www.maledatimes.com በኢሕአዴግ ጉባኤ፤ የአመራር መተካካት አተገባበር ጉዳይ ጥያቄ አስነሳ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

በኢሕአዴግ ጉባኤ፤ የአመራር መተካካት አተገባበር ጉዳይ ጥያቄ አስነሳ

By   /   March 27, 2013  /   Comments Off on በኢሕአዴግ ጉባኤ፤ የአመራር መተካካት አተገባበር ጉዳይ ጥያቄ አስነሳ

    Print       Email
0 0
Read Time:27 Minute, 15 Second

(ሪፖርታዥ) (በፋኑኤል ክንፉ-ባህርዳር)

(ሰንደቅ )

ሰሞኑን በባህርዳር በተካሄደው የኢህአዴግ ጉባዔ ላይ አመራር መተካካትን አፈጻጸም አስመልክቶ ውስጥ ለውስጥ ሲብላሉ ለነበሩ አስተያየቶች አቶ አዲሱ ለገሰ ምላሽ ሰጡ። የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በአመራር መተካካቱ በኩል ብዙ አልሄደበትም የሚለው ሐሜት መሰማቱን መነሻ በማድረግ አቶ አዲሱ ለገሰ ለኢህአዴግ ጉባዔ በሰጡት ማብራሪያ ብአዴን የአመራር መተካካት በተገቢው መንገድ አልፈጸመም በሚል የተነገሩ ሐሜቶች መሠረተቢስ መሆናቸውንና ሁኔታውም በአመለካከት ደረጃ ለግንባሩ አይጠቅምም ሲሉ በግልፅ የሰጡት አስተያየት በመተካካቱ አተገባበር ላይ ጉባኤው በስፋት እንዲነጋገርበት በር ከፍቷል።

አቶ አዲሱ መተካካትን አስመልክተው ሶስት ነጥቦችን በማስቀመጥ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለጉባዔው አቅርበዋል። ኀሳባቸውን ሲያስረዱ፤“በኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚና በኢሕአዴግ ምክር ቤት ደረጃ ከፍተኛ አመራር እና መካከለኛ አመራር ማነው? የሚለው መመለስ አለበት። በከፍተኛና በመካከለኛው አመራር መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? አንዳንዴ መካከለኛ የምንለው አመራር ከፍተኛውን በልጦ የሚገኝበት ሁኔታ አለ። ስለዚህም መተካካትን ስናስብ እነዚህን መሰል ጉዳዮች አብሮ መመለስ አለበት የሚል እምነት አለኝ። መተካካቱ በመጀመሪያ ደረጃ በከፍተኛ አመራሩ ላይ መመዘኛ መቀመጥ አለበት። እንደግንባርም ስንነጋገር፣ አንድ የጋራ የሆነ መስፈርት ያስፈልገናል። ይህን ሃሳብ እኔ እንደአዲስ የማነሳው ሳይሆን ገና ምላሽ እያገኘ ያለበት ሁኔታ መኖሩን ጉባኤው ማወቅ አለበት። ይህን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው፣ እውነተኛ የሆነ መተካካት ሊመጣ የሚችለው።”

“ስለመተካካት ስናነሳ ማነው፤ ማንን የሚተካው የሚለው መታየት አለበት ያሉት አቶ አዲሱ አንዳንዴ በትግሉ ጊዜ  አመራር የነበሩትን መተካት ተደርጎ ይወሰዳል ብለዋል።

አያይዘውም “እንደሰማሁት ብአዴን መተካካቱን በደንብ አልሄደበትም የሚል ሃሜት አለ። ግን ይሄ አይጠቅምም። አንዱ አደጋ የሚመስለኝ ለግንባራችንም በግሌም የሚሰማኝ ወደፊትም መታየት አለበት ብዬ የማምነው አንዱ ድርጅት ውስጥ ጉድለት እንኳን ቢኖር ጉድለቱ እንዲታረም እንደታጋይ መታገል ተገቢ ነው። የአንዱ ጉድለት ለሌላው ጥንካሬ ሊሆን አይችልም። የአንዱ ጥንካሬ ለሌላው ድርጅት ግን ጥንካሬ ሊሆን ይችላል። በስልጠናም ብዙ ጊዜ ያየነው ይህን ነው። አንድ ድርጅት ሲደክም ለምን ደከመ? አንድ አካሌ ነው የደከመው? ይህ አካሌ ደግሞ በዛው ከቀጠለ እንደኢሕአዴግ እደክማለሁ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። በፍጥነትም ለማደግ የአንዱ መድክም የእኔም መድከም ነው የሚል አመለካከት ሲኖር ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ ጨፍልቆ አንድ ማድረግ የሚቻል አይመስለኝም። ስለዴሞክራሲያዊ ድርጅትም ስናወራ በአስተሳሰብም በተግባርም ወደ አንድ መምጣት መቻል አለብን። አሁን ባለው አቀራረብ ከሄድን ግን መቀራረቡ አይደለም የሚጨምረው” ሲሉ ያላቸውን ስጋት አስቀምጠዋል።

አቶ ሕላዊ ዮሴፍም በበኩላቸው በጉባኤው ውስጥ ስለሚወራው ሃሜት ጥያቄ በማቅረብ ነበር ሃሳባቸውን ያብራሩት፤ “የመተካካት መሠረታዊ ጭብጥ የተጀመረውን መስመር ማስቀጠል መሆኑን ግንዛቤ ከወሰድን የግለሰቦች ጉዳይ በአጀንዳነት ማንሳቱ ለምን አስፈለገ? ምንስ ይጠቅማል? በተኪውና እኔ ነኝ ተኪው በሚለው ውስጥ ያሉት ዝንባሌዎች ምንድናቸው? ድርጅታችን እየጎዳው ያለው ነገር ምንድን ነው? የሚሉትን ትንሽ ፊት ለፊት ተገናኝቶ መነጋገሩ የሚጠቅም ይመስለኛል። ስለዚህም አዲስ አስተሳሰብ ይዘን ድርጅታችን ወደፊት ማራመድ በሚቻልበት አግባብ ላይ እርግጠኛ ምላሽ በምናገኝበት ሁኔታ ተግባብተን መውጣት አለብን። አለበለዚያ ምን ይሆናል፣ በነገሮች ሁሉ ፊት ለፊት ሳንተያይ በጎን እየተላለፍን ሊሆን ይችላል። በተረፈ ሁሉም በየድርጅቱ የነበረው ሂደት ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ። የእኛም ሁኔታ በበቂ መረጃ የቀረበ ነው። ከስልሳ አምስት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል ውስጥ ሰማንያ አምስት በመቶ የሚሆኑት አዲስ ተተኪዎች ናቸው። ይህ ሆኖ ሳለ፤ በሁለት ሰዎች ላይ እናተኩር፣ አይናችንን ጥለን እንሂድ የሚባል ከሆነ ልማቱን አላራምድ ያለ አደርባይነት እዚህ ቦታ እንዴት ይገለፃል ብለን ብናየው ጥሩ ይመስለኛል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ አባይ ፀሐዬ በበኩላቸው “በአሁን ሰዓት ስለመተካካት የሚወራው ማዕከላዊ ላይ ምን ተደረገ? ስራአስፈፃሚው ላይ ምን ለውጥ አለ? የሚሉ ናቸው። ቁምነገሩ ያለው መካከለኛው አመራር ላይ በጥራትና በስፋት የሚተካ አመራር መፍጠር ላይ ነው። ይህ ሲሆን ማዕከላዊ ኮሚቴውም ሌላውንም ለመተካት ብዙ አማራጭ ይኖራል። ስለዚህ የመተካካት ሂደቱን ስንገመግም ከበላይ ያለውን አመራር ብቻ መሆን የለበትም። ሆኖም፤ መገምገሙ ግን ተገቢ ነው። ዘላቂ የአመራር መተካካት ለመፍጠር ግን በመካከለኛው አመራር ላይ መስራት ሲቻል ብቻ ነው። ይህን ማድረግ ከቻልን ስራ አስፈፃሚውን ለመተካት ብዙ አማራጮች እናገኛለን” ብለዋል።

“አፈፃፀሙን በተመለከተ በተለይ ከፍተኛ አመራሩ ለመተካት ሁለቱንም አብሮ ማስኬድ የሚቻል ይመስለኛል። አንዱ አሁን የተሄደበት መንገድ ሲሆን፤ ሌላው ግን በኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ከዚህ በፊት የተሄደበት አግባብ በደንብ አመራር ተሰጥቶበት ተቀናጅቶ የተፈፀመ ነው። በቀጣይም፤ ለምንድን ነው የምንተካው? እንዴት ነው የምንተካው? መቼ ነው የምንተካው? ምን ያህል ርቀትስ ነው የምንሄደው? እያንዳንዱ ድርጅት ድርሻው ምንድን ነው? ስራ አስፈፃሚውስ እንዴት ነው የሚያቀናጀው? አቅጣጫ የሚያሲዘውስ? ለእነዚህ ምላሽ ለመስጠት በደንብ ተቀይሶ መሰራት አለበት። የአሁኑ አካሄድ ግን በየድርጅቱ የተፈፀመ ነው። እንደአንድ አካሄድ ይቻላል። ተገቢም ነው። በሶስተኛው የመተካካት ምዕራፍ ግን እንዴት እንሂድበት የሚለውን መመካከሩ ጥሩ ይመስለኛል” ሲሉ አቶ አባይ ፀሐዬ አስተያየተቻውን አቅርበዋል።

“የመተካካት ፖሊሲዎቻችን ምንድናቸው?” የሚለውን ለማስታወስ በሚያግዝ መልኩ አስተያየታቸውን ያቀረቡት አቶ በረከት ስሞዖን ናቸው። አቶ በረከት ስለመተካካት ፅንሰ ሃሳብ አስተያየታቸውን ሲዘነዝሩ እንዳሉት፤ “በድርጅታችን በተለያዩ ፅሁፎችም በአመራሩ የፖሊሲ ውይይቶችም እንዲሁም ለአባላት ግልፅ በሆኑ ሁኔታ እንዴት ነው የመተካካት ፖሊሲዎቻችን የተቀመጡት። አንደኛው እኔ እንደሚገባኝ፣ መተካካት የሚባለው ለትግል ቀጣይነት፣ ለመስመር ቀጣይነት የሚደረግ ሂደት ነው። ይህን ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር በትውልድ ቅብብሎሽ አማካኝት ዳር እንዲደርስና ሀገሪቷን ከስር መሠረቱ በሚቀይር ሁኔታ እንዲፈፀም ነው። የመተካካት ግቡ የሰዎች መተካካት አይደለም። ግቡ የመስመር ትግበራ ነው። ሁለተኛው፤ በዱላ ቅብብሎሽ ይፈፀማል። አንዱ ትውልድ ለሌላው ትውልድ እያቀበለ ተደጋግፈን ትግሉን ዳር እናደርሰዋለን። ሶስተኛው፤ ነባሮች በጣም ከመድከማቸው በፊት በተለይ ከፊት መስመር ቦታውን ለወጣቱ ትውልድ ማስረከብ አለባቸው። በተለይ ወጣቱ ትውልድ የተረከበውን መስመር በዲሲፕሊን በታማኝነት በፅናት ተግባራዊ በማድረግ መቀጠል አለበት። ነባሩም ከፊት መስመር በመውጣት በጎን ማገዝ ይጠበቅበታል። አራተኛው፤ በመንግስት ኃላፊነት ነባሩም ሆነ ተተኪው ከሁለት የምርጫ ጊዜ በላይ አያገለግልም። በፓርቲ ኃላፊነት ውስጥም አንድ ሰው እስከ ስልሳ አምስት ዓመት ብቻ ነው የሚያገለግለው። የፓርቲያችን የመተካካት ፖሊሲዎችም ዋነኛ ቁምነገሮች እኔ እስከማስታውሰው ድረስ እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ናቸው።”

በአቶ በረከት ገለጻ መሰረት፤ “ከአፈፃፀም አንፃር በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የመተካካቱ ሂደት ይፈፀማል የሚል አቅጣጫ ነበር የተቀመጠው። በሶስት ምዕራፎች ተከፍሎም ይፈፀማል። በዚህ ደረጃ ሁሉም ድርጅት ከራሱ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ብዙ ስራዎች ሲሰሩ ነው የከረሙት። ከዚህ ዓላማም ያፈነገጠ ድርጅት ያለ አይመስለኝም። ይህን የምልበት ምክንያት የተቀመጡትን የመተካካት የፖሊሲ አቅጣጫዎች መነሻ በማድረግ ሁሉም ድርጅቶች ለራሳቸው በሚጠቅማቸው መንገድ የሄዱበት ሁኔታ ነው በመኖሩ ነው። በተጨማሪም ሁሉም ድርጅቶች ኃላፊነት ባላቸው ሰዎች ነው የሚመሩት። እነዚህ የድርጅት መሪዎች የመተካካትን ፖሊሲውን አብጠርጥረው የሚያውቁ ናቸው። በዚሁ መሰረትም የመተካካት አፈፃፀሙን ሲመሩት ሰንብተዋል። ሆኖም የተለያየ አፈፃፀም ባሕሪ በድርጅቱ ለመኖሩ ብዙ የተለያዩ ምክንያቶች ማስቀመጥ ይቻላል። ለምሳሌ በየድርጅቱ ያለው የነባር ታጋይ ቁጥር የተለያየ ነው። ስለዚህም አንድ አይነት አፈፃፀም ሊኖር አይችልም። ይኖራል ተብሎም አይገመትም። ይህን ከግምት አስገብነት ብንመለከተው ጠቃሚ ይመስለኛል።”

በአጠቃላይ በጉባኤው ላይ የተንፀባረቀው የመተካካት አተገባበር ወጥነት የሌለው እና ድርጅቶቹ በተናጠል የሄዱበት በመሆኑ ግንባሩ የአፈፃፀም የፖሊሲ አቅጣጫ እንጂ የአተገባበር ዝርዝር መመሪያዎች የሌሉት መሆኑን መገንዘብ ተችሏል። ይህም በመሆኑ በጉባኤው ተሳታፊው አባላት ውስጥ የመተካካቱ ሂደት ለሃሜት የተጋለጠበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ሌላው ተተኪ ከሚባለው አዲሱ አመራርም መተካካቱን በተመለከተ ከፍተኛ ሙግት ያንፀባረቀ አልነበረም። በአብዛኛው የቀድሞ የድርጅቱ ነባር ታጋዮች ተሳትፎ የጎላበት ጉባኤ ነበር ማለት ይቻላል።

የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሰሞኑን በተናጠል ባካሄዱት ጉባዔ ነባር አመራሮችን ወደማዕከላዊ ኮሚቴ መልሶ የመምረጥ ሁኔታ መታየቱ ከመተካካት መርህ አንጻር በግንባሩ አባላት ሳይቀር ጉዳዩ መነጋገሪያ ሆኗል። ህወሃት አቶ አባይ ጸሐዬን፣ ብአዴን እነአቶ አዲሱ ለገሰን፣ አቶ ህላዊ ዮሴፍን በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት መርጧል። ሌሎችም በአዲስ መተካት ያለባቸው ነባር አባላት በአመራርነት መቀጠላቸው ጥያቄ አጭሯል።

ከሁለት ዓመት በፊት በአዳማ የተካሄደው 8ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ የአመራር መተካካትን በተመለከተ ካሳለፈው ውሳኔ የሚከተለው ይጠቀሳል። “…ነባሩ የአመራር ኃይል በስራ ብዛትና በእድሜ መግፋት መስራት የማይችልበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት ደረጃ በደረጃ በአዳዲስ የአመራር ኃይሎች እየተተካ እንዲሄድ ማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ ሊቀየስ ችሏል። በዚህ አቅጣጫ መሰረት ነባሩ አመራር ከፊት መስመር ለቆ በአዲሱ እንዲተካና በድርጅት አመራርነት ግን አስተዋፅኦውን እያበረከተ የሚቀጥልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ተወስኖ ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል።

በዚህ አቅጣጫ መሰረት ነባሩ አመራር በሶስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ከፊት መስመር የሚለቅና ሚናውን እየተጫወተ የሚቀጥልበት ሁኔታ ተመቻችቷል።

በተመሳሳይ መልኩ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አላማዎቻችንን ቀጣይ ተፈፃሚነት ለማረጋገጥ የአመራር መተካካት ስርአታችን መካከለኛ አመራሩንም የሚያካትት እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ አስቀምጠናል…” ብሏል።

በተያያዘም ዜና አሁንም የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነት እንዳለው በጉባኤው ግንዛቤ ተወስዷል። በተፈለገው ፍጥነትና ደረጃ ኪራይ ሰብሳቢነትን ድርጅቱ አለመተግበሩን ከስምምነት ላይ ተደርሷል። አሁኑም የስርዓቱ አደጋ እንደሆነም የጋራ ግንዛቤ ተወስዷል። ችግሮቹና ምንጮቹን መለየት የተቻለ ቢሆንም አተገባበሩ አሁንም ብዙ ርቀት መጓዝ እንደሚያስፈልገው ተገልፃል።

አቶ ስብሃት ነጋ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ጦርነት ሲመጣ በጋራ እንሰለፋለን፣ ችግር ሲመጣ በጋራ እንሰለፋለን። የኪራይ ሰብሳቢነት ችግርን በጋራ ተሰልፈን ማጥፋት ያልቻልንበት ሚስጢሩ ምንድነው በማለት በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ላይ ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስበዋል።

አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች በተፈለገው መልኩ እድገት ያላስመዘገቡት ለምን እንደሆነ ለተነሳው ጥያቄ አቶ መኩሪያ ኃይሌ በሰጡት ምላሽ አንዳንድ አንቀሳቃሾች በኪራይ መሰብሰብ ሥራ ላይ በመሰማራታቸው መሆኑን በይፋ ተናግረዋል። “የተሰጣቸውን ማሽን ይሸጣሉ። ለስራ የተሰጣቸውን መሬት ለሌላ ጥቅም ያውላሉ። በራሳቸው መፈጸም የሚገባቸውን ስራ ለሌሎች አሳልፈው በመስጠት ኪራይ ያድላሉ” ሲሉ አንዳንድ አንቀሳቃሾችን ወቅሰዋል።

ስብሰባው በአጠቃላይ ሲታይ ከተሳታፊው አባላት ብዛት አንፃር የጥቂት የአመራር አባላት ብቻ ተሳትፎ ብቻ የታየበት ነው። በተለይ ከነባር የኢሕዴግ ታጋዮች መተካካትም ሆነ ኪራይ ሰብሳቢነትን በተመለከተ የተሰነዘረ ኀሳብ አለመኖሩ የስብሰባው ሌላ ገጽታ ነበር።

የገዢውን ፓርቲ በአንድ ውህድ ፓርቲ እንዲደራጅ በአቶ ሥዬም መስፍን ጥያቄ አዘል ኀሳብ የቀረበ ሲሆን ለዚህ ጥያቄ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ በጉዳዩ ላይ ወስኖ ከላይ ወደታች ከማውረድ ይልቅ አባል ድርጅቶቹ በተናጠል ተወያይተውበት ቢመጣ የተሻለ እንደሚሆን ባቀረቡት ኀሳብ መሠረት ጉዳይ በይደር ታልፏል።

አጋር ፓርቲዎች እስከ መቼ አጋር ይባላሉ ተብሎ ለተነሳውም ጥያቄ፣ በጥናት የተደገፈ የመነሻ ሃሳብ እንዲቀርብና ውይይት እንዲደረግበት ኀሳብ ቀርቧል።

በመጨረሻም ጉባዔው ለቀጣይ ሁለት ዓመታት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን የግንባሩ ሊቀመንበር  አቶ ደመቀ መኮንንን ምክትል ሊቀመንበር በማድረግ በድጋሚ መርጧቸዋል።¾

 

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on March 27, 2013
  • By:
  • Last Modified: March 27, 2013 @ 1:36 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar