www.maledatimes.com የክሽፈት እንጉርጉሮ፣ ታሪክ ላይ ተሸንቅሮ! (በካሣሁን ዓለሙ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የክሽፈት እንጉርጉሮ፣ ታሪክ ላይ ተሸንቅሮ! (በካሣሁን ዓለሙ)

By   /   March 19, 2013  /   Comments Off on የክሽፈት እንጉርጉሮ፣ ታሪክ ላይ ተሸንቅሮ! (በካሣሁን ዓለሙ)

    Print       Email
0 0
Read Time:87 Minute, 30 Second

“አንድ ሰው በአደባባይ ሲናገርም ሆነ ጽሑፍ አሳትሞ ሲያሰራጭ ራሱን አጋልጦአል፤ የተናገረው ወይም የጻፈው መቶ በመቶ ያህል በራሱ ጉዳይ ላይ ብቻ ከሆነ፣ የመተቸት ወይም ሐሳብ የመስጠት ግደታ የለብንም፤ ነገር ግን የተናገረው ወይም የጻፈው በአገርና በሕዝብ ጉዳይ ላይ ከሆነ፣ የዚያ አገር ዜጋ ሁሉ በጉዳዩ ውስጥ የመሳተፍና ሐሳቡን በሙሉ ነጻነት የመስጠት መብት አለው።”

(ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም፣ መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ፣ ገጽ78-79)

 

 

1. መንደርደሪያ

“ክሽፈት! ክሽፈት!” ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የሚቀነቀን እንጉርጉሮ ነው፤ በብሎጎች፣ በማኅበራዊ ድራተ-ገጾች፣ በእርስ በርስ ጨዋታዎች…. በጭቅጭቅ ወይም በክርክር መልክ ይዘመራል። የዚህ እንጉርጉሮ መነሻ ደግሞ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም “መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ” በሚል ርዕስ በቅርቡ ያሳተሙት መጽሐፍ ነው። እንደኔ ዕይታ በዚህ ዓመት በአማርኛ ከታተሙ መጻሕፍት መካከልም እንደዚህ መጽሐፍ አመራማሪ፣ አወያይና አከራከሪ መጽሐፍ የተገኘ አይመስለኝም፤ ለዚህም የመጽሐፉ ርእሰ ክብደት፣ የአቀራረቡ ምርምራዊ ሙግት መሆን፣ ታሪክን ከፍልስፍናውና ከኩነቶቹ በመመሥረት ያስቀመጠበት ዐውዱ፣ ታዋቂ የታሪክ ሊቃውንት ሥራዎችን ወስዶ በቀጥታ መተቸቱ፣ በኢትዮጵያ ታሪክና ነባራዊ ሁኔታ ዙሪያ በቁጭት አቀራረብ መቃኘቱ፣ ጸሐፊው ቀድሞውንም ተፅዕኖ ፈጣሪ የአደባባይ ደፋር ምሁር መሆናቸው፣… መጽሐፉን ልዩና አነጋጋሪ ያደረገው ይመስለኛል። የሚያሳድረው ተጽዕኖም ከፍተኛ መሆኑ በግልፅ እየታየ ነው።

 

በዚህ መልክ ተፅዕኖው ከፍተኛ የሆነ መጽሐፍ ከሆነም መልካም ጎኖቹ እንዳሉ ሆነው አጠያያቂነትና አከራካሪነቱም በአግባቡ መመርመር ይኖርበታል ባይ ነኝ፤ ስለሆነም በመጽሐፉ ርዕስ፣ ይዘትና መዋቅር ዙሪያ መወያየት፣ መከራከርና መነጋገር ያስፈልጋል፤ የተጀመረውም ዝማሬያዊ ውዳሴም ሆነ ትችታዊ ነቀፋው መቀጠሉ የውይይት ባህልን ያዳብራል፤ ጠቃሚም የሚሆነው በትችት በመቃኘት ሲከራከሩበት ነው። በራሴ ግን የመሰለኝን አስተያያትና ትችት ላቅርብ ብዬ ይችን ጽሑፍ አዘጋጀሁ፤ ምንም እንኳን አስተያየቴ በሌሎች ተችዎች አልተነካም፤ አልተሞገተበትም ባልልም፤ ከኢትዮጵያ የሥልጣኔ ደረጃና የታሪክ አተያይ አንጻር ብዙም የታየ አልመሰለኝም። ስለዚህ መጽሐፉ ላይ በግሌ የማልስማማቸው የአቀራረብ፣ የመነሻና የአተያይ አስተያየቶች ጠቋቁሜያሉ፤ አቀራረቤም ትችታዊ ስለሆነ በዚህ ስሜት እንዲታይ ታዳሚዎችን አደራ እላለሁ።

 

መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ2. የርዕሱ አግባባዊነት?

የፕሮፌሰር መስፍን መጽሐፍ ከርዕሱ ጀምሮ “መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ” ሲል አጨቃጫቂነት ይንጸባረቅበታል፤ ይህ በንጽጽር ዘይቤ የተቀመጠ ርዕስ የኢትዮጵያ ታሪክ ከሽፎ አልቋል በሚል ለሌላ ጉዳይ ማነጻጸሪያ በመሆን የተጠቀሰ ያስመስላል። የመክሸፍን ምንነት ለመግለጽ እንጂ የኢትዮጵያን ታሪክ አከሻሸፍ ለማብራራት የተሠጠ ስያሜ አይመስልም። ይህም ልክ የኑሮን አስቸጋሪነትን ወይም ክብደትን አፅንዖት ለመስጠት “ኑሮ እንደድንጋይ ከብዶናል” እንደምንለው ዓይነት አገላለፅ ነው። “መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ” ማለት መክሽፍን ማወቅና መረዳት ከፈለጋችሁ የኢትዮጵያን ታሪክ ተመልከቱ ማለት ነው። ስለዚህ ከርዕሱ የምንረዳው የኢትዮጵያ ታሪክ የመክሸፍ ምንነት ማነጻጸሪያና ማሳያ ነው። “ኢትዮጵያ ታሪክ ከሽፏል ወይ?” የሚለው ጥያቄ ደግሞ ገና መልስ የሚፈልግ አከራካሪ ነጥብ ነው። ይህ ከሆነም ገና መክሸፉ ያልተረጋገጠ ጉዳይ የመክሸፍን ምንነት ለማብራራት አያስችልም፤ ባይሆን “የኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈት” ቢባል ኖሮ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከሽፏል፤ አልከሸፍም?” የሚለው ጥያቄ ላይ ክርካራችን ይሸከረከር ነበር። ከላይ እኮ “ኑሮ እንደድንጋይ ከብዶናል” ብለን የኑሮን ክብደት የገለጽነው የድንጋይ ክቡድነትን በማወቅ ስምምነት ስላለን ነው። እና! ፕሮፌሰር “መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ” ብለው ርዕስ የሰጡት ማን በኢትዮጵያ ታሪክ መክሸፍ ላይ ተስማምቶ ነው? ወይም “መክሸፉን በምን ያህል እርግጠኛ ሆነው ነው? ስለሆነም የፕ/ር መጽሐፍ ርዕስ ዐይቶ የማይሳብና ጭቅጭቅ ወይም ሙግት ውስጥ የማይገባ ቀለም ቀመስ ኢትዮጵያዊ አይኖርም። “እሺ! ፕ/ር ይህንን ርዕስ ለምን መረጡ?” ለሚለው ጥያቄ መልሱን በትክክል ለመገመት ያስቸግራል፤ በእኔ ግምት ግን ርዕሱ ምሬታቸውን አግዝፈው ለመግለጽ በመፈለግ የሰየሙት ይመስለኛል።

እንዲሁም ከርዕሱ ጋር አያይዘው ያስቀመጡት፡-

 

“እናት ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ፣ ተላላ፤

የሞተልሽ ቀርቶ፣ የገደለሽ በላ።” የሚል ግጥም አለ።

 

ግጥሙ ርዕሱን አጎላማሽ በማድረግ ያስቀመጡት ነው። ነገር ግን ይህንን ግጥም “ሥልጣን፣ ባህልና አገዛዝ፣ፖለቲካና ምርጫ” በሚለው መጽሐፋቸው ከራስ ወዳድነት ጋር ይያያዛል በሚል “ምን ማለት ነው? የሞተላትማ ሊበላ አይችልም፤ ሞቷል።… ትርጉም የለውም። ትልቁ ቁምነገር “የገደለሽ በላ” የሚለው ነው። ሌላው ቁጭት ነው፤ ቁጭቱ ለምን ላገሩ ሞተ? ወይስ የገደለው ስለበላ ግልፅ አይደለም።” በሚል ከሀገር ፍቅር ይልቅ ለራስ ጥቅም ያደረ መሆኑን አብራርተው ተችተውት ነበር። ጥያቄው “ለምን ተቹት?” አይደለም፤ ለማለት የተፈለገው በዚያኛው መጽሐፋቸው እንደዚያ ከተቹት በዚህኛው መጽሐፋቸው ግጥሙን በንዑስ ርዕስነት ያስቀመጡት በዚያ ያቀረቡትን መሟገቻ ሽረውታል? ነው ሌላ ትርጉም ሰጥተውት? ግልጽ አይደለም።

 

የርዕሱን አሰያየም አጨቃጫቂነት በአእምሯችን ይዘን ክርክራችን በአሳቡ ላይ ያተኮረ እናድርገው፤ እንግዲህ በርዕሱ እንደምንመለከተው የመጽሐፉ ዋና መሽከርከሪያ ነጥብ የመክሸፍን ጉዳይ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር እያነጻጸረ ማቅረብና ማስረዳት ነው፤ ይህ ከሆነ ደግሞ የክሽፈትን ምንነት ከሸፈ ከሚለው የኢትዮጵያ ታሪክ ጋር አንጽሮ ማሳየትና ማስረዳት ይጠበቅበታል፤ “ያን አድርጓል ወይ ነው?” ጥያቄው። መልሳችን አድርጓል ከሆነ የኢትዮጵያን ታሪክ ክስተትና በዘመናት ሁሉ የተፈጠረውን ክሽፈት ማሳየት ችሏል ማለታችን ነው። አላሳየም የምንል ከሆነም ያልንበትም ምክንያትና የምክንያታችንንም ማሳያዎች ማቅረብ ይጠበቅብናል። ለማንኛውም እስቲ መጽሐፉን ከመዋቅር አንጻር እንቃኘው።

 

3. እንዴት ተዋቀረ?

በአጠቃላይ መጽሐፉ በ12 ምዕራፎች ተከፋፍሎ የቀረበ ሲሆን በጥቅሉም በሦስት ክፍላት ሊከፋፈል የሚችል ነው፤ የመጀመሪያው ክፍል በምዕራፍ 1 የሚገኘው ሲሆን ቁጭት ባዘሉ ቃላትና ስሜት የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ስፖርት፣ ማህበራዊ ተቋማት፣ ፖለቲካዊ አድረጃጀት፣ ወዘተ መክሸፋቸውን በመግቢያ መልክ የሚገልፅ ነው። በዚህ ክፍል ዕይታ በመተባበር የውጭ ወራሪን ሆ! ብሎ ከመከላከል ውጭ ያልከሸፈ የኢትዮጵያ መለያ የለም ማለት ይቻላል፤ ስለዚህ ይህ ክፍል የርዕሱን ማጠንጠኛ ያካተተ ነው ማለት እንችላለን፤ ችግሩ ባይሆን “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” ከማለት አልፎ “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ!” የሚል አቀራረብን ይከተላል፤ አይ! ይሁን በታሪክ ውስጥ የማይካተት ጉዳይ የለም ብለን ብንቀበለው እንኳን የታሪኩን አከሻሸፍ በአግባቡ አላሳየም፤ በአብዛኛው የሚያጠነጥነው በ20ኛዋ መ/ክ/ዘ ኢትዮጵያ በተለይም በቀ/ን/ነ ኃ/ሥላሴ፣ በደርግና በኢሕአዴግ የአገዛዝ ሥርዓቶች በተፈጠረ የታሪክ ችግር ዙሪያ ነው፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ይህ ብቻ ነው እንዴ? የጥንቱ ታሪክስ? ነው የከሸፈው ከ20ኛ መ/ክ/ዘ ጀምሮ ያለው ታሪካችን ነው?

 

ሁለተኛው የመጽሐፉ ክፍል ልንለው የምንችለው ከምዕራፍ 2-6 ያለውን ስለታሪክ ምንነት፣ ፍልስፍና፣ አዘጋገብና ስለኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊዎች የአጻጻፍ ችግር የሚሞግተው ክፍል ነው። ምዕራፍ 2-3 የታሪክ ምንነት፣ ፍልስፍናዊ መሠረትና አተያይ በመዳሰስ ተቀምጦበታል፤ ይሁንና የመጽሐፉ ዋና ማቆሚያ ትልቅ ምሰሶ ያለው በዚሁ ክፍል ከምዕራፍ 4-6 ባለው ውስጥ ይመስላል፤ በእነዚህ በሦስት ምዕራፎች የኢትዮጵያ ታሪክ ዐውድ ተዳሶበታል፤ መሠረታዊ የሆኑ መመዘኛ ጽንሣተ ሐሳባትን (ሀገረ-መንግሥት፣ ኤምፓየር እና ወሰንና ጠረፍ የሚሉ ጽንሣተ-ሐሳብን) በመምረጥም በሦስት ምሁራን ሥራዎች ላይ አከራካሪና አመራማሪ ሙግት ቀርቦበታል። ምንም እንኳን ይኸ የመጽሐፉ ዋና ማጠንጠኛ የሆነውን የመክሸፍን ጉዳይ በአግባቡ የተከተለ ነው ማለት ባይቻልም፤ በዚህ ክፍል የሚገኘው ሐሳብ ምሁራንን የሚሞግትና የሞገተ፣ በጆግራፊያዊ ሥዕሉ አመራማሪ፣ የታሪክ ሊቃውንቱ ያዩበትን አንግል ቀይሮ ዐውዳቸውን ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው፤ ብዙዎችንም ለውይይትና ለክርክር የጋበዘው ይህ ክፍል ይመስላል።

 

ቀጣዩ ሦስተኛው ክፍል ከምዕራፍ 7 ጀምሮ ያለው ሲሆን በእኔ እይታ በውስጡ ሦስት ንዑሳን ክፍላት ይኖሩታል። የመጀመሪያው ንዑስ ክፍል ከምዕራፍ 7-10 ያለው ክፍል ሲሆን ኢትዮጵያ አንድነቷን ለማስጠበቅና ለማጠንከር ከቄሣራዊያን ኃይሎች ጋር ያደረገችውን ተጋድሎ ይተርካል። በዚህም አበው የቄሣሪያዊያን (የቅኝ ገዥዎችን) ተንኮልና የመከፋፈል ስልት ተቋቁመውና የሀገር አንድነት ለማስጠበቅ የጦርነት መስዋዕነት ከፍለው ኢትዮጵያን እንዳቆዩልን ያብራራል፤ ይህም ክፍል በተለይ ከዐፄ ዮሐንስ እስከ ደርግ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ያለውን የታሪክ ዐበይት ክንውኖች በጥቅል መልክ በመውሰድ ኢትዮጵያዊ ኩራት እንዲሰማን ሥዕል ይሥልብናል። ከርዕሱ አንጻር ግን “ታዲያ ይኸ በመስዋዕትነት ውጤታማ መሆንን ነው የሚገልጸው መክሸፍን?” ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው መልስ በአብዛኛው የርዕሱን ተቃራኒ ነው፤ አበው በመስዋዕትነት ነጻነታቸውን ማስጠበቃቸውን፣ አንድነታቸውን ማጥበቃቸውን ነው የሚመሰክረው። ምናልባት ይህ መስዋዕትነት የተከፈለበት ነፃነት፣ ተጠብቆ የቆየን አንድነት ጠፍቷል ወይም ከሸፏል ከተባለ በዚህ በዚህ ምክንያት ይህ ተበላሽቷል ብሎ ማሳየት ነበረበት፤ ያሳየው ነገር ግን የለም። “ምናልባት መክሸፉን በሌላ ምዕራፍ ለማሳያት ፈልጎ በጥቅል ማስቀመጡ ይሆን?” የሚል ጥያቄን ዐንስተን ወደ ቀጣዩ ንዑስ ክፍል እንለፍ!

 

የዚህ ክፍል ሁለተኛው ንዑስ ክፍል ስለመንደርተኛነትና ሕዝባዊነት የሚያወራው ምዕራፍ 11 ነው። ይህም መንድርተኝነት በሕዝባዊነት ላይ ያለውን ተፅዕኖ ያብራራል፤ በተለይ ሶማሌዎች በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን ፍላጎትና አመለካከት በመንደርተኝነት አስተሳሰብ የመጣ መሆኑን በምሳሌነት ወስዶ ያሳያል። በዚህ ክፍል እሳቤ የኢትዮጵያ ታሪክ የከሸፈው በመንደርተኛነት አስተሳሰብ ነው የሚል ይመስላል። ሆኖም ይህንን በአግባቡ ማሳየት ችሏል ማለት ግን አይቻልም። ምሳሌውም ሶማሌ ለምን እንደሆነች ግልፅ አይደለም፤ ምክንያቱም ሶማሌ የኢትዮጵያ ክፍል ባለመሆኗ አስተሳሰቡን ለመተቸት አግባባዊ ማሳያ አትመስልም። እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በሀገራችን ከሶማሌ የበለጠ የመንደርተኝነት አስተሳሰብ በንግግርም በመጽሐፍም በማቅረብ የሚሟገቱ ዘውጋዊ (መንደራዊ) አስተሳሰብ አራማጆች መኖራቸው እርግጥ በሆነበት የአንዳቸውንም ሥራ (አስተሳሰብ) እንደምሳሌ በማንሳት አልሞገተም።

 

ቀጣዩ ንዑስ ክፍል የመጽሐፉ መደምደሚያ እንደሚሆን የታሰበው ምዕራፍ 12 ነው፤ በዚህም ከአድዋ እስከ ማይጨው መሻሻል አለማሳየታችንና ጠላትን የመከላከል አቅም አለማዳበራችን ተተችቶበታል፤ አለመሻሻላችን ደግሞ “ባለህበት ሂድ” አድርጎን ኋላ ለሶማሌ የልብ ልብ ሰጥቶ እንዳስደፈረን ተነቅፎበታል ። እንዲሁም የመገለጥ ዕውቀት፣ ሥልጣንን አለመግራትና የመተባበር ባህልን አለማዳበር የሀገራችን ዐበይት ችግሮች መሆናቸው በግኝት መልክ ቀርበውበታል፤ ችግሮቹን ለማስወገድም አንደኛ የአባቶቻችን የመንፈስ ኩራት ገንዘብ ማድረግ፣ ሁለተኛም ከጉድለታችን መማር እንደሚያስፈልገን በመግለጽ ምዕራፉ ተጠቃሏል። ይህ ክፍል ስለ መክሸፍ በቀጥታ ባይናገርም ፕ/ር የመጽሐፉን ዓላማና ዋና ያሉትን ይዘት የጨመቁበት ስለሆነና ችግሮቹን አንጥረው በማውጣት የመፍትሔ አስተያየታቸውን ያቀረቡበት ስለሆነ በማጠቃላያነት “ይሁን” ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። ይሁንና የመጽሐፉ ዐቢይ ማጠንጠኛ ያልነውን የክፍል ሁለት ዕይታና ጭብጥ ግን በዚህ መደምደሚያ ምንም መጠቅለያ አልተሰጠውም።

 

መዋቅሩን ጠቅልለን ስናየው ከዚህ በላይ እንደጠቀስነው የመጽሐፉ ዐቢይ ጉዳይ በሁለተኛው ክፍል በምዕራፍ 4፣ 5 እና 6 ላይ ያርፋል፤ ሆኖም ግን ይህ ክፍል ከርዕሱ ጋር አብሮ አይሔድም፤ ከርዕሱ ጋር የሚሄደው በመግቢያነት የተጠቀሰው የመጀመሪያው ክፍል ሲሆን እሱም ቢሆን ከታሪክ ያለፉ ብዙ ጉዳዮች በዘመናዊት ኢትዮጵያ መነፅር የሚቃኝ ነው። ስለዚህ መጽሐፉ በመዋቅር አሰናሰል ከርዕሱ ውጭ ያሉ ብዙ ጉዳዮችን አጭቆ ይዟል።

 

ከርዕሱ ጋር አብሮ ይሔዳል አይሔድም የሚለውን ሙግት ትተን “ዋና ምሰሶ ነው” ካልነው ከምዕራፍ 4፣ 5 እና 6 ተነሥተን “መጽሐፉ ምን መምሰል ነበረበት?” የሚል ጥያቄ ስናነሳ በምዕራፍ 6 እንዳደረጉት ከጥንት ጀምሮ ያለውን የኢትዮጵያን ታሪክ እየቃኙ፣ ጸሐፊዎቻችን ያደረጉትን ቅሰጣና የታሪክ ዐውድ ችግር በመሞገት በእነሱ የተነሣ የኢትዮጵያ ታሪክ በተረትነት እንዴት ሊፈረጅ እንደቻለና አጻጻፋቸውም ካኩሪ ታሪካችን መለየቱን የተመረጡ የታሪክ ምሁራን ሥራዎችን ወስደው በመተቸት ቢያሳዩን ኖሮ፤ ይህም አሁን ላለንበት የመንፈስ ዝቅጠት (እሳቸው እንደሚሉት ለ”ቁልቁለት ጉዞ”) እንዳበቃን ቢያብራሩልን በአቀራረብም፣ በመዋቅርም ችግር አይኖርበትም፤ ሁሉንም ጉዳይ የመንከስ አቀራረብም አይከተልም ነበር። ምክንያቱም የመጽሐፉ ዐብይ ጉዳይ በክፍል ሁለት የጠቀስነው ከሆነ የኢትዮጵያ ታሪክ ምን ይመስል እንደነበረ ከመሠረቱ ጀምሮ በትችት መልክ ማሳየትና “አስቀያሽ” ወይም “የኢትዮጵያ ታሪክ አበላሽ” ያሏቸውን የታሪክ ምሁራን የአተያይ፣ የአዘጋገብ፣ የዓላማ፣ የመጻፊያ ቋንቋ፣ … ችግሮች አንጥሮ በማሳየት የታሪካችን አኩሪነትና የተበላሸበትን ምክንያት በቀላሉ በማሳየት ቁጭት እንዲያድርብን ማድረግ ይችሉ ነበር፤ መዋቅሩን ግን በዚህ መልክ ወጥ አላደረጉትም።

 

አንድም በክፍል ሦስት በምዕራፍ 7 እና 8 አጻጻፋቸው መሠረት የኢትዮጵያ ታሪክን በጥቅል መልክ ከጥንት ጀምሮ ያለውን ደረጃና አደረጃጀት በመዳሰስ ወይ በየምዕራፉ ወይም በመጨረሻው አካባቢ ይኸኛው ታሪካችን በዚህ በዚህ ምክንያት በዚህ ዘመን ከሽፏል ቢሉን በአቀራረቡ ላይ ችግር አይኖርበትም ነበር፤ በዚህ መልክ ግን አላቀረቡም። መጽሐፋ ግን በክፍል አንድ የያዘው የሀገራችንን የዚህ ዘመን የመክሸፍ ቅኝት ነው፤ አቀራረቡም ሙግታዊ ሳይሆን በቁጭት የተቃኘ ነው። ክፍል ሁለት የተመረጡ የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊዎች ሥራዎችን የሚተች ሙግት ነው፤ ክፍል ሦስት ደግሞ የታሪክ ትምህርት ዘገባ ነው። በተለይ በሁለተኛውና በሦስተኛው ክፍሎች መካከል የአቀራረብና የታሪክ ፍሰት ልዩነት በግልፅ ይታያል። የሁለተኛው ክፍል አቀራረብ የታሪክ ምሁራንን ሥራዎች መተቸት ሲሆን፣ ሦስተኛው ደግሞ ኢትዮጵያውያን ከቄሣራዊያን ጋር ያደረጉትን ትግልና መስዋዕትነት መዘገብ ነው የተከተለው፤ እንዲሁም ክፍል ሁለት ምሁራዊ ሙግትን ያነገበ ሲሆን ሦስተኛው ክፍል ግን በፖለቲካ ዕይታ ተቃኝቶ የቀረበ ክርክራዊ ዘገባ ነው።

 

የታሪክ ፍሰቱን በሚመለከትም ራሳቸው ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራትን “ከ14ኛ መ/ክ/ዘ ታሪክ (ከዐፄ አምደ ፅዮን) ተነስቶ ዥው ብሎ 19ነኛው (ዐፄ ምኒልክ) መ/ክዘ ጋር ይገባል” እንዳሉት፤ እሳቸውም የጎንደራዊያንን ዘመን ዝም ብለው በማለፍ ተሻግረው ከዐፄ ዮሐንስ ዘመን በመጀመር ሦስተኛውን ክፍል ይዘግባሉ። በሦስተኛው ክፍል አተያይ ፕሮፌሰሩ ታሪካችንን መዘገባቸው መልካም ሆኖ ግን የታሪክ ባለሙያዎችን ሊተቹ የሚችሉበት ልዩ አቀራረብ የላቸውም፤ ምክንያቱም አቀራረባቸው ዘገባዊ ነው፤ ከሌሎች ጸሐፊዎች ያላቸው ልዩነትም የማስረጃ አቀራረብ ሁኔታ ይመስላል፡- በተለይም ከቄሣራዊያን ኃይሎች ጋር የተደረጉ ውሎችን በሚመለከት ያቀረቡት። ከዚያ ይልቅ እንደ ሁለተኛው ክፍል በዚህም አስፈላጊ የሆኑ የታሪክ ጽሑፎችን በማሳያነት ወስደው በማነጻጸር በአቀራረብና በአተያይ የቄሣራዊያንን ሸርና የመንደርተኛነት ዐውድ ቢሞግቱ የአቀራረብ ሁኔታው ወጥነትን ይጠብቅ ነበር።

 

4. ዋናው ማጠንጠኛ እንዴት ታየ?

የመዋቅሩን ጉዳይ በዚህ እናቁምና ይዘቱስ ምን ይመስላል ወደሚለው ነጥብ እንዙር። ነገር ግን በመደምደሚያው ላይ ከሰጠሁት ከተወሰነ ምልከታ በስተቀር ከክፍል ሁለት በኋላ ያለውን ይዘት መዳሰሱ ብዙም አስፈላጊ አልመሰለኝም፤ ዋናው ክፍል ይኸኛው ነው ብዬ ስለማምን። ለማንኛውም ይዘቱንም አንዳንድ ነጥቦችንም በማንሳት እንገምግመው፤ በርዕሱ እንደተገለጸውና በመግቢያውም በእንጉርጉሮ አዝማችነት ቃሉ እንደተሰገሰገው “የኢትዮጵያ ታሪክ ከሽፏል” ተብሏል፤ እዚህ ላይ የዳንኤል ክብረት “ታሪክ ይከሽፋል ወይ?” የምትለው መሠረታዊ ጥያቄ ትመጣለች።

 

ፕ/ሩ “መክሸፍ የምለው አንድ የተጀመረ ነገር ሳይጠናቀቅ ወይም ሳይሳካ እንቅፋት ገጥሞት መቀጠል ሳይችል ዓላማው ሲደናቀፍና በፊት ከነበረበት ምንም ያህል ወደፊት ሳይራመድ መቅረቱን ነው፤” (ገጽ 7) ብለዋል፤ እኔ በግሌ ይህ ገለጻ “እሳቸው ብለውታልና እንስማማ” ካልተባለ በስተቀር “ታሪክ ያለፉትን ተከታታይ ትውልዶች ከዛሬውና ከወደፊት ትውልዶች ጋር የሚያገናኝ፣ የሚያስተዋውቅና የሚያስተሳስር ሰንሰለት ነው፤” (ገጽ 35) በማለት ካብራሩት ሐሳብ ጋር አብሮ ተሰናስሎ ክሸፈትን ይገልጻል ብዬ ለመቀበል ያስቸግረኛል። “የኢትዮጵያ ታሪክ ከሽፋል ወይ?” ለሚለው ጥያቄም ብቁ መልስ የሚያሰጥ አይደለም። ምክንያቱም “የኢትዮጵያ ታሪክ ከሽፏል” ከተባለ “የወደፊቱን ትውልድ ከባለፈው የሚያገናኘው ሰንሰለት በዛሬው ትውልድ ተበጥሷል” ማለታችን ነው እንጂ “ታሪክ ከየት ተነሥተን፣ ምን አጋጥሞን፣ ማን ጥሎን፣ ማንን ጥለን፣ ምንን ይዘን ቆይተን፣ ምንን ይዘን ለወደፊት እናስባለን? የሚሉትን ጥያቄዎች በትክክል የሚመልስልን” (ገጽ 38) አልሆነም ማለት ነው። የታሪክ መበጠስ (መክሸፍ) የሚገልፀው ፍሰቱ፣ ቅብብሉ መቆሙንና ዘገባው መደምሰሱን ነው። በታሪክ ክስተቶች መካከል የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች፣ መውደቅ መነሳቶችና ፍትጊያዎች ግን የታሪኩ አካል ክፍሎች ናቸው። ማለትም የታሪክ ሰንሰለት አንጓ አለው፤ በየአንጓውም ወድቀቶችና ውጤታማነቶች እየተፋተጉና እየተሰናሰሉ ታሪኩን ያሳድጉታል፤ ሰንሰለቱ ተበጥሷል ከተባለ ግን ዕድገቱ ወይም ርዝማኔው ተገትቷል፤ አብቅቶለታል ማለት ይሆናል። “የኢትዮጵያ ታሪክም ከሽፏል” ከተባለም ቀጣይነቱ ተበጥሷል፤ ለሚቀጥለው ትውልድ ከመተላለፍ ተገትቷል ማለታችን ነው።

 

እዚህ ላይ ምናልባት ከሸፈ የተባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ሳይሆን የጥንት ሥልጣኔዋ ቢሆን የሚያስኬድ ይመስላል፤ ሥልጣኔ በታሪክ ውስጥ ልዩ ክስተት (መሻሻል) የሚመዘገብበት አንድ የታሪክ አካል ነው፤ ስለሆነም ሊጠፋ ወይም ሊኮላሽ ይችላል፤ ለምሳሌ የግብፅ ምሥጢራዊ ጥበብ በአብዛኛው ተዘንግቶ ነበር፤ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ምሥጢራዊ ጥበባት በአሁኑ ትውልድ ተረት መስለዋል ወይም ተዘንግተዋል። የሐውልትና የአቤያተ ክርስቲያናት ዐሠራር ጥበባት አነዳደፋቸው ተዘንግተዋል፤ ስለዚህ “የጥንት ሥልጣኔያችን ከሸፈ” ቢባል መከራከሪያ ሊሆን ይችላል። መጽሐፉ ይህንን ለይቶ በመውሰድ የጥንት ሥልጣኔያችን መኮላሸቱን ወይም መክሸፉን አይሞግትም።

 

በሌላ በኩል መጽሐፉ በሙሉም ቢሆን “ከሸፈ” የሚለው የኢትዮጵያ ታሪክ የትኛው እንደሆነ ግልፅ አያደርግም፤ በገጽ 27 ላይ “የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ለኢትዮጵያውያን መጻፍ ሲጀምሩ ሊነግሩን የሚገባ በረጅሙ ታሪካችን ውስጥ ምንም መክሸፍ ሳይታይበት የቀጠለና እየቀጠለ ያለ ነገር ምን እንደሆነ ብናውቅ ትምህርት ይሆነን ነበር፤ እኔ ከመክሸፍ ሌላ የነበረና የአለ አይታየኝም፤” ብለዋል። ሆኖም ይህ ድምዳሜያዊ ገለጻ ጥያቄ ከመጠየቅ አይገታንም። “ትምህርት ይሆነን ነበር” ያሉት ያልከሸፈውን ታሪክ ከሆነ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ግን ከከሸፈ ታዲያ ለምን ጻፉት? መርዶ ለመንገር ነው? ለመሆኑ ከሸፈ የሚሉትስ የጥንቱን ታሪካችንን ነው ወይስ ዘመናዊ ታሪካችንን? ሁሉም ከተባለ ከመቼ እስከ መቼ ባለው ዘመን ነው የከሸፈው? ነው ሲከሽፍ ነው የኖረው? በማን የተሠራውን ታሪክ ማን አከሸፈው? እንዴት? በምንስ መሥፈርት? ነው አዘጋገቡ ነው ያከሸፈው?… ከሽፏል ከተባለ እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች አግባባዊና አጥጋቢ መልስ ማግኘት አለባቸው።

 

በዚህም የጥንቱ ታሪካችን ነው “የከሸፈው” እንዳይባል በመጽሐፉ ስለጥንታዊ ታሪካችን ምንነትና አከሻሸፍ የተገለጸ ነገር የለም፤ የተጠቀሰ ጥንታዊ ታሪክ ቢኖርም ቁጽል ነው፤ ለምሳሌ “ገና ተጠንቶ አላለቀም እንጂ ኢትዮጵያውያን ከሞሮኮ እስከ ህንድ ማኅተማቸው ይገኛል” ብለዋል። (ገጽ 37) ይህ ጥንታዊ ታሪካችን ነው የከሸፈው? ነው ከተባለ “ክሽፈቱ” አሻራቸው ባለመጠናቱና ባለመታወቁ ነው? ወይስ የነበረው የሥልጣኔያቸው አሻራ ቀጥሎ እኛ ዘንድ ባለመድረሱ? የተጠቀሰው የንግሥተ ሣባ (ንግሥት ማክዳ) ታሪክና የክብረ ነገሥት ገለፃም ቢሆን ጥንታዊ ኢትዮጵያን ለማሳየት ብቁ አይደለም። በአጭሩ ስለጥንታዊ ታሪካችን ልዕልና እና ውድቀት የምናገኘው ማብራሪያ አጥጋቢ አይደለም። ዘመናዊ ታሪካችንን ይሆን ብለን እንዳንወሰን ከውጭ ወራሪዎች ጋር የተደረጉ ተጋድሎዎችንና መስዋዕትነቶችን ከመዘገብ ያለፈ የትኛው ታሪካችን በምን ሁኔታ እንደከሸፈ የሚገልጸው ነገር ግልፅ አይደለም፤ ምናልባት ከቀ/ን/ነ ኃ/ሥላሴ ጀምሮ ያሉትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና የርዕዮተ ዓለም ችግሮች ማንሳቱ ክሽፈትን መናገሩ ነው ይባል ይሆናል፤ ይሁንና ይህ የታሪካችን ትንሹ ክፍል ስለሆነ ረዥሙን የኢትዮጵያን ታሪክ ሊወክል አይችልም፤ እንደገናም እነዚህ ችግሮች ውስብስብ ተግዳሮትን ይገልጻሉ እንጂ የታሪክ ክሽፈትን አያስረግጡም። ይህንን ስላስተዋለ ሳይሆን አይቀርም ዳንኤል ክብረት “በመጽሐፉ የምናጣው ታላቁ ነገር ይሄ ነው፤” በማለት በድፍረት “ክሽፈቱ የት አለ?” ዓይነት ገለጻ የተጠቀመው። እኔም እላለሁ መጽሐፉ ስለ ክሽፈት የሚገልጸው ገለጻ አጥጋቢ አይደለም። ወደ ሌላ ነጥብ እንለፍ!

 

በየትኛው ሀገርና ጊዜ በመረጃ ምንጭ፣ በአዘጋገብ ሁኔታ፣ በዘጋቢው አመለካከትና ዓላማ እና በታሪኩ ስፋትና ጥበት የተነሣ በታሪክ ዙሪያ ሙግት መኖሩ የግድ ነው፤ እሳቸው እንዳስቀመጡት የታሪክ እውነት “እሰጥ-አገባ የሌለበት ነገር አይደለም” (ገጽ 49)፤ ምክንያቱም አንዱ ምሁር የተስማማበትን ጉዳይ ሌላው በአተያዩና በመረጃ አዘጋገቡ ሁኔታ ተነስቶ ስህተት መሆኑን ይከራከርበታል። ቢሆንም በአብዛኛው በሁኔቶች ላይ መስማማት ይፈጠራል፤ የኢትዮጵያ ታሪክም በዚህ መልክ መቃኘቱ የግድ ይሆናል። ይሁንና የኢትዮጵያን ታሪክ ጥንታዊ መሠረትና ርዝማኔ በመመርመርና በዚያ ዙሪያ ለመሞገት ፕሮፌሰር አልደፈሩም፤ ወይም “አይነኬ” አድርገው አልፈውታል። የጥንታዊ ኢትዮጵያ ታሪክ ደግሞ በሥልጣኔ ምንጭነቱ፣ በስፋቱ፣ በርዝመቱ፣ በነገሥታቱ ኃያልነት፣ ከሌሎች ጥንታዊ ሀገራት ጋር በነበራቸው ግንኙነትና በፍትሐዊ የአስተዳደር ሁኔታው አከራካሪ እንደሆነ አለ። “ከግብፅና ከኢትዮጵያ ቀድሞ የሠለጠነው የቱ ነው?”፤ “የጥንት የኢትዮጵያ የግዛት ስፋት ከሞሮኮ እስከ ሕንድ ይደርስ ነበር” እየተባለ በብዙ የጥንት ጸሐፊዎች የተገለጸውስ ተረት ነው እውነት? ኢትዮጵያስ ከ4470 ቅ.ክ.ል. ጀምሮ እስከ ቀ/ን/ነ ኃ/ሥላሴ ድረስ 346 ነገሥታት ነግሠውባታል የሚባለው ከምን የመጣ ነው? የኢትዮጵያ ነገሥታት ኃያላን እንደነበሩ የተገለጸውስ ተረት ወይስ እውነት? ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ምንጭ መሆኗን የሚዘግቡትስ ከምን አምጥተውት ነው? ነው ተረት ተረት እያወሩ? በጥንት ጊዜ ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር የነበራት ግንኙነት ምን ይመስል ነበር? ከደቡብ አረብ ግዛቶቿስ ጋር? ነው ግንኙነት አልነበራትም? … እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች በተቿቸው ምሁራንም በአግባቡ አልተዳሰሰም፤ እሳቸውም በድምዳሚያው ገለጻ ነው ያለፉት፤ ፕ/ር “የኢትዮጵያ ጥንታዊ ኃያልነት እያነሰ መጥቶ መኮስመኑ” ከቆጫቸው እነዚህ ነጥቦችን አንስተው መሞገት ነበረባቸው፤ ዋናውን መሠረት ለማን ተውት?

 

እሺ ይሁን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ታሪክ መዳሰስና ያንን መሞገት የመጽሐፉ ዋና ዓላማ ስላልሆነ በዚህ መተቸት አይገባም ቢባል እንኳን ከተጠቀሱት የታሪክ ምሁራን መካከል ትልቁ መሟገቻ የሆነውን የኢትዮጵያን የታሪክ መነሻ ዝም ብለው ሊያልፉት አይገባም ነበር፤ ለምሳሌ የፕ/ር ስርገው ሐብለሥላሴ መጽሐፍን በእንግሊዘኛ ከመጻፉ ውጭ ችግር የሌለበት አድርገው ነው የወሰዱት፤ ይሁንና የፕ/ር ስርግው መጽሐፍ የኢትያጵያ ታሪክ መነሻ ከሜሶጶጣሚያ፤ በተለይም ከደቡብ አረቢያ (ከሳባቢያውያን) እንደሆነ አድርጎ ነው ያቀረበው፤ የፕ/ር ታደሰ ታምራት መጽሐፍም በተመሳሳይ ከደቡብ አረቢያ ተሰደን መምጣታችንን ነው የሚገልጸው፤ ይህ ጉዳይ ደግሞ እነዚህን ምሁራን ብዙ ያስተቸ ነው፤ (ለምሳሌ የፕ/ር አየለ በክሬን Ethiopic; an African Writing System: History and principles የሚለውን መጽሐፍ ወይም Assumptions and Interpretations of Ethiopian History (Part II) መጣጥፍ ማየት ይቻላል) ፕ/ር መስፍን ግን ይህን ጉዳይ ምንም ሳይነኩት ነው ያለፉት፤ የእነሱን ሐሳብ ይስማሙበታል ማለት ነው?

 

ምናልባት ከታሪካችን መነሻና ምንጭ አንጻር ምንም ሳይተቹ በማለፋቸው በታሪክ ሊቃውንቱ አቀራረብ ተስማምተው ከሆነ ጥያቄዎችን ለእሳቸውም ለመጠየቅ እንገደዳለን። ለመሆኑ መነሻችን ከደቡብ አረቢያ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ምንድን ነው? ማስረጃውስ? እውን በጥንት ዘመናት ደቡብ አረቢያ ከኢትዮጵያ የተሻለ የሠለጠነ ሕዝብ የሚኖርባት ሥፍራ ነበረች? ምናልባትም ሕዝቦች ከደቡብ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አረቢያ ሄደው ሥልጣኔን አስፋፍተው ቢሆንስ? የጥንት ደቡብ አረቢያውያን ኢትዮጵያውያን ነበሩ የሚባለው ለምን እውነት ሳይሆን የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ከደቡብ አረቢያ የመጣ ነው የሚለው ዕይታ ተቀባይነት ሊያገኝ ቻለ? እነዚህ ከደበቡ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው የመጡት ሕዝቦች የትኞቹ ናቸው? ከመቼ እስከ መቼ ባለው ዘመን ውስጥ ተሰደው መጡ? ለምን ከግብፅ ወይም ከሌላ ሥፍራ አልመጡም? ከደቡብ አረቢያ የተሰደዱት ሕዝቦች ወደ ኢትዮጵያ ብቻ ነው የተሰደዱት ወይስ ወደ ሌላም ሀገር (ሥፍራ)? ለምን? … የሚሉ ጥያቄዎችን እንጠይቃለን። “ሥልጣኔያችን የደቡብ አረቢያ ሕዝቦች ወይስ የእኛ የአፍሪካውያን?” የሚል የአንድምታ ጥያቄም ያስነሣል። እኔም በአንዲት ግጥሜ፡-

 

“አክሱማዊ ሥልጣኔህ ምንጩ ከሆነ ካረብ

አንተም ከመጣህ በመረብ

አፍሪቃዊ አይደህም፤

ሥልጣኔህም የለም።” ብዬ ነበር።

 

“የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ምንጭ ደቡብ አረቢያ ነው በሚለው አልስማማም” ካሉም የጠቀሷቸው ምሁራን ከሚተቹባቸው (በተለይ ስርግውና ታደሰ) ዋና የታሪክ አቀራረቦች አንዱና ዋናው ይህ ሆኖ ሳለ ለምን እሳቸው ይህን አስፈላጊ ነገር እንደ ቀላል ሊያልፉት ቻሉ? ምናልባት “ገና ተጠንቶ አላለቀም እንጂ ኢትዮጵያውያን ከሞሮኮ እስከ ህንድ ማኅተማቸው ይገኛል” ስላሉ የሚያውቁት የጥናት እንቅስቃሴ ኖሮ ከዚያም ጋር ተሰናስሎ እንደሚቀርብ እምነት ስላላቸው ከሆነ ግን ጠቁመውት ቢያልፉ መልካም ነበር። በአጭሩ አጨቃጫቂው የኢትዮጵያ ታሪክ መነሻ ወይም የሥልጣኔ ምንጭ ዝም ተብሎ የሚታለፍ አልነበረም።

 

ከዚህ በላይ ከጠቀስናቸው የትችት ነጥቦች በተጨማሪም የመጽሐፉን መደምደሚያ ነጥቦች ለጥቅል ግንዛቤ ማየትም አስፈላጊ ይመስለኛል፤ ፕ/ር በመደምደሚያቸው “እንግዲህ ሦስቱን የኢትዮጵያ ታሪካዊና መሠረታዊ ችግሮች ያገኘናቸው ይመስለኛል፤ አንዱ በጸጋ ከተገለጡ እውነቶች የሚመጣው የችግር ዘር ሲሆን፣ ሁለተኛው ከሥልጣን አለመገራት የሚመጣው የችግር ዘር ነው፣ ሦስተኛው ከአለመተባበር የሚመጣ የችግር ዘር ነው፤” (ገጽ 198) ይሉናል። እነዚህ ችግሮች “ታሪካዊና መሠረታዊ” መባላቸውን እናስተውል። ከሆኑ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የፈጠሩት ችግር ታይቶና ተመርምሮ የታወቀ ነው ማለት ይሆናል። ፕ/ር ግን ይህንን በማድረግ ያገኟቸው አይመስለኝም፤ ለምን እንዳልመሰለኝ ላስረዳ።

 

በፕ/ር መደምደሚያ አንደኛ ዋና ችግር የተባለው “በጸጋ ከተገለጡ እውነቶች የሚመጣው የችግር ዘር” ነው፤ ኢትዮጵያ ደግሞ “በጻጋ የተገለጠ እውነቶች ሀገር እንጂ በመረጋገጥ የሚገኙ እውነቶች ሀገር አይደለችም”፤ በጸጋ የተገለጠ እውነት ማለትም ከእምነት የሚነሣ መሆኑን ገልጸዋል፤ ይህ ትክክል ከሆነም የሀገሪቱ መሠረታዊ ችግሮች በሙሉ በዚህ ዙሪያ ለመሽከርከር ይገደዳሉ ማለት ነው፤ ሃይማኖትም ለሀገሪቱ ችግሮች ምንጭነት ተጠያቂ መሆኑ አግባብ ይሆናል። እውነታው ግን ይህ አይመስልም፤ ቢያንስ በሁለት ምክንያች እሳቤው ችግር ያለበት መሆኑን ማየት ይቻላል፤ አንደኛ “ሃይማኖት የመገለጥ እውነት ብቻ” እንደሆነ አድርጎ ማየቱ ስህተት አለበት፤ ምክንያቱም ምንም እንኳን ሃይማኖት በመገለጥ እውነት ላይ ቢመሠረትም በሚረጋገጥ እውነት ይቃኛል፤ ይመረመራል፤ ትክክለኛነቱም ተመዝኖ ይታወቃል፤ ይታመናል፤ ሰዎች እምነታቸውን ከአንዱ ሃይማኖት ወደ ሌላው የሚቀይሩት በዚህ ምክንያት ይመስለኛል፤ ዝም ብሎ መቀበል ከሆነማ ለምን አንዱን እምነት ትተው ሌላውን ይመርጣሉ? በኢትዮጵያም የነበረው ሁኔታም ከዚህ የተለየ አይደለም። ሁለተኛም የፕ/ር አቀራረብ በሃይማኖት እሳቤ ውስጥ ምንም ዓይነት ክርክር፣ ምርምርና ዐዲስ ግኝት የሌለበት አስመስሎ ያስቀምጣል፤ ይህ ሌላው ስህተት ነው፤ በክርክር በኩል በሃይማኖት ዙሪያ የተደረጉ ክርክሮችን (ለምሳሌ በሀገራችን እንኳን ጸጋ፣ ቅባትና ተዋህዶ የሚሉ ንትርኮችንና የቦሩ ሜዳ ክርክርን ማስታወስ፣ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን “መጽሐፈ-ምሥጢር” መጽሐፍ ማየትና የ”ሃይማተ አበው”ን ክርክሮች) መቃኘት ይቻላል፤ ከምርምርም አንጻር የሀገራችን አብዛኛው ፍልስፍና፣ ሕክምና እና ሌሎች ጥበባት በሃይማኖት አባቶች መዘጋጀታቸውን ማጤን ያስፈልጋል፤ ከአዳዲስ ሥራዎች አኳያም አብዛኞቹ የአቤያተ ክርስቲያናት፣ የአቤያተ መንግሥታት ሕንጻዎችና የሐውልታት ንድፎች ከሃይማኖት ጋር ተያይዘው የተሠሩ መሆናቸውን ማስታወስ፣ የፊደላችንም ጥበብ የተገኘው ከሃይማኖት እሳቤ መሆኑን ግምት ውስጥ ማስገባት… ያስፈልጋል። ፕ/ር ይህንን ባለማድረጋቸው ይመስለኛል የሀገሪቱ የጥበባትና የዕወቀቶች መሠረት የሆነውን ሃይማኖታዊ እሳቤ በችግርነት የፈረጁት። ይህ ግን ፕ/ር በምርምር ባገኙት ውጤት ሳይሆን ቀድመው በገመቱት አስተሳሰብ ድምዳሜ ላይ የደረሱ ያስመስልባቸዋል። ምናልባት “ሃይማኖት ሐሽሽ ነው” ከሚለው የማርክስ መርህ ጋር አያይዘውት እንደሆነ አላውቅም።

 

የመተባበር ችግርን በሚመለከት ፕ/ር በአንድ በኩል “የኢትዮጵያን ሕዝብ ያቃተው ነገር መተባበር ነው” ይሉናል፤ በሌላ በኩል ደግሞ “ያልከሸፈ የውጭ ወረራን በአንድነት ሆ ብሎ መመከት ብቻ ነው” ይሉናል፤ ሳይተባበሩ ነው… በዐድዋ፣ በማይጨው፣ … ጦርነቶች በአንድነት ጠላታቸውን ሆ! ብለው የተዋጉት? የውስጥ መተባበርና መስማማት ሳይኖርስ የውጭውን ጠላት በአንድነት ለመውጋት ይቻላል? ምናልባት “አለመተባበሩ ለልማትና ሥልጣንን ለመግራት በሚደረገው ጥረ ነው” ሊባል ይችላል፤ ይህን ለማለት ከሆነም አንደኛ ችግሩ ተለይቶ መገለጽ አለበት፤ እንደገናም የውጭ ኃይልን የመከላከል ትብብርና የውስጥ የመተባበር መንፈስ ተለያይተው አይሄዱም፤ አንዱ በሌላው ውስጥ ይገኛል፤ በተለይም የውጭ ወረራን ለመመከት የሚደረግ መሥዋዕትነት ያለ ውስጣዊ መተባበርና የጋራ መንፈስ አይገኝም፤ በሀገር ውስጥ ወንዝ ተለይቶ የሚካሔደው የርስ በርስ ጦርነትም ቢሆን በየደረጃው መተባበር አለበት፤ በልማት በኩልም ቢሆን የደቦ ሥርዓትን የመሠለ የትብብር አሠራር አለን፤ ይህንን የትብብር ልማድ አላሻሻልነውም ማለት አንድ ነገር ነው፤ የለንም ብሎ መፈረጅ ግን ሌላ ነገር ነው። በጥቅሉ ፕ/ር መተባበርን በተቃርኖ አስተሳሰብ ተጠቅመውበታል ማለት ይቻላል።

 

በተጨማሪም ምንም እንኳን ፕ/ር ሥልጣንን መግራት አለብን በሚሉት ብስማማም ሁሉንም ነገር ከሥልጣንና ከፖለቲካ ቅኝት አንጻር በማየት ያደረጉት ትንታኔ ግን በመጽሐፉ ላይ የፖለቲካው ድባብ እንዲያርፍበት አድርጎታል፤ ይህ ደግሞ በታሪካዊ መግባባት ላይ ችግር መፍጠሩ አልቀረም። ሥልጣንን መግራትን በሚመለከትም መታወስ ያለበት በታሪካችን በወረቀት በተደነገገ ሕግ ባይሆንም ቤተ-መንግሥት፣ ቤተ-ክህነትና ቤተ-ሕዝብ በሚል ክፍፍል የሥልጣን መግሪያ ሥርዓት ነበረን፤ ይህን ከእኔ የበለጠ ራሳቸው ያውቁታል፤ ይህ በዚህ መጽሐፍ ተዘንግቷል። እንደገናም በቅርብ ጊዜ የዓለማችን ነበራዊ የፖለቲካ ሚዛን የጥንቱን ጭምር መለካት አግባብ አይሆንም ። በዚህ አንጻር ሲታይ መጽሐፉ የሥልጣንን አለመግራት “ታሪካዊና መሠረታዊ ችግርነት” በአግባቡ አላሳየም፤ ከቅርብ ጊዜ ታሪካችንና ከዘመኑ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ግን “ሥልጣንን መግራት አለብን” መባሉ ትክክል ነው።

 

ከዚሁ ጋር ተያይዞ አንድ ነገር ልብል፤ እንደ እኔ ትዝብት መጽሐፉ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ባሉ ፖለቲካዊ ችግሮች ላይ በማጠንጠኑ በአረዳዱ ዙሪያ ችግር የፈጠረ ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ፕ/ር በመጽሐፉ ያንጸባረቁት የፖለቲካ አቋምና አካሔድ የተመቻቸው በውዳሴ መልክ ጥብቅና ሲቆሙና ውዳሴያቸውን ሲሽጎደጉዱት፤ ያን የማይደግፉ ወይም በዚህ አንጻር መቃኘቱ ያልጣማቸው ደግሞ በመጽሐፉ ውስጥ ያለውን ገንቢና መሠረታዊ የታሪክ ሙግት ሳያስተውሉ ወይም በሚፈልጉት የፖለቲካ አስተሳሰብ በመመዘን ያጥጥላሉ። በዚህ የተነሣም ይመስለኛል መጽሐፉን አምርረው የሚነቅፉ እንዳሉት ሁሉ ያለ ነቀፋ የሚዘምሩለትም የበዙት። ስለዚህ ፕ/ር መጽሐፉን ከፖለቲካው መከሻሸፍም ገለል አድርገው የጋራ የታሪክ መግባባቱ ላይ በማተኮር ቢያዘጋጁት ኖሮ ይበልጥ የተሻለ ይሆን ነበር። በጥቅሉ ሲታይም መጽሐፉ ሦስቱን “ታሪካዊና መሠረታዊ ችግሮች” በአግባቡ አላሳየም ማለት ይቻላል፤ ችግሮች የተባሉትም በግምት የተጠሩ እንጂ በጥናት መልክ ከሙሉ መጽሐፉ ቅኝት የተገኙ አይመስሉም። ይህን በዚህ ልግታና በመጽሐፉ አተያይ ላይ አንድ ነገር በመጠቆም ትችቴን ልቋጭ።

 

ይህ መጽሐፍ መልካም ጎኖቹ እንደተጠበቁ ሆነው የፀለምተኝነት የዕይታ ዳራውም መተቸት የሚያስፈልገው ይመስለኛል። ልብ ሊባል የሚገባውም በመክሸፍ መነፅር የተሸፈነው የፕ/ር መጽሐፍ በኢትዮጵያ ውስጥ ጭላንጭልም አይታየው፤ ሁሉንም (ባህሉን፣ ሃይማኖቱን፣ ታሪኩን፣ አስተዳደሩን፣ ጦርነቱን…) በዘመናዊ ጥላ የረዥም ዘመን ታሪካችንን ጉዞ ጨለማ አልበሶ ነው የሚያደናብረን፤ ለዚህም ፕ/ር “እኔ ከመክሸፍ ሌላ የነበረና የአለ አይታየኝም”(ገጽ 5) ያሉት ግልጽ ማሳያ ነው፤ ያልከሸፈ ከሌለን ታዲያ ምን ተስፋ አለንና እንለፋለን? እንደ እኔ አረዳድ ምንም ዓይነት ተስፋ አስቆራጭ ነገር ቢያጋጥመን የተስፋ ጭላንጭሎችን መቃኘት ይኖርብናል እንጂ ሁሉንም ዳፍንት አድርገን መውሰድ አግባብ አይመስለኝም። እንደ እኔ ትዝብት የፕ/ር መጽሐፍ ከርዕሱ አንጻር ካየነው ቁጭትን ከመፍጠር አልፎ የሔደና በመክሸፍ አዝማች ሁሉንም ነገር ትርጉም አልባ የሚያደርግ ነው።

 

ይህ የፀለምተኝነት አቀራረብም ሁለት ችግሮችን የሚጋብዝ ይመስለኛል፤ አንደኛ በጥንት ዘመናት ኢትዮጵያ የነበራትን የሥልጣኔ ገናናነት በአግባቡ ሳያሳይ በዘመናዊ የፖለቲካ ምህዋር ላይ ስለሚሽከረከር የራስ ታሪክን (ማንነትን) በአግባቡ ሳያውቁ በዘመኑ ተግዳሮቶች ዙሪያ ላይ ብቻ ትኩረት እንዲሽከረከር ያደርጋል፤ ይህ ደግሞ አግባባዊና ዘላቂ መፍትሔን ለማሰጠት አያስችልም፤ እንዳውም የኋላ የጋራ ማንነትን በአግባቡ ባለመረዳት ቡድናዊ ትምክህቶችና ንትርኮች ተበረታትተው የባሱ ውስብስብ ችግሮች ሊፈጥሩ ይችላሉ፤ ሁለተኛ ችግሮችን አግዝፎ፣ መልካም ሀብቶችን አቅልሎ ስለሚያቀርብ ለባሰ ችግር ማራገቢያ ይሆናል፤ በዚህ የተነሣ የሀገሪቱ ተግዳሮቶች የሚከሉበት ሳይሆን የሚወሳሰቡበት ነገር በዝቶ ለሀገሪቱ ችግሮች መፍትሔ ለማግኘት የሚጥሩ ኃይሎችም ተስፎ እንዲቆርጡ ይወሰውሳል። ስለዚህ የፕሮፌሰሩ መጽሐፍ በ“መክሸፍ” ድባብ ችግሮችን ማግዘፉ ከጠቀሜታው ይልቅ ጉዳቱ ያመዝን ይመስለኛል።

 

5. ይደልዎ ፕሮፌሰር!

ከይዘት አንጻር ምንም እንኳን ከላይ የዳሰስኳቸው የትችት ነጥቦች ቢኖሩም ብዙ እልልታ የሚገባቸውና ቢዘመርላቸውም አግባብነት ያላቸው መልካም ነገሮች በመጽሐፉ ውስጥ ሞልተዋል። ከእነዚህ መካከልም “የኢትዮጵያ ታሪክ ለማን ተጻፈ?”፤ “በማን?” የሚሉ ጥያቄዎችን በመመለስ ዙሪያ የጻፉት ጽሑፍ አንጀቴን ነው ያራሰኝ፤ ምናልባት ይህ ሊሆን የቻለው ጊዜ ወስደውና ከተለያየ አቅጣጫ አገናዝበውና ከታሪክ ምሁራንም ጋር ተከራክረው ያዘጋጁት ስለነበረ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ። ፕ/ር እነዚህን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስም የታሪክን ምንነት፣ ፍልስፍና እና አሰተሳሰብ በቅድሚያ ዳስሰዋል። በእውነት በዚህ ዙሪያ ያቀረቡትን በተለየ ሳያመሰግኑና ሳያደንቁ ማለፍ አይገባም። ለጥያቄዎቹ እንዴት መልስ ሰጡ? ምንስ ይጎድለዋል? የሚሉ ጥያቄዎችን እንደማጠንጠኛ ወስዶ ማየት ይቻላል፤ ይሁንና ትችቶች ከዚህ በላይ ስለተጠቀሱ እነሱው በቂ ይመስሉኛል። መልካምነቱን ግን በጥቅል ማየቱ አስፈላጊ ይሆናል።

 

በየትኛውም የዕውቀት ክፍል የትምህርቱን ፍልስፍና ማሳየት የአስተውሎታዊ አቀራረብ ነው፤ ፍልስፍና ለየትኛውም ትምህርት መሠረት ነውና። ፕ/ርም የታሪክን ዕውቀት ከፍልስፍናው ተነስተው፣ አስተሳሰቡን መዝነው ነው የቃኙት፤ በዚህም የታሪክ ሁነትን ዘርዝረውና አብላልተው ማሳየታቸውስ? ድንቅ አይሉልኝም፤ የታሪክ እውነት “እሰጥ-አገባ የሌለበት ነገር አይደለም” በማለት ስለታሪክ ጸሐፊው ማንነት “የታሪክ ባለሙያው ከዚህ የኑሮ ትግል ውጭ የሆነ ታዛቢ ስላልሆነ ሚዛኑና ግምቱ የራሱን እምነት ያንጸባርቃል”(ገጽ 49)፤ “የራሱ የሆነውን ታሪክ የራሱ እንዳልሆነ አድርጎ ታሪክ የሚጽፈው እውነትን ተከተለ ለማለት ያስቸግራል፤”(ገጽ 55) ማለታቸውስ? ታሪክ የሚጻፈው ለባለታሪኩ ወይስ ዐዲስ ዕውቀትን ለሚሹ ሰዎች የሚለው ሙግታቸውስ? “የኢትዮጵያ ታሪክ እየተጠናገረ መሄድ የጀመረውም ዋናዎቹ የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊዎችና አስተማሪዎች የውጭ ሀገር ሰዎች ሲሆኑ ነው”(54) ሚለው መከራከሪያስ? በሙሉ የምስማማበት መሟገቻ ነው። በአጠቃላይ ታሪክን የምንነቱን፣ የአስፈላጊነቱንና የሚጻፍበትን ምክንያት ዳስሰውና የቄሣራዊያንን የታሪክ ዕይታና የአጻጻፍ ዳራ ተችተው ማቅረባቸው “ኢትዮጵያም ልጅ አላት” የሚያስብል ነው።

 

በፕ/ር ዕይታ ታሪክ የተከታታይ ትውልዶች ቀጣይነት ዘገባ ተደርጎ ተወስዷል። ይህ ከሆነ ደግሞ ታሪክን የሚጽፈው ባለሙያ ለዕውቀት ብሎ ብቻ ሳይሆን የቅጥልጥሎሹን ትውልድ ስሜትና ማንነት ጠብቆ ለማስቀጠልና ለማስጠበቅ መሆን አለበት፤ ጸሐፊውም ልምዱንና ባህሉን የሚያውቅ ሊሆን ይገበዋል። ታሪካችንን የሚጽፉት የውጭ ሀገር ሰዎች ግን ይህ ኃላፊነትና ስሜት የላቸውም፤ የተለየ ዓለማ ያላቸውም አሉ፤ ኢትዮጵያን ለመጉዳት ብለው የጻፉም አይታጡም፤ የሚጽፉትም በውጭ ቋንቋ ስለሆነ ለኢትዮጵያውያን አይደለም። ስለዚህ የሀገራችን ታሪክ ኃላፊነት በሚሰማቸው በራሳችን ሊቃውንትና ሕዝባችን ሊረዳው በሚችል ቋንቋ መጻፍ ይኖርበታል፤ ወይም ቢያንስ የተሻለ ይሆናል።

 

ችግሩ የሀገራችን “የጥንቶቹ ታሪክ ጸሐፊዎች ታሪክን የሚጽፉትበት ቋንቋ ግዕዝ ነበር፤ ሁለተኛም የሚጽፉት ንጉሠ ነገሥቶቹን ለማወደስ ነበር፤ ስለዚህ በቋንቋ ብቻ ሳይሆን በዓላማውም የነገሥታቱ (ዜና መዋዕል) የተጻፈው ለሕዝቡ አልነበረም፤ … ዘመናውያን የታሪክ ምሁራንም የሚጽፉት በእንግሊዘኛ ቋንቋ ለውጭ አገር ሰዎች ነው፤ በዓለማቸው ከጥንቶቹ እምብዛም አይለዩም፤ ድሮም ሆነ ዛሬ የታሪክ ጸሐፊዎች ትኩረታቸው በእንጀራቸው ላይ ነው፤” ስለሆነም በታሪክ ዕውቀት የኢትዮጵያ ሕዝብ አልታደለም (ገጽ 75-76)፤ ለዚህ ደግሞ የታሪክ ጸሐፊዎቻችን የሀገራቸውን የታሪክ አደራና ኃላፊነት እያሰቡ ሳይሆን የፈረንጆችን ስሜትና የታሪክ መስፈርት ይዘው የሚጨነቁ በመሆናቸው ነው። በዚህ የተነሣ ልክ እንደውጭ ሀገር ባለሙያዎች ከማንነትና ከኃላፊነት ስሜት ይገለላሉ፤ ይህ ከሆነም የሚዘግቡት ታሪክ እውነት አይሆንም፤ በዚህ የተነሣ ጠቃሜታውም አናሳ ይሆናል። ፕ/ር የታሪክ ምሁራኖችን የተቹት በዚህ አስተሳሰብ ይመስለኛል።ምህራኑን መተቸታቸው ትክክል ነው አይደለም የሚለው ክርክርም በዚህ እሳቤ ላይ የተመሠረተ ነው።

 

በዚህ መልክ የታሪክ ሊቃውንቱን መተቸታቸው ደግሞ በግሌ የምስማማበት ጉዳይ ነው። እንዳውም የተቹባቸው የመመዘኛ ፅንሣተሐሳቦች (ሀገረ-መንግሥት፣ ኢምፓየር፣ ወሰንና ጠረፍ) ሳስተውላቸው የሚያስደነቁኝ ናቸው፤ ስለዚህ በዚህ አሞጋገታቸው አድናቆቴን በመግለጽ ብቻ ለማለፍ እፈልጋለሁ። ምሁራኑ መተቸት የለባቸው የሚል ካለም ከመጸሐፎቻቸው ጋር በማነጻጸር ተከራክሮ ያሳየን፤ በጥቅሉ “ለምን ተቿቸው?” ማለት ግን የተተቹት መጽሐፎች የያዙትን የታሪክ ክብደትና የጋራ የታሪክ ሀብት አለማስተዋል ይመስለኛል።

 

6. እንደ ማሳረጊያ

እንደ እኔ ከሆነ ፕ/ር በራሳቸን፣ ከራሳችን ተነሥተን ማንነታችን መፈለግና ኢትዮጵያዊ ክብራችንን ማክበር አለብን የሚለው አቀራረባቸው ልዩ ትኩረት ማገኘት የሚኖርበት ነው። ምንም እንኳን ዕይታቸው ፀለምተኛ ቢሆንም ያቀረቡት የኢትዮጵያዊነት መሠረተ አተያይ፣ የማንነት ሐሠሣ፣ ቁጭታዊ አቀራረብና ክብርን ለማስመለስ የሚደረግ ሙግት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሊጠይቀው የሚገባም ነው። በዚህ ጉዳይም ፕ/ርን ብዙ ትችቶችና ስድቦችም ጭምር ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉ መገመት አያቅትም፤ በተደረጉ እሰጥ አገባዎችም እነዚህ ነገሮች ተንጸባርቀዋል፤ ይህ የሆነው ደግሞ ፕ/ር ትልቅ ዋጋ ያለውና ሁሉንም ሊኮረኩርና ራሱን እንዲጠይቅ የሚያደርግ መጽሐፍ በማቅረባቸው ነው፤ በዚህ ሥራቸውም ኩራት ሊሰማቸው ይገባል።

 

አንባቢዎችም ብንሆን ምንም ዓይነት የግል አተያይ፣ አረዳድና ፍላጎት ቢኖረንም ይህን የመሰለ መከራከሪያና ማንነትን መፈተሻ መጽሐፍ ያቀረቡልን ምሁር ማመስገንና ክብር መስጠት ይኖርብናል፤ በፀለምተኝነት ድባብ ቢሆንስ ራሳችንን እንድንጠይቅ የኮረኮረን ኢትዮጵያዊ ምሁር ሌላ ማን አለ? በግሌም ምንም እንኳን መጽሐፋቸው የፖለቲካዊ ቅኝት ጫና ቢያርፍበትም፣ በፀለምተኝነት ዕይታ ቢቃኝም አንደ ፕ/ር ዓይነት ምሁርን ማወደስ፣ መንከባከብና የሚያቀርቡትን ሐሳብ አስተውሎ ማየት ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ፤ ባይልላቸው ነው እንጂ በዚህ ትጋታቸው ስንት በተባለላቸውና በተደረገላቸው ነበርም፤ ሀገሩ ኢትዮጵያ ሆኖ እንጂ እኝህን ደፋርና በሀገር ፍቅር የተነደፉ አንጋፋ ምሁር ስድብም ይጻፉ ወቀሳ ወይም ሌላ በአግባቡ እየተንከባከቡ እንዲጽፉ ነገሮችን ማመቻቸት አስፈላጊና ጠቃሚ ነበር፤ ነውም። እንዳውም አንጋፋ ምሁራን እንደዚህ በቁጭትና በብስጭት ሲጽፉ መልካም ነው፤ ምክንያቱም ከጽሑፋቸው ከተለመደው የተለዩ አሳቦች እየነጠሩ እንዲወጡ በር ይከፍታሉና።

 

አክብሮትና አድናቆታችን እንዳለ ሆኖም የሚጽፉት ጽሑፋቸው ካልተስማማን ግን መተቸት፣ መልካም ከሆነም ደግፈን መከራከር የራሳችን ፋንታ ነው። በዚህ እሳቤ ነው እኔም ቅር ያለኝን ለመተቸትና የተስማማኝን አስተሳሰብ ደግሞ ለማወደስ የሞከርኩት። ሆኖም አብዛኛው የጽሑፌ ማጠንጠኛ በትችት ላይ ያተኮረ መሆኑ ይገባኛል፤ ፍላጎቴ “በዚህ መልክም ቢሆን የተሻለ ይሆን ነበር” በሚል ቅንነት፣ በውዳሴ ያለ ስሚንቶ መካቡም ጥቅም የለውም ከሚል እምነትና የታሪካችንን ሰንሰለት ከመነሻው በመመሥረት መቃኘት ያስፈልጋል እንጂ በፖለቲካ ምህዋር ጫፍ ላይ መሽከርከር ችግር ይኖረዋል በሚል እሳቤ ነው። በተረፈ ግን የፕ/ር መጽሐፎች እንደታተሙ በጉጉት ለማንበብ ከሚቋምጡት ሰዎች መካከል አንዱ እኔ ነኝ። እስቲ የተለያዩ መከራከሪያዎች በማግኘት እንድንማማርና መተቻቸትም እንድናዳብር ሌላም ሌላም ቶሎ ቶሎ ይጻፉልን።


ካሣሁን ዓለሙ
kasiealemu@gmail.com

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on March 19, 2013
  • By:
  • Last Modified: March 19, 2013 @ 6:03 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar