www.maledatimes.com ኢትዮጵያዊ መልኮች በአሜሪካ Written by ጽዮን ግርማ tsiongir@gmail.com - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ኢትዮጵያዊ መልኮች በአሜሪካ Written by ጽዮን ግርማ tsiongir@gmail.com

By   /   March 24, 2013  /   Comments Off on ኢትዮጵያዊ መልኮች በአሜሪካ Written by ጽዮን ግርማ tsiongir@gmail.com

    Print       Email
0 0
Read Time:32 Minute, 8 Second

መልክአ ኢትዮጵያ – ፰

የእኛዋ ኢትዮጵያ አንድ ለእናቱዎች ከማንም የሚገጥሙ አይደሉምና አሜሪካ እንደ አገራችን ብቸኛ አየር መንገድ ሊኖራት ይችላል ተብሎ ባይገመትም በቅርበት ሲታዩ ብዛታቸውና የአገልግሎታቸው ስፋት ከግምትም በላይ ነው፡፡ በአሜሪካ መንግሥት ሥር የሚገኘው ‹‹ኤድዋርዶ ሙሮው›› በተባለ ታዋቂ ጋዜጠኛ ስም የተሠየመው ተቋም ከመላው ዓለም ለተውጣጡ ጋዜጠኞች በየዓመቱ የሚያዘጋጀው የጉብኝት ፕሮግራም ከሰጠኝ ዕድሎች አንዱ፣ በተለያዩ የአሜሪካን አየር መንገድ ድርጅቶች አውሮፕላን መብረርና በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ አየር መንገዶች መገልገል ነው፡፡ ሁሉም አየር መንገዶች እጅግ ዘመናዊና ሰፊ ናቸው፡፡ በሁሉም በርካታ መንገደኞች ይስተናገዳሉ፡፡

በአየር መንገዱ ሠራተኞች አክብሮትና ቀልጣፋ አሠራር ቅናት ቢጤ ተሰምቶኛል፡፡ በኢትዮጵያ የቦሌው ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተለይ ደግሞ በአገር ውስጥ በረራ ተርሚናሎች የሚፈጠረው ምሬት ፈጽሞ አላጋጠመኝም፡፡ በአሜሪካኖቹ አየር መንገዶች ወደ አውሮፕላኑ ሲገባና ከአውሮፕላኑ ሲወጣ በእኛ ዘንድ ያልተለመደውና እንደ ቀላል ነገር የሚታየው የተራ አጠባበቅ ሥነ ሥርዐት ሰላምን የሚሰጥ ነው፡፡ ከፊተኛው መቀመጫ ያለው ሰው የእጅ ቦርሳውን ከአውሮፕላኑ የሻንጣ ማስቀመጫ ውስጥ አውጥቶ ይዞ እስኪወጣ ከኋላ ያለው ሰው የእጅ ቦርሳ ባይኖረው እንኳን ቆሞ ይጠብቀዋል እንጂ አልፎ አይሄድም ወይም አይጋፋውም፡፡

ይህ ሥርዐት እንዲከበር የሚናገርና የሚያሳስብ አንድም አካል ባይኖርም በሁሉም በረራዎች ላይ ሳይዛነፍ የሚከወን ተግባር እንደኾነ ታዝቤያለኹ፡፡ ከትዝብቴ ከመማሬ በፊት እንደለመድኹት አፈፍ ብዬ ተነሥቼ ለመጋፋት ያደረግኹት ሙከራ የብዙ ዐይኖች ሽንቆጣ አድርሶብኛል፤ ሳልደግመውም ቀርቼያለኹ፡፡ በአየር መንገዱ ውስጥ የሚደረገው የከረረ ፍተሻ ግን አይጣል ነው፡፡ ፍተሻው በጣም መጥበቅ የጀመረው ከኒውዮርኩ የሽብር ጥቃት በኋላ መኾኑን አገር ዐዋቂዎቹ አጫውተውኛል፡፡ የአሜሪካን አገር የአውሮፕላን አገልግሎት የከተማ ታክሲ ያህል ነው፡፡ በመጠበቂያ ቦታዎቹ ላይ ተቀምጦ መጪ ሂያጁን አውሮፕላን በመስታወቱ ውስጥ ለሚመለከት ግራ ያጋባሉ፡፡ በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት አውሮፕላኖቹ ሲያርፉና ሲነሡ በነፍስ አድን ሥራ ላይ ተሠማርተው ምግብና ሰው የሚያጓጉዙ እንጂ መንገደኞችን የሚያመላልሱ አይመስሉም፡፡ ብዛታቸው የፈጠረው ፉክክር በሚሰጠው ምርጫ መንገደኛው የፈለገውን አማርጦ አገልግሎት ማግኘት ይችላል፡፡

አንድ መንገደኛ ከተነሣበት ከተማ በአንድ ቀጥታ በረራ ብቻ መሄድ ከፈለገ ጭማሪ ከፍሎ መሄድ በመሄድ ጊዜውንም ድካሙንም የመቆጠብ አማራጭ ያገኛል፡፡ በሁለት ወይም በሦስት መቆሚያዎች እያረፈ በሚሄድ አውሮፕላን መጠቀም የፈለገ ከዕጥፍ በላይ ቅናሽ ሊያገኝ ይችላል፡፡ ለአገር ውስጥ በረራ በርከት ያሉ ድርጅቶች ከትኬት ዋጋው በተጨማሪ በማለፊያ ሰነድ መውሰጃው ላይ ለአንድ ሻንጣ 25 ዶላር ሲያስከፍሉ አንዳንዶቹ ‹‹ሁለት ሻንጣ በነጻ እናጓጉዛለን›› በማለት ደንበኛ ለመሳብ ይሞክራሉ፡፡ የአገር ውስጥ በረራ የቱንም ያህል ሰዓት ቢወስድ÷ አውሮፕላኑ ውስጥ ከለስላሳና ትኩስ መጠጥ ውጭ ምንም ዐይነት የምግብና የአልኮል መጠጥ አገልግሎት በነጻ ማግኘት አይቻልም፡፡ አንዳንዶቹ እንደ ኩኪስና ቀለል ያሉ ሳንድዊቾችን በነጻ በማቅረብ ደንበኛ ለመሳብ ይጠቀሙበታል፡፡

ከዚህ ውጭ በሁሉም አየር መንገዶች ውስጥ የመብላትና መጠጣት ፍላጎትን ከሚያነሣሣው የአሠራር ውበታቸው ጋራ በአስገራሚ ፍጥነትና ቅልጥፍና የምግብና መጠጥ አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ መሸጫዎች መዓልት ከሌሊት ክፍት ኾነው አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ከእነዚህ ቦታዎች ምግብና መጠጥ ይዞ ወደ አውሮፕላን መግባት ክልክል አይደለም፡፡ አየር መንገዶቹን አንድ ትልቅ የገበያ ሥፍራ የሚያስመስሉ የገበያ ቦታዎችም በትጋት ይነግዳሉ፡፡ መስተንግዶዎቹና የዕቃዎቹ ውበት የመንገደኛውን ኪስ ለማራገፍ ታስበው የተዘጋጁ ይመስላሉ፡፡ አየር መንገዶቹ የመንገደኞችን ፍላጎት ለማሟላት በጥንቃቄ የተዘጋጁ በመኾናቸው በአንዳንድ በረራዎች ከአንዱ አውሮፕላን ወርዶ ወደ አንደኛው ለመሳፈር የሚኖረው ረዘም ያለ ጊዜ አሰልቺ አልኾነብኝም፡፡ ከንግድ ቦታዎቹ በተጨማሪ መጸዳጃና መታጠቢያ ቤት፣ መተኛ፣ ማንበቢያ፣ ኢንተርኔት መጠቀሚያ፣ ላፕቶፕ ኮምፒዩተሮችን የሚጠቀሙበት መቀመጫና ሶኬት፣ ማጨሻ ወዘተ ለመሳሰሉት አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ ቦታ ተመቻችቶላቸዋል፡፡ እኔ በተመለከትኋቸው 14 የአሜሪካን ከተሞች አየር መንገዶች ውስጥ ከፍሎሪዳው ‹‹ፔንሳኮላ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ››ና የሬኖ -ኔቫዳው ‹‹ሬኖ-ታሆ አየር መንገድ›› በቀር በጽዳትና በልዩ ልዩ የአየር መንገዱ ጥቃቅን የአገልግሎት መስጫ ቦታዎች ጀምሮ ከሚሠሩት ሠራተኞች አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ኢትዮጵያውያን ኾነው አግኝቻቸዋለኹ፡፡ በተለይ በአትላንታው የዓለም አቀፍ በረራ ተርሚናል የቀረጥ ነጻ መሸጫ ሱቆች ውስጥ ካሉት ከ15 በላይ የሽያጭ ሠራተኞች መካከል ከኢትዮጵያውያን ውጭ ሌሎችን ማየቴን አላስታውስም፡፡ ካረንና ጆን በተባሉ ትጉህ አሜሪካውያን የቡድን መሪዎቻችን አስተናባሪነት የቡድኑ አባላት እንዳንጠፋፋ እጅብ ብለን ስናልፍ የተመለከቱን ኢትዮጵያውያን ተንጠራርተውም ቢኾን እኔንና የቡድኑ አባል የኾነን ሌላ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ሰላምታ ይሰጡናል፡፡

ለማነጋገር ያመቻቸው ደግሞ ከቡና ግብዣ ጀምሮ በእንክብካቤ ያስተናግዱናል፡፡ ቀረብ ብሎ የማውራት ዕድሉን አግኝቼ ወደ አሜሪካ የመጣኹበትን ምክንያት ጠይቀውኝ በዝርዝር የነገርኋቸው የአገሬ ልጆች ያየኁባቸው ደስታ ትሕትናም ክብርም ኾኖኛል፡፡ በአየር መንገዶቹ ሁሉ ያገኘኋቸው ኢትዮጵውያን ይሰጡኝ የነበረው ክብካቤ የምረሳው አይደለም፡፡ *************** በትልቅነታቸው ከሚነገርላቸው የአሜሪካን አየር መንገዶች አንዱ የኾነው የቺካጎው ‹‹ኦሄር ዓለም አቀፍ አየር መንገድ››ን መጀመሪያ ያየኁት ወደ ከተማው ከመሄዴ በፊት ነበር፡፡ ዋሽንግተን ከሚገኘው ዱላስ አየር መንገድ ወደ ፊኒክስ ስናመራ በተያዘልን ፕሮግራም መሠረት በኦሄር አየር መንገድ የሁለት ሰዓት ቆይታ ነበረን፡፡ በአየር መንገዱ ውስጥ ሠራተኛ ከኾነችው የጓደኛዬ እኅት ዝናሽ ጋራ በስልክ በነበረን ጭውውት፣ አየር መንገዱ ውስጥ እንደምትሠራ ነግራኝ ልታገኘኝና በዚያውም ለአክስቷ ዶላሮችን እንዳደርስላት ተነጋግረን ነበር የተቃጠርነው፡፡ እንደ እኔ ትዝብት በአሜሪካ ያገኘኋቸውን ኢትዮጵያውያን ሁሉ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር ሁሉም ያገኟትን ነገር ቋጥረው ለቤተሰቦቻቸው ለመላክ ያላቸው ከፍተኛ ልምድና ዝንባሌ ነው፡፡ የቺካጎው ኦሄር አየር መንገድ ስንደርስ በተሰጠን የመግቢያ ቁጥር አቅራቢያ ኾኜ የጓደኛዬን እኅት ዝናሽን መጠበቅ ጀመርኹ፡፡ ብዙም ሳታስጠብቀኝ በነገርኋት መሠረት ካለኁበት ደረሰች፡፡

ዞር ዞር ብለን ትኩስ ነገር ይዘን ዐረፍ አልንና ወግ ጀመርን፡፡ ድሬዳዋ የተወለደችው ዝናሽ ጌታቸው፣ ከአገር ከወጣች 11 ዓመት ኾኗታል፡፡ ሦስቱ ዓመት የስደት ዘመኗ ያለፈው ግን በኬንያ ነበር፡፡ በአንድ የኦሮሞ ርዳታ ድርጅት ውስጥ በሥራ አስኪያጅነት ሲሠሩ የነበሩት አባቷ ከኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦነግ) ጋራ ይሠራሉ በሚል በደረሰባቸው ተደጋጋሚ እስር ምክንያት እሷንና አንድ ወንድ ልጃቸውን ይዘው ወደ ኬንያ ይሰደዳሉ፡፡ ባለቤታቸው አራት ሴትና አንድ ወንድ ልጃቸውን ይዘው ቤታቸውን ሸጠው አዲስ አበባ ኪራይ ቤት ይገባሉ፡፡ እነ ዝናሽ ሦስት የመከራ ዓመታትን በኬንያ ሲያሳልፉ ቀሪዎቹ ቤተሰቦች ደግሞ በአዲስ አበባ ችግርና መከራ ይፈራረቅባቸዋል፡፡ የቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ ገና በ12 ዓመቷ ሕይወቷ ያለፈው በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ እነዝናሽ ተሳክቶላቸው አሜሪካ በገቡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በአይ.ኦ.ኤም አማካይነት ከቤተሰቦቻቸው ጋራ ይገናኛሉ፡፡

ቤተሰቡ ኑሮውን በሲያትል አድርጎ ሁሉም ወደ ትምህርት ቤት ሲያመሩ ቀድሞም የትምህርት ነገር የማይኾንላት የቤተሰቡ ታላቅ ልጅ ዝናሽ፣ በወቅቱ አዲስ አበባ ያሉትን ቤተሰቦቿን ማገዝ ስለነበረባትም ‹‹በዎል ማርት›› ውስጥ በሽያጭ ሠራተኝነት ትቀጠራለች፡፡ ከነገረችኝ ውስጥ በጣም ያስገረመኝ የእኔን ጓደኛ ጨምሮ አምስቱም ልጆች የተማሩትና እየተማሩ ያሉት የጤና ባለሞያነት ነው፡፡ ስለሁሉም ሞያ ተራ በተራ ስጠይቃት÷ ‹‹እርሷ የጥርስ ነርስ ናት፤›› ‹‹እርሱ የዐይን ነው፤›› ትለኛለች፡፡ ሁሉም ትምህርት ለመቀጠል ሲወስኑ ከቀደምቱ ያገኙት ምክር ‹‹ነርሲንግ ያበላል›› የሚል በመኾኑ ቤታቸውን የነርሶች ማዕከል አስመስለውታል፡፡ ዝናሽ ግን ‹‹ተምሮም ያው ለገንዘብ ነው፤›› በሚል ወደ ሥራው ታመዝናለች፡፡ ሰባት ዓመት ሙሉ ከአንዱ ሥራ ወደ ሌላው ስትቀያይር፣ ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው ከተማ ስትዛወር ቤተሰቡ ከሚገኝበት ከተማ ርቃ አሁን በቺካጎ ትዳር መሥርታ የአንድ ልጅ እናት ኾና ነበር ያገኘኋት፡፡ ከዝናሽ ጋራ ወግ ይዘን ሰዓቱ መሄዱ ሳይታወቀን ብዙ ተጨዋወትን፡፡ ሌሎች እኅቶቿ እንዳደረጉት በወቅቱ ከቤተሰቡ ጋራ በአንድ ላይ ተረዳድታ አለመማሯ ቆጭቷታል፡፡

አንድ ሰው አሜሪካ በገባ የመጀመሪያ ዓመት ጨክኖ ትምህርት ካልጀመረ እየቆየ ሲሄድ ፍላጎቱ ከትምህርት እየራቀ እንደሚሄድ በብዙዎች አኗኗር ታይቷል፡፡ ዝናሽ ከዚህ በኋላ የመማር ፍላጎቷ የተሟጠጠ ይመስላል፤ ልጅ ከተወለደ በኋላ ደግሞ የበለጠ ከባድ ይኾናል፡፡ ዝናሽ ከአዲስ አበባ ስትወጣ የቋንቋ ችግር ይገጥመኛል የሚል ስጋት አልነበራትም፡፡ ናይሮቢ – ኬንያም በነበሩበት ወቅት አብዛኛውን ጊዜ ያሳልፉ የነበረው ከኢትዮጵያውን ጋራ በመኾኑ አልፎ አልፎ ከፖሊስ ጋራ ፊት ለፊት ካልተገጣጠሙ በቀር በእንግሊዝኛ ለመግባባት ሞክራ አታውቅም፡፡ እርሱም ቢኾን ጉቦ እስከ መስጠት ባለው ሂደት የሚደረግ መግባባት እንጂ ብዙም የጠለቀ አልነበረም፡፡ አሜሪካ እስክትገባ በውስጧ በእንግሊዝኛ መግባባት ያዳግተኛል ብላ አስባ አታውቅም ነበር፡፡ የቋንቋው እጥረቷ አሁንም ሙሉ ለሙሉ ባይቀረፍም ተቸግራበት እንደነበር አጫወተችኝ፡፡ ‹‹ቋንቋውን እንደማልችል የገባኝ ሥራ ስጀምር ነው፡፡ በወቅቱ እኔ አዲስ ቅጥር ስለነበርኁ ከእኔ ጋራ አንድ ዓይነት የሥራ መደብ የነበራት አንዲት ክፉ ጥቁር አሜሪካዊት ሥራውን ወደኔ ትገፋው ነበር፡፡

ሥራው ደንበኞች ለክተው የተዉትን ልብስ እየሰበሰቡ መልሶ መስቀልና መጸዳጃ ቤቱን ማጽዳት ነበር፡፡ አልሠራም ስላት ትጣላኛለች፤ አለቃችን ጋራ ስንቀርብ እርሷ ውሸትም እየጨመረች በደንብ ታስረዳታለች፡፡ እኔ በምኔ ላስረዳ፤ በቃ እንባ ይቀድመኛል፡፡ በተለይ ኬንያ የተሠቃየነውን ሳስታውስ እዛ ኾኜ ሳስባት የነበረችውን አሜሪካ አጣትና ‹በቃ ለዚሁ ነው› እላለኹ፡፡›› አለችኝ፡፡ ዝናሽ አንዱን ሥራ ለምዳው ስታበቃ ሙዝየም ውስጥ በጽዳት ሠራተኝነት ሌላ ሥራ ስትሠራ እንደነበር አጫወተችኝ፡፡ ሁለት ሥራ መሥራት ደግሞ ኬንያ ከለመደችው እንቅልፍ ጋራ ተጋጭቶ አበሳዋን አሳያት፡፡ የሰዓት መቀስቀሻ ደወል ድምፅ ያን ጊዜ እንደጠላችው ነው፡፡ ሙዝየሙ ውስጥ ስትሠራ ቅዳሜና እሑድ የሚመጡት አብዛኞቹ ጎብኚዎች ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ሥራው ወለሉን ከሥር ከሥር መጥረግና መጸዳጃ ቤቱን ማጽዳት ነበር፡፡ አንድ ቀን በመጸዳጃ ቤቱ ማረፊያ ክፍል ቆማ በግምት 16 ዓመት የሚኾናት ልጅ ከጓደኞቿ ጋራ መጸዳጃ ቤት ትገባና ቀድማ ወጥታ እጇን ትተጣጠባለች፡፡ ዝናሽ ልጅቷን ስታያት ወደ ፊት መኾን የሚገባው የልብሷ ገመድ ወደ ኋላ ዞሮ ተመልሶ ቀሚሷ ውስጥ ገብቷል፡፡ ልጅቷ ገመዱን እንድታወጣው በቃል መንገር ስለከበዳት በቅንነት ገመዱን ለማውጣት እጇን ትሰዳለች፡፡ ልጅቷ እጇን አፈፍ ታደርግና እሪ ትላለች፡፡ የልጅቷ ጓደኞች ከውስጥ ከወጡም በኋላ ልጅቷ እሪታዋን ትቀጥላለች፡፡ ዝናሽ እንግሊዝኛዋን እየሰባበረች ለማስረዳት ብትሞክርም ማን ይስማት፡፡

ጭራሽ ልጆቹ ወደ ውጭ ወጥተው አለቃዋን ይዘው ይመጣሉ፡፡ ለአለቅዬው በምን ቋንቋ ታስረዳው፤ በኋላ እዚያው ቤት በሓላፊነት ቦታ የሚሠራ የአገሯ ሰው ተጠርቶ እንዲህ ያለውን ርዳታ በቅንነት መስጠት የአገር ባህል መኾኑ ተነግሮላት በይቅርታ ታለፈች፡፡ ‹‹ቋንቋ ወሳኝ ነው፡፡ እኛ ከአገር ስንወጣ ምን ሊገጥመን እንደሚችል አስበን አንወጣም፡፡ እኔ አሜሪካ ስገባ ቀድሜ ዐውቀዋለኹ ብዬ ያልኁትን ቋንቋ በአጭር ጊዜ አሻሽላለኹ ብዬ ስላሰብኹ እንጂ በኬንያ ቆይታዬ ጥረት ባደርግ ኖሮ ሌላ ቋንቋ ጨምሬ እለምድ ነበር፤›› አለችኝ፡፡ ዝናሽ ቋንቋውን ጥንቅቅ አድርጎ መቻል ደግሞ በተቀጠሩበት ቦታ ዕድገት ያመጣል ባይ ናት፡፡ ዝናሽ አሁን ምንም ዐይነት የመግባባት ችግር ባይኖርባትም የልቧን ለመናገር ይሳናታል፡፡ በተለይ በጽሑፍ ሐሳቧን ለመግለጽ ጨርሶ አትሞክርም፡፡ ከዝናሽ ጋራ ጨዋታችንን ሳንጨርስ ሰዓቱ በመድረሱ ለመላክ የፈለገችውን ዶላር በፕሮግራሙ መሠረት ቺካጎ ስደርስ እንደማገኛትና እንደምቀበላት ቃል ገብቼላት ተለያየን፡፡ *********** በሬኖ የሚገኘው ‹‹የኔቫዳ ዩኒቨርስቲ›› የጋዜጠኞች ትምህርት ክፍልን ለመጎብኘት በሄድኹበት በአንዱ ቀን ነው፡፡ በዩኒቨርስቲው የሥነ ሕይወት ጥናትና ምርምር ኢትዮጵያዊ ምሁር ዶ/ር ተሾመን አገኋቸውና ተዋወቅን፡፡

በ‹‹ዕለተ አኰቴት›› /Thanksgiving Day/ ቀንም በቤታቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋራ ኾነው ምሳ ጋበዙኝ፡፡ እዚያው ተወልደው ያደጉ ሁለት ልጆቻቸው ሌሎች ኢትዮጵያውያን በሌሉበት አካባቢ አማርኛ አቀላጥፈው መናገር መቻላቸው በፈጠረብኝ መገረም ጨዋታ አንሥተን የቋንቋ ነገር ርእሰ ጉዳይ ኾነ፡፡ ዶ/ር ተሾመ እንደሚሉት ቋንቋ አንዱ የቤታቸው ችግር ነበር፡፡ የእርሳቸውን ከአዲስ አበባ ለትምህርት ወደ ‹‹ኦክላንድ›› መግባት ተከትሎ ባለቤታቸውም አብረዋቸው መጥተዋል፡፡ የባለቤታቸው የሥራና የመንደር ውሎ ከአገራቸው ሰዎች ጋራ ብቻ ስለነበርና ራሳቸውን በቋንቋ ለማሻሻል ምንም ጥረት ስላላደረጉ ልጆቹ ተወልደው አፍ መፍታት ሲጀምሩ በቤት ውስጥ ያለመግባባት ችግር ተፈጠረ፡፡ ቆይቶ ልጆቹ አማርኛውን ቢያንስ መናገር እንዲችሉ፣ እናት ደግሞ እንግሊዘኛውን መናገር እንዲጀምሩ በመወሰን ጊዜ ሰጥተው አንድ ላይ እርስ በርስ እንዲማማሩ በማድረግ ለውጥ አመጡ፡፡

አገር ሲቀይሩ ደግሞ በተለይ የባለቤታቸው የቋንቋ እጥረት መሉ ለሙሉ ተቀረፈ፤ ልጆቹንም በቤት ውስጥ በአማርኛ ብቻ እንዲያወሩ፣ አማርኛ ፊልም እንዲያዩና ሌሎች የቋንቋ ማዳበሪያ ዘዴዎችን እየተጠቀሙ የነበረውን ችግር ማስወገድ ቻሉ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ጥለው የሚሰደዱት ወደው አይደለም፤ በተለይ አሁን አሁን በፖሊቲካው ምክንያት የሚሰደዱ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ትምህርት ቀመስ በመኾናቸው ለብዙዎቹ የቋንቋ ነገር ችግር ላይፈጥርባቸው ይችላል፤›› አሉኝ የሥነ ሕይወት ምሁሩ፡፡ ‹‹በዲቪና በጋብቻ ምክንያት ከሚመጡት ጥቂት በማይባሉት ላይ ግን የቋንቋ ችግር በኑሯቸው ላይ እክል ሲፈጥርባቸው እናያለን፤›› የሚሉት ዶ/ር ተሾመ አክለውም ‹‹ችግሩን የሚያባብሱት ደግሞ ለረጅም ጊዜ ቢቀመጡም ቋንቋቸውን ለማሻሻል ጥረት ስለማያደርጉ ነው፡፡ ሰው ራሱን ለመለወጥ ከአገሩ ከወጣ እስከጠቀመው ድረስ እንኳን የሰው የወፍ ቋንቋም መልመድ አለበት፤›› በማለት ይመክራሉ፡፡ ከአገር እንደሚወጡ ቀደም ብለው የወሰኑና የተዘጋጁ ካሉ ባላቸው ጊዜ ቋንቋውንና ስለሚሄዱበት አገር ሌሎች መረጃዎችን አጥንተው ቢወጡ የችግሩን መጠን ሊቀንሰው እንደሚችል ያምናሉ፡፡ የሚሄዱበትን አገር ባህል፣ የሥራ ኹኔታ፣ አካባቢ፣ ሕጎችንና የመሳሰሉትን ከአካባቢው ጋር ተላምዶ ለመኖር የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማወቅ የቋንቋ ክህሎት ወሳኝ በመኾኑ ቋንቋን ማወቅ የጉዟችን ቅድመ ዝግጅት አካል መኾን አለበት ይላሉ፡፡ (ይቀጥላል)

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on March 24, 2013
  • By:
  • Last Modified: March 24, 2013 @ 9:24 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar