www.maledatimes.com የመለስ፣ የጳውሎስና የቀ.ኃ.ሥ ፋውንዴሽኖች በሰሎሞን ተሰማ ጂ. - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የመለስ፣ የጳውሎስና የቀ.ኃ.ሥ ፋውንዴሽኖች በሰሎሞን ተሰማ ጂ.

By   /   February 9, 2013  /   Comments Off on የመለስ፣ የጳውሎስና የቀ.ኃ.ሥ ፋውንዴሽኖች በሰሎሞን ተሰማ ጂ.

    Print       Email
0 0
Read Time:35 Minute, 14 Second

              (semnaworeq   )አዲስ ዘመን ጋዜጣ በጥር 9 ቀን 2005 ዓ.ም በፊት-ለፊት ገጹ ላይ የአንድን “አዋጅ መጽደቅ” ዜና አትሞ ነበር፡፡ ዜናው አዲስ አይደለም፡፡ “የአዋጁን በጆሮ” እንደሚባለው አይነት ነው፡፡ ከሁለት ቀናት በኋላ የወጣውም የአማርኛው ሪፖርተር ጋዜጣ ያንኑ ዜና ደግሞታል፡፡ ዜናውን ያነበበና የሰማ ሁሉ ወደአእምሮው የሚመጡበት ግዙፍ ጥያቄዎች አሉ፡፡ የእነዚህም ጥያቄዎች መሠረታቸው “ከፓርላማው ግልጽነት የጎደለው አሠራር” ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ የሪፖርተር ጋዜጣ ዘጋቢ እንደገለጸው፣ አዋጁ ሲጸድቅ የፓርላማው “ውይይቱ ለጋዜጠኞች ዝግ ነበር!” ልናነጋግራቸው የሞከርናቸው በርካታ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም፣ “ከነገሩ ጦም ይደሩ!” የምትለዋን የአበው ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ብለው፣ ምንም ነገር ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡….. በምክር ቤቱ የአሠራርና ሥነ ምግባር ደንብ የምክር ቤቱ ውይይቶች ለጋዜጠኞችክፍት እንደሚሆኑ፣ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ዝግ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻል፡፡  ይሄኛውም  ውይይት በምን ምክንያት ዝግ ሊሆንእንደቻለ በግልጽ አልተነገረም፡፡ በዝግ የተካሄደውን የምክር ቤቱን ውሎ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኅን ከምክር ቤቱ በደረሳቸው መግለጫመሠረት አቅርበውታል፡፡   (ፓርላማውና የፓርላማው አባላት በራሳቸው ላይ ማዕቀብ ለመጣል ምን እንዳነሳሳቸውም አልገባንም፡፡ ተጠሪነታቸው ለሕዝብ፣ ከሕዝብና በሕዝብ ከሆነ፣ ሕጎች ሲፀድቁ በይፋ ውይይት ተደርጎባቸው፣ ሕዝብና ጋዜጠኞችም በቂ መረጃ እንዲያገኙ መደረግ አለበት፡፡ ሆኖም፣ አልተደረገም፡፡ ይህ ደግሞ፣ “የምክር ቤቱን ሕዝባዊነትና ግልጽነት እንዲሁም ተጠያቂነት አጠያያቂ ሳያደርገው ይቀር ይሆን?!” የሚል ሥጋት ስላደረብን፣ ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ተነሣሣን፡፡

አዲስ ዘመን በገጽ አንድና ሁለት ላይ እንዳሠፈረው፤ “መለስ ፋውንዴሽን ሊቋቋም ነው” ካለ በኋላ፣ “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትየመለስ ፋውንዴሽን ማቋቋሚያ አዋጅን መርምሮ አጸደቀ፤” ሲልም ያክላል፡፡ ምክር ቤቱም ሆነ አዲስ ዘመን “ፋውንዴሽን”ያሉት የአማርኛውን “በጎ አድራጎት ድርጅት” ለማለት ነው፡፡ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ (“በጎ” ስላሰቡም ሊበረታቱ ይገባል፡፡ ግና፣ “መሸፋፈኑና ማለባበሱ ለምን አስፈለገ?” የሚለውን ጥያቄ አሁንም ልንደግመው እንወዳለን፡፡) አዲስ ዘመን እንዳለው፤ “አዋጁ የጸደቀውክቡር አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት ዘመናቸው ሲታገሉለት የነበሩትን የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት፣ የሰዎች ዴሞክራሲያዊ ግንኙነት፣እኩልነት ክብርና ብልጽግና እንዲረጋገጥ ብሎም የሰላም ጅምሮቻቸውን ማስቀጠል እንዲቻል ነው፡፡ 4ኛው ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት3ኛአመት የስራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባውን ጥር 9/2005 ባካሄደበት ወቅት ነው አዋጁን ያጸደቀው፡፡
“የፋውንዴሽኑ መቋቋም አቶ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት፣ በመከባበርና በአንድነት የሚኖሩባትአገር እንድትሆን ከልጅነት እስከ እልፈተ ህይወታው የከፈሉትን መስዋዕትነት ለመዘከር ያስችላል ብለዋል፡፡ በአገራችን ሰላም፣ መልካምአስተዳደርና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ለማድረግ የሰጡትን አመራር ለማስታወስና በአፍሪካ አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥ ከፍተኛ አርአያትያለው ተግባር የፈጸሙ በመሆናቸው ፋውንዴሽኑ እንዲቋቋም አስፈልጓል ነው” ያሉት አቶ አስመላሽ ፡፡
የምክር ቤቱ የህግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ እንዲህ አሉ፤ “የልማታዊና ዴሞክራሲያዊመንግስት አስተሳሰብን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ፋውንዴሽኑ ያለውን አስተዋፆዖ” በተመለከተም ሲያብራሩ፤ “ፋውንዴሽኑ የክቡርአቶ መለስ ዜናዊ አስክሬን የሚያርፍበትና በህዝብ የሚጎበኝበትን መናፈሻ መገንባትና ማስተዳደር እንደዚሁም አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀቤተመጻህፍት በመገንባት እርሳቸው የጻፏቸውን የተለያዩ መጽሐፍትና የተሰሩ ጥናታዊ ፊልሞች እንዲገኙበት ያደርጋል።
“በህዝቦችና በአገራት መካከል የመግባባትና የመተባበር መንፈስ እንዲዳብር በተለያዩ መንገዶች ትምህርት መስጠትና በኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊ ዴሞክራሲያዊ እና በሰላም አስተሳሰብ ምርምር ለሚያደርጉ ሁሉ አስፈላጊ ሁኔታዎችን ማመቻቸትም ሌላው የፋውንዴሽኑ ተግባርእንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በችግር ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል ለማይችሉ ዜጎች በተለይም ለሴቶች የነጻ የትምህርት እድልለመስጠትና የአረንጓዴ ልማት አስተሳሰብ ማስፋፋት፣ መተግበርና መደገፍ የፋውንዴሽኑ ዋና ዋና ተግባራት” እንደሆኑም የጋዜጣው ዘገባ ያትታል፡፡
ወገንተኛው “ሪፖርተር” ጋዜጣም በበኩሉ፣ “የመለስ ፋውንዴሽን አዋጅ ፀደቀ!” ሲል ጮቤ ረግጦ ከጣራ በላይ በደስታ ጮኋል፡፡ ይህንንም የሚያሳብቁት እነዚህ ዐረፍተ ነገሮች ናቸው፡፡ “በሕይወት ዘመናቸው ያለ ዕረፍት ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ካበረከቱት በተጨማሪለአፍሪካውያን ሰላምና ደኅንነት፣ በዓለም መድረክ የአፍሪካን ጥቅም ለማስከበር ያደረጉትን አስተዋጽኦ፣ እንዲሁም በዓለም የአየር ንብረትላይ የተጫወቱትን የአረንጓዴ አብዮት ሚና መዘከር ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ማድረግ፣ የመለስ ፋውንዴሽን መሠረታዊዓላማዎች መሆናቸውን አዋጁ እንደሚያስረዳ” ሪፖርተር ገልጧል፡፡ (ልብ በሉ፣ ይህንን ሁሉ ሃተቤተሰቦቻቸው፣ መንግሥት፣ ባለሀብቶችናጓደኞቻቸው ፋውንዴሽኑን ለማቋቋም በሚያዋጡት ገንዘብ ድርሻ እንደሚኖራቸው ታና ውዳሴ የተናገረው ሪፖርተር ጋዜጣ እንጂ አዲስ ዘመን አይደለም፡፡) ሪፖርተር አክሎም፤ “በቅርቡ ከፓርላማው አባላት የቀረቡ ጥያቄዎችን ለመመለስ ተገኝተው የነበሩት ጠቅላይሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በዚሁ የመለስ ፋውንዴሽን ዙሪያ ገለጻ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ገልጸዋል፡፡ ውይይቱን ጋዜጠኞችእንዳይከታተሉት ዝግ በመደረጉ ግን ዝርዝር የፋውንዴሽኑ ባለድርሻዎችንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ለማቅረብ አልተቻለም፤” ሲል ያቅማማል፡፡
“የመለስ ፋውንዴሽን/በጎ አድራጎት ድርጅትንም” በተመለከተ ከሚነሱት ጥያቄዎች መካከል አንዱ ይሄው የማቋቋሚያ ገንዘብ ወጪ ነው፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንዳሉት፣ “ቤተሰቦቻቸው፣ መንግሥት፣ ባለሀብቶችና ጓደኞቻቸው ፋውንዴሽኑን ለማቋቋም በሚያዋጡትገንዘብ ድርሻ እንደሚኖራቸው” ተወስቷል፡፡ “የማን ድርሻ ምን ያህል ይሆናል?” እና “በምን ያህል ጊዜስ ውስጥ መዋጮው ተግባራዊ ይሆናል?” የሚሉትን ባለማብራራቱ ጥርጣሬውን ከፍ ያደርገዋል፡፡ በተለይም፣ “ባለሀብቶች” የሚያዋጡት ገንዘብ መጠን በመቶኛ ካልተገደበ በስተቀር፣ ለሙስናና ለእከክልኝ-ልከክልህ በር ይከፍታል፡፡ በውጭው ዓለም የበጎ አድራጎት መዋጮዎች ሲደረጉ፣ ድርጅቶቹ ለሚከፍሉት/ለሚለግሡት የኮርፖሬት መዋጮ መንግሥታቸው የሚያስብላቸው ግልጽ መብትና ግዴታ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይህ የኮርፖሬት አስተሳሰብ ገና አልተጀመረም፡፡ ስለሆነም፣ የሕዝቡና የአካባቢ ጠንቅ በሆኑ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ “ባለሀብቶች” የፈለጋቸውን ጎጂ ተግባር ፈጽመው፣ ለመለስ ፋውንዴሽን እጅ-መንሻ አቅርበው እንደፈለጉ እንዲሆኑ በር ይከፍታል፡፡ ስለዚህም፣ ከመዋጮው በፊት የኮርፖሬቶች መዋጮን በተመለከተ፣ ምክር ቤቱ “በነካ እጁ” ሌላ አዋጅ በአፋጣኝ ማውጣት አለበት፡፡ አለበለዚያ፣ ደንበኛ የሚስናና የጭቦ በር ከፍቶ እንደተወ ሊያውቀው ይገባል፡፡
ተያይቀውም የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ “ለመሆኑ የዚህ ድርጅት የበላይ ጠባቂ የሚሆነው ማነው? ድርጅቱ በሥሩ የሚያስተዳድራቸው ድርጆቶች ምን ያህል ይሆናሉ? ወይስ እንደተባለው ቤተ-መጽሐፍት፣ ሙዚየምና መናፈሻ ብቻ ናቸው? (ይኼ ከሆነ ደግሞ በአዲስ አበባ፣ በባሕርዳር በመቀሌና በአዋሳ ካሉት የሰማዕታት ድርጅቶች በምኑ ሊለይ ነው? (ሃውልት ባለማቆሙ፣ እንዳይባል ገና ለይቶ-አለየለትም፡፡) በጎ አድራጎት ድርጅቱ የሚሠጡትን ንብረቶች በምን ሁኔታ ይቀበላል? በመንግሥታዊ ያልሆኑ (መያዶች) አዋጅ ስር ይተዳደራል እንዳይባል፤ ድርጅቱ ራሱ በአዋጅ የተቋቋመ ነው፡፡ ስለዚህም ቀደም ብሎ የወጣው የመያዶች አዋጅ አይመለከተውም ማለት ነው፤ ወይም እንዳይመለከተው ተደርጎ ተረቋል፡፡
ሁለተኛው ጥያቄ ደግሞ፣ “ፓርላማው ለምን የመለስን በጎ አድራጎት ድርጅት ብቻ ለማወጅ ፈለገ?” የሚል ነው፡፡ እዚህ ላይ ተያያዥ ጥያቄዎችም አብረው ይነሣሉ፡፡ ለምሳሌ፣ “ድርጅቱ እንዲቋቋም የገፋፉት ሰዎች እነማን ናቸው? የቤተሰቦቻቸውስ ሚና (መዋጮ ከማዋጣት ባሻገር) እሰውከምን ድረስ ነው? ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትርስ የበጎ አድራጎት ድርጅት የማቋቋም ፍላጎት ነበራቸው ወይ? ከነበራቸውስ፣ ለድርጅቱ መቋቋሚያ ምን ተናዘዙ? ወዘተርፈ…”  የሚሉ ጥያቄዎችን ያስነሳል፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ግን፣ ፓርላማው በእርግጥ በአንድ ግለሰብ ስም፣ የበጎ አድራጎት ድርጅት ለማቋቋም አዋጅ የማወጅ ሥልጣንና ኃላፊነትስ አለውን? የሚለውን መዝማዥ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በርግጥም የለውም፡፡ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ ታዲያን፣ የአቶ መለስ አድናቂዎችና ቲፎዞዎች ሌላ ጓደኛቸውን የሚዘክሩበት መንገድ ቢፈልጉ ይሻላቸው ነበር፡፡ ሆኖም፣ ሩጫቸው ፈሩን ለቆ በዝግ ስብሰባ አዋጅ እስከማጽደቅ አደረሳቸው፡፡ ያሳዝናል፡፡
ይህ የበጎ አድራጎት ወይም የፋውንዴሽን ሐሳብ የከማን-አንሼ አባዜም አለበት፡፡ ይህ ደግሞ የአንዳንድ “ወዳጅና ቲፎዞ ነን” ባዮች ወከባ ማሳያ ነው፡፡ ለምሳሌም ያህል የአቡነ ጳውሎስን ደጋፊዎች የአንድ ሰሞን ሽር ጉድ ማስታወስ ይገባል፡፡ አቡኑ ከማረፋቸው አንድ ወር በፊት አንድ ወጣት “የጳውሎስ ፋውንዴሽን” አቋቁማለሁ ብሎ ተነስቶ ነበር፡፡ ኻያኛው በዓለ ሢመት አከባበር ላይ የነበሩት ውሉደጳውሎስ (እነ እጅጋየሁ በየነ) በአቡነ ጳውሎስ ስም የሚጠራ “ጳውሎስ ፋውንዴሽን”እናቋቁማለን በሚል እየተሯሯጡ እንደነበረም ደጀ ሰላም የተሰኘው ድረ-ገጽ ዘግቧል (www.dejeselam.org/2012/08/blog-post_151.html ይመልከቱ፡፡) ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም እንደዘገበው ከሆነ፣ ያሁኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም የበላይ ጠባቂ እንዲሆኑ በፓትረያርኩ ተሾመው ነበር፡፡ የገንዘብ ምንጩም፣ ለ‹ፋውንዴሽኑ›መቋቋም ያስፈልጋል የተባለውን ገንዘብም እንደተለመደው ከአድባራትና ገዳማት እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱኢኮኖሚያዊ ምንጮች ለመሰብሰብ  ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነን፣ መልአከ ፀሐይ በቀለ ተሰማ (ቤቴል ቅዱስ ሚካኤል)፣ ሰሎሞን በቀለን (ቦሌመድኃኔዓለም)፣ ቀሲስ ግሩም መልአክ ታዬ (ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣ ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል (ጠቅላይ ቤተ ክህነት) በዋናአደራጅነት ሲዘጋጁ መቆየታቸውን” ዘግቧል፡፡ (ያም ሆነ ይህ፣ የጳውሎስ ፋውንዴሽን ከመለስ ፋውንዴሽን በአራት ነገሮች የተሻለ ይመስላል፡፡ አነርሱም፣ የበላይ ጠባቂውን በግልጽ በማሳወቁ፣ የገንዘብ ምንጩን ይፋ በማድረጉ፣ አቡኑ በሕይወት ሳሉ በመደገፋቸውና የመጽሐፋቸውንም ሽያጭ ገቢ ለዚሁ ተግባር በመፍቀዳቸው ነው፡፡)
ወታደራዊ ደርግ በ1970ዓ.ም በአዋጅ “የአብዮታዊት ኢትዮጵያን ሕጻናት ማሳደጊያን” ዝዋይ ላይ፤ “የአብዮታዊት ኢትዮጵያን ጀግኖች አንባን” ደብረ ዘይት ላይ (የዛሬውን የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ግቢ ነው)፤ “የጉለሌ ሕፃናት ማሳደጊያን (ኋላ የሚኪ ሊላንድ ሕጻናት አንባ ተብሎ ነበር) እና በደሴ፣ በኤርትራና በጎዴም የሕጻናት ማሳደጊያዎችን በአዋጅ አቋቁሞ ነበር፡፡ የበላይ ጠባቂውም ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ነበር፡፡ ብዙዎቹ ዝዋይና ጉለሌ ሕጻናት አንባዎች ውስጥ ያደጉት ልጆች ያባታቸው ስም መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እንዲሆንም ይደረግ ነበር፡፡ እነዚህ የ“የአብዮታዊት ኢትዮጵያ” በጎ አድራጎት ድርጅቶችም በጀታቸውን በቀጥታ የሚያገኙት ከመንግሥት ካዝና ነበር፡፡ ሁሉንም፣ የ“የአብዮታዊት ኢትዮጵያ” የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ደርግ መራሹ የወያኔ/ኢሕአዴግ መንግሥት ያለአዋጅ በተናቸው፡፡ እስከ1997ዓ.ም ድረስ ሲጓተት የቆየው የጉለሌ ሕጻናት ማሳደጊያም ሴቶቹን ወደቀጨኔ፣ ወንዶቹንም ወደከነማ ሕጻናት ማሳደጊያዎች አዛውሮ ሲያበቃ በለሆሳስ ተዘጋ፡፡
በኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ታሪክ ተወዳዳሪም ያልነበረው ድርጅት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጎ ድራጎት ድርጅት (የቀ.ኃ.ሥ ፋውንዴሽን) ነው፡፡ የድርጅቱ ማቋቋሚያ ቻርተር በሐምሌ 15 ቀን 1951ዓ.ም በመንግሥት ማስታወቂያ ቁ. 253/51 መሠረት ወጥቶ፤ በየካቲት 21 ቀን 1952ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 261/52 መሠረት ፀድቋል፡፡ ይህንን አዋጅ የመሰለና የተሳካለት ቻርተር ያለው የበጎ አድራጎት ድርጅት በኢትዮጵያ ተቋቁሞም አያውቅ፡፡ ዘርፈ-በዙ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ በሥሩም የቀ.ኃ.ሥ ሽልማት ድርጅትን፣ የአባድር እርሻ ልማትን፣ የቤተሳይዳ ቀ.ኃ.ሥ ሆስፒታልን (የዛሬው የካቲት 12 ሆስፒታል መሆኑ ነው)፤ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልን  (ያኔ የዛሬው ክፍለ ሀገር አውቶቡስ ተራ ጋር ነበር)፤ የሐረር ልዑል ራስ መኮንን ሆስፒታልን (በተለምዶ ጀጉላ ሆስፒታል ይባላል)፤ በቅደስ ኡራኤል ቤተ-ክርስቲያን ጀርባ የነበረውን የቀ.ኃ.ሥ ዕጓለ ማውታ ትምህርት ቤትን፤ ስድስት ኪሎ የሚገኘውን የመርሐ ዕውራን ትምህርት ቤትን፤ የማኅተመ ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታልንና ደብረ ሊባኖስ የሚገኘውን የቤተ ሰሊሆም (ጡረተኞች ቤት) የያዘ ነበር፡፡
ስለየዳይሬክተሮች ቦርድ ከአንቀጽ 18-29 ድረስ ሲያትት፣ ስለየበላይ ጠባቂዎችም ቦርድ አቋቋምና ኃላፊነት በተመለከተ  ከአንቀጽ 30 – 33 ባሉት አናቅጽት ሥር በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ከሁሉም በላይ፣ የበጎ አድራጎት ቻርተሩ (የአደራ መስጫ ሰነዱ) ሚስጢራዊ አልነበረም፡፡ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ታትሞ ወጥቷል፡፡ ከታኅሣሥ 15 ቀን 1952ዓ.ም ጀምሮም አዋጁ ተፈፃሚ እንደሆነ በግልጽ ደንግጓል፡፡ ለምን “ግልጽነታችንና ተጠያቂነታችን እያደር እያሽቆለቆለ”  እንደሄደ ያሳብቃል፡፡ በተጨማሪም፣ የምናቋቁማቸው ድርጅቶች ርዕይና ዓላማም ምን ያህል እየኮሰሱ እንደሔዱ ደህና አድርጎ ያሳያል፡፡ የጽናት፣ የበጎ ፍቃድ ማጣትና የጥድፊያ ነገር ምንያህል ቀልበ-ቢስ እንዳደረገንም የቻርተሩን መግቢያ ብቻ ማንበቡ ይጠቁማል፡፡
እንዲህ ይላል፤ “ሞዓ አንበሳ ዘእነገደ ይሁዳ፤ እኛ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ፤ ለመጣቶች፣ ለሽማግሌዎች፣ ለሕመምተኞች፣ ለአካለ ስንኩሎች፣ የአካል ወይም የምግባር ተሐድሶ ለሚያሻቸውና የገንዘብ ዐቅማቸው የማይፈቅድላቸው ከመሆኑ የተነሣ ከችሎታቸው ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ትምህርት ለማግኘት ለተሳናቸው ሰዎች በሚደረገው እርዳታና በትምህርት፤ በሳይንስና በሥነ ጥበብም መስፋፋት ረገድ የሚያሳየው አርአያነት ለሕዝብ አስፈላጊ፤ ለአገርም ጠቃሚ በሚሆኑት ነገሮች ሁሉ ቀዳሚና አበረታች በመሆን ለምንወዳት ኢትዮጵያ ጽኑ ኃይልንና ምግባራዊ መሪነትን የሚሠጥ፤ እንደዚሁም ደግሞ እኛም የምንወደውን የሕዝባችንን ደኅንነትና የእድገት እርምጃ ለማጎልመስ በሕይወታችን ዘመን ለፈጸምነው መሥዋዕትነትና ጥረት ዘላቂ መታሰቢያ የሚሆን አንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት ለማቋቋም አስበን፤ ቀጥሎ ያለውን ቻርተር (የአደራ መስጫ ሰነድ) እንዲወጣ አዘናል፡፡” ይላል፡፡ ምን ጭማሪ ያስፈልገዋል?! ራሱን በራሱ ገላጭ ነው፡፡
በዚህ ቻርተር መሠረት ተቋቁሞ ለአስራ አምስት ዓመታት ያህል ሢሠራ ከቆየ በኋላ፣ በወርኃ ጥቅምት 1967ዓ.ም ጊዜያዊ ታደራዊ አስተዳደር ደርግ፣ መመሪያውን ሶሻሊዝም ባደረገ ሰሞን፣ የቀ.ኃ.ሥ በጎ አድራጎት ድርጅትንም “ለሕዝብ ጥቅም” በሚል ሽፋን፣ በአንድ የመሰቀጥጥ ማርሽ በታጀበ አዋጅ ወረሰው፡፡ ያ፣ ታላላቅ የሀገርና የአኅጉር አርኣያነት ያላቸውን ግለሰቦችና ድርጅቶች ሲያበረታታ የነበረው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፌሎውሺፕም አብሮ ከሰመ፡፡ ይኼው እስከዛሬም ድረስ ኢትዮጵያውያን የታወቀና የታመነ፣ ባለሙያዎችናና የሀገር ባለውለታዎችን የሚሸልምና የሚያበረታታ ድርጅት ሳይኖራት ሰላሣ ስምንት (38) ዓመታት ነጎዱ፡፡ ደርግ፣ የአፍሪካውያን የኖቤል ሽልማት ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን እንድ ብሩሕ ድርጅት፣ ዐይነ-ስቡን አጠፋው፡፡ (ከዚያም፣ በስልጣን ሰክሮ አቀብ-ቁልቁል ሲል ኖሮ፣ ራሱን-በራሱ አጠፋ፡፡ “አይ የንትን ችኩል ነገር፣ ካላጣው ሥጋ ቀንድ ይነክሳል” አሉ! (ደህና ሰንብቱ!)

በሳምናታዊው የአዲስጉዳይ መጽሔት ቅጽ 7፣ ቁ. 148 ላይ፤ በጥር 18 ቀን 2005 ዓ.ም የወጣ

EDITOR’S NOTE: 

The Biased and TPLF affiliated Reporter Newspaper has 

published the following article after AddisGuday /አዲስጉዳይ/ Megazine published the above article on January 26, 2013. This is an indication for the unwise decision taken by the Parliament. We still insist the Parliament and the Standing Committee of  Legal Affairs in the Parliament to investigate and/or revise its Proclamation for the benefit of the Parliament. Otherwise, it will be a disaster for the parliament and the representatives by echoing how they worship the late Meles Zenawi.

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on February 9, 2013
  • By:
  • Last Modified: February 9, 2013 @ 10:31 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar