www.maledatimes.com ፒያሣ ከቅርሶቿ አንዱን በቃጠሎ አጣች ከአንድ ቤት የሦስት ሰው ሕይወት አልፏል - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ፒያሣ ከቅርሶቿ አንዱን በቃጠሎ አጣች ከአንድ ቤት የሦስት ሰው ሕይወት አልፏል

By   /   February 10, 2013  /   Comments Off on ፒያሣ ከቅርሶቿ አንዱን በቃጠሎ አጣች ከአንድ ቤት የሦስት ሰው ሕይወት አልፏል

    Print       Email
0 0
Read Time:15 Minute, 26 Second

Written by መታሰቢያ ካሳ addis admass 
ከትናንት በስቲያ ሌሊት መሃል ፒያሣ ላይ በተነሳ ድንገተኛ የእሳት አደጋ የሦስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፣ የሰላሳ ሰባት አባወራ የመኖሪያ ቤቶችና አራት ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ በቃጠሎው ወድመዋል፡፡
በተለምዶ ሠራተኛ ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም ከሌሊቱ 9፡30 ላይ በተነሳው የእሳት አደጋ ሕይወታቸው ያለፈው የአንድ ቤተሰብ አባላት ሲሆኑ እናት ሊያሳድጓት ከገጠር ካመጧት ልጅና ከቤት ሠራተኛቸው ጋር ህይወታቸው አልፏል፡፡
ከቀደምት የፒያሣ ቤቶች አንዱ እንደነበር በተነገረለት በዚሁ ባለአንድ ፎቅ ቤት ውስጥ ከ37 በላይ አባወራዎች ከ185 የቤተሰቦቻቸው አባላት ጋር ይኖሩበት ነበር፡፡

ከጥንታዊውና ከታዋቂው ኦመር ካያም ሆቴል ጐን የነበረውና ለዓመታት ሸዋ ሆስቴል በሚል ስያሜ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ቤቱ በመንግሥት ተወርሶ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ቢሮ በመሆን ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ በ2001 ዓ.ም በዚሁ ፒያሣ አካባቢ ቅቤ ግቢ እየተባለ በሚጠራው መንደር ውስጥ በደረሰ የእሳት አደጋ ቤት ንብረታቸውን ላጡ ነዋሪዎች በጊዜያዊ ማረፊያነት ተሰጥቶአቸው እስካለፈው ሐሙስ ሌሊት ኑሮአቸውን በዚሁ ግቢ ውስጥ ሲመሩ እንደበር ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ባለፈው ሐሙስ ሌሊት መንስኤው ባልታወቀ የእሳት አደጋ ነዋሪዎቹ ቤታቸውን ከነሙሉ ንብረታቸው አጥተዋል፡፡
በቃጠሎው ነዶ የአመድ ክምር በሆነው ቤታቸው ላይ ቆመው የሀዘን እንባ ሲያፈሱ ካገኘኋቸው መካከል ከአርባ ስምንት ዓመታት በፊት በጋምቤላ ከተማ ውስጥ በደረሰ የእሳት አደጋ ሳቢያ ሀብት ንብረታቸው ወድሞባቸው ወደ አዲስ አበባ የመጡት አቶ አቡላ ኡቦኔ አንዱ ናቸው፡፡ ተሰደው የመጡባት አዲስ አበባ አቶ አቡላን አላሳፈረቻቸውም፡፡ ምቹ መኖሪያ እንዲሁም ጥሩ የመሥሪያና የንብረት ማፍሪያ ስፍራ ሆነችላቸው፡፡ የመኖሪያ ቤታቸውን ፒያሣ ቅቤ ግቢ እየባለ በሚጠራው ቦታ ላይ አድርገው ኑሮአቸውን ጀመሩ፡፡ ሀብትና ንብረትም አፈሩ፡፡ ትዳር መስርተው ልጆችም ወለዱ፡፡ ልጆቻቸውን በማሳደግና በማስተማር በዚሁ ግቢ ውስጥ ደስተኛ ኑሮአቸውን ቀጠሉ፡፡ሆኖም ከአራት ዓመት በፊት ደስተኛ ኑሮአቸውን የሚረብሽና ተስፋቸውን የሚያጨልም ክስተት ተፈጠረ፡፡ ከትውልድ ቀዬአቸው ባዶ እጃቸውን ያሳደዳቸው የእሳት አደጋ ተከትሎአቸው ኖሮ፣ የእሳቸውና የጐረቤቶቻቸው ቤት ከነሙሉ ንብረቱ በቃጠሎ ወደመ፡፡ ደግነቱ አቶ አቡላ ከባለቤታቸውና ከልጆቻቸው ጋር በህይወት ተረፉ፡፡ በወጣትነት እድሜአቸው ንብረታቸውን አውድሞ ከትውልድ ቀዬአቸው ያሳደዳቸው እሳት፤ አዲስ አበባ ድረስ ተከትሎአቸው በጐልማሳነት እድሜ ዘመናቸው ያፈሩትን ንብረት ሁሉ አውድሞ ባዶ እጃቸውን አስቀራቸው፡፡

በእሳት አደጋው ቤት ንብረታቸውን ላጡት የቅቤ ግቢ ነዋሪዎች መንግሥት ማረፊያ ሲሰጣቸው አቶ አቡላም እድሉ ደርሶአቸው ኑሮአቸውን በቀድሞ ሸዋ ሆስቴል ግቢ ውስጥ አደረጉ፡፡
በደህና ጊዜ የያዙት የኮምፒዩተር ሥራ ሙያን ከልጃቸው ጋር በጋራ እየሰሩ ኑሮን እንደገና ከዜሮ ተነስተው ጀመሩት፡፡ እንኳንም ቤተሰቦቼ ተረፉልኝ እንጂ ንብረቱን ሰርቼ አገኘዋለሁ ብለው ሥራቸውን በትጋት ቀጠሉ፡፡
እድሜ ጫናውን ለማሳረፍ ሲታገላቸው እሳቸው ጠንክረው ሲታገሉት፤ ሲወድቁ ሲነሱ ቆይተው ንብረት ማፍራት ሀብት መቋጠር ጀመሩ፡፡ መጪውን የአረጋዊነት እድሜያቸውን በሰላምና በደስታ ለማሳለፍ ጠንክረው መሥራትና ጥሪት መያዝ እንደሚገባቸው ስለሚያምኑ ሥራቸውን ከልጃቸው ጋር በትጋት ያዙ፡፡ ሦስቱ ዓመታት በሰላም አለፉ፡፡ አቶ አቡላ ደንበኞችን ማፍራት ሀብትና ንብረት መያዝ ጀመሩ፡፡ባለፈው ሐሙስ ሌሊት 9፡30 ላይ አገር ሠላም ብለው ከልጆቻቸው ጋር በተኙበት ሰላምና ተስፋቸውን የሚነጥቅ፤ ህይወታቸውንም የሚያጨልም ድንገተኛ አደጋ ተከሰተ – የእሳት አደጋ፡፡
በለበሱት ፒጃማ ብቻ ልጆቻቸውን አንጠልጥለው ከቤት ወጡ፡፡ ቤታቸው ከነሙሉ ንብረታቸው ለሦስተኛ ጊዜ ወደመባቸው፡፡ አቶ አቡላ በቃጠሎው ያጡት የራሳቸውን ንብረት ብቻ ሳይሆን ለሥራ የመጡ ላፕቶፕና ዴስክቶፕ ኮምፒዩተሮችንና ለአንድ ወዳጃቸው በአደራ የገዙትን ላፕቶፕ ኮምፒዩተር ጭምር ነው፡፡ ሲሸሹት ሲከተላቸው ሲሸሹት ሲከተላቸው ኖሮ ንብረት አልባ ያደረጋቸው እሳት፣ ዛሬም አቶ አቡላን አውላላ ሜዳ ላይ እንዲወድቁ አድርጓቸዋል፡፡ በማረፊያና በመጦሪያ ዘመናቸው ዛሬም የእሳት አደጋ ባስከተለባቸው የቃጠሎ አደጋ ሙሉ በሙሉ ንብረታቸውን አጥተዋል፡፡
ፒያሣ አራዳ ህንፃ ሥር ለዓመታት በመኪና እጥበት ሥራ ላይ ተሰማርቶ ባለቤቱንና አምስት ልጆቹን ለሚያስተዳድረው በረከት ሱሩር የትላንት በስቲያዋ ሐሙስ የተባረከች እለት አልነበረችም፡፡ እሱም እንደ ጐረቤቶቹ ቤቱ ከነሙሉ ንብረቱ ወድሞበታል፡፡
በጥልቅ እንቅልፍ ላይ በነበረበት ውድቅት ሌሊት የጐረቤቶቹ ጩኸት ነበር የቀሰቀሰው፡፡ ህፃናት ልጆቹና ባለቤቱ በአካባቢው ወጣቶችና በፖሊስ ትብብር ከቤቱ ወጥተዋል፡፡ ቤቱ እንደ ጧፍ ሲንቀለቀል ቆሞ ሀዘን በተሞላበት ዓይኑ አየው፡፡ መኪና እያጠበ ከሚያገኛት እለታዊ ገቢ ላይ እየቆጠበ ለክፉ ቀን ትሆነኛለች ያላት ሳንቲም በእሳት እየጋየች እንደነበር ለአፍታ ትዝ አለው፡፡ ግን ምን ማድረግ ይችላል፡፡ ከነልጆቹ ከእሳት ያተረፈውን አምላክ ማመስገንን መረጠ፡፡
በአካባቢው ነዋሪዎችና በፖሊሶች ጭምር ከፍተኛ ቅሬታ የቀረበባቸው የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል መቆጣጠር ኤጀንሲ ሠራተኞች፤ ከስፍራው የደረሱት እሳቱ በአካባቢው ወጣቶችና በፖሊስ ሠራዊት አባላት ትብብር ከጠፋ በኋላ ስለበር የጠፉ ሰዎችን ፍለጋ ቁፋሮ ተጀመረ፡፡ ይህ ቁፋሮ ግን በአደጋው ጉዳት የደረሰበትን ሰው ሳይሆን አቶ በረከት የተባሉ ነዋሪ ንብረት የሆነውን በሳንቲም የተሞላ ባሊ ይዞ ብቅ አለ፡፡ “ለመሆኑ ስንት ይሆናል?” ጠየቅሁ፡፡ “እኔንጃ ለብዙ ጊዜ ያጠራቀምኩት ነው፤ ምናልባት ከአራት እስከ አምስት ሺህ ሊሆን ይችላል” ሲል መለሰልኝ፡፡
እሳቱ ይህንን ያህል ጉዳትና አደጋ ሳያስከትል በቁጥጥር ስር ማዋል ይቻል እንደነበር የገለፁት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ ሌሊት ከ10 ሰዓት በፊት በአካል በመገኘት ሪፖርት ቢያደርጉም የእሳት አደጋ መኪናና ሠራተኞቹ የመጡት ከሌሊቱ 12 ሰዓት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ወደ ስፍራው የመጡት ሠራተኞች እድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆነ፣ የደከሙ እንደልብ መንቀሳቀስ የማይችሉ፣ ከመኪና ለመውረድ እንኳን ረዳትና ደጋፊ የሚፈልጉ እንደነበሩም ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ኤጀንሲ የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር አቶ ንጋቱ ማሞ ግን ይህንን ቅሬታ አጥብቀው ይቃወማሉ፡፡ አደጋው በከተማው ውስጥ ከደረሱ ከባድ የእሳት አደጋዎች መካከል የሚጠቀስ መሆኑን ጠቁመው፤ አደጋው ከዚህ የበለጠ ጉዳት ሳያስከትል እንዲጠፋ ያደረጉት የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል መቆጣጠር ኤጀንሲ ሠራተኞች ናቸው ብለዋል፡፡
በአደጋው ቤት ንብረታቸውን ያጡት ወገኖች፤ በአሁኑ ወቅት 10 ቀበሌ አዳራሽ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ የአካባቢው ህብረተሰብ በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የምግብና የአልባሳት እርዳታ በማድረግ ሰብአዊ ተግባር እየፈፀመ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ አደጋው በደረሰበት ስፍራ ላይ ተገኝተው ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ያፅናኑ ሲሆን በቅርቡም የመኖሪያ ቤት እንደሚሰጣቸው ቃል ገብተውላቸዋል፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on February 10, 2013
  • By:
  • Last Modified: February 10, 2013 @ 9:42 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar