www.maledatimes.com የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥሪ! “ክርስቲያኑ ወገናችን፣….ተሰለፍ ከጎናችን!”በሰሎሞን ተሰማ ጂ. - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥሪ! “ክርስቲያኑ ወገናችን፣….ተሰለፍ ከጎናችን!”በሰሎሞን ተሰማ ጂ.

By   /   March 9, 2013  /   Comments Off on የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥሪ! “ክርስቲያኑ ወገናችን፣….ተሰለፍ ከጎናችን!”በሰሎሞን ተሰማ ጂ.

    Print       Email
0 0
Read Time:38 Minute, 15 Second

   semanaworeq.blogspot.com

እነዚህ ጎሰኛ የሳዑዲ ወገኖች/ቅጥረኞች በጫሩት እሳት ነው-ዛሬ በርካታ ኢትዮጵያውያን  ሙስሊሞችበማዕከላዊና በቃሊቲ እስር ቤቶች የሚማቅቁት፡፡ እነዚህ ዋሀቢስቶች በጎነጎኑት ከንቱ ደባ ነው፣ ዛሬ የእስልምና ተከታዮች የገዛ መጅሊሳቸውን በመስኪዶቻቸው እንዳይመርጡ የተደረጉት፡፡ ያሳዝናል፡፡……….

***********************************

ጉደኛው ሪፖርተር ጋዜጣ ባለፈው እሑድ የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም ባወጣው እትሙ ላይ ትኩረት የሰጠው ለሳዑዲው ከፍተኛ ባለሥልጣን ንግግር ነው፡፡ ጋዜጣው በፊት ለፊት ገጹና በርእስ አንቀጹ ሥር ያወጣቸው ጽሑፎች የሳዑዲውን ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ንግግር በተመለከተ ነበር፡፡ የፊት-ለፊት ገጹ ዜና “በሳዑዲው ከፍተኛ ባለሥልጣን ንግግር የተቆጣው መንግሥት ማብራሪያ ጠየቀ” የሚል ሲሆን፣ በርእስ አንቀጹ ሥር ደግሞ “የካሊድ ቢን ሡልጣን ፀረ ኢትዮጵያ መግለጫ ገጠመኝ ወይስ መርህ?” ይላል፡፡ የሚገርመው፣ ስንትና ስንት ባለሙያዎችን አባሮ በካድሬዎቹ የተካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ሆነ ጋዜጣው ለምን የሳዑዲ ባለሥልጣናት ማብራሪያ እንዲሰጧቸው እንደጠየቁ ግልጽ አይደለም፡፡ መልሱ እቅርባቸው፣ አይናቸው ሥር ነው ያለው፡፡ (እኛ፣ ለአንባቢያኑ ይረዳ ዘንድ ነገሩን ከሥሩ ልንፈትሸው ወደናል፡፡ መልካም ንባብ ይሁንላችሁ፡፡)
በአራተኛው ምዕት ዓመት የኢትዮጵያ ቤተ-መንግሥት ክርስትናን በብሔራዊ የዕምነት ደረጃ ሲቀበል፣ አሁን “በሥልጣኔ ተራምደናል፣ በሃብት ደልበናልና የጦር ሃይል አካብተናል” የሚሉት አገሮች በአረመኔነትና በአረማዊነት (ሃይማኖት አልባነት) የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ነበሩ፡፡ በሰባተኛው ምዕት ዓመትም፣ የእስልምና ሃይማኖት በመካከለኛው ምስራቅ ሲመሠረት፣ የሃይማኖቱ ተከታዮች አዲሱን ሃይማኖታቸውን በሰላምና በፀጥታ ለማከናወን ስላልቻሉና ከፍተኛ በደልም በመዲናና በመካ ገዢዎች (የቆረሺ ጎሰኞች) ስለተፈፀመባቸው፣ የሃይማኖቱ መስራች ነቢዩ መሐመድ ራሳቸው ነበሩ፣ “ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ! እንግዳ ተቀባዮች ናቸውና ከዚያ ሄዳችሁ በሰላም ተቀመጡ!” ያሏቸው፡፡ እንደተባሉትም (በ607 ዓ.ም ወይም በአምስተኛው ዓመተ ሂጅራ) የነቢዩ መሐመድን ሴት ልጅ፣ ሩቂያን ጨምሮ፣ 12 ወንዶችና አምስት ሴቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር፡፡ (ሰርገው ሐብለ ሥላሴ፣ 1972፤ Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270፡፡ ገጽ 182)፡፡
 
የዛሬዋ ሳዑዲ አረቢያ የምትባለው አገር መሪዎች፣ (የዚያን ጊዜዎቹ የቆረሺ ጎሰኞችም) አሳደው ሊይዛቸው እስከ ቀይ ባህር ድረስ ገሥግሠው ነበር፡፡ ሆኖም፣ እነሩቂያ በሰላም አክሱም ደርሰው የሞቀና የደመቀ የዕንግዳ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡ እነሩቂያ አክሱም ከደረሱ ከሦስት ወራት በኋላም፣ በቆረሺ መሪዎችና በነቢዩ መሐመድ መኻከል የሰላም ድርድር ተደርጎ፣ “ዕርቅ ወርዷል” ሲሏቸው ተመልሰው ወደ መካ ሄዱ፡፡ ነገር ግን፣ ዕርቁ ካንገት በላይ ነበረና እንደገና በጃፋር ቢ. አቡ ጣሊብ የሚመራ 107 ወንዶችና 18 ሴቶችን ያካተተ ስደት ወደ ኢትዮጵያ ተደረገ፡፡ ይኼኛው ስደት ልጅ አዋቂ ሳይለይ የተደረገ ከመሆኑም በላይ፤ ስለኢትዮጵያ ንጉሥ ከፍተኛ የሆነ ፍትሐዊነትም የተሰማማ በመሆኑ እንደማያቋርጥ ጎርፍ ዓይነት ነበር፡፡ ባሎች ሚስቶቻቸውን አስከትለው፣ “ፍርድ ወደማይጓደልባትና ርትዕ ወደሰፈነባት ኢትዮጵያ” መትመም ተጀመረ፡፡ ከስድስተኛው ዓመተ-ሂጅራም አንስቶ፣ እስላሞች አዲሱን ሃይማኖታቸውን በሰላምና በፀጥታ በአክሱም ማካሄድ ጀመሩ፡፡ ስለዚህም፣ “የእስልምና ሃይማኖት፣ ከኢትዮጵያም አልፎ ወደአፍሪካ የገባው በኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ-በአክሱም በኩል ሆነ፤” ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡

እዚህ ላይ አንዳንድ ጥያቄዎች እንደሚነሱ አያጠራጥርም፡፡ ለመሆኑ፣ ነቢዩ መሐመድ ለምን “ወደኢትዮጵያ ሂዱ አሉ?” “እንደምንስ ስለኢትዮጵያና ስለንጉሷ ሊያውቁ ቻሉ?” የሚሉት ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው፡፡ ኢብን ቁጣቢያ የተባሉት በ881 ዓ.ም እንደገለፁት፣ “ነቢዩ መሐመድን ያሳደገቻቸው ሞግዚት (ኡማ/እማማ አይማን የተባለችው ሴትዮ)፣ ኢትዮጵያዊት ክርስቲያን ነበረች፡፡ ነቢዩ መሐመድ ከአላህ የተደረገላቸውን ጥሪ ከመቀበላቸው በፊት በነበረው ዘመን፣ በቆራሺ አረማውያን/አረመኔዎች መካከል በርካታ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በነቢዩ መሐመድ የትውልድ ሥፍራ በመካ ይኖሩ ነበር፡፡ በተለይም “ጋብር እና ያሳራ የተባሉት ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ቶራ የተባለውን የአይሁድ ቅዱስ መጽሐፍና አራቱን ወንጌላት ጮክ ብለው በሚያነቡበትና በሚያነበንቡበት ወቅት፣ ልጅ የነበሩት ነቢዩ መሐመድ በጥሞና ያዳምጧቸው ነበር”-ይላል (G. Parrinder. Jesus in the Qur’an. 1965፤ ገጽ 161)፡፡ በዚህም እውቀታቸው የተነሳ ነው፣ ነቢዩ መሐመድ በርካታ (ወደ 200 ገደማ) የግዕዝ ቃላትን በቅዱስ ቁራን ውስጥ ሊጠቀሙ የቻሉት ተብሎ ይገመታል (ሰርገው ሐብለ ሥላሴ፣ 1972፤ Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270፡፡ ገጽ 181)፡፡ ባጠቃላይ ነቢዩ መሐመድ እንኳን ቋንቋችንንና ከብዙዎቻችን ሱሪና ቀሚስ ሥር ዊን-ዊን የምትለዋን ቀጭኗን እግራችንን ሳትቀር አሳምረው ያውቋታል፡፡ ለዚህ ነው፤ በ620/1 ዓ.ም መዲናን ለመደምሰስ ዘምቶ በነበረው ጠንካራ ጦር ውስጥ አንድ አርድህ አቡ-ያሰር የተባለ ኢትዮጵያዊ የነቢዩን ተከታዮች እንቅስቃሴ በቅርብ ሆኖ እየተከታተለ ሊደምሰስም ለመጣው ጦር መረጃ ያቀብል ስለነበር፤ ነቢዩ መሐመድ “ከነዚህ እግረ ቀጫጭኖች ተጠንቀቁ!” ሲሉ አዘዙ፡፡

ያም ሆኖ፣ ነቢዩ መሐመድ ከነበሯቸው ሚስቶች ሁሉ እንደኡማ ሀቢባ የሚወዱት አልነበራቸውም፡፡ ይህቺን ኢትዮጵያዊት ለማግባት ከፍተኛ ጥሎሽ (400 የሳውዲ ዲናር ወይም 220 ፓውንድ ገደማ) ሰጥተዋል፡፡ ኢማ ሀቢባንም ተከትላ ከኢትዮጵያ መጥታ የነበረችው ለግላጋዋን ማርያምን እጅግ ይወዷት ነበር፡፡ ነቢዩ መሐመድ በጣር አልጋቸው ላይ ሆነው የመጨረሻዎቹን ሰዓቶች ያሳለፉት የኡማ ሀቢባና አኩማ ሰላማ ጋር ሆነው፣ የኡማ ሀቢባን ወግና ጨዋታ በማዳመጥ ነበር፡፡ ኡማ ሀቢባ ስለየአክሱም ጺዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያንና ጣሪያው ላይ ስለተሳሉት የቅዱሳን ስዕሎች እያወራችላቸው ነበር፡፡ ሰር ሙይር የተባለው ተመራማሪ እንደገለጸው፣ “የቅዱሳኑ ሥዕል ነገር” ነቢዩ መሐመድን አላስደሰታቸውም ነበር፡፡የመጀመሪያው ሙዓዚን፣ ቢላልም ቢሆን ኢትዮጵያዊ ነበር (Sir W.Muir. The Life of Mohammad. 1923፤ ገጽ-490)፡፡

ከላይ እንደጠቆምነው፣ በምድረ ኢትዮጵያ ክርስትናና እስልምና ከሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንስቶ  ከዘመን ወደ ዘመን በአንድነት ሲሸጋገሩ ቆይተዋል፡፡ በመሃልም፣ የሥልጣን ትንቅንቆች ቢኖሩም፣ እንደግራኝ መሐመድ ባሉት የጦር መሪዎች አነሳሽነት፣ ከፍተኛ ጉዳት በሁለቱም ሃይማኖት ተከታዮች በኩል ተከስቷል፡፡ ከጀርባ የነበሩት አጫፋሪዎችም የኦቶማን ቱርክና የተወሰኑ የአረብ ነጋዴዎች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም፣ ላለፉት 1,400 ዓመታት ያህል ዕልቂቱን በጋራ አልቀንበታል፡፡ ችግሩንም በጋራ ተቸግረን፣ በጋራም ተወጥተናል፡፡ አሁን ለደረስንበትም የለውጥና የተስፋ ዘመን በጋራ ደርሰናል፡፡ በኢትዮጵያዊነታችንም፣ የጋራ የሆኑ የመልካም አስተዳደር፣ የእኩልነትና የመብት ረገጣ ችግሮችን ባንድነት ተጋርተናል፡፡ ገዢዎቻችን ከሥልጣናቸው ውጭ የሚታያቸውና የሚያልሙት አንዳችም ነገር ስለሌላቸው፣ ዝንት-ዓለም ዜጎች እንደተበዘበዙና እንደቆረቆዙ ኖረዋል፡፡ ገዢዎቹ፣ “ክርስቲያኖች ነን! ወይም እስላሞች ነን!” ይበሉ እንጂ ለሕዝቡ የሚበጅ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ጭላንጭል አላሳዩም፡፡ የመጡት ሁሉ፣ በለከፋቸው የሥልጣን ዛር-ፈረስ ተኮፍሰው፣ ለክርስቲያኑ ወይም ለእስላሙ የሚያደሉ ቢያስመስሉም ሕዝቡ አልተጠቀመም፡፡ እነርሱ የሥልጣን ኮርቻቸውን ከማደላደል የዘለለ እንዳችም የሃይማኖት ወይም የዕምነት ወገንተኝነት ያላቸው አልነሩም፡፡ አይዱምም፡፡

የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በአሁኑ ጊዜ በርካታ የዲሞክራሲያዊ መብትና የእኩልነት፣ የፍትሕና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ማቅረብ ከጀመሩ፣ (ባለፈው ጥር 2005) ድፍን አንድ ዓመት ሆናቸው፡፡ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ዛሬም ሆነ ትናንት ያቀረቧቸው የመብት ጥያቄዎች በኢትዮጵያዊነት መንፈሥ ለጋራ ዕድገትና ለጋራ ዓላማ የታቀዱ ሲሆን፣ የተሳሳተና ሌላ ትርጉም ሲሰጣቸው ይታያል፡፡ ከስህተትነትም አልፎ፣ “ጅሃዳዊነት” አድርጎ የማቅረብም ዘመቻ/ውንጀላም ተካሂዷል፡፡ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ የወንዙ ወኃ ሲደፈርስ ዓሣ ለመያዝ የውሸት መቃጥንና መረብ የሚጥሉና አዳፋ እጃቸውንም አሾልከው የሕዝቡን አጀንዳ ለመቀልበስ ወይም ለመሸወድ የሚሞክሩ ወገኖች አሉ፡፡ አንዴ “ጂሃድ”፣ ሌላ ጊዜም “ሃረካት”፣ ሲያሰኝ ደግሞ “አኬልዳማ” እያሉ በግብር ከፋዩ ሕዝብ ጊዜና ገንዘብ ላይ ማፌዝ አያዛልቅም፡፡

እስከምናውቀው ድርስ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞ ጥያቄ ውስጥ-ውስጡን መነሳትና መቀጣጠል ከጀመረ አርባ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የዛሬ 39 ዓመት ገደማ በሚያዝያ 01 ቀን 1966 ዓ.ም፣ ከአዲስ አበባ መጊዶች የተውጣጡ የእስልምና ሃይማኖት ተወካዮች፣ ለዚያን ጊዜውን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልካቸው መኮንንን ባለ13 ነጥብ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን አቅርበው ነበር፡፡ በሚያዝያ 10 ቀን 1966 ዓ.ም (በዕለተ ሐሙስ)፣ ተወካዮቹ ጠቅላይ ሚኒስሩን በድጋሚ አነጋግረው ነበር፡፡ በውይይቱም ወቅት፣ ከተጠየቁት ጥያቄዎች መካከል ሰባቱ አዲስ በሚረቀቀው ሕገ-መንግሥት ላይ የሚሻሻሉ እንደሆኑና ሌሎቹን ጥያቄዎች ግን በአፋጣኝ ለመመለስ የሚቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ጠ/ሚ/ሩ ቃል ገቡ፡፡ ሆኖም፣ በመልሱ ያልረኩት ተወካዮች ከአንድ ቀን በኋላ ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 12 ቀን 1966 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ከታላቁ አንዋር መስጊድ ተነስተው በቡድን በቡድን እየሆኑ፣ በአትክልት ተራ አድርገው፣ በሲኒማ ኢትዮጵያ አልፈው፣ የልዑል ራስ መኮንንን ድልድይ ተሻግረው አራት ኪሎ አደባባይ ደረሱ፡፡ ከዚያም በታላቁ ቤተ-መንግሥት በኩል አድርገው በውጭ ጉዳይና በእዮቤልዩ ቤተ-መንግሥት በኩል ወርደው መስቀል አደባባይን አለፉና ወደ ለገሃር አቀኑ፡፡ በመቀጠልም፣ ወደብሔራዊ ቴያትር የሚወስደውን መንገድ ይዘው የቴድሮስ አደባባይን ካለፉ በኋላ በመዘጋጃ ቤት ፊት-ለፊት ወደአንዋር መስኪድ ተመለሱ፡፡ ሰላማዊ ሰልፉም ያላንዳች ሁከትና ረብሻ በሰላም ተጠናቀቀ (አዲስ ዘመን፤ ሚያዝያ 13 ቀን 1966 ዓ.ም፤ ገጽ 1 እና 2)፡፡

እንደአዲስ ዘመን ዘገባ፣ ሠልፈኞቹ ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ይገመቱ ነበር፡፡ ሽማግሌዎች፣ ባልቴቶች፣ ጎልማሶችና ወጣቶች ተካፋዮች ነበሩ፡፡ እሊህ ሠልፈኞች፣ ልዩ ልዩ መፈክር ያለባቸውን የጽሑፍ ሰሌዳዎች የያዙ ሲሆን መዝሙሮችንም ይዘምሩ ነበር፡፡ ከያዟቸውም የጽሑፍ ሠሌዳዎች መካከል፣ “ሃይማኖት ከመንግሥት የአስተዳደር አካልነት ይገለል! ኢትዮጵያ በሃይማኖትና በዘር ልዩነት መከፋፈል የለባትም! የሃይማኖት እኩልነት ለዘላለም ይኑር! ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ደሴት ናት! የአንድነት መሠረቱ እኩልነት ነው፡፡ እኩልነት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ! የእስላም በዓል የብሔራዊ በዓል ይሁን!” ወዘተርፈ፣ የሚሉ መፈክሮችን ከፍ ባለ ድምጽ ያሰሙ ነበር፡፡ በተጨማሪም፣ ሠልፈኞቹ መዝሙሮችንም ያሠሙ ነበር፡፡ “ሀገር የጋራ ነው፣ ሃይማኖት የግል ነው፤ የሚለው መሪ ቃል፣ ቢሠራበት ምነው?” የሚለውን ዜማ በተደጋጋሚ አሰምተዋል፡፡ እንዲሁም፣ “ክርስቲያኑ ወገናችን፣ ተጠብቆ መብታችን፤ እንድንሠራ ላገራችን፣ ተሰለፉ ከጎናችን!” የሚልም ዝማሬ ያሰሙ ነበር፡፡

ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (ያሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ)ና ከተለያዩ የአዲስ አበባ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች ከበርካታ ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ሰልፈኞቹን አበረታተዋል፡፡ በተለይም ሚያዝያ 27 አደባባይ (የትምህርት ሚኒስቴር ሕንፃ ፊት-ለፊት) ተሰብስበው የእስልምና ተከታዮቹን የዓለማ መንፈሥ በመደገፍ “ኢትዮጵያ የሁላችን፣ እኩል ይሁን መብታችን፤ እንድንሠራ ላገራችን፡፡” በማለት የመልስ ኅብረ-መዝሙር አሰምተዋል፡፡ በመዝሙሮቹ ውስጥ እንደተገለጸው፣ ኢትዮጵያ የሁላችን ቤት ናትና፣ አድሎና ፍርደ-ገምድልነት ተወግዶ፣ በእኩልነት እንድንኖር ጎን ለጎን መሰለፍ ያስፈልጋል፡፡

ይህ የእኩልነት፣ መብትና የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነፃነት ጉዳይ ህገ መንግሥታዊ መብት ነው፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 25፣ መሠረት የእስልምና ተከታዮች የእኩልነት መብታቸውን ነው እየጠየቁ ያሉት፡፡ በአንቀጽ 27ም መሠረት፤ የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነፃነት ጥያቄ ነው ያቀረቡት፡፡ በተጨማሪም፣ በአንቀጽ 30 መሠረት፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የመድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብታቸውን ነው የሞገቱት፡፡ ሁሉም ሕገ-መንግሥታዊ መብት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ የሚነሣው የዋህቢዝም አስተምህሮትና እርሱን ለማስረጫም የአወሊያ ትምህርት ቤትን መጠቀሚያ ስለማድረጋቸው ተደጋግሞ ይነሣል፡፡ ይህ ትምህርት ቤት እንደሚታወቀው በሳዑዲ ተወላጆች (በቆረሺ ጎሰኞች) አማካይነት የተመሠረተ መ.ያ.ድ (NGO) አንድ ክንፍ ነው፡፡ እርግጥ ነው ከትምህርት ቤቱ ጋር ተያይዞ መስጊድ አለው፡፡ የረብሻው መነሻ የሆነውም ይሄንን ትምህርት ቤትና መስጊድ ሚና በሚያወሳስቡ የሳዑዲ ተወላጆች/የተገዙ ቅጥረኞች ሴራ ነው፡፡እነዚህ ጎሰኛ የሳዑዲ ወገኖች/ቅጥረኞች በጫሩት እሳት ነው-ዛሬ በርካታ ኢትዮጵያውያን እስላሞች በማዕከላዊና በቃሊቲ እስር ቤቶች የሚማቅቁት፡፡ እነዚህ ዋሀቢስቶች በጎነጎኑት ከንቱ ደባ ነው፣ ዛሬ የእስልምና ተከታዮች የገዛ መጅሊሳቸውን በመስኪዶቻቸው እንዳይመርጡ የተደረጉት፡፡ እጅግ ያሳዝናል፡፡

ይኼው የዋሃቢስቶቹ መፍጨርጨርና መሳከር የሚጀምረው ከ1933 á‹“.ም ነው፡፡ እንደሚታወቀው እስከ 1928 á‹“.ም ድረስ ግብጽ የኢትዮጵያን ቤተ-ክርስቲያን በፕትርርክና ትመራ በነበረበት ወቅት፣ የኢትዮጵያንም እስልምና እንደፈለገችው ትሰልቀው ነበር፡፡ ሆኖም፣ በ1928 á‹“.ም ጣሊያን ኢትዮጵያን ሲወር፣ ልፍስፍሱና ለሆዱ ያደረው አቡነ ቅርሎስ ከግራዚያኒ ጋር ስላበረ፣ የኢትዮጵያ አርበኞች ሰውዬውን/አቡኑን ካገር አባረሩት፡፡ በሃይማኖት የተተገነው የኢትዮጵያና የግብፅም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ቅርቃር ውስጥ ገባ፡፡ ነገሮች እስኪሻሻሉም ዘጠኝ ዓመታት ያህል ፈጁ፡፡ በዚህ ቀዳዳም ተጠቅማ፣ ሳዑዲ ዋሀቢዝም የሚባለውን አክራሪ የእስልምና ዘርፍ ወደባሌና ወደአሩሲ ክፍለ ሃገሮች በእርዳታና በበጎ አድራጎት ስም አስገባች፡፡ አንዴ ያዝ፣ ሌላ ጊዜ ለቀቅ ያደርግ የነበረውም የግብፆች ተፅዕኖ በደርግ ዘመን ሙሉ ለሙሉ ቅጥ-አምባሩ ሲጠፋ፣ ግርግር ለሌባ ይመቻልና፣ ሳዑዲ በቴምርና በልባሽ ጨርቆች አማካይነት የኢትዮጵያን ሙስሊሞችማማለል ጀመረች፡፡ በተለይም፣ ከ1981 ጀምሮም፣ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መረጃና ደህንነት ሰዎች በተለያዩ ሥራዎች ስለተጠመዱላቸው፣ ለሃጂና ኡምራ የሚሄዱትን የዋህ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ዳጎስ ባለ ማህለቅና ዲናር  መሸንገል ጀመረች፡፡ “በየአምስት ኪሎ ሜትሩም አንድ መስኪድ!” የሚል ህቡዕ እቅድ ነድፋ እንደልቧ መፈንጨት ጀመረች፡፡ በተለይም በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልሎች ውስጥ ቁጥራቸው የበረከቱ መስኪዶች በጠፍ – ጨረቃ መሰራት ጀመሩ፡፡ ለዚህም ተጠያቂ የሆኑትን የከተማ ከንቲባዎችና የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ኢህአዲግ/ወያኔ በወቅቱ ባለመቆጣጠሩ ችግሩ እየከፋ ሄደ፡፡
ይሄው የሳዑዲ ቅብጠትም ከልክ በላይ ደርሶ የአቶ ጁነዲን ሚስትና የሌሎች ታዋቂ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ኤምባሲያቸው ድረስ በመጥራት ከፍተኛ ገንዘብ በተለያዩ ቁሳቁሶች ውስጥ እየሸሸጉ እንዲያወጡ በማድረግ ሥራ ላይ ተጠምዶ ቆየ፡፡ በተለይም፣ በ1993፣ በ1997 እና በ2003/4 ዓ.ም ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ከሳዑዲ ወደኢትዮጵያውያን እጅ በህቡዕ ገባ፡፡ እነዚህ ጊዜዎች ለምን እንደተመረጡ የማይገምት ይኖራል ብለን አናምንም፡፡ ካለ ግን፣ በኢህአዲግ መራሹ መንግሥት መሪዎች መካከል ያልተረጋጉ የስልጣን ትግሎች ስለተከሰቱ፣ የመረጃና የደኅንነቱም መሥሪያ ቤት የቤቱን ሸረሪት ድር የሚያጸዳበት ወቅት ላይ ነበር፡፡ ስለሆነም፣ እንደአቶ ጂኔዲ የመሳሰሉትን የሳዑዲ ቅጥረኞች ለውስጣዊው ፖለቲካ ፍጆታ ሲል አንድም አይቶ እንዳላየ አለፋቸው፤ ወይም ደግሞ የትም አይደርሱም ብሎ ተዋቸው፡፡ ሆኖም የሙስሊሙ ጥያቄ እየበረታ ሲሄድና ዓለም አቀፋዊ ቅርጽን ሲይዝ፣ ይይዝ ይጨብጠው አጣ፡፡ (“ባያዩኝ እሰርቅ፣ ቢያዩኝ እስቅ!” ይላል ተብሎ የሚጠበቀው አቶ ጁኔዲ፣ ሲያቀብጠው “ሚስቴን ፍቱልኝ፣ ኦናው ቤት ቀፈፈኝ!” አለና ከሁሉም ኃላፊነቶቹ በጠፍ-ጨረቃ ተባረረ፡፡ ጥቂት ቀናት ካወላዳም በኋላ በቅርብ ጓደኞቹ አማካይነት ለህክምና ብሎ ሳዑዲ-ሪያድ ሄዶ ሰነባበተ፡፡)
እንግዲህ የሰሞኑ የሳውዲው ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ዲስኩር የሚመጣው እዚህ ጋር ነው፡፡ ሚኒስትሩ በአንድ ዲንጋይ ሁለት ወፍ ለመምታት ስለከጀለ፤ “ኢትዮጵያ እየሠራችው ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሱዳንንና ግብፅን የሚጎዳ ነው” አለ፡፡ የሱዳኑን እንተወውና ስለግብፅ ጉዳይ ለመናገር የደፈረው፣ ከላይ እንዳየነው፣ የእትዮጵያውያንን

ሙስሊሞች ጉዳይ ከ1933 ዓ.ም ወዲህ ከግብፅ መንግሥት የተረከብኩትና በሞግዚትነት የማሳድገው እኔ ነኝ ከሚል እብሪት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃም፣ የዓባይን ውኃ ጉዳይ በማንሳት ከግብፅና ከሱዳንም በተጨማሪ ሌሎች የአረብ አገሮችንም ጠላት አድርጎ ሊገዛልን ያለመ ነው፡፡ (“በግብፅ አመካኝቶ፣ ይናገሯል ደንፍቶ!” ማለት ይሄንን ነው፡፡) ከሁሉም-ከሁሉም ደግሞ፣ የሚኒስትሩ ንግግር፣ ምንቅርቅሩ በወጣው የሳዑዲ መ.ያ.ዶች (NGOs) ጉዳይ በሪያድ ባለስልጣኖች ዘንድ ተስፋ-ቢስነትንና ከፍተኛ ብሽቀትን እንደፈጠረም ያሳብቃል፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው፣ ለምሳ ግብዣ ወይም ለራት ግብዣ እየተጠሩ፣ በትልልቅ የብረት ድስቶች እየደበቁ የሚያጡት ባለሥልጣኖችና ሚስቶቻቸውም፣ “ጁኔዲንንና ሚስቱን ያየ፣ በእሳት አይጫወትም!” የማለታቸው ሪፖርት ከአዲስ አበባ ተነስቶ ሪያድ ሲደርስ የተፈጠረውን ድብልቅልቅ ስሜት ነው ሰውዬው ያመለጠው፡፡ በተጨማሪም፣ በጥር ወር ሽብርተኝነትን በገንዘብ የሚረዱ አካላትን ለመቆጣጠር የተረቀቀው አዋጅ ለማን እንደተዘጋጀ ስለገባቸው፣ አዲስ አበባ ያሉት የሳዑዲ ወኪሎችና ቅጥረኞቻቸው በእጅጉ ተረበሹ፡፡ (የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ታዲያ፣ እነዚህን ፍንጮች ይዞ፣ የሳዑዲ አረቢያን መንግሥት አቋም በመረዳት ፈንታ ለምን ማብራሪያ ከሪያድ እየጠበቅኩ ነው ይላል?) ውድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆይ፣ ባለችኝ የትርፍ ሰዓት ብትቀጥሩኝ/ብትፈቅዱልኝ አብጠርጥሬ እንደምተነትንላችሁ አልጠራጠርም፡፡ በደንብ አስቡበት፡፡ (የሳምንት ሰዎች ይበለን!)

በሳምናታዊው የአዲስጉዳይ መጽሔት ቅጽ 7፣ ቁ. 154 ላይ፤ በየካቲት 30 ቀን 2005 ዓ.ም የወጣ ነው::

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on March 9, 2013
  • By:
  • Last Modified: March 9, 2013 @ 9:33 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar