www.maledatimes.com የፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴው ሥራውን ጀመረ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴው ሥራውን ጀመረ

By   /   February 3, 2013  /   Comments Off on የፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴው ሥራውን ጀመረ

    Print       Email
0 0
Read Time:10 Minute, 39 Second
  • ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ በኮሚቴው ስብሰባ አልተገኙም
  • ቅ/ሲኖዶሱ የኮሚቴውን ሊቃነ መናብርት ሠይሟል
  • በኮሚቴው እና በቅ/ሲኖዶሱ ሥልጣን መካከል ጥያቄዎች ተነሥተዋል
  • ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ወደ ዋና ጸሐፊነት ሓላፊነታቸው ተመልሰዋል

ቅ/ሲኖዶስ ለ፮ኛው ፓትርያሪክ ምርጫ የሠየመው አስመራጭ ኮሚቴ የመጀመሪያ ስብሰባውን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አካሄደ፡፡ የኮሚቴው ቀዳሚ ስብሰባ የተካሄደው ኮሚቴው በአወዛጋቢ ውሳኔ ታኅሣሥ 6 ቀን 2005 ዓ.ም ከተሠየመ ከአንድ ወር በኋላ በእጅጉ ዘግይቶ ነው፡፡ የመዘግየቱ መንሥኤ ከምርጫው በፊት ለዕርቀ ሰላሙ ፍጻሜ ቅድሚያ ከመስጠት፣ ውጤቱን ከመጠበቅና ለውጤቱ ከመሥራት አኳያ በቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ በታየው ከፍተኛ ውዝግብ ምክንያት ነው፡፡

ጥር 6 ቀን 2005 ዓ.ም የቅ/ሲኖዶሱ አስቸኳይ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ሲጀመር በሚበዙት አባቶች ከፍተኛ ድጋፍ የተሰጠው ይኸው የሰላምና አንድነት አጀንዳ በቀጣዩ የስብሰባው ቀን በውጭ ተጽዕኖ ጭምር ከተቀለበሰ በኋላ የዕርቅና ሰላም ጉባኤው ተስፋ ጨልሞ የምርጫው ሂደት እንዲቀጥል ውሳኔ ተላልፏል፡፡

ቅ/ሲኖዶሱ ታኅሣሥ 8 ቀን 2005 ዓ.ም ባጸደቀው የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ አንቀጽ 6/ሀ መሠረት÷ አስመራጭ ኮሚቴው በተቋቋመ በአንድ ወር ውስጥ÷ ለሥራው የሚያስፈልጉትን ግብአቶች፣ የምርጫውን ቦታ፣ ቀንና ሌሎች ከምርጫው ጋራ የተያያዙ ጉዳዮችን በሙሉ ከዝርዝር የድርጊት መርሐ ግብር ጋራ አዘጋጅቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ በማቅረብ አስወስኖ ተግባሩን ማከናወን ይጠበቅበታል፡፡ በዚህም መሠረት የኮሚቴው አባላት ታኅሣሥ 26 ቀን 2005 ዓ.ም በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በተጻፈላቸው ደብዳቤ መሠረት ጥር 8 ቀን 2005 ዓ.ም በቅ/ሲኖዶሱ ጽ/ቤት ተገኝተው ሥራቸውን እንዲጀምሩ ማሳሰቢያ የተሰጣቸው ቢኾንም የተባለው አልተፈጸመም፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አስመራጭ ኮሚቴው የመጀመሪያ ስብሰባውን ሊያካሂድ የቻለውም ቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ የኮሚቴውን ሊቃነ መናብርት ከሠየመ በኋላ ነው፡፡ በቋሚ His Grace Abune Estifanosቅ/ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት የ፮ኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴን በሰብሳቢነት የሚመሩት የኮሚቴውን በችኮላ መሠየም ከተቃወሙት አባቶች አንዱ የነበሩት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ሲኾኑየኮሚቴው ም/ሰብሳቢ ደግሞ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ናቸው፡፡ ኮሚቴውንበጸሐፊነት እንዲያገለግሉ የተመረጡት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ መኾናቸው ታውቋል፡፡

በኮሚቴው የመጀመሪያ ቀን ስብሰባ የኮሚቴው አባል የኾኑት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ አልተገኙም፡፡ የብፁዕነታቸው በስብሰባው አለመገኘት፣ ቀድሞ በቅ/ሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ካንጸባረቁት አቋም ጋራ በተገናኘ እንደኾነ ቢገመትም ሌሎች ምንጮች ደግሞ በሀ/ስብከታቸው ከተደረገ የአዲስ ቤተ ክርስቲያን ምረቃ መርሐ ግብር መደራረብ ጋራ አያይዘውታል፡፡

በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡ መሠረት 13 አባላት የተሠየሙበት ኮሚቴ÷ በመጀመሪያ ቀን ስብሰባው፣ የእርስ በርስ ትውውቅና የሥራ ክፍፍል ማድረጉ ተዘግቧል፤ በቀጣይ የሚያከናውናቸውን ዝርዝር ተግባራት ከጊዜ መርሐ ግብር ጋራ የመቅረጽ ሥራም መጀመሩ ተገልጧል፡፡ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ታኅሣሥ 4 ቀን 2005 ዓ.ም ለአስመራጭ ኮሚቴው አባላት በጻፉት ደብዳቤ መሠረት÷ ኮሚቴው ለ፮ኛው ፓትርያሪክ ዕጩ ኾነው የሚቀርቡ ከሦስት ያላነሱ ከአምስት ያልበለጡ ተወዳዳሪ ዕጩ ሊቃነ ጳጳሳትን በሕገ ደንቡ ተለይተው ከተዘረዘሩ አካላት በሚቀርቡ ጥቆማዎች አማካይነት ለይቶ እስከ ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ የማቅረብ ሓላፊነት አለበት፡፡

ሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አባላት እስከኾኑ ድረስ ለውድድሩ የተጠቆሙትን ዕጩ ሊቃነ ጳጳሳት መልሶ ለምልአተ ጉባኤው የማቅረቡ ጉዳይ ከጅምሩ በአስመራጭ ኮሚቴው አባላት መካከል ክርክር አሥነስቷል፡፡ የክርክር ነጥቦቹ በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ÷ በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡ ለአስመራጭ ኮሚቴው በተሰጠው ሥልጣንና በቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ በኾነው ቅ/ሲኖዶስ የሥልጣን ክልል መካከልም ተነሥቷል፡፡ ለአብነት ያህል የኮሚቴው ሊቃነ መናብርት በቅ/ሲኖዶሱ መወሰኑ ለሚበዙት የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት አልተዋጠላቸውም፡፡ ወዲህም መራጮች ተመርጠው የሚመጡበት አግባብና አመዘጋገብ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ በዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ፣ በየአህጉረ ስበከቱ ደግሞ በሊቃነ ጳጳሳት አረጋጋጭነትና ቁጥጥር ሥር መኾኑም ለምርጫው ነጻነት መጠበቅ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው የሚተቹ አሉ፡፡

በሌላ ዜና በጥር 6ቱ የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አስቸኳይ ስብሰባ ሂደትና ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ጋራ በተፈጠረ የሥራ አለመግባባት፣ ከሓላፊነታቸው የመልቀቂያ ደብዳቤ ለዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ያቀረቡት የቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ወደ ቢሯቸው ተመልሰዋል፡፡ ብፁዕነታቸው ከሓላፊነት የመልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ካቀረቡበት ዕለት አንሥቶ ጥያቄያቸውን እንዲስቡ ከውስጥም ከውጭም ግፊቱ በርትቶባቸው ሰንብቷል፡፡ ‹‹መናገር የማልፈልገው ብዙ ነገር አለ›› ብለዋል ብፁዕነታቸው ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ከወጣው ‹‹ላይፍ›› መጽሔት ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on February 3, 2013
  • By:
  • Last Modified: February 3, 2013 @ 10:44 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar