www.maledatimes.com ነብር ዥንጉርጉርነቱን፤ ኢትዮጵያዊ ክሽፈቱን (ታምራት ነገራ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ነብር ዥንጉርጉርነቱን፤ ኢትዮጵያዊ ክሽፈቱን (ታምራት ነገራ)

By   /   March 21, 2013  /   Comments Off on ነብር ዥንጉርጉርነቱን፤ ኢትዮጵያዊ ክሽፈቱን (ታምራት ነገራ)

    Print       Email
0 0
Read Time:69 Minute, 3 Second

      “ክሽፈት እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” የተሰኘው አዲሱ የፕሮፌሰር መስፍን መጽሐፍ በሕይወቴ ካነብበዃቸው መጻሕፍት መካከል አእምሮዬን ብቻ ሳይኾን መንፈሴንም ጭምር ማነገጋር ከቻሉት ጥቂት መጻሕፍት ውስጥ እመድበዋለሁ። ይህ ለምን ኾነ? ስለማንነቴ በተለይም ስለኢትዮጵዊነት፤ ስለሐበሻነት፤ ስለኦሮሞነት፤ ስለጥቁርነት፤ ስለስደተኝነት፤ ስለ ሥነቋንቋ፣ ስለስኬት እና ስለሌሎችም ተጓዳኝ ጉዳዮች በጥልቁ እንዳስብ ሕይወት አስገዳጅ ጥያቄ ባቀረበችልኝ ወቅት የደረሰኝ መጽሐፍ በመኾኑ ነው፡

ከአገር ከወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ አንዳንዴ በስደት ወሬ፣ አንዳንዴ በትምህርት ወሬ፣ ሌላ ጊዜ በብስጭት፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በሥራ ወሬ ጊዜ ከማጥፋት ነገሮች ቀስ በቀስ በሕይወቴ እየሰከኑ ነው፡፡ ለምን ከአገር ወጣኹ? ለምን አልታሰርኩም? ለምን እስከመሞት ድርስ ለመቆየት ወኔ ከዳኝ? የሚሉትን ጥያቄዎች አሁን ብቻ ሳይኾን ዕድሜ ልኬን የምጠይቃቸው ናቸው። በተለይ አዲስ ነገርን አብረን ፀንሰን፤ አብረን ወልደን፤ አብረን አሳድገን፤ አብረን ሞት ከፈረድንባት ወዳጆቼ ጋራ እነዚህን ጥያቄዎች ለዕድሜ ልክ ደግመን ደጋግመን ማንሳታችን የሚቀር አይመስለኝም።

 

በስደት ሕይወት ከገጠመኝ ማንኛውም መንከራተት ይልቅ ነፍሴን የሰነጣጠቃት ግን ለመሰደድ መወሰኔ ያስከተለውን  ጣጣ ማወቄ ነው፡፡ ይህን  ጣጣ በሚገባ ለመገንዘብ ባልሳሳት አንድ ዓመት ፈጅቶብኛል፡፡ ቢያንስ ነፍስ ካወቅኹበት ጊዜ ጀምሮ ዓላማዬ ብዬ የያዝኩት ፖለቲካዊ ሕይወት ለካ ከበቀለበት አፈር ሲወጣ ምንም ትርጉም የለውም። አዲስ ዓላማ በአዲስ አገር እንዴት ይፈጠራል? አዲስ ዓላማ በባዕድ ቋንቋ  ምን ማለት ነው? የሚሉ መሠረታዊ የትርጉም ጥያቄዎች  እስኪበቃኝ ናጡኝ፡፡ መናጡ ሲረጋጋ የተረፈኝ ድፍድፍ ከትውስታ ቋንቋ፣ ከናፍቆት እና ከዕድሜ ንባብ ጋር የተለወሰ በመኾኑ ገና ለብዙ ዘመን የማነጥረው ቁም ነገር ይኾናል ብዬ አስባለኹ፡፡   ከዚህ በኋላ መናጡ እየደቀረልኝ ቢኾንም፤ የተሰነጠቀችው ነፍሴ ግን መልሳ አልተጠገነችም። ብርሌ ብቻ ሳይኾን ነፍስም ከነቃች ወደኋላ አትመለስም፡፡ ከነፍሴ ስንጥቅ ውስጥ ከስንት አንዴ ፍንቅል እያለ የሚወጣው ትዝታ እና አንዳንድ ጥልቅ ሐሳብ ግን እንደ ቅዠት እያባነነ ሊፈረካክሰኝ ሲተናነቀኝ አገኘዋለኹ፡

የፕሮፌሰርን መጽሐፍ ሳነበው ከስድሳ ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን አሻሽላለኹ፤ ለሕዝቤ አገለግላለኹ ብላ የምትታገለው ነፍሳቸው በራሷ ጉዞ የገጠማት ስንጥቅ ታየኝ፡፡ ከዚህ የነፍሳቸው ስንጥቅ የሚወጣውን መልዕክት መዓዛ ደግሞ በደንብ አውቀዋለኹ። “በእኔ ዕድሜ ያደኩበት ሰፈር ስም፤ የተማርኹበት ተማሪ ቤት ስም፤ ያስተማርኹበት ተማሪ ቤት ስም፤ የሠራኹበት መሥሪያ ቤት ስም ተለውጧል። ስለዚህ እኔ የሌለ ሰፈር አድጌ፤ የሌለ ተማሪ ቤት ተምሬ፤ የሌለ ተማሪ ቤት አስተምሬ፤ የሌለ መሥሪያ ቤት ሰርቼ፤ የሌለ ዩኒቨርስቲ አስተምሬ … እኔ በጡረታ መኖሬ ያስገርማል! ከሽፎ የከሸፈ ኑሮ መኖር እንበለው!” ፕሮፌሰር መስፍን መልካሙን ገድል ተጋድያለኹ ማለት በሚገባቸው የሕይወት ዘመናቸው ላይ ‘ከንቱ! ሁሉም ነገር ከንቱ!’ የሚሉ አይመስልምን? ነፍስ ስትሰነጠቅ እውነት እውነቱን እንዲህ ታናግራለች፡፡

 

ይህ ማለት መጽሐፉ አላስፈላጊ በኾኑ፤ እንዲያውም በፕሮፌሰር መስፍን ማዕረግ ላለ የአደባባይ ምሁር ሊመጥኑ በማይችሉ አላስፈላጊ ሐሳቦች አልተጥለቀለቀም ማለት አይደለም። የፕሮፌሰር መስፍን መልዕክት የሚቀርበው ለስድሳ ዓመታት ሲጠነስሱት፣ ሲያጠምቁት እና ለአደባባይ ሲያድሉት  ከኖሩት የቀኝ ዘመም ፖለቲካ ጠላ ጋር ተደባልቆ ስለኾነ ብዙ ሰው መጽሐፋቸው ባዘለው መልካሙ መልዕክት መዓዛ ከመሳብ ይልቅ በዚህ ቀኝ ዘመም ጠላ ጠረን ብቻ ሊገፈተር ይችላል፡፡ኢትዮጵያ ውስጥ የመጽሐፍ ሐሳብ ተቀብሎ፤ ለመጽሐፉ የቀብድ ገንዘብ ከፍሎ፤ ሐሳቡን ከጸሐፊው ጋር አዳብሮ፤ ለጸሐፊው አርታዒ መድቦ፤ ለአርታዒው የምርምር እና ለሌላም ሥራ የሚኾኑ አጋዥ ረዳቶች አዘጋጅቶ መጽሐፉን ከደራሲው ጋር የሚፀንስ፤ መጽሐፉን እንደ ደራሲው ኾኖ ለአደባባይ የሚያደርስ አሳታሚ የሚባል ነገር ጭራሹንም ስለሌለ፤ ለተወሰነው የመጽሐፉ ክሽፈት ተጠያቂው ያው የከሸፈው የኢትዮጵያ የኅትመት ኢንዱስትሪ ነው

በመጽሀፉ አላስፈላጊ ሐሳቦች እንዲሰገሰጉ ሌላው ተጠያቂ ራሳቸው ፕሮፌሰር መስፍን ናቸው። ምሁራን መጽሐፍ ለማሳተም በሚያፍሩባት ኢትዮጵያ እስከ አሁን ድረስ በራሳቸው ጥረት (ብቻቸውን) ያለማቋረጥ እና ያለማንም ረዳትነት መጻሕፍትን በአማርኛ መጻፋቸው እጅግ አስገራሚ ቢኾንም፤ አሁንም ድረስ መጽሐፋቸውን አንድ ሁለት ዙር እንዲያነብላቸው፤ ከዚያም እንዲተችላቸው የሚፈቅዱለት ሰው እንዲኖር ማድረግ አለመቻላቸው ከራሳቸው “እኔ ስናገር ብቻ ስሙኝ” ከሚለው ባሕርያቸው የመነጨ ይመስለኛል። ‘እስኪ ጽሑፌን እይልኝ፤ ከዚያም ይስተካከሉ እና ይብራሩ የምትላቸው ሐሳቦች ካሉም ጠቁመኝ፤’ ብሎ ጽሑፍን ለአርታኢ መስጠት ምሁራዊ ትህትና ይጠይቃል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍንን ደግሞ በትህትና ማማት ትንሽ ይከብዳል፡፡

 

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ መጽሐፉን ሙሉ ለሙሉ መገምገም፣ መዳሰስ፣ ወይም መተቸት አይደለም፡፡ ስለዚህ በዚህ ጽሑፌ መጽሐፉ ውስጥ የተጀቦኑትን አላስፈላጊ እና አርቲ ቡርቲ ናቸው ብዬ የወሰድኳቸውን ሐሳቦች፣ ማስረጃዎች እና መከራከሪያዎች በሙሉ አልነካቸውም።  በመጽሐፉ ውስጥ ፕሮፌሰር መስፍን ሊያስተላልፉ የፈለጉት መልእክት በምዕራፍ አንድ ማለትም ከገጽ 7 እስከ 33 እና በምዕራፍ 12 መደምደሚያ፤ ማለትም ከገጽ 182 እስከ 202 ውስጥ በሚገባ ተካቷል ። የተቀረው የመጽሐፉ ክፍል የተዘጋጀው እንደመልእክቱ ማስረጃ እና ለመልእክቱ ፍልስፍናዊ መሠረት ለማቅረብ ቢኾንም በዓላማው ፈጽሞ የከሸፈ በመኾኑ እንዳለ ተቆርጦ መጣል ነበረበት፤ ወይም እንደገና በሚገባ ተፈትኖ እና ታሽቶ መጻፍ ነበረበት፡፡ ፕሮፌሰር መስፍንን በአማርኛ ቋንቋ ምርጥ ከሚባሉ ጸሐፍያን የሚያስመድባቸው አንደኛው ነገር በጽሑፎቻቸው ትልልቅ እና ውስብስብ የሚባሉ ሐሳቦችን በቀላሉ፤ ያውም እጅግ ውብ በኾነ የቃላት አጣጣል የማስቀመጥ ችሎታ ስላላቸው ነው። ይህ የመጽሐፉ ክፍል ውበትም ኾነ የሐሳብ ጥራት ከማጣቱ የተነሳ ፕሮፌሰር መስፍን እንደልማዳቸው ከሥራቸው አረፍ ለማለት ለቡና ወደ ቶሞካ ጎራ ሲሉ ሌላ ሰው ጽፎ ያስቀመጠው ይመስላል። የዚህ መጽሐፍ ክፍል መበላሸት አሳዛኝ የሚኾነው፤ ፕሮፌሰር መስፍን ሊያስተላልፉ የፈለጉትን መልእክት በተገቢ እና ጠንካራ የመከራከሪያ ሐሳቦች እንዳይደገፉ በማድረጉ እና በዝባዝንኬ ዋናውን መልእክት እንዳያፍታቱ ጋሬጣ ኾኖ መገኘቱ ነው።

 

መጽሐፉ ጥሩ አርታኢ ቢያገኘው ኖሮ የፕሮፌሰርን መልእክት በሚገባ የያዙትን ገጾች ብቻ በመምረጥ (እንደ አሁኑ በመጽሐፍ መልክ ሳይኾን) ሰፋ እና ጠንከር ያለ ዦርናል ጽሑፍ ይወጣው ነበር፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረትም በተጠቀሱት ገጾች ላይ በተሳካ ኹኔታ ተላልፏ ብዬ በማስበው መልእክት ላይ ማነጣጠር ብቻ ነው። ምናልባትም መጽሐፉን ማንበብ የሚፈልግ ሰው እነዚህን ገጾች ብቻ መርጦ ቢያነብ የፕሮፌሰሩን መልእክት በሚገባ ያገኘዋል። እኔም ትኩረቴን እና ትንቅንቄን የማደርገው ከመጽሐፉ ዋነኛ ክፍል ጋር ብቻ ይኾናል፡፡

 

መክሸፍ እና ኢትዮጵያ በፕሮፌሰር መስፍን ዕይታ

 

የፕሮፌሰር መስፍን የክሽፈት ትርጓሜ በሁለት ነጥቦች ላይ ያተኩራል፡፡ አንደኛ አንድ የተጀመረ ነገር የታቀደለት ግብ ጋር ሳይደረስ መቅረት፡፡ ሁለተኛ ጅማሮው ምንም እድገት ሳያሳይ እዚያው ባለበት እየተራመደ መቅረት፡፡ በፕሮፌሰር መስፍን ትርጓሜ መክሸፍን የሚያስከስተው ሌላው ምክንያት የተፈጥሮ ሕግ ነው፡፡ የመለወጥ የተፈጥሮ ሕግ፡፡ ይህን የተፈጥሮ ሕግ እንዲህ ያስቀምጡታል “ወደተሻለ ደረጃ ካልተለወጡ ወደባሰ ደረጃ መውረድ የማይቀር ነው፤ ወይም በሌላ አነጋገር ካላደጉ እና ካልተሻሻሉ መሻገት እና መበስበስ፤ በስብሶ መፈራረስ ግዴታ ነው፡፡” ገጽ10 ይህ የክሽፈት ትርጓሜ ብዙዎቻችንን ሊያስማማ ይችላል፡

በመቀጠል ፕሮፌሰር መክሸፍ በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ ሥፍራ እንዳለው ያስረግጣሉ። ከዚህ የመክሸፍ ታሪክ የተረፈው ምናልባት ለአገር የመሞት ታሪክ ብቻ ሊኾን እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሕልውናን የማስረገጥ ረጅም ልምድ እንዳለ፤ ሌላው ነገር ሁሉ የሚከተለው ሕልውናን በማስረገጥ ላይ እንደኾነ ይናገራሉ፡፡  በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሕልውናን ከማስረገጥ ባሻገር ያለውን የኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ፕሮፌሰር መስፍን የከሸፈ ብለውታል

 

የፕሮፌሰር መስፍን  “ሕልውና” እና “ለአገር  የመሞት” ፅንሰ ሐሳቦች የተወሰኑ ጥያቄዎችን እንድናነሳ ይጋብዛል፡፡ ስለሕልውና ጥያቄ እንድናነሳ የምንጋበዝበት የመጀመሪያ ምክንያት ፕሮፌሰር መስፍን ራሳቸው ለሕልውና የሚሰጡት ከፍተኛ ዋጋ እና ትርጉም ነው፡፡ በቅድሚያ ሕልውና ያስፈልጋል፤ ሁሉም ነገር ከሕልውና በኋላ ይከተላል ይላሉ ፕሮፌሰር፡፡ የነገሮች ሁሉ መሠረት ነው ያሉትን ሕልውናን ግን ሳያብራሩት ያልፋሉ፡፡ ስለኢትዮጵያ መክሸፍ ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ መክሸፍ ስለመኖሩ እና አለመኖሩ ለመወያየት ኢትዮጵያ የምትባል አገር መኖሯ ላይ መተማመን የመጀመሪያው አስማሚ ነጥብ እንደሚኾን አያጠራጥርም፡፡

በአካል የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ኢትዮጵያ የምትባል ፖለቲካዊ ግዛት ያላት አገር መኖሯን አልጠራጠርም፡፡ በዚች ግዛት ውስጥ ግን በአንድ ዐይነት ወይም ቢያንስ በተቀራራቢ ምናባዊ ማሕበረሰብ ውስጥ (Imagined Community) የሚኖሩ ዜጎች አሉ ብዬ አፌን ሞልቼ ለመናገር ግን አልደፍርም፡፡ ምናባዊ ማሕበረሰብ ስንል በአንድ ፖለቲካዊ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ስለሚኖሩባት አገር ታሪክ ፤ ማንነት እና ፍፃሜ አንድ ዐይነትም እንኳን ባይኾን እጅግ ተቀራራቢ የኾነ ምስል መቅረጽ ሲችሉ ነው፡፡ ምናባዊት ኢትዮጵያ ተፈጥራለች የምንለው ሲያዴ፤ አበበ፤ ተስፋፂዮን፤ ጀሚላ እና አሌሮ ስለ ኢትዮጵያ አንድ ዐይነት ምስል ሲፈጠርላቸው ወይም ስለኢትዮጵያ ተቀራራቢ መግለጫ ሲሰጡን ነው፡፡

 

ፖለቲካዊ ሕልውና አንድን ግዛት ከወራሪ በመከላከል እና አጠገብ ያለን አገርም ኾነ መንደር በውድም በግድም በማስገበር ይፈጠራል፤ ይሠራል፡፡ አገሮች ሁሉም የተገነቡት በዚህ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ መንገድ ነው፡፡ ከምናባዊ ማሕበረሰብ የሚወለደውን መንፈሳዊውን አንድ አገር ለመገንባት ግን ረጅም፣ ውስብስብ እና አታካች የኾነውን ውስጣዊውን የፖለቲካ የባሕል ጉዞ መጓዝ ግድ ይላል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን አሁንም አብዛኛው ተደጋጋሚው ትኩረታቸው እና ቁጭታቸው የሚያተኩረው ከውጭ ወደ ውስጥ በኢትዮጵያ ላይ ስለሚደረግ የዳር ድንበር ጥቃት ነው፡፡

ለፕሮፌሰር መስፍን እና መሰሎቻቸው ዐይነት የኢትዮጵያ አማኞች የኢትዮጵያን ምናባዊ እና መንፈሳዊ ሕልውና እንዲጠይቁ መጠበቅ አንድን ዲያቆን የተገለጠውን እውነት እንዲጠይቅ የመጋበዝ ያህል ይኾንብኛል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍንን በዚህ ጉዳይ መሞገትም ኾነ ከፕሮፌሰር መስፍን ጋር በዚህ ጉዳይ መወቃቀስ ከዲያቆን ጋር ከመጨቃጨቅ ስለማይለያይ የሚበጀን ፕሮፌሰር መስፍን ስለ “ክሽፈት” የከፈቱልንን ተዋስዖ  በመጠቀም ለምን አንዲት ዐይነት ምናባዊ ኢትዮጵያን ሳንፈጥር ቀረን? ለምን በዚህ የቤት ሥራ ከሸፍን? ብለን አዲስ ጥያቄ፤ አዲስ የቤት ሥራ ለራሳችን መስጠት ይሻላል፡፡

 

ዳርድንበሯ ስላልተደፈረችው ኢትዮጵያ ሕልውና በማውራት፣ በመሸለል እና መፎከር ብቻ ጊዜ ከማጥፋት ስለምናባዊቷ  ኢትዮጵያ ሕልውና መጨነቅ የሚገባን ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን በዚህ መጽሐፋቸው ያነሷቸው ጥልቅ መንፈሳዊ እና ፍልስፍናዊ ጥያቄዎችን ስናሰናነስል፤ ራሳችንን መጠየቅ ያለብን ስለአካላዊቷ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ስለመንፈሳዊቷ ኢትዮጵያም ጭምር ነው፡፡ በተለምዶው በኢትዮጵያ ተዋስዖ ስለምናባዊዋ ኢትዮጵያ ሲወራ የራሱን ምናባዊ ኢትዮጵያ ሁላችንም ላይ ይጭናል እየተባለ የሚከሰሰው የእነፕሮፌሰር መስፍን ቀኝ ዘመም መንደር ነው፡

በዚህ መጽሐፋቸው ፕሮፌሰር መስፍን በተደጋጋሚ “ወያኔ ወያኔ” እያሉ ሲጮሁ እናም ወያኔን እንደ ኢትዮጵያዊ ሳይኾን እንደ አንድ ባዕድ አካል ሲቆጥሩ ሳይ ቆረቆረኝ፡፡ እስከመቼ ነው ወያኔ ወያኔ የምንለው? እስከመቼ ነው የእነመለስን ኢትዮጵያዊነት የምንጠራጠረው? ለዚህኛው ጥያቄዬ መልስ ከመስጠቴ በፊት ግን በአእምሮዬ ሌሎች ጥያቄዎች መጡብኝ፡፡ የእነመልስ ቡድን እና ትውልድ ለአንዲት የጋራ ምናባዊ ኢትዮጵያ መፈጠር ምን አስተጽኦ አበረከተ? ይህ የህወሓት ቡድን ሥልጣን በያዘበት ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ የራሱን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከማጋበስ እና ከማስፋፋት አልፎ ከእኛ እንደ አንዱ የሚያስቆጥርው እና ለኢትዮጵያውያን በሙሉ የሚጠቅም ምን ነገር አበረከተ? ይህን የአእምሮዬን ጥያቄ ዝም ብሎ መሻገር አቃተኝ፡፡

 

የብሔር ብሔረሰቦች መብት አስከብራለው ብሎ የጮኸው ኢሕአዴግ ዛሬ ኢትዮጵያን ወደ ትልቅ የብሔሮች እስር ቤት እና የብሔሮች መናቆሪያ መድረክነት ለውጧታል፡፡ ኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤት ለማድረግ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን በሙሉ እየሸሸ ኢትዮጵያን በዓለም ላይ ትልቋ የባሕር በር ዐልባ አገር አድርጓታል፡፡ መሬት ለአራሹ ብለው የዘመሩት እነ በረከት ስምዖን አያቶቻችን ለምዕተ ዓመታት በጠላት ባለቤትነት እንዳይያዝ የሞቱለትን መሬት ለዐረብ፤ለቻይና እና ለኮሪያ ነጋዴዎች እና ኮርፖሬሽኖች ረከስ ባለ ዋጋ ለአንድ ዓመት ሳይኾን ለመቶ ዓመት እየቸበቸበው ነው። ታዲያ በምን መሠረት ላይ ቆሜ ፕሮፌሰር መስፍንን “የእነ መለስን ኢትዮጵያዊነት ተቀበሉ!” ልበል?  ይህን ሁሉ የታሪክ ጉድ እየኖርኩኝ በምን ማስረጃ ላይ ተመሥርቼ ለአንዲት ምናባዊ ኢትዮጵያ አለመፈጠር ተጠያቂው የእነፕሮፌሰር መስፍን ካምፕ ብቻ ነው ልበል?  ከዚህ የክሽፈት አዙሪት ማን ያወጣናል? ክሽፈቱ ዙሪያ ጥምጥም ነው። አንዱ ለራሱ የሳለው ምናባዊ ኢትዮጵያዊነት ሌላው ከሳለው ምናባዊነት ጋራ የሚለያየው በጠላትነት እስከመፈራረጅ በሚያደርስ ልዩነት የሚገለጥ ነው። በሁለት በኩል በተሳለ ቢላ ላይ የተቀመጠ ምናባዊነት።

 

ፕሮፌሰር መስፍን ስለክሽፈት ሲተነትኑ በመስክ በመስኩ በዘርፍ በዘርፉ መደርደር መርጠዋል፡፡ ቴክኖሎጂ ከሽፏል፤ ልማት ከሽፏል፤ በሕግ መተዳደር ከሽፏል፤ ንግድ ከሽፏል፤ ኢንዱስትሪ ከሽፏል፤ እርሻ ከሽፏል እያሉ በየዘርፉ ክሽፈትን ያትታሉ፡፡ በዘርፍ ማስቀመጥ አልበቃ ካላችሁ ይመስላል በኢትዮጵያ የከሸፉ የሚሏቸውን ተቋማት ይዘረዝራሉ፡፡ እዚህ ዝርዝር ውስጥም ራሳቸው አፈር ፈጭተው እና ጭቃ ጠፍጥፈው የፈጠሩትን ኢሰመጉን ያስቀምጣሉ፡፡ “ኢሰመጉን ወያኔ አከሸፈው ይባላል እንጂ እኛ ከሽፈን አከሸፍነው አንልም” በማለት ራሳቸውን ከዚህ የክሽፈት አዙሪት ውጭ አድርገው እንደማያዩ፤ እርሳቸው የነኩት አንዳንዱም እንደከሸፈባቸው በምሬት ይናገራሉ፡፡ ይህ የፕሮፌሰር መስፍን የክሽፈት ትርጓሜ እና የከሸፉ ዘርፎች፤ የከሸፉ ተቋማት፤ እና የከሸፉ ፕሮጀክቶች ዝርዝር የመልእክታቸው አንደኛው ክፍል ነው፡፡ በዚህ ክፍል ፕሮፌሰር ያስቀመጡት መልእክት ኢትዮጵያ ራሷ ሕልውና ከማስጠበቅ አልፋ እንደ አገር አንድም ርምጃ እንዳልተራመደች ነው። ዝርዝሩ የቀረበበት አንደኛው ምክንያት ተፈጥሯዊ ግዴታውን እየተወጣ ለረጅም ጊዜ ያለማቋረጥ እያደገ፣ እየተመነደገ፣ እየገሰገሰ ያለምንም መጨናገፍ የቀጠለ ዘርፍም ኾነ ተቋም እንደሌለን ለማስረገጥ ነው።

 

ይህ ምን አዲስ ነገር አለው? እነዚህን የኢትዮጵያን ክሽፈቶች መዘርዘር እኛ ራሳችን በየጊዜው እና በየአጋጣሚው ከምናወራው ክሽፈት በምን ተለየ ብሎ የሚጠይቅ ሰው ሊመጣ ይችል ይኾናል። መልእክቱ እና መልእክተኛው ሚዛን ላይ የሚቀመጡት እንግዲህ ይኼኔ ነው። ፕሮፌሰር መስፍን በሞያም፤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ፖለቲካ፣ ታሪክ፣ ማኅበራዊ ሕይወት እና ሚዲያ ባላቸው ተሳትፎ ለአገር አድባር ሊባሉ ከሚገባቸው ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን እጅግ ከመውደዳቸው የተነሳ ለማቀፍ ሲንደረደሩ ሊያንቋት ከሚዳዳቸው የቀኞች ወገን ፓትያርክም አያቶላህም ናቸውና እርሳቸው የሚናገሩትን ባንወደው እንኳ የኢትዮጵያን ፖለቲካ እከታተላለሁ የሚል ቃላቸውን ችላ ሊል አይችልም። ዕድሜያቸውን ሙሉ በአንድም በሌላም መልክ ስደትን ሳይመርጡ ከሕዝቡ ጋር እየታሰሩም፤ እየተንገላቱም፤ እየተጋፉም የኖሩ ሰው በዚህ እድሜአቸው የሚናገሩት ነገር ተስፋ የሚጭር ሳይኾን  ስለ አገርም  ስለ ራሳቸውም ያቀረቡት የመረረ ትችት መኾኑ ቆም ብሎ ለማየት የሚጋብዝ ነው።

 

ፕሮፌሰሩ ዝም ብለው የሽምግልና ጨለምተኝነት ተጠናውቷቸው፤ አዲሱን የኢትዮጵያ እውነታም መቀበል ተስኗቸው ነው እንጂ ስለ ኢትዮጵያ እንዲህ ድፍን ያለ ድምዳሜ ላይ የሚያደርስ ነገር የለም የሚሉ ሊነሱ ይችላሉ፡፡

ለእነዚህ ሰዎች የምላቸው አንደኛ፦ ፕሮፌሰር መስፍን በዚህ መጽሐፍ ለብዙ ሰዎች በቀላሉ ሊዋጡ የማይችሉ ሐሳቦችን በተጀቦነ መንገድ አቅርበዋቸዋል ማለት ስለ ክሽፈት ያቀረቡትን ትንታኔ እና መልእክት የግድ ሙሉ ለሙሉ  ያፈርሳል  ማለት አይደለም። ፕሮፌሰር መስፍን ስለእኛ መክሸፍ ያነሷቸው ትንታኔዎች ብቻቸውን የመቆም ብቃታቸው እጅግ ጠንካራ ነው፡፡ ለዚህም ነው ንጥር መልእክቱን ከአላስፈላጊ የመጽሐፉ ክፍል ፈልቅቀን ማውጣት ያስፈለገን። ሁለተኛ፦ በዋነኛነት ከላይ ፕሮፌሰር ባቀረቡት መለኪያ ያልከሸፈ መስክ በኢትዮጵያ አለ የሚል ካለ እስኪ በማስረጃ ያቅርብ? መቼም የፈረደበትን የአዲስ አበባ የፎቅ ጋጋታ እና የመንገድ ግንባታ፣ የዐባይ ግድብ እና መሰል ፕሮጀክቶችን እንደ አለመክሸፍ ማስረጃ ለማቅረብ የምትንደረደሩ ካላችኹ ይህን ጹሑፍ ማንበብ ትታችሁ ጊዜያችኹን ልማታዊ ነገር ላይ አውሉ።

 

ለፕሮፌሰር መስፍን ክሽፈትን ከኢትዮጵያዊነት ጋር እንዲዋሀድ ያስቻሉት ሦስቱ ሥላሴዎች (በሕግ ሊገራ ያልቻለው ሥልጣን፤ ሃይማኖት እና ተባብሮ ያለመሥራት) ናቸው። “በኢትዮጵያ  ጉልበት ሥልጣን ነው፤ ጉልበት መብት ነው፤ ጉልበት ሕግ ነው፤ ጉልበት ሥነ ሥርዐት ነው፤ የገዢዎች መብት ያልተገደበ ነው፤ የገዢዎች ግዴታ ያልተገደበ ነው” ገጽ 194። ይህ ያልተገደበ ጉልበት ሰዎቸ በፍርሃት እንዲኖሩ ከማድረጉም ባሻገር ዜጎች ከአእምሯቸው ያፈለቁትን ሐሳብ አዳብረው በሥራ ከመበልፀግ እና ከማደግ ሥልጣን በመቆናጠጥ ወይም ለሥልጣን በማጎብደድ መክበርን እንዲመርጡ መሬት አደላድሏል ሲሉ ያስረዳሉ

ከዚህም የተነሳ እንደፕሮፌሰር መስፍን ትንታኔ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ ውስጥ በአእምሮ ውጤት ወይም በሥራ ለመበልጸግ ከመጣር በሥልጣን መበልፀግ የሚያዋጣ መንገድ መኾኑም ተደርሶበታል፡፡ ምክንያቱም በሕግ ያልተገራ ሥልጣን በነገሠባት ኢትዮጵያ አንድ ሰው በአእምሮው አሰላስሎ ለፍቶ የሠራውን ማንኛውንም ነገር አንድ ባለሥልጣን በፈለገው ሰዓት ሊቀማው እንደሚችል ጠንቅቆ ያውቃል። በኢትዮጵያ ሕግ የቆመው የአንድን ሰው የአእምሮ ወይም የጉልበት ልፋት ውጤት ባለቤትነት ሕልውና ለማስጠበቅ ስላልኾነ ለአንድ ዜጋ ሠርቶ ለማደግ ምንም የሚያነሳሳ ነገር አይታይም ይላሉ ፕሮፌሰር። እንዲያውም ለመበልጸግ ከመጣር ይልቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድህነትን እንደጥቃት መከላከያ ተሸፋፍኖት ይቀመጣል፤ ወይም ባለሥልጣን ቢኾን ሀብት አጋብሶ ሀብቱን በሥልጣኑ ያስጠብቃል። “በሕግ እና በሥርዐት የሚገዛ አስተዳደር ከሌለ የማኅበረሰቡ እድገት እና  እና መሻሻል እንኳን ወደፊት ሊሄድ እና ባለበት ለመቆየትም ያዳግተዋል” ገጽ 23።

 

ፕሮፌሰር መስፍን በኢትዮጵያ ያልከሸፈ ነገር ስለአለመኖሩ የሰጡን ጥንታኔ ትክክልነት የሚጠራጠሩ ካሉ ስለየትኛዋ ኢትዮጵያ እንደሚያወሩ እንጠይቃቸዋለን፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲል ስለ ምናባዊት ኢትዮጵያ ሕልውና ስንወያያይ ያነሳናቸው የምናባዊ ማሕበረሰብ ግንባታ ነጥቦች አስፈላጊነት በድጋሚ የሚነሳው እንግዲህ እዚህ ጋር ነው፡፡ አንድ ዐይነት ወይም ተቀራራቢ ምናባዊ ማሕበረሰብነት የሌለው ሕዝብ እንዴት አድርጎ አንድ የጋራ መተዳደሪያ፤ ደንብ፤ ሕግ፤ ሥርዐት እና ተቋማት የሚወልደው አንድ ምናባዊ ማሕበረሰብ ሳንፈጥር እንዴት ወደ አንድ አቅጣጫ ማየት እንችላለን? ይህን ጥያቄ የመጀመሪያ ደረጃ (First Order) ጥያቄ ልንለው እንችላለለን፡

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በርካታ ብሔሮች አገር አንድን ወጥ ምናባዊ ማሕበረሰብ መፍጠር የረጅም ዘመን ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ አንድን ምናባዊ ማሕበረሰብ እስክንፈጥር የሕግ የበላይነትን አስመልክቶ በርካታ ሥራዎች መሥራት ይቻላል፡፡ አገሮች የረጅም ጊዜ ተጓዥ ናቸውና የመጀመሪያ ሥራውን እስክንጨርስ ከምንጠብቅ ከሥር ከሥር ሕግ እና ሥርዐት እየገነባን ቀስ በቀስ አንድ ምናባዊ ማሕበረሰብን ወደመገንባት መሄድ እንችላለን የሚሉም ይኖራሉ፡፡ የእነዚህ ሰዎች ትኩረት የመጀመሪያ ደረጃ ጥያቄዎችን በመመለስ ላይ ሳይኾን ሁለተኛ ደረጃ (Second Order) ጥያቄዎችን በመመለስ ላይ ነው።ይህ የቅደም ተከተል ጥያቄ መኖሩን ከማሳየት አልፌ ‘ይህ ይቅደም፤ ይህ ይከተል’ ወደሚለው ውይይት በጥልቀት ብገባ  የጽሑፉን ትኩረት ያዛባብኛል።

 

ቢያንስ ከአብዮቱ ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ ሥልጣንን ለመገደብ የተሻለው አማራጭ የመጀመሪያውን ጥያቄ መመለስ (አንዲት ምናባዊት ኢትዮጵያን መገንባት)፤ አይደለም የሁለተኛውን ደረጃ ጥያቄ መመለስ (ሕግ ማውጣት ተቋማትን መገንባት) ነው በሚል በርካታ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን በሚያነሷቸው መለኪያዎች ከተወያየን ግን በኢትዮጵያ በሁለቱም መንገድ ሥልጣንን ለመገደብ የተደረጉት ሙከራዎች ከሽፈዋል፡፡ ስለዚህ ጥያቄው የቅደም ተከተል መኾኑ ይቀራል፡፡ ተጨማሪ የክሽፈት ሂደት፡

ፕሮፌሰር መስፍን ለኢትዮጵያ የክሽፈት ማንነት ምንጭ የሚሉት ሌላው ነገር ሃይማኖት ነው፡፡ ፕሮፌሰር በሃይማኖት ላይ የሚያቀርቡት ትችት በግልጽ የተነጣጠረው ሃይማኖት ለአስተሳባችን ከሚጫወተው የእውነት ምንጭነት (Epistemic Role) ጋራ በተያያዘ መልኩ ነው። ፕሮፌሰር ሁለት የእውነት ምንጮች እንዳሉ በዚህ ትንታኔያቸው ያስቀምጣሉ። አንደኛው የእውነት መሠረት እምነት ነው። ከእምነት የሚመነጨውን እውነት ፕሮፌሰር “የተገለጠ እውነት” ሲሉ ያስቀምጡታል። ይህ እውነት በባሕርይው አይጠየቅም፤ አይገረሰስም፡፡

 

እንደፕሮፌሰር ሁለተኛው የእውነት ምንጭ እውቀት ነው። ከእውቀት የሚመነጭ እውነት ግን ለፈተና፣ ለጥያቄ እና ለትችት የተጋለጠ ነው፡፡ እንዲያውም ከእውቀት የሚገኝ እውነት መለኪያው ተጠይቆ የተገኘ እና የተፈተነ መኾኑ ነው፡፡ ከመገለጥ የተገኘ እውነትነትን አዳጋችነት ሲያስቀምጡ “በአንድ ጉዳይ ላይ በአንድ ጊዜ ሁለት በፀጋ የተገለጡ ተቃራኒ እውነቶች ሲኖሩ ቅራኔው የሚፈታው እንዴት ነው?” ገጽ 196 ሥልጣንን መግታት ያልቻልንበት አንዱ ምክንያትም ይላሉ ፕሮፌሰር “ሥልጣን በፀጋ ከተገለጠ እውነት ጋር በመያያዙ ነው፡፡” ከዚህ ሃይማኖታዊ እውነታ የወለድነውን ማኅበራዊ ውል (Social Contract) ፕሮፌሰር “ገዢዎች ረግጠው ለመግዛት ተገዢዎችም በበኩላቸው የተገለጠ እውነት እየተጠቀሰላቸው ለመገዛት የተስማሙበት ..” በማለት ይጎሽሙታል

በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከተቀመጡት ዕንቁዎች ውስጥ ለእኔ ትልቁ ዕንቁ ይህ ፕሮፌሰር ስለተገለጠ እውነት የሰነዘሩት ትችት ነው፡፡ ፕሮፌሰር ፍልስፍናን ማንበብ ብቻ ሳይኾን ከሚኖሩበት ማሕበረሰብ እና እውነታ ጋር እንደሚያጋቡት ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡ በአገራችን ፍልስፍናን ማንበብ እንደጀመሩ ሃይማኖት ለይ መሳለቅ ፋሽን ነው፡፡ እነዚህ ጀማሪ የፍልስፍና አንባቢዎች ስለሃይማኖት እና ኢትዮጵያ ሲያስቡ ብዙ ጊዜያቸውን የሚያጠፉት በዓላት እያበዛ ሥራ አስፈታን፤ ታታሪ እንዳንኾን አደረገን የሚል አርቲ ቡርቲ መከራከሪያ በማቅረብ ነው፡፡

 

እንደ ፕሮፌሰር መስፍን አገላለጽ ሃይማኖት ለክሽፈት መበራከት ዐይነተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል። እርሳቸው ይህን ከሥልጣን አለመገደብ ጋራ አሰናስለው በሰፊው ትንታኔ ሰጥተውበታል። ነገር ግን ይህን ጉዳይ ከእውነት ምንጭነት ጋራ በማገናኘት ሃይማኖት የመናገር ነጻነትን እንዴት ዋጋ አሳጥቶት እንደኖረ መተንተን እንችላለን። ለምሳሌ ገጣሚ እና ደራሲ በእውቀቱ ስዩም አቡነ ተክለሃይማኖትን ተችቷል ተብሎ በቡጢ የተመታ ጊዜ አሳፋሪ በሚባል መልኩ ትንሽ ትልቁ ለበእውቀቱ እና ሐሳብን ለመግለጽ ነጻነት ከመቆም ይልቅ “ስቀለው!”፣ “ስቀለው!”፣ “ስቀለው!” ሲል ዐይተናል፡፡ እንዴት ነው ይህ ማሕበረሰብ የተለያዩ እውነታዎችን በአንድ እና ተመሳሳይ ጊዜ ማስተናገድ የሚችለው? እንዴት ነው ሳይንስ በዚህ ወዶ በደነቆረ ማሕበረስብ ውስጥ የሚያድገው? ዛሬ አቡነ ተክለሃይማኖት የማይነኩ ከኾነ፤ ነገ ደግሞ በሌላው አገር እንደሰማነው ነብዩ መሐመድን ተናገራችኹ ተብለን ፈጠዋ ሊታወጅብን ነው ማለት ነው?  የተረጋገጠ እውነት ሳይኾን ሃይማኖታዊ እውነት በሚገነባበት ማሕበረስብ እንዴት ነው አንድ ዐይነት ምናባዊ ማሕበረስብ የምንገነባው? ማን የማን ሃይማኖት በገነባው ምናባዊ ማሕበረሰብ ጥላ ስር ሊኖር?

 

ፕሮፌሰር ለኢትዮጵያ የክሽፈት ባህል መንስዔነት የሚከሱት ሌላኛው ነገር አብሮ ያለመሥራት እና ያለመተባበር ዝንባሌያችንን ነው፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ዕይታ ትብብራችን በሙሉ ከመቃብር እና ከተዝካር ያለፈ ትልቅ ነገር ሊወልድ፣ ሊያሳድግ እና ለማዕረግ ሊያበቃ አልቻለም። ፕሮፌሰር ለክሽፈት ምክንያትነት ካቀረቧቸው ሦስት ምክንያቶች ስለ አለመተባበር ያቀረቡት መከራከሪያ በእጅጉ አናሳ ነው፡፡ ስለ እውነት፣ ስላልተገራ ሥልጣን ያብራሩትን ያህል ስለተባብሮ አለመሥራትም ብዙ ሊሉ ይችሉ ነበር።

ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ እጅግ በጨነቀው የመጨረሻው ሰዓት “ዔሎሄ ዔሎሄ ላማሰብቅታኒ” ያለው ሲሰብክበት በነበረው የእብራይስጥ ቋንቋ ሳይኾን አፉን ፈትቶበታል ተብሎ በሚገመተው የአረማይክ ቋንቋ ነበር። ኢየሱስ ይህን መልዕክት ለመናገር ለምን የአረማይክ ቋንቋን እንደተጠቀመ በርካታ ሃልዮቶች አሉ፡፡ እኔ የሚስማማኝ ኢየሱስ አፉን በፈታበት ቋንቋ ይህን ሰቆቃ ያቃሰተው በሕይወታችን የመጨረሻ ወቅት ሰቆቃ ሲገጥመን የምናቃስተው በተማርነው ቋንቋ ሳይኾን አፋችንን በፈታንበት ቋንቋ ስለኾነ ነው የሚለውን የሥነልቦና ምሁራን ሃልዮት ነው፡፡

 

ለፕሮፌሰር መስፍን ትውልድ የኢጣልያ ወረራ እጅግ ዘግናኝ እና ወሳኝ የሰቆቃ (Trauma) ምንጭ እንደኾነ መጽሐፋቸውን በማየት መረዳት ይቻላል፡፡ በኢጣልያ ወረራ ወቅት አርበኞች ቢኖሩንም የነበረን የባንዳ ብዛት እና በመጨረሻም አገር ነጻ ስትወጣ አርበኛ ሳይኾን ባንዳ ሲያሸንፍ መመልከት በወቅቱ ልጆች እና ወጣት ለነበሩት ለእነ ፕሮፌሰር መስፍን የዕድሜ ልክ ጠባሳ ትቶ አልፏል፡፡ ፕሮፌሰር በዕድሜያቸው መጨረሻ በሰቆቃ ላይ ሰቆቃ እያስተዋሉ ይኼው በመጨረሻ ላይ አፋቸውን በፈቱበት የክህደት ትዕይንት ኢትዮጵያ ተውጣ እያዩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ተባብሮ አለመሥራት (Collective Action) እጅግ ያቃተን ለምንድን ነው? በተለይ በተለይ ኢትዮጵያዊነት/ኢትዮጵያ የሚሉት ነገሮች አስተባብረው ከአንድ ቦታ ለማድረስ ለምን ሰነፉ? ሐበሻ ለብሔሩ ሲኾን መንግሥት ይጥላል (ትግሬ፤ ኤርትራ) ለሃይማኖት ሲኾን አንድ ዓመት ሙሉ በሰላማዊ መንገድ ይታገላል። ይኼው ሙስሊሞች ሰላማዊ ትግል ከጀመሩ አንድ ድፍን ዓመት ኾናቸው፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ሲባል ለምን ሐበሻ ልቡ ይፈሳል? ይህ አብሮ ያለመሥራት ስንፍና እና ታካችነት ምንጩ የትጋር ነው?

 

 

የክሽፈት ተዋስዖ

 

ፕሮፌሰር መስፍን በዚህ መጽሐፋቸው አዲስ የክሽፈት ተዋስዖ ፈልፍለዋል እላለኹ፡፡ አዲስ ስል ግን ከምንም የተነሳ ምንም ከሌለበት ውስጥ አዲስ የተወለደ  (Ex nihilo) የሚባለውን ዐይነት አፈጣጠር አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ፈጥረዋል ከሚለው ቃል ይልቅ ‘ፈልፍለዋል’ የሚለውን የመረጥኹት፡፡ መፈልፈል ከእንጨት፣ ድንጋይ ወይም መሰል ተጨባጭ ነገር ውስጥ የራስ የኾነን ፈጠራ በመጨማመር አዲስ ነገርን ፈልቅቆ ማውጣትን ያመለክታል፡፡

በአንድም ኾነ በሌላም መልኩ ስለመክሸፍ የኢትዮጵያ ምሁራን አውርተዋል፡፡ ለምሳሌ የተማሪዎች አብዮት ከሽፏል አልከሸፈም? (ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ) ኢሕአዴግ የመራው የሽግግር መንግሥት ከሽፏል አልከሸፈም? (ሌንጮ ለታ) ኦነግ ከሽፏል አልከሸፈም? (ጃዋር መሐመድ) እነዚህ ምሁራን በፍልስፍና፤ ፖለቲካ እና ታሪክ በኩል መክሸፍ ሊዳስሱት የሞከሩት ጥያቄ ነው፡፡

 

ከመክሸፍ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ የሚነሳው ሌላው ጥያቄ ኢትዮጵያ የተለያዩ የጥናት ተቋማት የሚያወጧቸውን የከሸፉ አገራት (Failed States) ዝርዝር ማሞቅ ከጀመረች ሰንብታለች። ኢትዮጵያ በእነዚህ የከሸፉ አገራት ዝርዝር መካተቷ አሳመኝ የማይሆንባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ምንኛ ተዳክሟል ፤ተልፈስፍሷል ቢባል በፈለገው ሰዓት የፈለገው የግዛቱ ክልል ውስጥ ያለማቋረጥ አንቀጥቅጦ ግብር ይሰበስባል፡፡ የተለያዩ አቅርቦቶችን ለዜጎች ያከፋፍላል ለምሳሌ መንገድ ይሰራል፤ ሰዎችን በሰላም አስወጥቶ በሰላም ያስገባል፤ ለሰራተኛ ደሞዝ ይከፍለል፡፡ ይህን አይነት ጠንካራ መንግስት መቼም መንግስት የሚባል ከሌለበት ከሶማሊያ ወይንም  የመንግስት ሰራተኛ ደሞዝ ካየ አምስት አመት ከተቆጠረባት ኮንጎ ጋር ማወዳደር አዳጋች ነው፡፡ እንደውም ይህ የመንግስት ጥንካሬ (Strong State)ባሕሪይ የኢትዮጵያን መንግስት ከአፍሪካ በርካታ መንግስታት  ጋር ሲነጻጸር አልከሸፈም ለማለት ሊጋብዘን ይችላል፡፡

 

ፕሮፌሰር መስፍን ስለክሽፈት የሰጡት ሁለተኛ ትርጓሜ እንደሚያስታውሰን መክሸፍ ማለት የተነሱበትን ግብ አለመምታት ብቻ ሳይሆን አለማደግ ፤አለመሻሻል ፤ ባሉበት ፤በጀመሩበት መቆም ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ጥንካሬ የጀመረው ዛሬ አይደለም፡፡ ከአፈጣጠሩ የኢትዮጵያ መንግስት እጅግ ጨካኝ እና መራራ መንግስት ነው፡፡ እስቲ ግብር የሚለውን ቃል ትርጉም አስተውሉ፡፡ ማንበርከክን ፤ማሰቃየትን፤ አገር ማስፋፋትን፤ ገቢ ከመሰብሰብ ጋር አዋህዶ የያዘ አስገራሚ ፖለቲካዊ ቃል ነው፡፡ በኢትዮጵያ መሸፈት የሚጀመረውም  አልገብርም ወይንም  ግብሩ በዛብኝ  ከሚል እምቢተኝነት ነው፡፡ ይህ የእምቢተኝነት አዙሪት ግን የሚጠናቀቀው የግብር ስርአቱን በማሻሻል ወይንም በማላላት ሳይሆን ከቀደመው ስርዓት አስከፊ በሆነ መልኩ  አስገባሪ በመሆን ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት አሁንም ጠንካራ አስገባሪ ነው ነገር ግን መንግስት የመሆን ጽንሰሀሳብ አስገባሪ ብቻ ከመሆን ከሰፋ ስንት ዘመኑ?

 

ፕሮፌሰር መስፍን ስለክሽፈት እና ኢትዮጵያ የሚያነሱትን ጥያቄ በአቀራረብ ልዩ ያደርገዋል የምልበት ሌላው ምክንያት  የመክሸፍን ክስተት ከአንድ ታሪካዊ አጋጣሚ ወይም ፕሮጀክት አውጥተው ከማንነት ጋር በማያያዛቸው ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ስለ ክሽፈት እና ኢትዮጵያዊነት ያላቸው ትንታኔ በኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈት ድግግሞሽ መኾኑን በማሳየት ከጀመረ በኋላ ክሽፈት ባህል ነው ወደሚል ድምዳሜ ይሻገራል፡፡ ይህ ድምዳሜያቸው ክሽፈትን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በአንድ ወቅት ወይም በተደጋጋሚ ከሚታይ አጋጣሚ ወደ አንዱ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ያሸጋግረዋል፡

ይህ ማለት በኢትዮጵያ ውስጥ ሐሳቦች፣ ዕቅዶች፣ ተቋማት የሚከሽፉት አመቺ ኹኔታዎች ስላለተፈጠሩላቸው ብቻ ሳይኾን መክሸፍ ኢትዮጵያዊነትን ከኬንያዊነት እንዲሁም ከጃፓናዊነት ከሚለዩት ልዩ ባሕርያት አንዱ ስለኾነ ነው ማለት ነው። ኢትዮጵያዊ ከኾንክ/ከኾንሽ መክሸፍ ባህልህ/ባህልሽ ነው፡፡ በአጭሩ ኢትዮጵያዊ መክሸፉን ነብር ዥንጉርጉርነቱን አይተውም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን በግልም ኾነ በጋራ የምንሠራው ነገር በሙሉ ገና ሳንተገብረው ክሽፈትን ፀንሷል፡፡ ይህ የክሽፈት ፅንስ የተቀመጠው በማንነታችን ውስጥ ነውና እንደፕሮፌሰር አባባል ከአገር ስንሰደድም ይዘነው እንጓዛለን፤ ስደታችንም ገና ከቦሌ ሳንደርስ ይከሽፋል።

 

የፕሮፌሰር መስፍንን መልእክት በአትኩሮት እንደከታተል ያደረገኝ ሌላኛው ነገር ስለታሪክ ያላቸው ምሬት ከተለምዶው የቀኞች መንደር  ምንጭ ብቻ የተቀዳ አለመኾኑ ነው። ስለኢትዮጵያ ታሪክ እንዲኖረን የሚሹት ትውስታ(Memory) አሁንም ልክ እንደ ርዕዮተ ዓለማዊ መንደራቸው በጋራ ጭቆና እና የጋራ ጋሬጣ ላይ ብቻ መኾኑ አልቀረም፡፡ ነገር ግን ከታሪክ ትንታኔ ብቻ ወጥተው ወደ ታሪክ ፍልስፍና (Philosophy of History) ሲጓዙ ስለኢትዮጵያዊነት የሚያቀርቧቸው የክሽፈት ትችቶች ከርዕዮተ ዓለም እስረኝነታቸው ፈታ ለማለት ሲታገሉ ይታያል። በርዕዮተ ዓለም ብቻ የታሠረ የኢትዮጵያ የቀኝ መንደርተኛ ኢትዮጵያን/ኢትዮጵያዊነትን ከሽፋለች ለማለት አንጀት የለውም።ቀኞች በተለምዶ ስለክሽፈት ሲያወሩ እነርሱ አገር ስላልገዙ የእነርሱ ፕሮጀክት ስለከሸፈ አገሪቷ የከሸፈች ይመስላል። የፕሮፌሰር የክሽፈት ትንታኔ ከቀኝ መንደር የተለቀሙ ቅመሞች  የበዙበት ቢኾንም መልእክቱ እና የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ፈጽሞ ችላ ልንላቸው የሚገቡ አይደሉም፡፡

 

አንድ ተዋስዖ የሚጀምረው ተዋስዖው ራሱ ሊያወያየው የሚፈልገው ጥያቄ ተገቢ ነው አይደለም? ጥያቄው  አለ ወይስ የለም? የሚሉትን ጥያቄዎች በመዳሰስ ነው፡፡ የፕሮፌሰርን መጽሐፍ በብዙ የመጻሕፍት መለኪያዎች  የከሸፈ ልንለው ብንችልም መልዕክቱን ከመጽሐፉ ጋር አሽቀንጥረን ከጣልነው ግን እኛ ከመጽሐፉም ከፕሮፌሰር መስፍንም ይልቅ የከሸፍን እንኾናለን፡፡ ይልቁኑ ፕሮፌሰር መስፍን የከፈቱልንን የክሽፈት ጥያቄ ቀዳዳ ወደ ትልቅ በርነት በርግደን በመግባት  ራሳችንን መበርበር እንጀምር፡፡ ስኬት ሩቅ ነች፤ በመንገዷ የሚገናኛትም/የሚደርስባትም እንደከሸፈ በማመን ጉዞውን  የጀመረው ብቻ ነው፡፡

 

 

የፕሮፌሰርን መጽሐፍ ሳነበው ከስድሳ ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን አሻሽላለኹ፤ ለሕዝቤ አገለግላለኹ ብላ የምትታገለው ነፍሳቸው በራሷ ጉዞ የገጠማት ስንጥቅ ታየኝ፡፡ ከዚህ የነፍሳቸው ስንጥቅ የሚወጣውን መልዕክት መዓዛ ደግሞ በደንብ አውቀዋለኹ። “በእኔ ዕድሜ ያደኩበት ሰፈር ስም፤ የተማርኹበት ተማሪ ቤት ስም፤ ያስተማርኹበት ተማሪ ቤት ስም፤ የሠራኹበት መሥሪያ ቤት ስም ተለውጧል። ስለዚህ እኔ የሌለ ሰፈር አድጌ፤ የሌለ ተማሪ ቤት ተምሬ፤ የሌለ ተማሪ ቤት አስተምሬ፤ የሌለ መሥሪያ ቤት ሰርቼ፤ የሌለ ዩኒቨርስቲ አስተምሬ … እኔ በጡረታ መኖሬ ያስገርማል! ከሽፎ የከሸፈ ኑሮ መኖር እንበለው!” ፕሮፌሰር መስፍን መልካሙን ገድል ተጋድያለኹ ማለት በሚገባቸው የሕይወት ዘመናቸው ላይ ‘ከንቱ! ሁሉም ነገር ከንቱ!’ የሚሉ አይመስልምን? ነፍስ ስትሰነጠቅ እውነት እውነቱን እንዲህ ታናግራለች፡፡ ታምራት ነገራ
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on March 21, 2013
  • By:
  • Last Modified: March 21, 2013 @ 12:04 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar