www.maledatimes.com የተቃዋሚዎች ድክመትና ለስልጣኑ ያላቸው ርቀት (ተመስገን ደሳለኝ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የተቃዋሚዎች ድክመትና ለስልጣኑ ያላቸው ርቀት (ተመስገን ደሳለኝ)

By   /   March 18, 2013  /   Comments Off on የተቃዋሚዎች ድክመትና ለስልጣኑ ያላቸው ርቀት (ተመስገን ደሳለኝ)

    Print       Email
0 0
Read Time:52 Minute, 18 Second

በኢትዮጵያ ታሪክ የተደራጀ የፖለቲካ ትግልን ማን ጀመረው? መቼ ተጀመረ? የሚሉት ጥያቄዎች ዛሬም ድረስ ሁሉንም ወገን በሚያሳምን
መልኩ መልስ አልተገኘላቸውም፡፡ በተለይም በኢህአፓ እና መኢሶን መካከል ‹‹ጀማሪው እኔ ነኝ›› የሚለው ክርክር ብዙ
እንዳወዛገበ ይታወቃል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ጥናቶች የሚያመላክቱት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የፖለቲካ ፓርቲ በ1961 ዓ.ም.
የተመሰረተው መኢሶን እንደሆነ ነው፡፡ የትኛውም ፓርቲ ቀዳሚ ይሁን፣ በሀገሪቱ በተደራጀ መልኩ የፖለቲካ ትግል መታየት የጀመረው
በ1960ዎቹ መጀመሪያ መሆኑ ግን ሁሉንም ያስማማል፡፡
(በነገራችን ላይ የአቶ መለስን ህልፈት ተከትሎ በተፈጠረው የኃይል ትንቅንቅ ሀገሪቱ ልትፈርስ ወደምትችልበት ጠርዝ የሚገፋት ድንገቴ
አደጋ ቢፈጠር፣ መታደጊያ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ አማራጮች በተጨባጭ መኖር ያለመኖራቸው፣ ከስርዓቱ መዳከም ጋር
ባልተያያዘ ሁናቴ ያልታሰበ ህዝባዊ ንቅናቄ ቢቀሰቀስና ኢህአዴግ ብሄራዊ ዕርቅ ማመቻቸት፣ ለሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች እና እስረኞች
ምህረት ማድረግ፣ ነፃና ተአማኒነት ያለው ምርጫ ቦርድ ማቋቋም፣ የዲሞክራሲያዊ መብቶችን ያለገደብ ማክበር፣ መከላከያን፣ ደህንነትን፣
ፖሊስን… ገለልተኛ አድርጎ ለህዝብ ጥያቄ እጅ ባይሰጥና የአብዮቱ ጎርፍ ታሪክ ቢያደርገው የተቃዋሚ ፓርቲዎች አቅምና ሚና እስከ ምን
ድረስ ሊዘልቅ ይችላል? ስልጣን የሚረከብ ትከሻስ አላቸው? ወይስ ነገሩን ሁሉ ‹‹ከድጡ ወደማጡ›› ያደርጉታል? የሚሉት ጥያቄዎች
በፖለቲካ ድርጅቶችም ሆነ በምሁራኖች ትኩረት አለማግኘቱን ሳስበው በእጅጉ ያስፈራኛል)
የሆነ ሆኖ ወቅቱ ወደ ምርጫ የሚገባበት መሆኑ እና የተቃውሞ መድረኩ በእንሳተፋለን አንሳተፍም መከፈሉ የዚህ ፅሁፉ ዋነኛ ገፊ
ምክንያት ነው፡፡ ቀጣዩ የፌደራል ምርጫ ከሁለት ዓመታት በኋላ መካሄዱም ስለእነዚህ ፓርቲዎች መሰረታዊ የድክመት መለያዎችና
ችግሮቻቸውን ለመሻገር ስለሚያስችሏቸው መንገዶች ከአሁኑ መነጋገር ይኖርብናል፡፡ እናም በዚህ ፅሁፍ የተሻለ የተቀባይነት እድል
ሊኖራቸው ይችላል ብዬ የማስባቸውን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሊያሻሽሉ የሚችሉትን ድክመታቸውን መጠቆም፣ እና በመውጫ
እስትራቴጂያቸው ላይ ዕይታዬን አንጸባርቃለሁ፡፡ (መቼም በዚህች አጭር ፅሁፍ ላይ የህይወት ታሪካቸው ከምርጫ ቦርድ የምዝገባ ፍቃድ
የማይዘለውን እና የህልውናቸው መገለጫ የድርጅታቸው ማህተም ብቻ የሆነውን ህልቆ መሳፍርት ያሌላቸውን አጃቢ ፓርቲዎች
መዘርዘሩ ከማሰልቸት ያለፈ ጥቅም የለውም)፡፡ ስለዚህም ከወል ድክመታቸው ልጀምር፡፡
አስራ ሁለቱ ድክመቶች
1ኛ. ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ ‹‹የፖለቲካ ፕሮግራማቸው›› የሀገሪቱን የፖለቲካ መልክዐ-ምድር፣ የህዝቡን ባህል፣ አመለካከት፣
ታሪክ፣ እምነት፣ የሃብት ምንጭ… ከግምት አስገብቶ የተቀረፀ ሳይሆን እንደ ኢህአዴግ ውጤት አልባ ፖሊሲ ስርዓተ ነጥቦቹ ሳይቀየሩ
ከሌሎች ሀገራት የተኮረጀና የተገለበጠ መሆኑ፤
2ኛ. አብዛኞቹ የፓርቲው መስራቾች የተሰባሰቡት በርዕዮት አለም ተግባብተውና ተማምነው ሳይሆን በጉርብትና በወንዝ ልጅነት፣
በጓደኝነት… ላይ በተመሰረተ ግንኙነት መሆኑ፤
3ኛ. አባሎቻቸውን ኢህአዴግ እንደሚያደርገው ከላይ የመጣ ትዕዛዝን የሚተገብሩ እንጂ በውይይት፣ በክርክር፣ በመግባባት… በአጠቃላይ
ከዴሞክራሲ ባህሪያት ጋር ዝምድና ባለው መልኩ እንዳይሰሩ ባልተፃፈ ህግ ማገዳቸው፣
4ኛ. ወቅታዊ እና ተጨባጭ ሁኔታን ከግምት ያስገቡ ወይም ‹‹የሚሸጡ›› (የሚያማልሉ) አጀንዳዎችን በየጊዜው ያለመጠቀማቸው፣
5ኛ. አመራሩ ማንኛውንም መስዋዕትነት ሆነ ኃላፊነትን ለመውሰድ ቁርጠኛ ያለመሆኑ (የህወሓት አመራሮች በትግሉ ዘመን ‹‹እኛን
ከሌላው የሚለየን ለመግደል ብቻም ሳይሆን ለመሞትም ያለን ቁርጠኛነት ነው›› ይሉ ከነበረው ቢማሩ የተሻለ ይሆናል)
6ኛ. በሰላማዊ ትግል ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኙ ስልቶችን የመተግበር በህግ የተደነገገ መብት እንዳላቸው አውቀው አለመፈፀማቸው፣
7ኛ. በተለያየ ደረጃ የሚያስቀምጡት ካድሬ (የአካባቢ ተጠሪ፣ ሰበሳቢ…) በብቃት የሚመደብ ሳይሆን ለአመራሩ ሎሌ (አስፈፃሚ) ሊሆን
የሚችለው ላይ ብቻ በማተኮር መሆኑ፣8ኛ. እንደፖለቲካ ፓርቲ በማንቃት፣ በማደራጀት እና አባላትን በማብዛት ላይ ከማተኮር ይልቅ የምርጫ ወቅትን ብቻ እየጠበቁ
መንቀሳቀሳቸው፣
9ኛ. በእጃቸው ያለውን የሰው ሀይል በአግባቡ አለመጠቀማቸው (ለምሳሌ በመዝገባቸው ላይ ከሰፈሩት አባላት መዋጮን በትክክል
አለማስከፈል)፣ በንቃተ ህሊና የተሻሉ የሚባሉ አባሎችን በማስተማር እና በማሰልጠን አቅማቸውን ገንብተው የአስተዋጽኦ ደረጃቸውን
ከፍ አለማድረግ፣ የግምገማ ባህል አለመኖር፣ በጥናትና ምርምር ላይ የሚያተኩር ዘርፍ አዋቅሮ ያለመጠቀም፣
10ኛ. ከአመራር አባላት መካከል በስልጣን ፍቅር የናወዙ እና በቀቢፀ ተስፋ የተሞሉ ቁጥር መብለጥ፣
11. በሌሎች ሀገራት ከሚገኙ ስኬታማ ፓርቲዎች ጥንካሬ ያለመማር፣
12.የትውልዱን ጥያቄ አለማወቅ እና እርሱን የሚወክሉ ወጣቶች በላይኛው አመራር ላይ እንዲኖር አለማመቻቸታቸው በአጠቃላይ
ለፓርቲዎቹ ደካማነት ምክንያት ናቸው ብዬ አስባለሁ።
(ከዚህ በላይ ያነሳዋቸውም ሆነ ከዚህ በታች የማነሳቸው ወቀሳዎች /ነቀፌታዎች/ አስተዋጾን ለማንኳሰስ ወይም ዋጋ ላለመስጠት
አለመሆኑን አስቀድሜ እገልፃለሁ፡፡ ምክንያቱም የፓርቲዎቹ መሪዎች ምንም እንኳ ውጤታማ ባይሆኑም በአስፈሪው የስርዓቱ ወጀብ
ውስጥ በተቃውሞ ፖለቲካ ላይ በግልፅ መውጣታቸው በራሱ ከብዙ አድርባይ እና በፍርሃት ካቀረቀሩ አቻዎቻቸው የሞራል የበላይነት
እንዳላቸው ይመሰክራል፤ በወለም ዘለምም ቢሆን ለህሊናቸው የመታመን ሙከራ ማድረጋቸውን ስለሚያሳይም እንድናከብራቸው
ያደርገናል፡፡ ከዚህ ባለፈ ‹‹ፓርቲውን የመሰረትኩት እኔ ነኝ›› በሚል ጊዜው ያለፈበትን ‹‹በአምናው መንገዴ ዘንድሮም እጓዛለሁ›› ማለቱ
አንድም ገዥው ፓርቲ ያለድካም ዕድሜውን እንዲያረዝም ማመቻቸት ሲሆን፣ ሁለትም በአገዛዙ በትር የተደቆሱ፣ ፍትህ ያጡ፣ የተጎሳቀሉ፣
ለነጭ ድህነት የተዳረጉ ኢትዮጵያውያኖች ላይ መቀለድ ነውና የመቀየሪያው ጊዜ ላይ ተደርሷል ብዬ አስባለሁ)
ተፎካካሪ ፓርቲ አለን?
በእርግጥ ይህንን ጥያቄ በቀጥታ መመለሱ አስቸጋሪ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ አውድ ‹‹ተፎካካሪ ፓርቲ›› እያልን የምንጠራቸው የምርጫ
ቦርድ የምዝገባ ወረቀት እና ማህተምን መስፈርት በማድረግ ባለመሆኑ፣ በእኔ እምነት አንድነት፣ ኦፌዴንና አረና ምንም እንኳ አፍ ሞልቶ
‹‹የተደራጁ›› ባይባሉም የተጠቀሱትን አስራ ሁለት ድክመቶችን አስተካክለው በአንድ አውድ መሰባሰብ ከቻሉ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ
ወሳኝ ሀይል ሆነው ሊወጡ የሚችሉበት እድል አሁንም የሰፋ ነው (የዶክተር መረራ ጉዲና ኦህኮ ከኦፌዴን ጋር ሙሉ በሙሉ በመዋሀዱ
በተናጥል ተጠቅሶ ሊተችም ሊመሰገንም የሚችልበት ምክንያት የለም)
እነዚህ ፓርቲዎችም ቢሆኑ ‹‹መድረክ›› የሚል የዳቦ (የከተማ ትግል) ስም ለራሳቸው ሰጥተው ‹‹ግንባር መስርተናል›› የሚሉትን
ፕሮግራም እና መዋቅር አልባ ጥምረታቸውን እንደ ቁምነገር ከወሰድነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አልገባንም ማለት ነው። መድረክ
መጀመሪያም በመለስተኛ ፕሮግራሙ እንጂ በአካለ ስጋ ያልነበረ፣ ዛሬም የሌለ ሀይል መሆኑን እነ ገብሩ አስራት እና ነጋሶ ጊዳዳ ራሳቸውን
ካሳመኑ በኋላ አቅማቸውን መዝነው ለአዲስ እና ብርቱ ትግል ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡ ፡ በተቀረ ‹‹ግንባር›› አደረግነው የሚሉትን
ፖለቲካ ከእኔ ይልቅ አንድ የአመራር አባሉ በተሻለ ሁኔታ እንዲህ ሲሉ ገልፀውታል፡- ‹‹መድረክ ልክ እንደ አፍሪካ ኅብረት የመሪዎች እንጂ
የፓርቲዎች ስብስብ አይደለም››
መቼም አፍሪካ ኅብረትን በአህጉሪቱ የሚገኙት የሃምሳ አራት ሀገራት ህዝቦች ኅብረት አድርገን ልንወስደው አንችልም። መድረኩም እንዲያ
ነው። በትክክልም የአመራሩን አገላለጽ ስንመነዝረው የአምስት ፓርቲ መሪዎች ‹‹የፅዋ ማህበር›› እንደማለት ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ
ተጣመርን ከሚሉት ፓርቲዎች ውስጥ ከአባሎቻቸው በዓመት አስር ብር መሰብሰብ የማይችሉ፣ መዋቅር አልባዎች መብዛታቸው ነው፡፡
በእርግጥም መድረኩ በመሪዎቹ ልቦና እና ስድስት ኪሎ ከሚገኘው የቀድሞ ኅብረት ጽ/ቤት ግቢ የዘለለ ተፅዕኖ ሊፈጥር ያልቻለው
በእነዚህ ትክክለኛ ማንነቶቹ ይመስለኛል። እናም መድረኩ መጪው ጊዜ ሰናይ ይሆንለት ዘንድ ‹‹ወደ ግንባርነት ተሸጋግሬያለሁ›› ከሚል
መታበይ ወጥቶ አቅሙን ቢፈትሽ የተሻለ ነው። እንዲሁም ‹‹ግንባር››ነትን ያን ያህል ያስጮኹት፣ የግንባር አስፈላጊነትን እና ጠቃሚነትን
ከስብስቡ ጋር አስተጋብሮ በመተንተን የሚያገኘውን ፖለቲካዊ ጠቀሜታ አስልተው አይመስለኝም፡፡ ‹‹ኢህአዴግ ግንባር መሆኑ ነው
የጥንካሬው ምንጭ›› ከሚል የስህተት ድምዳሜው የተኮረጀ ይመስለኛል። ይህም ሆኖ በኩረጃው መካከል የዘነጉት አንድ እውነት አለ፡፡
ኢህአዴግ ራሱን ግንባር ብሎ ሲሰይም ቢያንስ በግንባሩ አባላት መካከል የርዕዮተ-ዓለምም ሆነ የፕሮግራም ልዩነት ያለመኖሩ፣
የፍልስፍናው ስበትም ብሄር ተኮር መሆኑ እና ከፓርቲዎቹ የተናጥል አደረጃጀት ጋር መመሳሰሉን ልብ ያሉ አይመስልም፡፡ በተቃራኒውመድረክ በኢትዮጵያ ፖለቲካ መሰረታዊ የልዩነት መስመሮች ተብለው በሚጠቀሱት ‹‹የፌዴራሊዝም ቅርፅ›› እና ‹‹የመሬት ፖሊሲዎች››
ላይ ጠርዝ ለጠርዝ የቆመ አቋም ያላቸው ፓርቲዎችን ጭምር አቅፎ ነው ግንባር ሆኛለሁ እያለን ያለው፡፡ እንግዲህ የመድረክ አመራሮች
ይህ ስህተታቸው ነው ‹‹ሰነፍ ኮራጅ ተማሪ›› የሚያደርጋቸው፡፡ ይህን የሚያስረግጥልኝ አንድ መድረኩ በቅርቡ ያወጣው ማኔፌስቶ ጉዳይ
ነው፡፡ ከሳምንታት በፊት ‹‹የኢትዮጵያ ወቅታዊና ዘላቂ ችግሮች የመፍቻ አቅጣጫዎች ማኒፌስቶ›› በሚል ርዕስ በፀደቀው የመድረኩ
ዶክመንትም ላይ የግንባሩ መሪዎች በየመግለጫዎቻቸው ችግሮች ያሏቸውን የኢህአዴግን ክስረቶች ከመዘርዘር ያለፈ የሚረባ ጭብጥ
አላየሁበትም፡፡ ለዚህ ማሳያ እንዲሆነኝ አንድ ነጥብ ከዶክመንቱ ልጥቀስ፡፡ ይኸውም ‹‹ገዥው ፓርቲ ‹ጦረኛና ሽብርተኛ› ብሎ
ከፈረጃቸው ጋር እየተደራደረ፣ እኛን ከድርድር ማራቁ ‹ጦር አምላኪነቱን› ያሳያል›› የሚል ነው፡፡ መቼም እንኳን ፖለቲከኛ ነኝ ከሚል
ቀርቶ፣ ኢህአዴግን በጨረፍታ እንኳን የሚያውቅ ይህን መሰል አቋሙ ይጠፋዋል ብዬ አላምንም፡፡ ለድርድር ጠርቷቸዋል የተባሉት
ፓርቲዎች ለምን እንደተጠሩ ግልፅ ነው፡፡ አገዛዙ ተጨባጭ አደጋ የሚፈጥርበትን ኃይል በሚገባ ያውቃልና፡፡ ስለዚህም ፓርቲውን
በሚገባ በማስጨነቅ ወደ ድርድር መግፋት እየተቻለ ይህን ጥያቄ ማቅረብ የለየለት የዋህነት ይመስለኛል፡፡ …እነዚህ ሁሉ አክሳሪ
ፖለቲካዎች በተከማቹበት የተቃውሞ ሰፈር እውን ተፎካካሪ ፓርቲ አለ ወይ? ብሎ መጠየቅም ሆነ መፈተሽ ለነገ የማይተው ነው።
ተስፈኞቹ እነማን ናቸው?
በእኔ ግምት አንድነት፣ አረና እና ኦፌዴን ግንባር ቢፈጥሩ የተሻለ ሀይል ሆነው ሊወጡ ይችላሉ። (እነዚህ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ
ያላቸውን የንባብ ልዩነት ለአጥኚዎች ትተው፣ መሬት በወረደው ጭብጥ ላይ ማተኮር እንደሚሻላቸውም ማስታወስ ያሻል)፡፡ የሆነ ሆኖ
የግምቴ መነሻ አንድነት ራሱን የ97ቱ ቅንጅት ወራሽ አድርጎ በማቅረቡ የአባላት ቁጥሩ የተሻለ ከመሆኑ በተጨማሪ በሀገር ውስጥም ሆነ
ከሀገር ውጪ በአንጻራዊነት የተሻለ የሚባል መዋቅር አለው፡፡ ብዙዎች የሀገሪቱ መንፈሳዊ አባት የሚሏቸው ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም
እና ተወዳጇ የህግ ምሁር ብርቱካን ሚደቅሳ መስራች የነበሩ መሆኑ (ዛሬ ሁለቱም ከድርጅቱ ለቀዋል)፣ የህወሓት መስራቹ ስዬ አብርሃ እና
የቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የአመራር አባል መሆናቸው አንድነት የተሻለ ትኩረት የሚያገኝበትን አጋጣሚ የፈጠረለት
ይመስለኛል፡፡
አረና ለሉአላዊነትና ለፍትህ /አረና/ ፓርቲ ጠንካራ ሊያደርጉት የሚችሉ ሁለት ገፊ ምክንያቶች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ህወሓት በትግሉ
ዘመን የነበረውን ድጋፍ እያሰላ ‹‹ትግራይ የህልውና መሰረቴ ነው›› በማለት ህዝቡ የተለየ የፖለቲካ አመለካከትን እንዳይከተል በጉልበት
ለረጅም ዘመን ማፈኑ አዲስ አማራጭ እንዲፈልጉ ማስገደዱ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የአረና መስራቾች በትግሉ ዘመንም ሆነ ከድሉ በኋላ
የህወሓት አመራር በነበሩበት ወቅት በአካባቢው ተወላጆች የተሻለ እምነት የሚጣልባቸው መሆኑ ነው፡፡
ሌላኛው ፓርቲ ኦፌዴን ደግሞ በኦሮሞ ስም ከተመሰረቱ ድርጅቶች የበለጠ ድጋፍ ያለው ከመሆኑም ሌላ ለፓርቲያቸው ራሳቸውን
አሳልፈው የሚሰጡ በርካታ ወጣቶችን ማፍራት መቻሉ ነው የጥንካሬው ምንጭ፡ ከእነዚህ ውጭ ያሉት የመድረክ መስራች ፓርቲዎች
የጀመሩትን ውህደት መቀጠልና የምዝገባ ሰርተፍኬታቸውን በክብር ሙዚየም ከማስቀመጥ ውጪ አመራጭ አላቸው ብዬ አላስብም።
(የፕሮፌሰር በየነ ‹‹የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)››፣ ‹‹ከደቡብ ህብረት›› ጋር የውህደት ሰነድ ፈርሟል። በዚህ መቆም
የለበትም፤ ራሱን በአንድነት ውስጥ እንዳሰጠመው ‹‹ብርሃን›› ፓርቲ፣ የደቡብ ህብረት እና የኢሶዴፓ ውህድም ከአንድነት ጋር ቢቀላቀል
የተሻለ ይሆናል። ሁለቱም ፓርቲዎች በዕድሜ ከአንድነት የሚልቁ ቢሆንም በቂ የአመራር አባላት የሌላቸው እና አቅመቢስ መሆናቸው፣
እንዲሁም ብዙ ጊዜ ከዘውግ የዘለለ አጀንዳ ከማራመዳቸው አኳያ ማረፊያ ቤታቸው አንድነት ቢሆን ተጠቃሚ ይመስሉኛል፡፡
ሌላኛው በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ላይ ግዙፍ አሻራውን ጥሎ ለፍትሀት የተዘጋጀው ‹‹የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት
/መኢአድ/›› ነው። መኢአድ በአሁኑ ወቅት በፀጥታ ‹‹ዕለተ ሞቱን›› እየጠበቀ ካለ አዛውንት ጋር ይመሳሰልብኛል። እነዚያ ሁሉ ጠንካራ
እና ለመስዕዋት የማያመነቱ አባላቱ በምድረበዳ ይንከራተቱ ዘንድም አሳልፎ ከሰጣቸው አመታት እየተቆጠሩ ነው። አመራሩም ቢሆን
ከሌሎች ከተሰነጠቁ ፓርቲዎች በባሰ መልኩ ወርዶ በግለሰብ ደረጃ መከፋፈል ላይ ደርሷል። የግለሰብ ክፍፍሉንም እንዲህ ብለን
ልንጠቅሰው እንችላለን ‹‹የኃይሉ ሻወል-መኢአድ፣ የጌታቸው መንግስቴ- መኢአድ፣ የማሙሸት አማረ- መኢአድ… የብዙ ሰዎች፣ ብዙ-
መኢአዶች›› መቼም ለአንድ ድርጅት መሞት ከዚህ የበለጠ ምልክት አያሻውም።
የሆነ ሆኖ በዚህ መልኩ የመድረኩ ችግር ከተፈታ በኋላ አንድነት፣ አረና እና ኦፌዴን በጋራ ‹‹ግንባር››ም ይበሉት ‹‹ጥምረት›› ፈጥረው
በአመቻቸው መንገድ ተባብረው መጓዝ ከቻሉ እና ራሳቸውን ንቃተ ህሊናው በዳበረ የሰው ኃይል ካዋቀሩ፣ ለሃሳብ የበላይነት ቦታ ከሰጡ፣
ከጥላቻ ከራቁ… በመከፋፈል ጠርዝ ላይ ከቆመው ኢህአዴግ የተሻለ ሆነው የሚውጡበት ሰፊ እድል ይኖራቸዋል ብዬ አስባለሁ።ፓርቲዎቹ ከላይ ከጠቀስኳቸው ዋነኛ ችግሮቻቸው ባሻገር በእስትራቴጂያቸው ላይ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ተጨማሪ ተግዳሮታቻቸውን
መቅረፍ መቻልም ሌላው የቤት ስራቸው ነው። ለምሳሌ በፓርቲ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ አሰራር ወሳኝ የመሆኑን ያህል ‹‹ዲሲፒሊን››ም
እንዲሁ እጅግ አስፈላጊ ነው። በሀገራችን ግን አንዱ የአመራር አባል የሰጠውን መግለጫ፣ ሌላኛው ሲያጣጥለው ወይም በተቃራኒው ሄዶ
ሲያፈርሰው ማየቱ የተለመደ ነው። ትግሉን በነሲብ ለመምራት በመሞከራቸውም የመታገያ አጀንዳ የመቅረጽ ልምዱም አቅሙም
እንዳይኖራቸው አድርጓቸዋል። ይህንን ድክመታቸውን ከኢህአዴግ በሚዋሱት አጀንዳ ለመሸፈን የሚሞክሩበት ሁኔታ ደግሞ ሌላው
የፖለቲካው አስቂኙ ክፍል ነው። ለማስታወስ ያህልም አንድነት የብሄር ብሄረሰብ ቀን ማክበሩን እና በሃያ ዘጠነኛው የአፍሪካ ዋንጫ
ተሳትፎ ከ16 አገራት 16ኛ ሆኖ ለተመለሰው ብሄራዊ ቡድናችን ‹‹የደመቀ አቀባበል ሊደረግለት ይገባዋል›› ሲል ያወጣውን መግለጫ
መጥቀስ በቂ ነው፡፡
እናም በግሌ አጀንዳ መንጠቅ ካስፈለገም አስቀድሞ አዋጭነቱንና ከፖለቲካ አመለካከተ ጋር አለመጣረሱን መገምገም አስፈላጊ ነው ብዬ
አስባለሁ፡፡ ለእንዲህ አይነቱ ተሞክሮ ከራሱ ከኢህአዴግ መማር ይቻላል። ኢህአዴግ ከዓመታት በፊት ‹‹ባንዲራ ጨርቅ ነው›› ሲል
የአንድነት መሰባሰቢያ ተደርጎ የሚወሰድውን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ አርማ አጣጣለ። ነገር ግን ይህ ሁኔታ ከህዝብ ጋር የሚያጣላ ሆኖ
ባገኘው ጊዜ ‹‹የባንዲራ ቀን››ን በአዋጅ እስከማክበር ደርሷል። የኢትዮጵያ ታሪክም የመቶ አመት ነው የሚለው የታሪክ መፅሀፉም
ሚሊኒየሙን በማክበር ወደ ሺህ አመታት የቀየረው ይመስላል። ይህ የኢህአዴግ ጠንካራ ጎኑ ነውና መማር የፈለገ ሊማርበት ይችላል፡፡
በተቀረ ከደካማ ጎኖቹ (የመሬት ፖሊሲው የሚቀየረው በመቃብሬ ላይ ነውና ከመሳሰሉት) ትምህርት ለመውሰድ መሞከሩ ገንቢ
አይመስለኝም፡፡
በጥቅሉ የድክመት መገለጫ ሆነው የሚጠቀሱት አብዛኛው የተቃዋሚ ፓርቲ የአመራር አባላት ‹‹ኢህአዴግ አያውቀውም›› የሚሉትን
ዴሞክራሲ በባሰ መልኩ አለማወቃቸው፣ ነቃፊን እንደደመኛ የሚቆጥሩ፣ የማሻሻያ ሀሳብ የሚያቀርብን የስልጣናቸው ገልባጭ አድርገው
ማየታቸው፣ ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነት የኢህአዴግን ያህል ባዕድ መሆናቸው፣ ዘመኑንም ሆነ ገዢው ፓርቲን አለማንበብ
/አለመረዳት/፣ ተቀናቃኛቸው የሚያትማቸውን የህትመት ውጤቶች መከታተል እንደመርከስ መቁጠር፣ ከአይናቸው ይልቅ ጆሮአቸውን
ማመናቸው፣ ለተጋጋለ ክርክር ጊዜ የሚኖራቸው እቅዳቸውን ወይም የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን በተመለከተ ሳይሆን ለእርስ በርስ መካሰስ
መሆኑ፣ በመከለስ፣ በመበረዝ፣ በመቀልበስ መጠመዳቸው ዛሬ ላሉበት የተተራመሰ ፖለቲካ ያጋለጣቸው እና ሳይወዳደሩ የተሸነፉ
ያደረጋቸው ይመስለኛል፡፡
ሌላው የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ጉልህ ችግር ራስን ወደ አለም አቀፍ ማህበረሰቡ አለማምጣት ነው፤ ወይም አለማስተዋወቅ፡፡ የራሳቸውን
አጀንዳም ይሁን ወቅታዊ ጉዳዮችን ተንተርሰው አለም አቀፍ ሚዲያዎችን ለመጠቀም ሲሞክሩም አይታዩም። ይህ ደግሞ በዲፕሎማቲክ
ማህበረሰቡ ዘንድ አመኔታን እንዳያገኙ ያደርጋቸዋል። ለዚህም ነው አቶ መለስ ባለፉበት ሰሞን የአሜሪካን ሴናተሮች የኢትዮጵያን ወቅታዊ
ሁኔታ ከግምት አስገብተው ሀገር ውስጥ ካሉ ፓርቲዎች ይልቅ፣ ዋሽንግተን ከሚገኙ ፖለቲከኞች ጋር መወያየትን የመረጡት። እንደ
ኢትዮጵያ ባለ ደህነት ጥግ በደረሰበት ሀገር፣ መቼም ታላላቆቹ ሀገራት የሚኖራቸው ተፅእኖ ታሪክ እስከመቀየር የሚደርስበት አጋጣሚ
ሊኖር ይችላል፡፡ እናም ለአለም አቀፍ ማህበረሰቡ ጠንካራ መሆንን ማሳመን ለፖለቲካ ክምችት ወሳኝ ነው። የአለም አቀፍ ፖለቲካን
አለመከታተልም የተቃዋሚ ፓርቲዎች መገለጫቸው ሆኗል።
ሳይደራጁ መቃወም?
ማደራጀት ላይም ቢሆን ፋሽኑ ያለፈበት ስልት ከመከተል ባሻገር አዳዲስ ፈጠራዎችን አይጠቀሙም። ይህ ሁኔታም ነው በ‹‹ስብሰባ
አዳራሽ ተከለከልን›› አይነት ጩኸታቸው መቀለጃ ያደረጋቸው፡፡ ለአንድ ፓርቲ ከዚህ በላይ አሳፋሪ ነገር አለ ብዬ አላስብም። ምክንያቱም
‹‹ኢህአዴግ አምባገነን እና አፋኝ ስለሆነ ከስልጣኑ መነሳት አለበት›› በሚል መደምደሚያ ላይ ቆመው ሲያበቁ፣ ጥቃቅን ችግሮችን ሳይቀር
በማጎን ከእንቅስቃሴ ሲገቱ እየታዩ ነውና፡፡ መቼም ‹‹ኢህአዴግ ዴሞክራት ነው›› የሚል ክርክር ካልተነሳ በቀር፣ በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ
እንቅስቃሴያቸውን ማስተጓጎሉ ‹‹ያልጠበቅነው ነው›› ሊሉ አይችሉም፡፡ በዚህ ከተስማመን ለችግር ጊዜ የሚሆን አማራጭ መፍትሄን
ማዘጋጀት አለባቸው። ለምሳሌ የአዳራሽ ችግርን ለማስወገድ ከፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች መኮረጅ ይቻላል፡፡ የእምነቱ ተከታዮች
እንደአሁኑ በቂ የማምለኪያ ቦታዎች ባልነበራቸው ጊዜ ወይም የመንግስት ጫና ባገዳቸው ዘመን መኖሪያ ቤታቸውን ወደጊዜያዊ
ቤተክርስቲያንነት ለውጠው አምልከዋል። ግቢያቸውንም ድንኳን ጥለውበት ፕሮግራማቸውን ሲያካሄዱ ማየቱ የተለመደ ነበር። ዋናው
ፅናት እና ቁርጠኝነት ነው። በፓርቲው ላይ እምነት አሳድሮ የተቀላቀለ ታጋይ ግቢውን እና መኖሪያ ቤቱን ለስብሰባ በማዋል እነዚህንጥቃቅን ግዴታዎችን ሳይወጣ ስለመስዕዋትነት ሊያወራ አይችልም፡፡ እንዲሁም አንድ ሺህ ሰው በአዳራሽ ለመሰብሰብ ከተከለከሉ፣ መቶ
ሰዎችን መኖሪያ ቤታቸው ሰብሰበው ፕሮግራማቸውን ከማካሄድ የበለጠ የፖለቲካ ትርፍ የለም፡፡ እንዲህ አይነት አማራጮች የፓርቲውን
መዋቅር በቀላሉ ወደ ህዝብ አስርጎ ለማስገባት ያስችላል፡፡ በዚህም ከብዙሀኑ መረጃ ሰብስቦና አስጠንቶ የፍላጎት ድምርን (Intrest
Agregation) በማወቅ ውጤቱን ወደፖሊሲ በመቀየር የተሻለ ድጋፍ ማሰባሰብ ይችላል። ከዚህ ባለፈ ‹‹ለአዳራሽ ገንዘብ ከፍዬ
ተከለከልኩ››፣ ‹‹ስርዓቱ ሊያስረኝ ይችላል››፣ ‹‹ንግዴን ይዘጉብኛል››፣ ‹‹ከስራዬ ያባርሩኛል››፣ ‹‹በቤተሰቤ ላይ ቢመጡስ››… የሚሉ
ተልካሻ ሰበቦች የሚሰሙበት ዘመን መቆም አለበት፡፡
በአናቱም የተለያዩ ‹‹ክርታሶችን›› የማዘጋጀት ልምድም ከኢህአዴግ መኮረጁ እንዲሁ ጠቃሚ ነው። ኢህአዴግ የማያውቀውን ወይም
የማይቀበለውን ‹‹አባላትን በውስጥ ክርክር አዳብሮ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እንዲለማመዱ እና እንዲተገብሩ ማድረጉ›› መሰረት ያለው
መዋቅር ይፈጥራል። በተቃዋሚዎች ሰፈር በተጨባጭ ያለው ግን አምባገነናዊ የፓርቲ መዋቅር ነው፡፡ አባላትን ለማብዛት አለመስራትም
ተጠቃሽ ድክመት ነው፡፡ የሰበሰቡትንም ጥቂት አባላት ማንቃት፣ መረጃ ማቀበል፣ የንባብ ባህልን ማለማመድ ከስራቸው ዋነኛው አድርገው
አይወስዱትም፡፡ መቼም ዛሬም ድረስ በብዙ ኢትዮጵያውያን ህሊና ሊረሱ ያልቻሉት ኢህአፓ እና መኢሶን በመሪዎቹ ዝና አይመስለኝም፡፡
አባሎቻቸው ለፖለቲካ ቅርብ እንዲሆኑ አቅደው በመስራታቸው እንጂ፡፡ በወቅቱ የፓርቲ አባል ለመሆን ማንበብ ግድ ይላል፡፡ አልፎ
ተርፎም ፓርቲዎቹ ለአባሎቻቸው ‹‹ይሄንን ይሄንን መጽሐፍ አንብቡ›› ብለው መመሪያ ያወርዱ ነበር፡፡ ያወረዱት መመሪያም ምን ያህል
እንደተተገበረ አባላቶቻቸው በየአካባቢያቸው እንዲወያዩበት በማድረግ ይገማገሙ ነበር፡፡ ይህ አካሄዳቸው ነው ‹‹ከየት ተነስተው፣ ወዴት
እንደሚሄዱ›› የሚያውቁ፣ በታላቅ ዲሲፕሊን የታነፁ፣ የሚሞቱለት ራዕይ ያላቸው፣ ከግለኝነት የራቁ ሀገር እና ህዝብ ምን ማለት እንደሆነ
ጠንቅቀው የሚያውቁ መሪዎች እና አባላትን በብዛት ያፈራላቸው፡፡ አንድነት፣ አረና እና ኦፌዴን ይህንን ተሞክሮ ቢጠቀሙበት አትራፊ
ይመስሉኛል፡፡
እንደመውጪያ
የሀገራችን ተቃዋሚዎች የተለያዩ የዘመኑን ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀምም ፕሮግራማቸውን ለህዝብ ለማስተዋወቅ ሲሞክሩ
አይታዩም፡፡ ድረ-ገጾችን፣ ፌስቡክን፣ ቲውተርን… የመሳሰሉ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በሚገባ መጠቀሙ ዘመኑ ያመጣው የትግል ስልት
በመሆኑ የኢህአዴግን ሴራ እና ጫና አሸንፎ ለመውጣት ወሳኝ ነው። እንዲሁም የግብፁን “Muslim Brotherhood” (የሙስሊም
ወንድማማቾች) የመሳሰሉ በአምባገነን ስርዓት ውስጥ ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠር ከቻሉት ብዙ መማር ይቻላል። ርዕዮተ-ዓለሙ ምንም
ይሁን ምን፣ ጥንካሬን ያገኘበት መንገድ ነው ትምህርት የሚሆነው፡፡ ይህ ፓርቲ እ.ኤ.አ. በ1928 ዓ.ም. ነው Hassah Al-Bahha (ሃሳህ
አል-ባሃ) በተባሉ ግብፃዊ የተመሰረተው። የመጀመሪያው የድርጅቱ ሊቀመንበርም እኚሁ ሰው ነበሩ፡፡ ሆኖም እእአ በ1948 ዓ.ም በግፍ
ተገድለዋል። በነገራችን ላይ ሙስሊም ብራዘር ሁድ ከሶስት ያላነሱ መሪዎቹ በተለያ ጊዜ ተገለውበታል። ይህም ሆኖ ሲበታተን እና
ሲፍረከረክ አልታየም፡፡ እንድያውም ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር እየተዋሃደ በማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ (ትምህርት ቤት በመክፈት፣
ሆስፒታል በመገንባት፣ የስፖርት ክለብ በማቋቋም…) በመሳተፍ ራሱን ወደ ህዝቡ ሲያሰርግ ነው የቆየው፡፡ እነሆም ከተመሰረተ ከ80
አመት በኋላ ለስልጣን በቅቷል።
ሌላኛው ነጥብ ከባህር ማዶ ደጋፊዎቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይመለከታል፡፡ ተቃዋሚዎች ከትውልደ ኢትዮጵያውያን የዳይስፖራ
ደጋፊዎቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከታሪካቸው በመማር በቅጡ ማረም ይገባቸዋል፡፡ ዲያስፖራው የሚያደርገውን የገንዘብና የቁሳቁስ
ድጋፍ በተሻለ መልኩ የሚያገኙበትን መንገድ ማጠናከር ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን የፖለቲካው እርግማንም ሆነ በረከት ያለው
እዚሁ አገር ውስጥ እስከሆነ ድረስ አጣብቂኝ በመጣ ቁጥር መውጪያ ለመፈለግ ባህር መሻገር አለባቸው ብዬ አላስብም፡፡
በተጨማሪም በትውልዱ ጥያቄ ላይ የተመሰረተ እቅድ አዘጋጅተው ፍርሃታቸውን አሸንፈው በምርጫም ሆነ ከምርጫ ውጪ በሚደረጉ
ሰላማዊ እምቢተኝነት የስርዓቱን እድሜ ማሳጠር ቀዳሚ የቤት ስራቸው ለመሆኑ ነጋሪ መጠበቅ የለባቸውም፡፡ ፍራቻንም ከመዘገበ
ቃላታቸው መፋቅ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም አመራሩ ካልደፈረ አባል ሊደፍር አይችልም፤ አባሉ ካልደፈረ አዲስ አባል ደፍሮ ሊመጣ
አይችልም፤ አባል ካልበዛ ደግሞ በምንም መልኩ ጠንካራ መሆን አይቻልም፡፡
በመጨረሻም አንድነት፣ አረና እና ኦፌዴን እነዚህን ድክመቶቻቸውን አስተካክለው መቆም ከቻሉ (የሚችሉም ይመስለኛል) በትክክልም
አማራጭ ፓርቲ የመሆን እድል አላቸው። ዛሬ ፓርቲዎች ከቆሙበት የማውገዝ ፖለቲካ አልፈው ስርዓቱ ላይ ጫና በመፍጠር እጅ
እስከመጠምዘዝ ሊደርሱ የሚችሉበት እድል ብዙ ነው። ለውጥ ለማምጣትም የምርጫ ዘመንን ብቻ ለመጠበቅ አይገደዱም። …ተቃዋሚ
ፓርቲዎች በጊዜ ነቅተው ቢሆን ኖሮ ደግሞ ከሰሞኑ የፖለቲካው መንፈስ ለውጤት የሚያበቃ ድል ባገኙም ነበር፡፡ ግና! አሁንም ጊዜ አለ፤
እናም ‹‹ከምርጫው ወጥቻለሁ›› ብሎ መግለጫ ከመስጠት አልፈው፣ ሌላ አማራጭን መከተል ይጠበቅባቸዋል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on March 18, 2013
  • By:
  • Last Modified: March 18, 2013 @ 2:23 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar