ ለ31 ዓመታት ያህል ከአፍሪካ ዋንጫ መድረክ እልም ብሎ ጠፋ፡፡ በዋናነትም የተጫዋቾቹ የብሔራዊ ስሜት ማጣትና የፌዴሬሽኑ በፖቲከኞችና በካድሬዎች በመጠርነፉ የተነሣ ተሣትፎውን ተጎዳ፡፡ የፋይናንስና የበቂ በጀት ባለመመደቡም፣ ኢትዮጵያን ከተወዳጁ የእግር ኳስ አደባባይ አለያያት፡፡ (የዛሬን አያድርገውና፣ “ባለራዕዩ መሪ” አቶ መለሠ ዜናዊ ራዕይ ባላዩበት ዘመን፣ “ኢትዮጵያ መሬቶቿን ለግብርና እንጂ፣ ለኳስ ሜዳነት አትጠቀምበትም!” ተብሎ ነበር፡፡… “ተባለ እንዴ?! ህምም… ተባለ እንዴ?!” አለ ዘፋኙ፡፡) ድል ለብሔራዊ ቡድናችን እየተመኘሁ፣ የስፖርት ጋዜጠኞቻችንና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እውነቱን ዘግበው ለተተኪው ትውልድ እንዲያስተላልፉት እንመክራቸዋለን፡፡ አለበለዚያ ግን፣ በዚህ የድረ-ገጽ ዘመን ለማስተባበል መሞከሩ የማያዋጣና ፋይዳ ቢስ መሆኑንም ልናስታውሳቸው እንፈልጋለን፡፡ (ቸር እንሰንብት!)

 

በሳምናታዊው የአዲስጉዳይ መጽሔት ቅጽ 7፣ ቁ. 147 ላይ፤ በጥር 11 ቀን 2005 ዓ.ም የወጣ፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on January 29, 2013
  • By:
  • Last Modified: January 29, 2013 @ 11:53 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar