www.maledatimes.com በቆብ ላይ ሚዶ (አንድ) ትምህርትና ተማሪ ቤት - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

በቆብ ላይ ሚዶ (አንድ) ትምህርትና ተማሪ ቤት

By   /   March 25, 2013  /   Comments Off on በቆብ ላይ ሚዶ (አንድ) ትምህርትና ተማሪ ቤት

    Print       Email
0 0
Read Time:12 Minute, 18 Second

መስፍን ወልደማርያም

ጥር 2005

በአለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ አንድ ልብ ያላልነው መሠረታዊ ለውጥ አለ፤ እንዲያውም የመከራችን ሁሉ ምንጭ ነው ለማለት ይቻላል፤ የመሪዎቻችን አለመማር ብቻ ሳይሆን ትምህርትን መናቅ ወይም ጭራሹኑ መጥላት ዋና ባሕርያቸው ሆነ፤ እስከደርግ ዘመን የነበሩት የአገር መሪዎች ቢያንስ የአንደኛ ደረጃውን (ዳዊት መድገም) የአገሩን ባህላዊ ትምህርት ያከናወኑ ነበሩ፤ ከዚያ በኋላ ለጨዋ ቤተሰብ ልጆች ትምህርት ማለት በቤተ መንግሥት በመዋል የሚገኝ ልምድ ነበር፤ ተፈሪ መኮንን በአሥራ ሦስት ዓመቱ ደጃዝማች የሆነውና ሥልጣን ላይ የወጣው በመወለድ ያገኘውን ዕድል በልምድ እንዲያዳብረው ነበር፤ ተክለ ሐዋርያት ከአሥር ዓመታት በላይ ሩስያ ተምሮ ሲመለስ ተፈሪ ያገኘውን አላገኘም።

በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ትውልድ ለሥልጣን መነሻ አይሆንም ነበር ባይባልም፣ ለእድገት ትምህርት አስፈላጊ መሆኑ በመታመኑ የዓየር ኃይል እጩ መኮንኖችም ሆኑ መኮንኖቹ ከደብረ ዘይት እየተመላለሱ ይማሩ ነበር፤ በማታው ትምህርት ብዙ የፖሊስና የጦር ሠራዊት መኮንኖች (ኮሎኔል ሚካኤል አንዶም ጭምር) ይማሩ ነበር፤ ማታ ከተማሩት የፖሊስ መኮንኖች ውስጥ ሁለቱ አምባሳደሮችም ሚኒስትሮችም ሆነው ነበር፤ ከሐረር አካደሚ የወጣ መኮንንም አምባሳደር ሆኖ ነበር፤ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝ የደሀ ልጆች ወደሥልጣን ወንበሩ አልተጠጉም የሚሉ ካሉ የማያውቁ ናቸው፤ ትምህርታቸውን በታማኝነት ከፍነው ቀብረው ሚኒስትርና ሌላም ሹመት ያገኙ የደሀ ልጆች ብዙዎች ናቸው።

ከዚያ ወዲህ ከጨዋ በመወለድ ሥልጣንን ከማግኘት በባለጌ ጡንቻ ሥልጣን ወደማግኘት ተዘዋውረናል፤ ትውልድን ወደእኩልነት የሚገፋ አስተሳሰብ ስንቀበል ብልግናንንና ጡንቻን ወይም ሕገ አራዊትን፣ ተሳዳቢነትንና ዘራፊነትን፣ድንቁርናንና ሚዛነ-ቢስነትን የእኩልነትና የነጻነት አካል አድርገን የተቀበልን ይመስላል፤ በስድነትና በነጻነት መሀከል ያለውን ገደል ባለጌ አያየውም፤ የጨዋ ልጅ ዳዊት ከደገመ በኋላ እንደበቅሎ እየተገራ ያድጋል፤ ከጃፓን እስከእንግልጣር ተመሳሳይ ሁኔታ የነበረ ይመስላል፤ ነገር ግን ወደአውሮፓውያን ሥልጣኔ ስንንደረደር በጃፓናውያንና በእኛ መሀከል የታየው ልዩነት እነሱ ጨዋነታቸውን እንደያዙ እኛ ደግሞ ጨዋነታችንን ትተን መነሣታችን ነው።

አብዮት ወይም ወያኔ ማለት ትምህርትም ሆነ ጨዋነት ለሥልጣን አስፈላጊ እንዳልሆኑ በአደባባይ ማሳየት ሆነ፤ (አብዮትን ከማየቴ በፊት አብዮተኛ ነበርሁ ለማለት የምችል ይመስለኛል፤ አብዮትን ካየሁ በኋላ ግን ወዲያው ጠላሁት፤) አብዮተኛ ማለት አእምሮ የሌለው፣ ኅሊና የሌለው፣ እግዜአብሔር የሌለው፣ ሚዛን የሌለው ከጡንቻ በቀር ሌላ ኃይል የማያውቅ ማለት ሆነ፤ በጡንቻ የማይሠራ ነገር ከሌለ ትምህርት ለምን ያስልጋል? ከሁሉም ይበልጥ የሚያስደንቀውና የሚያስደነግጠው ትምህርትን በሥልጣን የመለወጡ ሙከራ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መጀመሩ ነው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ላዩን በግልቢያ የተደረጉ ጥናቶች ብዙ ቢሆኑም ጠለቅ ያለና የውስጡን መነሻ እየመዘዘ የሚያወጣ አንድም የለም።

ደርግ ሥልጣን እንደተሸከመ በየመሥሪያ ቤቱ አንዳንድ መኮንኖችን ‹‹የለውጥ ሐዋርያ›› በሚል ስያሜ ፈላጭ-ቆራጭ አድርጎ አስቀመጠ፤ ትእዛዙ በወታደራዊ ፍጥነት እንደውሀ ከላይ ወደታች እንዲፈስ ተፈልጎ ነበር፤ ነገር ግን ሥራ ሁሉ ወደመቆም ስለደረሰ ደርግ ቶሎ ብሎ ተለወጠና የለውጥ ሐዋርያት የሚባሉትን አነሣቸው፤ ከዚያ በኋላ ደርግ በሁለት ተቃራኒ ሁኔታዎች ተወጥሮ ተያዘ፤ በአንድ በኩል ከባሕር ኃይልና ከዓየር ኃይል፣ ከሐረር የጦር ትምህርት ቤትና ከአገር ውጭም የተማሩ መኮንኖች ነበሩ፤ በሌላ በኩል ከሆለታ ማሠልጠኛ የወጡ ነበሩ፤ በነዚህ በሁለቱ በተለያየ የትምህርት መሠረት ላይ በቆሙ መኮንኖች መሀከል አጉል ፉክክርና መናናቅ ነበረ፤ በተለይም ጄኔራል አማን በተማሩት መከበቡ የተማሩትን ዓይን እንዲገቡ አደረጋቸው፤ አብዛኛዎቹ የከፍተኛ ትምህርት ምሩቆች የሆኑ መኮንኖች በየሰበቡ የተጠረጉት በዚህ ምክንያት ይመስለኛል፤ በዚህም ምክንያት ደርግ ገለባ ያንሳፈፈበት ድርጅት ሆኖ ነበር ለማለት ቢቻልም ከደርግ ውጭ የተመለመሉት ሎሌዎች (ባለሥልጣኖች) የተማሩና በማናቸውም መመዘኛ የማያሳፍሩ ነበሩ።

የደርግ አባሎችም አለመማር ያስከተለባቸውን ጉድለት ለመሙላት በየሶሺያሊስት አገሩ የይድረስ-ይድረስ ለብ ለብ ትምህርት-ቢጤ በጉርሻ እየተሰጣቸው ተመለሱ፤ (የዛሬ ዘመን ትውልድ ያለጉርሻ ያደገ ነው፤ አሽከር ወይም ልጅ ገበታ ከመቅረቡ በፊት እጅ ያስታጥባል፤ ቆሞ፣ ኩራዝ ይዞ ካበላ በኋላ ጉርሻ ይቀበላል፤ ከዚያም እጅ አስታጥቦ ጉርሻውን ይበላል፤) በአቋራጭ ዲግሪም አገኘን ብለውም ተኩራርተው ነበር፤ በሶሺያሊስት አገሮች ሁሉ እየተሽከረከሩ ትምህርት የተባለውን ቢያርከፈክፉባቸውም ውሀ በስንጥቅ መሬት ውስጥ ሰተት ብሎ እንደሚገባ በእነሱ አንጎል ውስጥ አልገባም፤ ሆኖም በሶሺያሊስት መንግሥቶች ዓለም-አቀፋዊ ፍቅርና ብርቱ ሎሌዎችን የማፍራት ፍላጎት ለስድስት ወራት ያህል በድሎት አቆይተው የፈለጉትን ብራና አስታቅፈው ይልኳቸው ነበር፤ ብዙዎቹ ምንም ቢሆን ኢትዮጵያዊ ይሉኝታ እየያዛቸው ‹‹ዶክተር›› የሚለውን የትምህርት ማዕርግ አልደፈሩትም ነበር፤ ከመሀከላቸው አንዱ ግን እንደተመለሰ በያለበት እየዞረ ‹‹ዶክተር›› መሆኑን ሰዎች ሁሉ እንዳይረሱት እያደረገ አስታወቀ፤ ራሱን ለፌዝ አጋለጠ፤ መሳቂያ ሆነ፤ በመጨረሻም አውነቱና አጉል ፍላጎቱ እየተጋጩ በመቸገሩ ከፎቅ ላይ ተከስክሶ ሁለቱንም ራሱን (ማለት የእውነቱንም የውሸቱንም) አጠፋ፤ ያሳዝናል።

በቆብ ላይ ሚዶ ጥቅም አይሰጥም፤ በቆብ ላይ ሚዶ ለጌጥ አይሆንም፤ ትምህርትን መሣሪያ አድርገው ሊጠቀሙበት የማይችሉ ሰዎች፣ ከዚያም አልፈው ሥልጣንን በትምህርት ማስጌጥ የማይችሉ ሰዎች ሥልጣንን ያዋርዳሉ፤ በኋላ ሥልጣንም ያዋርዳቸዋል።

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on March 25, 2013
  • By:
  • Last Modified: March 25, 2013 @ 9:10 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar