www.maledatimes.com “ኡመተ ፈናን- ኡመተ ቀሽቲ ዲሬ ደዋ” (አርቲስቱና ሽቅርቅሩ የድሬ ዳዋ ህዝብ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

“ኡመተ ፈናን- ኡመተ ቀሽቲ ዲሬ ደዋ” (አርቲስቱና ሽቅርቅሩ የድሬ ዳዋ ህዝብ)

By   /   March 22, 2013  /   Comments Off on “ኡመተ ፈናን- ኡመተ ቀሽቲ ዲሬ ደዋ” (አርቲስቱና ሽቅርቅሩ የድሬ ዳዋ ህዝብ)

    Print       Email
0 0
Read Time:57 Minute, 36 Second

ጸሐፊ-አፈንዲ ሙተቂ

በደርግ ዘመን ነበር አሉ። ሰፊው የድሬ ዳዋ ህዝብ ከማዕከል የመጣው የደርግ አባል የሚያደርገውን ንግግር ለማዳመጥ በከተማዋ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተሰብስቧል። የስብሰባው ሰዓት ደርሶ የደርግ አባሉ ንግግር ወደሚያደርግበት መድረክ ወጣ። ንግግሩን ከመጀመሩ በፊት ግን አማርኛ መስማት የማይችሉ በርካታ ሰዎች በአዳራሹ ውስጥ ሊኖሩ እንደሚችሉ ገመተ። ስለሆነም ከፊት ለፊት ከተቀመጡ ወጣቶች መካከል አንዱን ጠርቶ ከአማርኛ ወደ ኦሮምኛ መተርጎም ይችል እንደሆን ጠየቀው። ወጣቱም “አሳምሬ እችላለሁ፤ ኦሮምኛ የመጀመሪያ ቋንቋዬ ነው እኮ!” በማለት መለሰ። የደርግ አባሉም በወጣቱ መልስ ተደስቶ ንግግሩን ለህዝቡ በኦሮምኛ እንዲተረጉም ነገረውና ለራሱ ወደ መነጋገሪያው ቀረበ።
የደርግ አባሉ ንግግሩን ለመጀመር ያህል “የተወደድከውና የተከበርከው የድሬ ዳዋ ህዝብ” ሲል ወጣቱ ቀበል አድርጎ “ያ ኡመተ ፈናን ያ ኡመተ ቀሽቲ ድሬ ዳዋ” በማለት ወደ ኦሮምኛ ተረጎመው። ይህን የሰማው የድሬ ዳዋ ህዝብ አዳራሹን በሳቅና በፉጨት አናወጠው።
******************
ይህ ነገር በትክክል ደርሶ ሊሆን ይችላል፤ ፈጠራም ሊሆን ይችላል። እውነተኛ ነገር ከሆነ ግን እኔንና ብዙዎችን በሳቅ እንደሚያንፈራፍር እርግጠኛ ነኝ። ደግሞም ብዙዎች ሲስቁ አጋጥሞኛል። ነገር ግን ቀልዳ ቀልድ የሚመስለውን የልጁን ቱርጁማን በጥልቀት ያስተዋለ ሰው የድሬ ዳዋን ህዝብ በትክክል የሚገልጽ አባባል ሆኖ ያገኘዋል። “እንዴት?” ብሎ ለሚጠይቀኝ አንባቢ ነገሩን እንደሚከተለው አብራራለሁ።
“ኡመተ” በኦሮምኛ “ህዝብ” ማለት ነው። “ፈናን” ደግሞ በዐረብኛ “አርቲስት” ወይም “ከያኒ” ማለት ነው። በድሬ ዳዋና በሌሎችም የምስራቅ ኢትዮጵያ ከተሞች ግን “ፈናን” ከመደበኛው ትርጉሙ ሰፋ ያሉ ፍቺዎች አሉት። ለምሳሌ አለባበሱ የሚያምርበትን ሰው “ፈናን” ማለት ይቻላል። አዳዲስ ፋሽን የሚከተሉ “ዘናጭ” ሰዎችንም “ፈናን” ማለት ይቻላል (በተለምዶ “ቴክሳስ” እንደምንለው ማለት ነው)።
ነገር ግን “ዘናጭ” ወይም “ቴክሳስ” መሆን ብቻውን “ፈናን” አያሰኝም። ወግና ጨዋታ አዋቂነት ሲጨመርበት ነው “ፈናን” የሚያስብለው። ንግግሩ የሚጣፍጥለት፣ ሌሎች ሊቀርቡት የሚጓጉለት፣ ከሌሎች ጋር ለመላመድ ጊዜ የማይወስድበት ሰው ወዘተ.. “ፈናን” ነው። እንዲህ ሰፋ አድርገን ካየነው የድሬ ዳዋ ህዝብ በእውነትም “ፈናን” ነው።
“ቀሽቲ” የድሬ ዳዋ ልጆች የፈጠራ ውጤት ነው። በየትኛውም ቋንቋ ውስጥ እንዲህ የሚል ቃል አይገኝም። ትክከለኛ ፍቺውን የሚያውቁትም ቃሉን ፈጥረው የሚጠቀሙበት የድሬ ልጆች ናቸው። በምስራቅ ኢትዮጵያ ከተሞች በሚታወቅበት አገባብ ግን “ቀሽቲ” በመጠኑ ከ“ፈናን” ጋር ይመሳሰልና በአገልግሎቱ በጣም ይሰፋል። ለምሳሌ ፍጥነትና ቅልጥፍናን ለመግለጽ “ቀሽት ነው” ማለት ይቻላል። አንጀት-አርስ የሆነ አገልግሎት የሚሰጥ ካፍቴሪያ፣ በፈለጉበት ጊዜ ከች የሚል አውቶቡስ፣ በፈገግታ ደንበኞችን የሚያስተናግድ የባንክ ኦፊሰር ወዘተ.. “ቀሽት” ሊባሉ ይችላሉ። እንዲሁም አስደሳች የሆነ የመኪና ሞዴል፣ አዳዲስ የብር ኖቶች፣ ግርማ ሞገስ ያለው ቪላ ቤት ወዘተ ሁሉም “ቀሽት” ናቸው።
ታዲያ እንዲህ በስፋት ከዘረዘርኳቸው ትርጓሜዎች አንፃር የድሬ ዳዋ ህዝብን “ፈንና” እና “ቀሽት” ነው ለማለት አይቻልምን? እንዴታ!! የድሬ ህዝብ በጨዋታ አዋቂነቱ፣ ከአዳዲስ አሰራሮችና የቴክኖሎጂ ትሩፋቶች ጋር በፍጥነት ለመላመድ ባለው ክህሎት፣ በንቃተ ህሊናውና በፈጠራ ችሎታው ወዘተ… “ፈናን” እና “ቀሽት” ነው። ጨዋታው የማይሰለች፣ ለእንግዳ አክብሮት የሚሰጥ፣ ደሃና ሀብታሙን በእኩሌታ የሚያይ ህዝብ ነው-የድሬ ህዝብ። ስለዚህ “ፈናን” እና “ቀሽት” የሚለው የወጣቱ አባባል በትክክል ይገልጸዋል። ነገር ግን ከሁሉም በላይ “ፈናን” እና “ቀሽት” መባል ያለባት ድሬ ዳዋ ራሷ ናት።
አዎን! ድሬ ዳዋ እንደ ሀረር እና እንደ ጎንደር እድሜ ጠገብ አይደለችም። ነገር ግን በ110 ዓመታት ጉዞዋ ከአንድ ከተማ የሚጠበቀውን ሁሉ አበርክታለች። የንግድ፣ የኢንዱስትሪ፣ የትራንስፖርት፣ የቴክኖሎጂ ወዘተ… ማዕከል በመሆን መላውን የምስራቅ ኢትዮጵያ ህዝቦች አገልግላለች። ለኪነ-ጥበብ እድገትና ለመንፈሳዊ ተሀድሶ ያበረከተችው አስተዋጽኦማ አይነገረም። አዲስ ፈጠራ ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ ሲደርስ መጀመሪያ በረከቱን የሚቀምሱት የድሬ ዳዋ ልጆች ናቸው።
በዚህ ጽሁፌ የድሬ ዳዋን ማንነትና ታሪካዊ እውነቶች በሙሉ እዘረዝራለሁ የሚል ዓላማ የለኝም። ከዚያ ይልቅ የከተማዋን አመሰራረት፣ ከድሬ ሰፈሮች የአንዳንዶቹን መጠሪያና ገጽታ፣  እንዲሁም የድሬ ዳዋ ልጆችን የቋንቋና የቃላት አጠቃቀም በመጠኑ አስቃኛችኋለሁ።
******************
በጥንት ዘመን አሁን ድሬ ዳዋ ባለችበት አካባቢ ሶስት አርብቶ አደር ማህበረሰቦች ይኖሩ እንደነበር የከተማዋ ሽማግሌዎች ያወሳሉ። እነርሱም የኖሌ ኦሮሞ፣ የኢሳ ሶማሌ እና የጉርጉራ ሶማሌ ናቸው። ታዲያ የኖሌ ኦሮሞ በሚኖርበት ክልል የአካባቢው ሰው ለመጠጥ ውሃ የሚሻማበት ምንጭ ነበር። ምንጩ በኦሮምኛ “ዻዋ” (dhawa) የሚል መጠሪያ የነበረው ሲሆን ምንጩ ያለበት ቦታ ለማለት አካባቢው “ዲሬ ዻዋ” ተብሎ እንደተሰየመ ሽማግሌዎች ጨምረው ያስረዳሉ።
ከጅቡቲ እስከ አዲስ አበባ የተዘረጋው የባቡር ሀዲድ ስራው ሲታቀድ በመጀመሪያ ምዕራፍ እስከ ሀረር ደርሶ እንዲቆምና በሁለተኛው ምእራፍ ከሀረር ተነስቶ አዲስ አበባ እንዲደርስ ነበር የተፈለገው። ነገር ግን መስመሩን ሀረር ባለችበት ከፍተኛ ስፍራ ላይ ለማሳለፍ እንደማይቻል የተገነዘቡት የፈረንሳይ መሃንዲሶች ሀዲዱን ከሀረር በሚጎራበተው ቆላማ ሜዳ ውስጥ ለመዘርጋት ወሰኑ። የሀዲዱ የመጀመሪያው ምዕራፍ በ1895 ዓ.ል. ተሰርቶ ሲጠናቀቅም “ዻዋ” የተሰኘው ምንጭ ያለበትን  ቦታ መዳረሻ በማድረግ የባቡር ኩባንያው ዋነኛ ጣቢያ በስፍራው ተገነባ። እርሱን ተከትሎም በአካባቢው ላይ የቆርቆሮ ቤቶች ተቀለሱ። በጥቂት ዓመታት ውስጥ በአካባቢው ሞቅ ያለ የገበያ አጀብ በመታየቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ ዋነኛ የንግድ ማዕከል የነበረችውን ጥንታዊቷን የሀረር ከተማ የምትቀናቀን ሌላ ከተማ በአካባቢው ተወለደች። በወቅቱ በራስ መኮንን እግር ተተክተው የሀረርጌ ገዥ የሆኑት ደጃች ይልማ መኮንን (የተፈሪ መኮንን ታላቅ ወንድም) ለአዲሷ ከተማ “አዲስ ሀረር” የሚል ስያሜ ቢሰጡም ህዝቡ ጥንት አካባቢው የሚጠራበትን “ድሬ ዳዋ” የሚለውን ስም ለከተማዋ አጸደቀ።
******************
ድሬ ዳዋ የተወለደችው ከላይ በተገለፀው ሁኔታ ነው። ታዲያ ጥንት “ዻዋ” እየተባለ ሲጠራ የነበረው ምንጭ የሚገኝበትን ትክክለኛ ስፍራ በአሁኑ ዘመን በሚታወቅበት ስሙ ማመልከት አይቻልም። በዚያ ላይ “ድሬ ዳዋ” የስፍራው መጠሪያ ብቻ ሳይሆን ከሀረር በስተሰሜን ያለው አውራጃ በወል የሚጠራበት ስም መሆኑም ስለሚነገር ጥንታዊው ምንጭ የነበረበትን ስፍራ ማፈላለጉን ለጊዜው እንርሳውና ሌላ ሌላውን እናውጋ።
“ባቡር ጣቢያ”ው ለከተማዋ መወለድ ትልቅ ምክንያት እንደሆነ ከላይ ተገልጿል። ታዲያ የድሬ ደዋ ቀደምት ሰፈርም በባቡር ጣቢያው ስም “ለገሀር” ተብሎ ይጠራል (ከፈረንሳይኛው la gare የተገኘ ቃል ነው)። “ለገሀር” የባቡር ትራንስፖርት የሀገሪቷ ዐይነተኛ የመገናኛ አውታር በነበረበት ዘመን በጣም የደራና የደመቀ ሰፈር እንደመሆኑ የድሬ ዳዋ ዐይን ተብሎ ይጠቀስ ነበር። እያደር መኪናና አውሮፕላን ወደ ከተማዋ ሲደርሱ “ለገሀር” ፊት መሪነቱን ለሌሎች መልቀቅ ግድ ሆኖበታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሀዲድ እድሳት ምክንያት የባቡር ትራንስፖርት ቀጥ ብሎ ቆሟል። በዚህም የተነሳ የለገሀር ነፍስም ጸጥ ብላለች። ቢሆንም ግን በአንድ ዘመን አገር በሙሉ የሚርመሰመስበት ስፍራ እንደነበር ማንም ይመሰክራል።
አንዳንዶቹ የድሬዳዋ ሰፈሮች የሚጠሩት ጥንት በነበራቸው ስያሜ እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል። አንዳንዶቹ ስያሜዎች ደግሞ በንግድ መስፋፋት ሂደት የተገኙ ናቸው። በአንዳንዶቹ ላይ ግን የድሬ ልጆች የፈጠራ ጥበብ ይታያል። እስቲ ሁሉንም በምሳሌ ላስረዳ።
“ለገ ሀሬ” በቅርብ ዘመን የወጣ ስያሜ አይመስልም። “ለገሀሬ” በኦሮምኛ “የአህያ ወንዝ” ማለት ነው። እንደምገምተው ወንዙ በሚፈስበት በአንደኛው ስፍራ አህዮችን ውሃ ለማጠጣት ይዘወተር ነበር። ደግሞ በዚሁ የአህዮች ማጠጫ ስፍራ ወንዙ ጥልቀት አልነበረውም፤ ምክንያቱም በተለምዶ እንደምናውቀው አህዮች ጥልቀት ባለው ወንዝ አቅራቢያ እንዲደርሱ አይደረግምና። ታዲያ የድሬ ዳዋ ህዝብ በአንድ ወቅት የመጠጥ ውሃ የሚያገኝበት ዋነኛ ወንዝ ይኸው “ለገሃሬ” እንደሆነ ታሪክ አዋቂዎች ያወሳሉ። ለዚህም ይመስላል ዓሊ ቢራ፡
“ዲሬ ዳዋ ዹጋ ቢሻን ለገሀሬ
“ጃለለ አከና ተካቱ ሂንአገሬ” በማለት የዘፈነው።” ትርጉሙ
“የለገሀሬን ውሃ የሚጠጣው ድሬ ዳዋ ነው
እንዲህ ዓይነት ፍቅር ያለዛሬም አላየሁ” የሚል ይሆናል።
የድሬ ዳዋ ዐይን የሆነው ሰፈር ከዚራ ነው። ብዙ የተባለለትና የተዘፈነለት የድሬ ሰፈር ነው-ከዚራ። የስያሜው መነሻ ምን እንደሆነ በትክክል ለማወቅ አልቻልኩም። የከተማዋ ታሪክ አዋቂዎችም ቁርጥ ያለ መልስ ሊሰጡኝ አልቻሉም። እንደምገምተው ከሆነ ግን “ኸዲራ” (በዐረብኛ “አረንጓዴ” ለማለት ነው) የሚለው ቃል ተለውጦ ነው “ከዚራ” የተገኘው። ይህንን ያሰኘኝ ድሬ ስትወሳ በሁላችንም ዓይነ ህሊና ቶሎ ከተፍ በሚሉት ውብ “ጥላዎች” የተሽቆጠቆጠ ሰፈር በመሆኑ ነው። ድሮ ዘፈን እሰማ በነበረበት ዘመን አርቲስት ነዋይ ደበበ
“ከተፍ አለ ልቤ ደረሰልሽ
ከዚራ ጥላው ስር ተነጥፎልሽ” የማለቱ ፍቺ የገባኝ ከዚራ ከደረስኩ በኋላ ነው።
አዎን! ድሬ ዳዋን ያስገኘው ሰፈር “ለገሀር” ቢሆንም በሌሎች እንድትናፈቅ ያደረጓት ዋነኛ ምልክቶቿ የከዚራ ጥላዎች ናቸው። ሰፋ ባሉት የድሬ ጎዳናዎች ዳርቻ የተሰደሩት የከዚራ ጥላዎች ባይኖሩ ኖሮ ድሬም የምትኖር አይመስለኝም። አነዚህ ጥላዎች የጂኦሜትሪ ጥበብ በጠገበ አትክልተኛ ተኮትኩተው ያደጉ ይመስል ከመንገዱ ወዲያና ወዲህ ትይዩ (Symetric) ሆነው ቀጥ ቆመዋል። እኔ እንደማውቀው በኢትዮጵያ ውስጥ ከተሞቻችንን “ፅዱ እና አረንጓዴ” እናድርግ የሚል መፈክር መነዛት የተጀመረው አርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) በ1993 ዓ.ል. የከተማ ጽዳት አብዮት ከለኮሰ ወዲህ ነው። የከዚራ ጥላዎች ግን ከጥንትም ጀምሮ የድሬዳዋ የዐይን ማረፊያዎች ነበሩ።
“ከዚራ” በጥንቱ ዘመን የውጪ ሰዎች መኖሪያ ነበር። ግሪኮች፣ ዐረቦች፣ አርመኖችና ጣሊያናዊያን በብዛት ይኖሩበት ነበር። በኋላ ላይ ደግሞ እንግሊዛዊያን የሰፈሩ ዋነኛ መንደርተኞች ሆኑ። ታዲያ የከዚራ ጥላዎች መነሻም እነዚያ የውጪ ዜጎች እንደ ንዳድ የሚያቃጥለውን የድሬ ዳዋ ሙቀት ለመቀነስ በአካባቢው ሲሰሩት የነበረው የዛፍ ተከላና የጽዳት ስራ ነው። የጥላዎቹ አገልግሎት በከተማዋ ብቻ አይወሰንም። ለዚህም ሁለት አብነቶችን ልጥቀስ።
 አብዛኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ ለሰርግና ለጫጉላ ሽርሽር የሚመርጠው የሶደሬና የላንጋኖ መዝናኛዎችን ነው። የምስራቅ ኢትዮጵያ ነዋሪዎች ለሽርሽር የሚመርጡት ደግሞ ሁለት ቦታዎችን ነው። ከነርሱም አንደኛው የሀረማያ ሀይቅ ነው። ነገር ግን የሀረማያ ሀይቅ በአሁኑ ወቅት የለም። እነ ዓሊ ሸቦ፣ ማህዲ ጃፖን፣ ያህያ አደም፣ ሀሎ ዳዌ ወዘተ… እንደዚያ የዘፈኑለት ሀይቅ ምን እንደነካው ሳይታወቅ ታሪክ ሆኖ ከምድረ-ገጽ ጠፍቷል። ሁለተኛውና በአሁኑ ዘመን በአካባቢው የቀረው ታላቅ የሽርሽር ስፍራ “ከዚራ” ነው። በተለይ ሰርግ ደግሶ ከሚዜዎቹና ከአጃቢዎቹ ጋር በከዚራ ጥላዎች ስር የተንፈላሰሰ ሙሽራ “እገሌ እኮ በይህን ያህል መኪና በከዚራ ጥላ ስር ተንፈላሰሰ” ይባልለታል። በአንድ ወቅት ነጂብ ዓብደላ ዓሊ የሚባል የበዴሳ ተወላጅ በአስራ ስድት መኪናዎች በከዚራ ጎዳናዎች ላይ በመንሸራሸሩ እንደ ሪከርድ ሲወራለት ትዝ ይለኛል። (ነጅብ አሁን ሞቷል፤ አላህ ይማረው)።
በሌላ በኩል ጸሀይ በምስራቅ አፍሪቃና በዐረብ ሀገራት ጠንከር ስትል፣ ከጅቡቲ፣ ከሶማሊላንድ (ሀርጌሳ) እና ከየመን ለሚመጡ ጊዜያዊ ተፈናቃዮች የመሸሻ ቦታዎቸው የከዚራ ጥላዎች ናቸው። ለዚህም ነው አንዳንድ ሰዎች ድሬዳዋን “የበረሀ ገነት” እያሉ የሚጠሩት።
******************
በድሬ ዳዋ ከተማ “ገንደ” (በኦሮምኛ “ሰፈር” ማለት ነው) የሚል የመነሻ ቅጥያ እየተጨመረባቸው የሚጠሩ በርካታ ሰፈሮች አሉ። ገንደ ቆሬ፣ ገንደ ጋራ፣ ገንደ ሚስኪን፣ ገንደ ቱሽቱሽ ወዘተ… ጥቂቶቹ ናቸው። “ገንደ ጋራ” በኦሮምኛ “ኮረብታማው ሰፈር” ወይም “በኮረብታ ላይ ያለው ሰፈር” እንደ ማለት ነው። በእርግጥም ሰፈሩ የሚገኘው በኮረብታ ጥግ ነው። “ገንደ ቆሬ” ቃል በቃል “እሾሀማው ሰፈር” ለማለት ቢመስልም አውዳዊ ፍቺው “እሾሃማ ዛፍ ያለበት ሰፈር” የሚል ይሆናል።  እንደነዚህ ዓይነት ስሞች በመላው የኦሮሞ ምድር የተለመዱ በመሆናቸው ጥንታዊነታቸው አያጠራጥርም።
“ገንደ ሚስኪን” እና “ገንደ ቱሽቱሽ” የተሰኙት ስሞች የድሬ ልጆች ፈጠራ ውጤት መሆናቸው በግልጽ ያስታውቃል። “ገንደ ሚስኪን”-የደሃ ሰፈር ማለት ማለት ነው። ስያሜው ለምን እንደወጣለት ባይታወቅም በአንድ ወቅት በልመና የሚተዳደሩ ወገኖች ደሳሳ ጎጆዎችን ከጆንያና ከማዳበሪያ ከረጢት ቀልሰው የኖሩበት ሰፈር ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ። ይሁንና ሰፈሩ በአሁኑ ወቅት “የደሃ ሰፈር” የሚያስብለው አንዳች ገጽታ የለውም።
“ገንደ ቱሽቱሽ” የሚለው ስያሜ በመደበኛ የቃላት አጠቃቀም ውስጥ አይገኝም። በድሬ ልጆች አነጋገር “ቱሽቱሽ” ሲባል በአማርኛ “ዝባዝንኬ” ወይንም ቅራቅምቦ፣ ወይ ደግሞ ኮተት እንደምንለው ነው። ሆኖም ሰፈሩ እና “ኮተት” በምን እንደተገናኙ እስካሁን ድረስ መረዳት አልቻልኩም። (የድሬ ልጆች በዚህ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን በአክብሮት እንጠይቃለን)።
******************
የድሬ ዳዋ የኢኮኖሚ ሞተር የሆነው ሰፈር “መጋላ” ይሰኛል። መጋላ በምስራቅ ኢትዮጵያ በሚነገሩት ቋንቋዎች (አሮምኛ፣ ሶማሊኛ እና ሀረሪ) የገበያ ስፍራ ማለት ነው። ደግሞም “ከተማ” ማለትም ይሆናል። ጥንት አነስተኛ የመነገጃ ስፍራ የነበረው የድሬዳዋው “መጋላ” በአሁኑ ዘመን እጅግ ሰፍቶ የከተማዋን ግማሽ ጠቅልሏል። “መጋላ” ማንኛውም ዓይነት ግብይት የሚካሄድበት ስፍራ ነው። በአጭሩ አዲስ አበባ ሲወሳ “መርካቶ” እንደሚጠቀሰው ሁሉ የድሬዳዋ ስም ከተነሳም “መጋላ” መጠቀሱ አይቀሬ ነው። (የአዲስ አበባው “መርካቶ”ም ልክ እንደ መጋላ “የገበያ ቦታ” ማለት ነው-በጣሊያንኛ)። የአዲስ አበባው መርካቶ “ሸማ ተራ”፣ “ሚስማር ተራ”፣ “ሳጥን ተራ”፣ “ቦምብ ተራ”፣ “በርበሬ ተራ”፣ “ዱባይ ተራ”፣ “ምናለሽ ተራ” የሚሉ ንዑሳን ክፍሎች እንዳሉት ሁሉ የድሬዳዋው መጋላም ቀፊራ፣ ታይዋን፣ አላይበዴ፣ ጫት ተራ፣ ወዘተ… የተሰኙ ክፍሎች አሉት፡፡ ከዚህ በተረፈም “መጋላ” የሚለው ቃል ከመነሻው እየተጨመረባቸው የሚጠሩ በርካታ የግብይት ስፍራዎች አሉት። ከነዚህም መካከል “መጋላ ጉዶ”፣ “መጋላ ሶጊዳ”፣ “መጋላ ጨብጡ” ወዘተ.. የተሰኙት ይጠቀሳሉ።
“መጋላ ጉዶ” ትልቁ ገበያ ማለት ነው። “መጋላ ሶጊዳ” ደግሞ “የጨው ገበያ” ማለት ነው። እነዚህ ስያሜዎች ቀዳሚነትን (መጋላ ጉዶ) እና የግብይት ሸቀጥን (መጋላ ሶጊዳ) ተንተርሰው የተሰጡ በመሆናቸው ከመነሻቸው ህዝባዊ መሆናቸው አያጠያይቅም። በተጨማሪም በሌሎች ከተሞች ተመሳሳይ ስያሜዎች ስላሉ በብዛት የተለመዱ ህዝባዊ ስሞች የመሆናቸው ነገር ጥያቄ የለውም።
“መጋላ ጨብጡ” ግን የድሬ ልጆች ፈጠራ ነው። ከድሬ ልጆች ምትሀታዊ የፈጠራ ጥበብ ነጻ የወጣ የድሬ ዳዋ ክፍል በጭራሽ አይገኝም። “ገንደ” እየተባሉ በሚጠሩት ሰፈሮች ተርታ እነ “ገንደ ቱሽቱሽ” እንዳሉት ሁሉ በ“መጋላ” ተርታ ውስጥም “መጋላ ጨብጡ” አለላችሁ። ስያሜው ቃል በቃል ሲፈታ (በኦሮምኛ) “የስባሪ ገበያ” እንደማለት ነው። ትክክለኛ ፍቺውን የሚያውቁት ግን የድሬ ልጆች ናቸው።
******************
የድሬ ዳዋ ልጆች ብዙ የሚያስደንቁ ነገሮች አሏቸው። በተለይ እኔን የሚያስደንቀኝ ግን የቋንቋ ችሎታቸው ነው። የድሬ ልጅ ሆኖ ሶስት ቋንቋ መናገር የማይችል ምናልባት ከቤት ሳይወጣ ያደገ ልጅ መሆን አለበት። ኦሮምኛ፣ አማርኛና ሶማሊኛ የሁሉም የድሬ ልጆች የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ናቸው ማለት ይቻላል። ዐረብኛ እስከ አሁን ድረስ የከተማዋ የንግድ ቋንቋ ስለሆነ በርካታ የድሬ ልጆች እርሱንም ይጨምራሉ። የኮኔል (ሰባታች) አካባቢ ልጆች በ“ጌይ ሲናን” (ሀረሪ) እንደ ቋንቋው ባለቤቶች ይግባቡበታል። ለገሀር አካባቢ የተወለደ ልጅ ፈረንሳይኛ ይናገራል ብለን በእርግጠኝነት መናገር ቢከብደንም “ቋንቋውን ይሰማል” ብንል ከእውነታው ብዙም አንርቅም።
ብዙ ቋንቋ መናገር ጸጋ ነው። የእውቀት በሮችን ያሰፋል። በችግርም ሆነ በደስታ ጊዜ መድኃኒትነት አለው። ከዚህም በላይ ጨዋታን በእጅጉ ያሳምራል። ድሬ ዳዋ ሄዳችሁ አንድ ጓደኛችሁ ከሚያዘወትረው የበርጫ ጀመዓ ብትሄዱ ወይንም በአንድ ካፍቴሪያ ሰብሰብ ብለው ጭማቂ የሚገባበዙ የድሬ ወጣቶችን ብታስተውሉ በቋንቋ ችሎታቸው ተገርማችሁ “አጃኢብ” ትላላችሁ። በአማርኛ እየተነጋገሩ ቆይተው ወደ ኦሮምኛ ሲዞሩ፣ በቅጽበት ከኦሮምኛ ወደ ዐረብኛ ሲተላለፉ፣ ከአፍታ ቆይታ በኋላ ከዐረብኛ ወደ ሶማሊኛ ሲረማመዱ “ወይኔ ድሬ በተወለድኩ” ያሰኛሉ።
የድሬ ልጆች ፈጣን ናቸው። ከቴክኖሎጂ ትሩፋቶች ጋር በቀላሉ እንደሚዋሀዱት ሁሉ የመነጋገሪያ ዘይቤያቸውንም ለነርሱ እንደሚመች አድርገው ፈጥረውታል። ለምሳሌ ኦሮምኛን የነርሱ መለያ በሆነ ቅላፄ ይነጋገሩበታል። አማርኛውንም እንደዚያው የከተማቸው መለያ በሆነ ስልት ያስኬዱታል። በዚህም የንግግር ቅላጼና ዘዬ የድሬ ልጆችን በቀላሉ መለየት ይቻላል። እስቲ ነገሩን በምሳሌ ላስረዳ!
በድሬ ዳዋ የሚነገረው ኦሮምኛ በመሰረቱ የሀረር ኦሮምኛ ነው። በዚህ የሀረር ኦሮምኛ ዘዬ “አይቼዋለሁ” ለማለት ከፈለጋችሁ “አርጌቲን ጂራ” ትላላችሁ። የድሬ ልጆች ግን “አገሬቲን ጂራ” ይላሉ። በኦሮምኛ “አለፍኩ” ለማለት ካሻችሁ ደግሞ “ደብሬ” ትላላችሁ። የድሬ ልጆች ግን “ደበሬ” ይላሉ። እንደዚሁም በኦሮምኛ “እኔ ብቻ” ለማለት ከፈለግን “አነ ቆፋ” እንላለን። የድሬ ልጆች ግን “አነ ቁልሊ” ሲሉ ትሰማላችሁ። በኦሮምኛ “ቀጣፊ” (ውሸታም) ለማለት ከፈለግን “ኪጂባ” ወይንም “ሶባ/ሶብዱ” እንላለን። የድሬ ልጆች እንዲህ ዓይነቱን ሰው “ፈረዳ” ይሉታል።
ከሁሉም የሚያስገርመኝ ግን የድሬ ልጆች ቃላትና ሀረጋትን የመፍጠር ችሎታ ነው።  ከዚህ ቀደም እንደጠቀስኩት “ቀሽት”/“ቀሽቲ” የነርሱ የፈጠራ ውጤት ነው። በአንድ ወቅት ደግሞ “ኡላ” የሚል ቃል አምጥተውብን መነጋገሪያ ሆኖብን ነበር። “ኡላ” በመደበኛ የኦሮምኛ ፍቺው “የማር ቆራጭ” ወይም “ማር ሲቆረጥ የንብ ቆፎዎችን በጭስ የሚያጥን ሰው” ማለት ነው። በድሬ ልጆች መዝገበ ቃላት ውስጥ ያለው ፍቺ ግን “የለየለት አጭበርባሪ” ወይንም “አወናባጅ” የሚል ነው።
የድሬ ልጆች እውነታቸውን ነው። ማር ቆራጩ “ኡላ” ፊቱን ሸፋፍኖ በጭሳጭስ ቀፎዎችን እያጠነ ንቦች አመቱን በሙሉ የለፉበትን ማር “እንደሚዘርፈው” ሁሉ አጭበርባሪው “ኡላ”ም ሰዎችን በውሸት እያጠነ ገንዘብና ንብረት ይመዘብራል። በውሸት ቀረርቶ የሚያቅራራ፣ የበሬ ወለደ ወሬ የሚነዛና በሌለው ነገር የሚኩራራ ሰው በድሬ ልጆች ቋንቋ “ቦንባ” ይሰኛል።(“ቦንባ” የውሀ ቧንቧ ማለት ነው።)
በአማርኛ “የቀበሮ ባህታዊ” የሚባለው ሰው በድሬ ልጆች አነጋገር “ሀቱ ሰላቱ” በሚል ይጠራል (ቃል በቃል “የሚሰግድ ሌባ” እንደማለት ነው)። ወደ አንድ ሆቴል ገብታችሁ፣ ወይንም ከመደብር እቃ ወስዳችሁ ያልተጠበቀ ዓይነት ሂሳብ እንድትከፍሉ ስትጠየቁም ኩነቱን “ሂሳበ ፊኒና” (የሞቀና የሚፋጅ ሂሳብ) በማለት ትገልፁታላችሁ። የአስተሳሰብ አድማሱ የተዛነፈ ወይም አዕምሮው የተቃወሰን ሰው በድሬ ልጆች ቋንቋ “ቀልቢን ኢሳ ዹፍቴ” (ልቡ ፈስቷል) በማለት እንገልጸዋለን። “ሰውየው እብደት ጀምሮታልና ቶሎ ይታከም” እንደማለትም ይመስላል።
ከዚህም ሌላ ከዐረብኛ የተወረሱ በርካታ ቃላት በድሬ ልጆች ማሻሻያ እየተደረገባቸው በኦሮምኛና በአማርኛ መደበኛ ንግግሮች ውስጥ ገብተዋል። ለምሳሌ ያህልም “ፈታላ” (አቃጣሪ)፣ ፈዱሊ (“በማይመለከተው የሚገባ” ወይንም “የእርጎ ዝንብ”)፣ ኢያለ-ሱቅ (ዱርዬ) የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል።
እነዚህ የጠቀስኳቸው በድሬ ልጆች የተፈጠሩት ቃላትና ሀረጎች በአሁኑ ዘመን በሌሎችም የሀረርጌ ክልሎች ተወርሰው በስፋት ያገለግላሉ። እንዲህም ሆኖ ግን የድሬ ልጅ በኦሮምኛ ሲነጋገር በቅላጼው በሌላው የሀረርጌ ክፍል ከተወለደ ወጣት በእጅጉ ይለያል። ለምሳሌ እኔ ገለምሶ የተወለድኩት አፈንዲ (ጸሀፊው) በኦሮምኛ ሳወራ እንደ ድሬ ልጆች “አገሬቲን ጂራ”፣ “አነ ቁልሊ”፣ “ፈረዳ”… አልልም። አስመስላለሁ ብል እንኳ በጭራሽ አልችልበትም (በነገራችን ላይ ከሀረርጌ የተገኘነው ሰዎች ድሬ ዳዋ ሳይወለዱ “የድሬ ልጅ ነኝ” የሚሉ ቀጣፊዎችን በቀላሉ የምንይዝበት ፎርሙላ ሰውዬው በዚህ የድሬ ልጆች የንግግር ቅላጼ የሚነጋገር መሆኑን በደንብ ማስተዋል ነው)።
የድሬ ልጆች ተረትና ምሳሌ በመፍጠር ጭምር የተካኑ ናቸው። ከነዚህም ውስጥ ጎላ ብሎ የሚጠቀሰው በአንድ ሰሞን በድፍን ሀረርጌ መነጋገሪያ የነበረው “ኸበጃን ኩንታላ አብባን ቁምጣቲ ዴቢሳ” (“Khabajaan kuntaala, Abbaan qumxatti deebisa”) የሚለው ምሳሌ ነው። ትርጉሙ “ክብር ኩንታል ነው፣ ባለቤቱ ግን ወደ ሀምሳ ኪሎ ያቃልለዋል” የሚል ነው። ይመቻል አይደል?
******************
ድሬ ዳዋን በወፍ በረርም ቢሆን አይተናታል። ስለርሷ የተጨዋወትነውን ሁሉ የበረካ ያድርግልን። ታዲያ ወጋችንን የምናሳርገው ከባቡር ትራንስፖርት ጋር በእጅጉ የተቆራኙትን የገለሀር ልጆች የቋንቋ አጠቃቀምና ታሪካዊውን የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት በመጠኑ በማስቃኘት ይሆናል።
ከባቡር መስመር በሚርቁ አካባቢዎች ለተወለድን ሰዎች ባቡር ሁሉ አንድ አይነት ሊመስለን ይችላል። የለገሀር ልጆች ግን ባቡሮቹን በሚሰጡት አገልግሎትና በምቾታቸው በመፈረጅ በልዩ ልዩ ስሞች ይጠሯቸዋል። ከነዚህም ጥቂቶቹን ላስተዋውቃችሁ።
“ኦቶራይ” የብዙሁኑ ህዝብ የመጓጓዣ ባቡር ነው። አብዛኛው የአውቶቡስ ተጠቃሚ በካሚዮንና በካቻማሊ ወደ ክፍለ ሀገር እንደሚጓዘው ሁሉ በባቡር የሚገለገሉ ሰዎችም ለጉዞ የሚያዘወትሩት “ኦቶራይ”ን ነው። ይሁን እንጂ “ኦቶራይ” እንደ አውቶቡስ አንድ ወጥ አይደለም። በውስጡ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ማእረጎች አሉት። በአንደኛው ማዕረግ የተሳፈረ ሰው ሲፈልግ በሶፋ ላይ ለሽ ብሎ እየተጋደመ፣ ሲያሻው ብድግ ብሎ ውጪውን እያየ ይጓዛል። የሁለተኛው ማዕረግ ተሳፋሪዎች እንደ አንደኛ ማእረግ ተሳፋሪዎች በሶፋ ላይ የሚያንፈላስስ ምቾች ባያገኙም ለመቀመጫ የሚሆን ወንበር አያጡም። ሶስተኛው ማእረግ ግን በሁለመናው ከአዲስ አበባው የከተማ አውቶቡስ ጋር ይመሳሰላል። በቅድሚያ ወደ ፉርጎው ከገቡ ጥቂት ተሳፋሪዎች በስተቀር አብዛኛው ሰው በቁሙ ነው ረጅም ርቀት የሚጓዘው። በበረሃ ወበቅ መተፋፈግ፣ በትንፋሽ እጦት መሰቃየት፣ በሰዎች እርግጫና ግልምጫ መንጫረር…ወዘተ የሶስተኛው ማዕረግ የዘወትር ትይንቶች ናቸው።
ከ“ኦቶራይ” ትንሽ አነስ ያለው ባቡር ደግሞ “ዴዴ” ይሰኛል። ሁለቱ የባቡር ዓይነቶች የሚለያዩት በባቡሩ ላይ በተቀጠሉት ተጎታቾች (ፉርጎዎች) ብዛት ነው፤ “ኦቶራይ” በፉርጎ ብዛት “ከዴዴ” ይበልጣል። በዚህም የተነሳ አነስተኛ ፉርጎዎችን በሚጎትተው “ዴዴ” የማዕረግ ልዩነት ላይኖር ይችላል። ሲፈልግ ባለሁለተኛ ማዕረግ ፉርጎዎችን ብቻ ይጭናል። ሲያሻው ደግሞ የሶስተኛ ማዕረግ ፉርጎዎችን ብቻ ደርድሮ ሊመጣ ይችላል።
ከ“ዴዴ” ጋር የሚመሳሰል ሌላኛው የባቡር ዓይነት “ሀሰን ጆግ” ይሰኛል። ይሁንና እስከ አሁን ድረስ ባላወቅኩት ምክንያት የ“ሀሰን ጆግ” የጉዞ መስመር ከድሬ ዳዋ አይሻገርም። ዘወትር የሚሽከረከረው በድሬዳዋ እና በጅቡቲ መካከል ነው። ምናልባት ረጅም ርቀት ከተጓዘ ሞተሩ ስለሚግል ይሆን? የድሬ ልጆች የሚሰጡንን ምላሽ እንጠብቃለን።
እያንዳንዱ ተሳፋሪ ከላይ በተጠቀሱት ባቡሮች ሲሳፈር የሚከፍለው ክፍያ “ኖሊ” ይባላል። “ኖሊ” ከህጻናት በስተቀር ሁሉንም ተሳፋሪ ይመለከታል። ተሳፋሪው “ኖሊ” የከፈለበትን ቲኬት እንዲያሳይ በባቡሩ ተቆጣጣሪ ሲጠየቅ ይሁንታውን መግለጽ አለበት። “ኖሊ” ሳይከፍል የተሳፈረ ሰው ከተገኘ ግን ወዮለት! የተቆጣጣሪው እንግልት ብቻ ሳይሆን የተሳፋሪው ዱላም ሊያርፍበት ይችላል። ምክንያቱ ደግሞ ምን መሰላችሁ? በባቡር ላይ የሚተራመሱ ሌቦች በባህሪያቸው “ኖሊ” መክፈል አይፈልጉም። ዘወትር ከፉርጎ ፉርጎ እየዘለሉ ለማምለጥ ነው የሚፈልጉት። ስለዚህ “ኖሊ” አልከፍለም የሚሉ ሰዎችን ተሳፋሪው ሊሰርቁት የገቡ ሌቦች አድርጎ ነው የሚመለከታቸው። እንደነዚህ አይነት ሰዎች ከተገኙ ተቆጣጣሪው ይዛቸውና በሚቀጥለው የባቡር ጣቢያ ላይ በማስወረድ ለፖሊሶች ያስረክባቸዋል። ይህ የባቡር ላይ ተቆጣጣሪ በገለሀር ልጆች ቋንቋ “ሸፍትራን” ተብሎ ይጠራል።
“ኖሊ” ሳይከፍሉ በባቡር ለመጓዝ የሚፈለጉ ሰዎች ለጉዞ የሚተማመኑበት ሌላ የባቡር ዓይነት አለ። ሆኖም የዚህኛው ባቡር መደበኛ ስራ የደረቅ የጭነት አገልግሎት መስጠት እንጂ ሰዎችን ማጓጓዝ አይደለም። የዚህ የባቡር ዓይነት መጠሪያ ስም “ፋልቶ” ይሰኛል። “ፋልቶ” በርካታ ተጎታች ፉርጎዎች አሉት። ይህ ባቡር ሲፈልግ በሁሉም ፉርጎዎች አንድ ዐይነት እቃ (ጨርቅ፣ ስኳር፣ ሩዝ፣ ወዘተ) ጭኖ ይከንፋል። ሲያሻው ደግሞ በአንዱ ፉርጎ ፍየሎች፣ በሌላኛው ፉርጎ ዱቄት፣ በሶስተኛው ፉርጎ ቡና፣ በሌሎችም ፉርጎዎች ሌሎች ሸቀጦች እየጫነ ይጓዛል። ከላይ እንደጠቀስኩት “ኖሊ” ለመክፈል የማይፈልጉ ሰዎች ወይንም ቤሳቤስቲን የሌላቸው ልጆች “ፋልቶ”ን የሚያዩት እንደ ነፍሳቸው ነው። በውንብድናና በሌብነት ሙያ ለተሰማሩ ዜጎች ደግሞ “ፋልቶ” የዘወትር ደንበኛቸው ነው። እነዚህ ሁሉ ወገኖች ፋልቶን የሚፈልጉበት ምክንያት በሌሎች ባቡሮች ላይ ቲኬት አልያዝክም ብሎ ማጅራታቸውን የሚይዘው “ሸፍተራን” እዚህ ስለሌለ ነው።
ታዲያ በፋልቶ መጓዝ የሚፈለጉ ሰዎች የሚሳፈሩት በባቡሩ ውስጥ እንዳይመስላችሁ። የባቡሩ የውስጠኛው ክፍል የእቃ መጫኛ ነው። ተጓዦቹ የሚሳፈሩት በባቡሩ ጎንና በጣሪያው ላይ ነው። ስለዚህ በፋልቶ ለመጓዝ የሚሻ ሰው በባቡሩ ላይ በቅልጥፍና የሚሳፈርበትንና የሚወርድበትን ጥበብ በደንብ ማወቅ አለበት። ይህም “ሀርፋ” ይሰኛል። “ሀርፋ” ባቡሩ ከጣቢያው ንቅናቄ ሲጀምር ቀልጠፍ ብሎ መውጣትን፣ በባቡሩ ጣሪያና በጎኖቹ ላይ ሚዛን ሳይስቱ መቀመጥን፣ በአንደኛው ፉርጉ የመቀመጫ ቦታ ከጠፋ ወደሌሎች ፉርጎዎች እየተፈናጠሩ መቀመጫ መፈለግን፣ ባቡሩ በኮርባ ላይ ሲታጠፍ ሰውነትን መቆጣጠርንና ባቡሩ በሚቀጥለው ጣቢያ ከመቆሙ በፊት ፈንጠር ብሎ መውረድን ያካትታል። እነዚህን የ“ሀርፋ” ስልቶች ጠንቅቆ ያላወቀ ሰው የአካል ጉዳትና የሞት አደጋ ሊደርስበት ይችላል። እንዲህ ዓይነት አደጋ የደረሰበትን ሰው
የለገሀር ልጆች “ኘም ሆነ” ይሉታል (በኦሮምኛ “ተበላ” ለማለት ነው)። በባቡር አደጋ “ኘም ለመሆን” የማይፈልግ ሰው ሁለት እድሎች ብቻ  አሉት። በስነ-ስርዓቱ “ኖሊ” ከፍሎ መሄድ፣ ወይንም በእግሩ መጓዝ። የለገሀር ልጆች የኋላኛው ምርጫ ሲሰጡን “በለፎ ግባ” ይሉናል። “በእግርህ ተጓዝ” ማለታቸው ነው። (“ለፎ” በኦሮምኛ “እግረኛ” ወይንም “እግረኛ ሰራዊት” እንደማለት ነው)።
******************
ከላይ እንደገለጽኩት በስርቆት የተሰማሩ ሰዎችም ባቡርን ያዘወትራሉ። በሌሎች ቦታዎች እንደለተመደው ሁሉ በባቡር ላይ ስርቆት የተሰማሩ ሌቦችም ሌሎችን ለመሸወድ የሚጠቀሙባቸው ኮድ መሰል ቃላት አሏቸው። ለምሳሌ ሌቦቹ “ይህ ሰው ዩያ ነው” ካሉ “ከባላገር የመጣ ሰው ነው፣ ለስርቆት ያመቻል” ማለታቸው ነው። “ፎቄ ግባ” ሲባል ደግሞ “የላይኛውን ኪስ (የሸሚዝ ኪስ) በርብር”  ማለት ነው። “ቀስቴ ግባ” ከተባለም “የሱሪ ኪስ ግባ” ወይም “የሱሪ ኪስ በርብር” ማለት ነው። ሌቦቹ ገንዘብ የሚቆጥሩትም “ዴች” (አንድ ብር)፣ ቢጫ (አምስት ብር)፣ ዲናሬ (አስር ብር)፣ “ሴካ” (ሀምሳ ብር)፣ “ቼንቶ” (መቶ ብር) በማለት ነው።
                              ******************
ድሬ ዳዋ በኔ ብዕር ይህችን ትመስላለች። የድሬ ልጆች በጎደለው ላይ እንደሚሞሉበት በመተማመን የራሴን ድርሻ በዚሁ አበቃለሁ።
አፈንዲ ሙተቂ
መጋቢት 6/2005 ዓ.ል
ሀረር-ምስራቅ ኢትዮጵያ
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on March 22, 2013
  • By:
  • Last Modified: March 22, 2013 @ 3:54 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar