www.maledatimes.com “ነብዩ ኤልያስ በአራት ኪሎ”በዲያቆን ዳንኤል ክብረት ከ አዲስ ጉዳይ መጽሔት - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

“ነብዩ ኤልያስ በአራት ኪሎ”በ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ከ አዲስ ጉዳይ መጽሔት

By   /   March 18, 2013  /   Comments Off on “ነብዩ ኤልያስ በአራት ኪሎ”በ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ከ አዲስ ጉዳይ መጽሔት

    Print       Email
0 0
Read Time:43 Minute, 32 Second

ተዋናይት ጀማነሽ ሰለሞን የካቲት 25 ቀን 2005 ዓ.ም ለአዲስ ጉዳይ መጽሔትና ለሌሎች ሚዲያዎች በበተነችው ጥሪ “የኢትዮጵያ ትንሳኤ ሊያረጋግጥ ኃያል ባለስልጣን ቅዱስ ኤልያስ ከብሔረ ሕያዋን መጥቷል”ብላለች፡፡ ጀማነሽ “ይህንን እጅግ ታላቅ አስፈሪና ጥልቅ ሃይማኖታዊ ምስጥር በተመለከተ ትንታኔና ትምህርት የሚሰጥበት ጉባኤ ከጽዋ ማኅበሬ ጋር በመሆን አዘጋጅቻለሁና በኢግዚቢሽን ማዕከል ተገኝታችሁ ተካፈሉልኝ” በማለት ነው ግብዣውን የላችው፡፡ በግዕዝ በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ በተጻፈውና ማኅበረ ሥላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ .. ብሎ የሚጀምረው  የጽዋ ማኅበሯ አማካኝነት በበተነችው ጥሪዋ “በጉባኤው የኢትዮጵያ ትንሳኤ ይታወጃል” ብላለች፡፡ የተለያዩ አርቲስቶችና ሌሎች ታዋቂ ሰዎች እየተሳተፉበት መሆኑ የሚነገረው በዚህ ጉባኤ ላይ  የተለያዩ ወገኖች ጥያቄ በማንሳት ላይ ይገኛሉ፡፡በብዙዎች ዘንድ ይህ እንቅስቃሴ ከዚህ ቀደም ተሐድሶ በሚል ስያሜ እንደተካሄደው ዓይነት በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጥላ ስር አዲስ ሃይማኖት ፤ አዲስ አስተምህሮ የመመስረት አላማ ያለው ነው የሚል አስተያየት እየተሰነዘረበት ነው፡፡ ለመሆኑ ይህ “ተዋሕዶ” የሚል ስያሜ በመካሄድ ላይ ያለው እንቅስቃሴ ከኦርቶዶክስ እምነት አንጻር ምን ያህል ተቀባይነት አለው? የነብዩ ኤልያስ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትስ ምን ያህል ተዓማኒ ነው? የዚህ እንቅስቃሴ መሰረታዊ ባህርያት ምን ምን ናቸው? እነዚህንና ሌሎች ጥያቄዎች እንዲመልስን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን  የእምነት መሰረቶችና ከኦርቶዶክስ ሃይማኖት ጋር የተያያዙ በርካታ መጽሀፍት ደራሲ የሆነው ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ጋብዘናል፡፡

ዲ/ን ዳንኤል ከላይ ያነሳናቸውን ጥያቄዎች ተንተርሶ በላከልን ጽሁፍ በርካታ ጉዳዮችን ይዳስሳል፡፡ “ነብዩ ኤልያስ ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል የሚለው” ጉዳይን በመሰረቱ በመፈተሸ ሃይማኖታዊ ትንታኔ ሰጥቶበታል፡፡
ሰሞኑን በከተማችን አዲስ አበባ “ነብዩ ኤልያስ መጥቷል ፤ የአለም ፍጻሜ ቀርቧል”  የሚሉ አካላት ተነስተዋል፡፡ እነሱ እንደሚሉት ነብዩ ኤልያስ መጥቶ አዲስ አበባ ይገኛል፡፡ ቤተመንግሥቱንና ቤተክህነቱን ለማጥራት ተዘጋጅቷል ፡፡ ከሚያጠራቸው የቤተክህነት ጉዳዮችም ሦስቱ ትኩረት አግኝተዋል ይላሉ፡፡ “የመጀመሪያው ኦርቶዶክስ የሚለው ስም ስህተት ነው  ፤ ስማችን ተዋህዶ ነው ፤ መለበስ ያለበት ልብስ ነጭ ብቻ ነው ፤  እሱም ቢሆን ጥለቱ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ መሆን መቻል አለበት ፤ አሁን ያሰርነውን ክር በመበጠስ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ክር ማሰር አለብን” የሚል ነው፡፡ በየአጋጣሚው ቤተክህነቱንና ቤተ መንግሥትን በመንቀፍ አሁን የሚታዩትን ችግሮች መሰረት አድርጎ ህዝቡ መጥቷል የተባለው ኤልያስን መከተል እንጂ ወደ ቤተክርስቲያን መሄዱ ጥቅም እንደሌለው እየተነገረ ነው፡፡ የሚከናወኑ ማናቸውም የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችም የኤልያስን መምጣት የሚያመላቱ እንጂ ምዕመና ሊሳተፍባቸው የሚገቡ አለመሆናቸው ይነገራል ፡፡ እስኪ እነዚህ ነገሮችን በዝርዝር እንመልከታቸው፡፡
ኤልያስ ማነው?
ኤልያስ ማለት “እግዚአብሔር አምላክ ነው” ማለት ነው፡፡ከክርስቶስ ልደት በፊት በስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ከእስራኤል የተነሳ ነብይ ነው፡፡ኤልያስ የሚታወቀው በሶስት ሃይማኖታዊ ተግባሮች ነው፡፡የመጀመሪያው በእስራኤል ተንሰራፍቶ የነበረውን የባአድ አምልኮ ያጠፋና አምልኮተ እግዚአብሔርን ያጸና መሆኑ ሲሆን ፤ ሁለተኛው ደግሞ ንጉስ አክአብ አሕዛባዊት ኤልዛቤልን አግብቶ ይፈጽም የነበረውን ግፍና ጥፋት ሳይፈራና ሳያፍር ፊት ለፊት የገሰጸና ለእውነት ብቻ የቆመ ነብይ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ አቋሙ ምክንያት በሰሜን እስራኤል በሚገኙ ሰንሰለታዊ ተራሮች ፈፋ ለፈፋ ሲንከራተት ኖሯል፡፡ መጀመሪያ ቁራዎች ሲመግቡት ቆይተው ከዚያ በሰራፕታ የምትገኝ አንዲት መበልት አገልግለዋለች፡፡
ይህ ቆራጥነቱና ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቋሚ መሆኑ በእግዚአብሔር ዘንድ ባስገኝለት ሞገስ የተነሳ ኤልያስ ከኄኖክ ቀጥሎ ሳይሞት ወደ ብሔረ ሕያዋን በመወሰዱ ይታወቃል፡፡ ዮርዳኖስን ወንዝ ከደቀ መዝሙሩ ከኤልሳዕ ጋር ከተሻገረ በኋላ የእሳት ሰረገላ መጥቶ ኤልያስን ወስዶታል፡፡ ይህ ኤልያስ የሚታወቅበት ሦስኛው ነገር ነው፡፡
ኤልያስ ይመጣል ?
ከ470 እስከ 440 በኢየሩሳሌም ትንቢት የተናገረው ነብዩ ሚልኪያስ “የእግዚአብሔር ቀን ነብዩ ኤልያስን እልክላችኋለሁ” ብሎ ትንቢት ተናግሮ ነበር፡፡ (ሚል 4፤5) ይህንንም በመያዝ አይሁድ በፋሶች ፤ በግሪኮች ፤ በሶሪያውያንና በሮማውያን መከራ በተፈራረቁባቸው 400 ዓመታት ውስጥ ነብዩ ኤልያስን ሲጠባበቁት ነበር፡፡ በየምኩራባቸውም የኤልያስ መንበር የተባለ ከፍ ብሎ የተሰራ ባለ መከዳ ወንበር ያስቀምጡ ነበር፡፡ ከክርስቶስ ልደት 6 ወራት ቀድሞ ተወለደውና  ከበረሀ የመጣው መጥምቁ ዮሐንስ በብዙ መልኩ ኤልያስን ይመስለው ስለነበረ የተወሰኑት የአይሁድ ክፍሎችና በኋላም ክርስቲያች ይመጣል የተባለው ነብዩ ኤልያስ እርሱ ነው ብለው ተቀብለውታል፡፡
ዮሐንስ መጥምቅ እንደ ኤልያስ ሁሉ በርኽኛ ባህታዊ ነው፡፡ እንደ ኤልያስ ሁሉ ጸጉር የለበሰ ነው ፤ እንደ ኤልያስ ሁሉ እስራኤል ተስፋ የቆረጠችበት ዘመን የመጣ ነው ፤ እንደ ኤልያስ ሁሉ ሄሮድስን ሳያፍርና ሳይፈራ የገሰጸ ነው ፡፡ በእነዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች መጥምቁ ዮሐንስ ኤልያስን ይመስለው ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይመጣል የተባለው ኤልያስ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑን መስክሮለታል፡፡(ማቴ 11፤14 17፤10-13 ፤ ሉቃ 1፤17)
ስለ ኤልያስ መምጣት የሚነግረን ሌላው መጽሀፍ የዮሐንስ ራዕይ ነው፡፡ ዮሐንስ ራዕይ በምዕራፍ 11 ላይ ዓለምን የሚያጠፋው ሀሳዊ መሲህ  ከመጣ በኋላ ዙፋኑን አደላድሎ የዓለምን ክርስቲያኖች ሲጨርስና ምስክር ሲጠፋ ሁለት ምስክሮች መጥተው 1260 ቀናት ምስክርነት እንደሚሰጡና በመጨረሻም በሐሳዌ  መሲህ እንደሚገደሉ ይገልጣል፡፡ ከሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተነሱ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እነዚህን ሁለት ምስክሮች ኄኖክና ኤልያስ መሆናቸውን ተርጉመዋል፡፡
ሐሳዊ መሲሕ ሲነሳና ሁሉንም እንደ ሰም አቅልጦ እንደ ገል ቀጥቅጦ ሲያጠፋ ፤ ለእውነት የሚመሰክርም ሲጠፋ ፤ ምዕመናንም በሚደርሰው መከራ ምክንያት የሚከተሉት የእምነት መንገድ  “ስህተት ይሆን…” ብለው ሲጠራጠሩ እነዚህ ሁለቱ ሳይሞቱ ወደ ብሔረ ሕያዋን ያረጉ ነብያት መጥተው እውነትን በመመስከርና የሐሳዌ መሲሕን ነገር በማጋለጥ ምስክርነታቸውን በደም እንደሚያጸኑ የሊቃውንቱ ትርጓሜ ያብራራል፡፡
ዮሐንስ አፈወርቅ ፤ አቡሊዲስ ዘሮምና ቪክቶሪያንስ እንደሚገልጡት ኤልያስና ኄኖክ በኢየሩሳሌም ያስተምራሉ ፤ በኢየሩሳሌም ተዓምራት ያደርጋሉ ፤ በኢየሩሳሌም ይገደላሉ ፤ በኢየሩሳሌም ይነሳሉ ፤  በኢየሩሳሌም ያርጋሉ ፡፡ ይህም ለጌታችን መምጣት የመጨረሻው ምልክት ነው፡፡ ከኤልያስና ኄኖክ  መምጣት በኋላ የሚጠበቀው የክርስቶስ ለፍርድ መምጣት ነው፡፡
ነብዩ ኤልያስ  በአራት ኪሎ
በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ነብዩ ኤልያስ መጥቷል ይባላል፡፡ የሚኖረው አራት ኪሎ ነው፡፡ አንዳንድ ታዋቂ የሆኑ ሰዎች  በተለይም አርቲስቶች ተከታዮች ሆነናል ይላሉ፡፡ ይህንን ሁኔታ ከቅዱሳት መጻህፍትና ከሊቃውንት ትምህርት ጋር ስናነጻጽረው ትክክል ሆኖ አናገኝውም፡፡
መጀመሪያ ነገር ኤልያስ ብቻውን አይመጣም፡፡ በነብዩ ሚልኪያስ ለብቻው እንደሚመጣ  የተነገረለት  ኤልያስ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑን ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ስለ መሰከረ ሌላ ምስክር ማምጣት አያስፈልግም፡፡  በሌላ በኩልም አሁን መጥቷል ተባለው  በመጨረሻው ዘመን የሚመጣው ኤልያስ  ከሆነ ደግሞ እንደ ሊቃውንቱ ትምህርት ብቻውን አይመጣም ፤ አብሮት ኄኖክም ይመጣል፡፡ አሁን ግን  ኤልያስ ከኄኖክ ተነጥሎ ነው መጣ የተባለው፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ነብዩ ኤልያስ የሚመጣበት ጊዜ በራዕይ ዮሐንስ ላይ ምዕራፍ 11 ተገልጧል፡፡  አስቀድሞ ሐሳዊ መሲህ ይመጣል፡፡ ዙፋኑንም በተቀደሰችው ከተማ በኢየሩሳሌም ይዘረጋል፡፡ ምዕመናንም(በተለይም የስድስት ስድሳ ስድስትን አምልኮ ያልተቀበሉትን) በግፍ ይገድላቸዋል፡፡ በዚህም ጊዜ እውነት ትቀጥንና ምስክር ታጣለች ፤ ኤልያስና ኄኖክ የሚመጡትም እውነትን በአደባባይ ለመመስከር ነው፡
ይህ ከሆነና በአዲስ አበባ እየተባለ እንዳለው ኤልያስ ከመጣ ሐሳዊ መሲህ መጥቷል ማለት ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ምዕመናን በግፍ ተገድለዋል ፤ በዓለምም ላይ አማኞች በአብዛኛው አልቀዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሲፈጸም አላየነውም፡፡ በኢየሩሳሌምም ሐሳዊ መሲህ ገና አልነገሰም፡፡
ሌላም ሦስተኛ ነገር መነሳት አለበት፡፡ ሐሳዊ መሲሕ የሚነግሠው ፤ ኄኖክና ኤልያስም የሚገለጡት ‹በተቀደሰችው ከተማ” በኢየሩሳሌም ነው፡፡ የሚሠውትም  እዚያ መሆኑን “እርስዋም  በመንፈሳዊ ምሳሌ ሶዶምና ግብጽ የተባለችው  ደግሞ ጌታችን የተሰቀለባት ናት› ብሎ ኢየሩሳሌም መሆኗን  ነግሮናል(ራዕይ 11፤8) ፡፡ አሁን ግን ኤልያስ ተገለጠ የተባለው ያለው አዲስ አበባ አራት ኪሎ ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ተልዕኮውም ከመጽሀፍት ጋር የሚጣረስ ነው፡፡ ጌታ የተሰቀለው አራት ኪሎ ነው ካላልን በቀር፡፡
ራዕይ ዮሐንስ እንደሚነግረን ኄኖክና ኤልያስ ምስክርነት የሚሰጡት ለ1260 ቀናት ወይም ለ42 ወራት ወይም ለሦስት ዓመት ከስድስት ወራት ነው፡፡ አሁን ግን አዲስ አበባ መጣ የተባለው ኤልያስ መጣ ከተባለ አራት ዓመት ሊያልፈው ነው፡፡
ምጽአትና መሲሕን መናፈቅ
በዓለም ሆነ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የምጽአትን ቀን የመናፈቅና የምጽአትን ምልክቶች ደርሰዋል ብሎ የመጨነቅ አዝማሚያ የሚከሰትባቸው ምክንያቶች አሉ፡፡ እነዚህም ኢኮኖሚያዊ ፤ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶች ሲከሰቱና ሕዝብ ተስፋ ሲቆርጥ ነው፡፡
እስራኤራዊያን ከፋርሶችና ከግሪኮች ወረራ በኋላ ሀገራቸው ስትመሰቃቀል ፤ መንፈሳዊነት ሲጎድልና መንግሥታቸው ፈርሶ ተስፋ ወደ መቁረጥ ሲመጡ “መሲሕ እየመጣ ነው ፤ ኤልያስ እየደረሰ ነው” የሚል አስተምህሮ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ2ኛው መቶ ክፍተ ዘመን ጀምረው ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ አንዳንድ ሰዎች ይመጣል የተባለው መሲሕና ኤልያስ እኛ ነን እያሉ አጋጣሚውን ሊጠቀሙበት ሞክረው ነበር፡፡ ከእነዚህ መካከል ከክርስቶስ ልደት በፊት በ2ኛውና አንደኛው መ.ክ.ዘ ላይ የተነሱ ቴዎዳስና ይሁዳ ይጠቀሳሉ፡፡ ቴዎዳስ አራት መቶ ሰዎችን አስከትሎ ነበር ፡፡ በኋላ ግን ሐሰተኛ መሆኑ ሲታወቅ ሕዝቡ ተወው ፡፡ ይሁዳም ሕዝቡን አስነስቶ እስከ ማሸፈት ደርሶ ነበር፡፡ መጨረሻው ግን አላማረም(የሐዋ 5፤37-39)
በቅርብ ጊዜ በኡጋንዳ ኢኮኖሚ ሰደቅና የእርስ በርስ ጦርነት ሲባባስ ይህም የሕዝቡ ማኅበራዊ ሕይወት ሲያቃውሰው “እኔ ክርስቶስ ነኝ” የሚል ሰው ተነስቶ በአንድ አዳራሽ ውስጥ  የነበሩ ተከታዮች መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ሲሉ በእሳት ተቃጥለው እንዲያልቁ አድርጓቸው ነበር፡፡ በአሜሪካ የደረሰው ኢኮኖሚ ድቀት ካስከተላቸው መዘዞች አንዱ በየአካባቢ “እኔ መሲሕ ነኝ” የሚሉ እና  ሕዝቡ ችግሩን  ከማሸነፍ ይልቅ ችግሩን እንዲረሳው የሚያደርጉ ሰዎች  መከሰታቸው ነው፡፡ በ2012 የተደረሰ አንድ ጥናት ባለፉት 3 ዓመታት በአሜሪካ ውስጥ 132 ሰዎች መሲሕ ነን ብለው ተነስተው ወደ 4.5 ሚሊየን የሚደርስ ሕዝብ አስከትለዋል፡፡
በሀገራችን ታሪክ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተከሰተው የግራኝ ጦርነት በኋላ ሕዝቡ መንፈሳዊ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተስፋ መቁረጥ ደረጃ ደርሶ ነበር፡፡ አብያተ ክርስያናቱ ተቃጠሉ ፤ ኢኮኖሚው ወደመ ፤ መንግስት ተዳከመ ፤ ትዳና መስተጋብር የመሰሉ ማኅበራዊ ተቋማት ፈረሱ፡፡ ብዙ ሰዎች ሞቱ ፡፡ ይህ ሕዝቡ ላይ ባስከተለው ተስፋ መቁረጥ የተነሳ ከዚህ መከራ እና ስቃይ የሚያወጣውን አንዳች ሰማያዊ ኃይል ይጠብቅ ነበር፡፡
በሀገራችን ላይ የበልጥ ራዕይ ዮሐንስ የታወቀውና በገልባጮች እጅ በብዛት የተገለበጠው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ በሚሰሩት አብያተ ክርስቲያናትም የሐሳዊ መሲህ ፤ የኤልያና የኄኖክ ፤ የአዲሲቱ ሰማይና ምድር ስዕሎች በብዛት ተሳሉ፡፡
ከግራኝ ጦርነት በኋላ በአጼ ሰርጸ ድንግል ወራሾች መካከል በተፈጠረው የርስ በርስ ውጊያ ሀገሪቱ ስትታመስና ሕዝቡ በተደጋጋሚ ጦርነትና የሕዝብ ፍልሰት ሲታወክ እኔ ክርስቶስ ነኝ ፤ ሕዝቡንም ከችግር ላወጣውና መንግሥተ ሰማያት ላወርሰው መጥቻለሁ የሚል ሐሳዊ መሲሕ በአማራ ሳይንት አካባቢ ተነስቶ ነበር ፡፡ አስራ ሁለት ሐዋርያት ፤ 72 አርእድትንና 36 ቅዱሳት አንስትንም መርጦ ነበር፡፡ ብዙውም ሕዝብ በተስፋ መቁረጥ ላይ ስለነበረ ተከትሎት ነበር፡፡ በኋላ ግን በሞት መቀጣቱን አቡነ ጎርጎርዮስ በኢትዮጰያ ቤተክርስቲያን ታሪክ መጽሐፋቸው ጠቅሰውታል፡፡
በቅርቡ በሀገራችን ታሪክ ዐጼ ምኒሊክ አርፈው ሞታቸው በተደበቀበት ጊዜ ፤ በታህሳስ ግርግር ጊዜ ፤ በአብዮቱ ዋዜማና ማግስት ፤ እንዲሁም ኢሕአዴግ አዲስ አበባ በገባበት ጊዜ አያሌ “ባሕታውያን” ተነስተው ነበር፡፡ ይህ ነገር መጣ ፤ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ስለ ንግሥት ዘውዲቱ  ዘመን በጻፉት የትዝታ መጽሀፋቸውም ይህንን ገልጠውታል፡ ይህም ያም ነገር ታየ ፤ ተገለጠ የሚለው ብሂልም  ነባርና የሀገር አለመረጋጋትና በኑሮ ተስፋ መቁረጥ ተገን አድርገው የሚመጡ ናቸው፡፡
የኤልያሳውያን ሁለት አስተምህሮዎች
አሁን በዘመናችን የተከሰቱ ኤልያሳውያን ሁለት ነገሮች ላይ አተኩረው እየሰሩ ነው፡፡ የመጀመሪያው “ኦርቶዶክስ” ትክክለኛ ስም አይደለም የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሰንደቅ አላማን ከጽድቅና ከኩነኔ ጋር ማያያዛቸው ነው፡፡
ኦርቶዶክስ የሚለው ቃል የግሪክ ሲሆን “ኦርቶ” ርቱዕ “ዶክስ” ደግሞ እምነት ፤ መንገድ ፤ ጠባይ ፤ ባህል ማለት ነው፡፡ ይህንን ስም የክርስቲያን አብያ ክርስያናት መጠቀም የጀመሩት በ325 ዓ.ም በተደረገው ጉባኤ በኋላ ነው፡፡ ከጉባኤ ኬልቄዶን የ451 ዓ.ም ጉባኤ በኋላ ደግሞ የምዕራብ አብያተክርስቲያናት ካቶሊክ ሲባሉ ምስራቆቹ “ኦርቶዶክስ”  የሚለውን ስም ይዘው ቀሩ ፡፡ በምስራቆቹ መካከል  የጉባኤ ኬልቄዶንን  ውሳኔ በመቀበልና ባለመቀበል መካከል ልዩነት ስላለ የግሪክ መሰል አብያተክርስቲያናት የምስራቅ ኦርቶዶክስ ሲባሉ  ፤ አርመን ፤ ግብጽ ፤ ሕንድ ፤ ሶሪያና ኢትዮጵያ ደግሞ “ኦሪየንታል ኦርቶዶክስ” ተባሉ፡፡
ኦርቶዶክስ ፤ ኦርዶክሳዊ የሚለው ስም በሀገራችን ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በሁለት መንገድ ተገልጠዋል፡፡ በአንድ በኩል ጥሬ ቃሉ እንዳለ የተቀመጠ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ግዕዙ ተተርጉሞ “ርቱዕ ሃይማኖት” እየተባለ ተቀምጧል፡፡ ፍትሐ ነገስት ‹ይኩን ምእመነ ኦርቶዶክሳዌ ይላል› (42፤2) ያዕቆብ ዘእልበረዲም ‹ሃይማኖት ኦርዶክሳዊት› ሲል እምነቱን ይገልጣል፡፡ መጽሐፈ ቄርሎስም ‹ሃይማኖተ ርቱዕ› እያለ ተርጉሞ ይገልጠዋል፡፡
‹ተዋሕዶ› የሚለው ቃል ነጥሮ የወጣው በጉባኤ ኤፌሶን በ431 ዓ.ም ነው፡፡ በጉባኤው ንስጥሮስን ባሕል ለማየት የተሰበሰቡ አበው በእስክንድርያ ቄርሎስ የተሰጠውን ትምህርት በመቀበል ሁለት ባሕርይ የሚለውን አውግዘው መለኮት ከስጋ ተዋህዶ ሥግው ቃል ሆነ የሚለው ርቱዕ እምነት መሆኑን መሰከሩ፡፡ ይህ ቃል የእምነት ዶክትሪን መገለጫ ሆኖ ነው የኖረው ፡፡ በኬልቄዶን ጉባኤ በኋላም ይህ ስያሜ የኦርቶዶክሶቹ ዋና መጠሪያ እየሆነ መጣ፡፡ በኢትዮጵያ ጥንታዊ መጻሕፍት ላይ ተዋህዶ እምነት ሆኖ እንጂ የቤተክርስቲያ መጠሪያ ሆኖ አናገኝውም ‹ኦርቶዶክሳዊ› የሚለው ቃል የምናገኝውን ያህል  ‹ተዋህዶ› የሚል መገለጫ አናገኝም ተዋሕዶ የሚለው ቃል በነገረ ሥጋዌ ትምህርት ላይ በሀገር ውስጥ የተነሳ የተለየ አስተያየት ስላልነበረ መጠሪያነቱ አልጎላም፡፡
በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአውሮፓ በመጡ ካቶሊካውያን ምክንያት የተፈጠረውን የእምነት ክፍፍል ተከትሎ ይህ የእምት መጠሪያ የአማያንና የወገን መጠሪያ እየሆነ መጣ፡፡ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቅባትና ጸጋ የሚባሉ ባሕሎች መጥተው ነበር፡፡ እነዚህን ባሕሎች የሚቃወሙትና ኢየሱስ ክርስስ መለኮት ከስጋ በተዋሕዶ ሥግው ቃል እንጂ እንደ ነገስታትና ነቢያት በመቀባት አይደለም ያሉት ደግሞ መጠሪያቸው ከእምነታቸው ተወስዶ “ተዋሕዶዎች” ተባሉ፡፡ ከቦሩ ሜዳ ጉባኤ በኋላም የቤተክርስቲያኒቱ ሕጋዊ ስም ‹‹ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ›› የሚለው ጎላ፡፡
ኦርቶዶክስ የሚለው ስም  ቤተክርስቲያኒቱ በዓለም የምትታወቅበት የወገን ስሟ ነው፡፡ ሌሎችም ‹የግብጽ ኦርቶዶክስ› ፤ ‹ የሕንድ ኦርቶዶክስ› ብለው ይጠሩ እና ከአካባቢያቸው ራሳቸውን ለመለየት ደግሞ ‹የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ› ፤ ‹የሶርያ ያዕቆባዊት ኦርቶዶክስ› እያሉ ይጠራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንም  ‹ኦርዶክስ ተዋሕዶ› ትባላለች ፡፡
አንዳንድ ሰዎች በዘመናውያን መዛግብት ቃላት ስለ ‹ኦርቶዶክስ› የተሰጡ ፍቺዎችን ይዘው ይሞግታሉ፡፡ ኦርቶዶክስን ‹ከአክራሪነትና ከለውጥ አለመቀበል› ጋር እያዛመዱ ይፈቱታል፡፡ በዚህ ምክንያት ኦርቶዶክስ የሚለው ቃል ለኮንሰርቫቲቭ ፓርቲዎችና ለአይሁድ ሲሰጡት ይታያሉ፡፡ ይህ ግን ኦርቶዶክስ የሚለው ስም ከመነጨበት ጠባይ በእጅጉ የራቀ ነው፡፡
አሁን ወደ ሁለተኛ ነጥብ እንመለስና ሰንደቅ አላማን እንመልከት፡፡ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የኢትዮጵያውያን መለያ ናት፡፡ ለዚች ሰንደቅ አላማ  ብዙዎች ውድ ሕይወታቸውን  ከፍለዋል፡፡ ከእነዚህ ውድ ሕይወታቸውን ከከፈሉ መካከልም የቤተክርስቲያኒቱ አባቶችና ልጆች ይገኙበታል፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ታሪክን ከማቆየት ፤ ባሕልን ከማሻገርና ኢትዮጵያዊነትን ከማስረጽ ሚናዋ አንጻር ሰንደቅ አላማንም  በማስከበርና ለትውልድ በማስተላለፍ የበኩሏን ድርሻ ተወጥታለች፡፡
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ  ሰንደቅ አላማ ከሀገራዊ እሴትነቱ ፤ መስዕዋትነትና ነጻነት ከማንጸባረቁም ፤ ለኢትዮጵያውያን ከደማቸው ጋር የተዋህዶ ልዩ ምልክት ከመሆን አልፎ ግን ጽድቅና ኩነኔ ውስጥ የሚገባ ፤ እርሱን ያልተቀበለ እና ያላደረገ ሰማያዊ ዋጋ የሚቀርበት ፤ ከእርሱ ውጪ ቀለም ያለው ነገር የለበሰና ማህተብ ያሰረ ሃጥያት እንደሰራ ተቆጥሮ ንስሃ የሚገባበት ግን አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ ያለ ዜጋ የቤተክርስቲያኒቱ አባል ለመሆን የቤተክርስቲያቱን ዶግማ እና ቀኖና መቀበልን እንጂ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራን መቀበል ግዴታው አይደለም፡፡ በኡጋንዳ ባንዲራ ፤ በአሜሪካ ባንዲራ ፤ በሶማሊያ ባንዲራ አሸብርቆም ቢሆን የኦርዶክስ ተዋሕዶ ልጅ መሆን ይችላል፡፡ አስከ አሁን በቀኖና በሚደነገጉ መጻህፍቶች ውስጥ ሰንደቅ አላማን የተመለከተ ቀኖና የለንም፡፡
በመሆኑም ሰንደቅ አላማችን ከኢትዮጵያዊነታችን ጋር እንጂ ከኦርቶዶክስ  እምነታችን ጋር  የታሪክ እንጂ የድኅነት ተዛምዶ የለውም፡፡
እንደዚህ አይነት አመለካከቶች የሚያይሉት እንዲሁ አይደለም፡፡ በሕዝቡ ዘንድ ኢትዮጵያዊ ስሜት  ደብዝዟል ፤ ለሰንደቅ አላማና ለሀገራ እሴቶች የሚሰጠው ዋጋ ቀንሷል ተብሎ ሲታሰብ ሰንደቅ አላማን የመሰሉ ሀገራዊ እሴቶች ጉልበት ያገኙ ዘንድ ተጨማሪ ሃይማኖታዊ ኃይል ይሰጣቸዋል፡፡ ቤተክርስቲያቱ የሰንደቅ አላማን ክብርና ትርጉም ማስተማርዋ እና በትውልድ ውስጥ ማስረጿ ባልከፋ ፡፡ አስተምህሮ ግን ከሀገራዊ ግዴታ የሚመጣ እንጂ ከሃይማኖታዊ ግዴታ የሚመጣ መሆን የለበትም፡፡ ከሕዝብ እሴቶች እንደ አንዱ ሆኖ እንጂ ከጽድቅና ኩነኔ ጋር መሆን ለበትም፡፡
ምን ይደረግ ?
የሃይማኖት ትምህርት በሚገባ መሰጠት ሲያቆምና ሰዎችም በተደላደለው እምነት መንገድ ላይ በእውቀትና በእምነት እየተመሩ መጓዝ ሳይችሉ ሲቀሩ ‹ባለ ተስፋዎች ይሆናሉ› ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በላከው መልዕክቱ መጀመሪያ ላይ ‹በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን ፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ባሉት ምዕመናን›  በማለት የገለጠው አባባል ታላቅ ነገር አለው፡፡ ምእመናኑ በሁለት ዓለም መኖራቸውን እንዳይረሱ ለማድረግ ነው፡፡ ‹በክርስቶስና በኤፌሶን› ክርስቲያችም ምድራዊነታቸውንም ሰማያዊነታቸውንም  መርሳት የለባቸውም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ምድራዊ ጎዳና ሲያቅተንና ፈተና ሲበዛበት ፤ የኢኮኖሚ የፖለቲካ ሁኔታ አልቃና ሲል ፤ የምናየው የምንሰማው ተስፋ ሲያሳጣን ፤ ምድር ላይ መሆናችንን ፈጽመን ረስተን ኅሊናችን ወደሚፈጥረው ልዩ አለም እንገባለን፡፡ ያንንም እጅግ ከመመኝታችን የተነሳ የደረስንበት ይመስለናል፡፡
በዚህ ጊዜ የሚሰጡ ትምህርቶች ለሰዎች ቀላል የሆኑ ፤ ንባብና ትምህርትን የማይጠይቁ ፤ በቀላሉ የሚተገበሩ ፤ የሚነኩና የሚዳሰሱ ይሆናሉ፡፡ ቡና መጠጣት አለመጠጣት ፤ አረንጓዴ ቢጫ ክር ማሰር አለማሰር ፤ በባዶ እግር መሄድ አለመሄድ ፤ ጸጉርን ማስረዘም አለማስረዘም ፤ መቁጠሪያ አለስርዓቱ ማሰር አለማሰር ፤ ከመምህራን ቃል ይልቅ የሰይጣንን ቃል መቀበልና ማመን እየሰለጡ ይመጣሉ፡፡
ለዚህ ትልቁ መፍትሔው የእምነት ተቋማት የራሳቸውን ሥራ (ወንጌል ማስተማር) ትተው በሰዎች ስራ ውስጥ መግባታቸው ነው፡፡ ስለዚህ ተቋማቱ መጀመሪያ ራሳቸውን ወደ ተልዕኳው መልሰው ፤ የማይጨበጥ ተስፋ የሚዋልለውን ሕዝብንም ወደ ትክክለኛ ኑሮ እና ተስፋ መመለስ አለባቸው፡፡  እዚህ ኤልያስ ነኝ ፤ እዚያ ድንግል ማርያም ነኝ ፤ እዚያ አቡዬ ነኝ የሚሉ በተነሱ ቁጥር ሕዝቡ ስራና ትዳር ፈትቶ ተንከራቶ አይዘልቀውም፡፡ ይህ አዲስ እንቅስቃሴ ለምእመናኑ የተለየ ፋይዳ ይዞ አልመጣም፡፡
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on March 18, 2013
  • By:
  • Last Modified: March 18, 2013 @ 10:33 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar