www.maledatimes.com ሰመጉ ለአዳራሽ ኪራይ ፈቃድ መጠየቁ ህገ-ወጥ ነው አለ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ሰመጉ ለአዳራሽ ኪራይ ፈቃድ መጠየቁ ህገ-ወጥ ነው አለ

By   /   March 27, 2013  /   Comments Off on ሰመጉ ለአዳራሽ ኪራይ ፈቃድ መጠየቁ ህገ-ወጥ ነው አለ

    Print       Email
0 0
Read Time:14 Minute, 3 Second

በመስከረም አያሌው

ሰንደቅ

ሆቴሎች እና ሌሎች የአዳራሽ አከራዮች አገልግሎት ለመስጠት ፈቃድ የሚጠይቁበት ሁኔታ ህገ-ወጥ መሆኑን የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) ገለፀ።

የተለያዩ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪክ ማህበራት በተደጋጋሚ እያቀረቡ ያሉት ቅሬታዎች በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት እና የደጋፊዎች ስብሰባ ለማካሄድ የአዳራሽ ችግር እየተፈጠረባቸው መሆኑን ያመለክታል ያለው ጉባኤው፣ በአሁኑ ወቅት ሆቴሎች ወይም አዳራሽ አከራዮች በህግ ያልተጠየቀ መስፈርት ተሰብሳቢዎችን ሲጠይቁ የአዲስ አበባ አስተዳደር በበኩሉ ማረጋገጫ ለመስጠት የአዳራሽ ውል ይጠይቃል ብሏል። በዚህ ተያያዥ ምክንያት ስብሰባዎች እየተደናቀፉ መሆኑን የገለፀው ጉባኤው፣ እንዲህ አይነት ከሆቴሎችና አዳራሽ አከራዮች የሚቀርቡት ፈቃድ አምጡ ጥያቄዎች የሚታዩት ፖለቲካዊ ይዘት ባላቸው ስብሰባዎች ላይ ብቻ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ ብሏል።

የተለያዩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመሰብሰብ እና ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣት መብታቸው እየተጣሰ መሆኑን ለጉባኤው በተደጋጋሚ አቤቱታ እያቀረቡ መሆናቸውም ነው የተገለፀው። የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ታህሳስ 11/2005 ባቀረበው አቤቱታ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ ታህሳስ 5 ቀን 2005 ዓ.ም ለሰሜን ሆቴል ክፍያ የፈፀመ ቢሆንም፣ ሆቴሉ ከመንግስት የስብሰባ ፈቃድ ካለመጣችሁ ውሌን አቋርጫለሁ ሲል ደብዳቤ ፅፏል። ማህበሩም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስብሰባውን ለማሳወቅ ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ስብሰባውን ለማሳወቅ ቦታ እና ጊዜ መግለፅ ስላለባቸው አስተዳደሩ ጥያቄውን ሳያስተናግድ ቀርቷል።

ማህበሩ ስብሰባውን በ21/04/2005 ለማካሄድ በጠየቀው መሰረት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ቦታ እንዳለ በመግለፅ ቅድሚያ ክፍያ እንዲፈፅመ ገልጾላቸው ነበር። ነገር ግን ክፍያ ሊፈፅሙ በሄዱበት ወቅት የምዝገባ ችግር በመዝገብ ሰራተኛቸው ምክንያት ተፈጥሮ እንደነበር እና ቦታ እንደሌላቸው ገልፀዋል። ሰመጉ ጉዳዩን ባጣራበት ወቅትም ተመሳሳይ ምላሽ ማግኘቱን ገልጿል። ጥያቄውን ያፀደቁት ዳይሬክተር በበኩላቸው ችግሩ የተፈጠረው በምዝገባ ሳይሆን የባለራይ የወጣቶች ማህበር ስብሰባ በሚካሄድበት እለት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሰራተኞች ስብሰባ ለማድረግ በመፈለጉ ስምምነታቸው እንደተሰረዘ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ በበኩሉ የ2005 ዓ.ም የአካባቢ እና የከተሞች ምርጫ ቅድመ ዝግጅትን አስመልክቶ ከአባላቱ እና ደጋፊዎቹ ጋር ስብሰባ ለማካሄድ ለአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት የአዳራሽ ጥያቄ አቅርቦ በቃል ተስፋ ተሰጥቶት ነበር። በተገባላቸው ቃል መሰረት የአዳራሽ ኪራይ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምክንያቱ ሳይገለፅ ጥያቄው ሳይስተናገድ መቅረቱን ፓርቲው ገልጿል። ሌሎች የስብሰባ አዳራሽ ማፈላለጋቸውን በመቀጠል ለሌሎች የአዳራሽ ባለቤቶች ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ የስብሰባ ፈቃድ በፅሁፍ አስቀድማችሁ አምጡ ሲሏቸው የአዲስ አበባ ፈቃድ ሰጭ አካል በበኩሉ የስብሰባ አዳራሽ ፈቃድ ውል አምጡ በማለት በቅብብሎሽ ህገ-መንግስታዊ መብታችን ተጥሷል ሲል አቤቱታ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት (መድረክ) እና ሰማያዊ ፓርቲም ህገ-መንግስታዊ የመሰብሰብ መብታችንን ተነፍገናል ሲሉ በሰመጉ ጥያቄ ያቀረቡ ፓርቲዎች ናቸው። የስድስት ፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ ድርጅት የሆነው መድረክ በህዳር 18 ቀን 2004 ዓ.ም የወጣውን “የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ አዋጅ” አስመልክቶ ህዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ ከሙገር ሲሚንቶ ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኢንተርፕራይዝ ኃ.የተ.የግ.ማህበር ጋር በአዳራሽ ኪራይ ስምምነት ፈፅሞ መጋቢት 15 ቀን 2004 ዓ.ም ክፍያ መፈፀሙ በማህበሩ የገንዘብ ደረሰኝ ቁጥር 22988 ተረጋግጧል። ስምምነቱን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላማዊ ሰልፍ እና ስብሰባ ማሳወቂያ ቢሮ በማቅረብ መጋቢት 19 ቀን 2004 ዓ.ም ከአስተዳደሩ የማሳወቂያ ማረጋገጫ ደብዳቤ ተሰጥቶታል። ሆኖም በስብሰባው እለት በሙገር ሲሚንቶ አዳራሽ ሲደርሱ ውሉ መሰረዙ ተነግሯቸዋል።

መድረክ በመቀጠል ያመራው ወደ ኮልፌ ቀራኒዮ ወጣቶች ማእከል ሲሆን፣ ግንቦት 1 ቀን 2004 ዓ.ም ለማእከሉ በደብዳቤ የአዳራሽ ጥያቄ አቅርቦ ማእከሉም ከመንግስት የስብሰባ ፈቃድ እንዲያመጣ ተነግሮታል። መድረክ ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አምርቶ ጥያቄውን ሲያቀርብ የስብሰባ ቦታውን ማሳወቅ አለባችሁ መባሉን እና በዚህም ምክንያት ከማዕከሉ ጋር ስምምነት ሳይፈፅሙ መቅረታቸውን የመድረክ ጉዳይ አስፈፃሚ አቶ ወንደሰን ክንፈ ለሰመጉ ገልፀዋል።

ሰማያዊ ፓርቲ በበኩሉ የካቲት 30 ቀን 2005 ዓ.ም በዋቢሸበሌ ሆቴል የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ምሽት ጠርቶ ከሆቴሉ ጋር ሁሉንም ስምምነት እና ክፍያ ቢፈፅምም፣ ዝግጅቱ ተጠናቆ ታዳሚው ወደ ሆቴሉ በመግባት ላይ እያለ የሆቴሉ አስተዳደር በድንገት ከአቅሜ በላይ በሆነ ምክንያት ዝግጅታችሁን ማድረግ አትችሉም በማለት ምክንያቱንም ለመናገር እንደማይችሉ በመግለፅ የተሰበሰበው ህዝብ ሊበተን መቻሉን ገልጿል።

እነዚህ ድርጊቶች በህገ-መንግስቱ የሰፈሩት መብቶች እና ሌሎች ሰብአዊ መብቶች ብቻም ሳይሆን መብቶቻቸውን በማጣታቸው የሚያደርጉት ተቃውሞም አብሮ የሚያፍን መሆኑን ያስረዳል ያለው ሰመጉ፤ እንዲህ አይነቶቹ ጫናዎች ከበስተኋላ የሚደረግ አሉታዊ ጫና እንዳለባቸው አመልካች ነው ብሏል።

ከፖለቲካ ፓርቲዎች የመሰብሰብ መብት በተጨማሪም ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት ጥሰትም እየተፈፀመ መሆኑን የገለፀው ሰመጉ፤ ለማሳያም ባለፈው መጋቢት 8 ቀን 2005 ዓ.ም የተከሰተውን ክስተት አንስቷል። የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር፣ ሰማያዊ ፓርቲ እና ሌሎች አካላት በኢጣሊያ አፊል ከተማ ፊልድ ማርሻል ሩዶልፍ ግራዚያኒ ሙዚየም መገንባቱን እና በስሙም መናፈሻ መከፈቱን ተመልክቶ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰልፍና ህዝባዊ ስብሰባ ማሳወቂያ ቢሮ የካቲት 25 ቀን 2005 ዓ.ም ደብዳቤ አስገብተዋል። መጋቢት 7 ቀን 2005 የባለራእይ ወጣቶች ማህበር ስምንት አባላት በመኪና እየተንቀሳቀሱ ጥሪ ሲያደርጉ በፖሊስ ተይዘው ታስረዋል። እነዚህ ወጣቶች በራስ ደስታ፣ ጃን ሜዳ እና አራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ታስረው ክስ ሳይመሰረትባቸው ከሁለት ቀናት በኋላ ተለቀዋል። ሰልፉ በሚካሄድበት መጋቢት 8 ቀን 2005 ዓ.ም ስድስት ኪሎ በተሰበሰቡበት አንድ ሲቪል የለበሰ የመንግስት የፀጥታ ሰራተኛ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ አትችሉም ማለቱን እና እነ ዶ/ር ያዕቆብ ሀይለማርያምን ጨምሮ ሌሎች በፖሊስ መኪና ወደ አራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ተወስደው ታስረው ከአንድ ቀን በኋላ በዋስ መፈታታቸውን ሰመጉ ገልጿል። በመሆኑም እነዚህን ዜጎች ለእስራት እና ለድብደባ የዳረጉት አካላት ተጣርተው አጥፊዎቹም ህግ ፊት እንዲቀርቡ ጠይቋል።n

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on March 27, 2013
  • By:
  • Last Modified: March 27, 2013 @ 1:42 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar