www.maledatimes.com ሁለት፦ ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም! የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዢንና ራድዮ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ሁለት፦ ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም! የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዢንና ራድዮ

By   /   May 1, 2013  /   Comments Off on ሁለት፦ ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም! የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዢንና ራድዮ

    Print       Email
0 0
Read Time:9 Minute, 29 Second

መስፍን ወልደ ማርያም

መጋቢት 2005

  ልክ ወያኔ/ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን መገናኛ ዘዴዎች ሁሉ ለአንድ የወያኔ ዓላማ ብቻ እንዲውል እንዳደረገው ኢሳትም የኢትዮጵያን ሕዝብ ለአንድ ቡድን ዓላማ ተገዢ ለማድረግ የታሰበ ነው የሚሉ ሰዎች አሉ፤ እስቲ ማስረጃ ቁጠሩ ሲባሉ ከስሜትና ከጥርጣሬ በቀር ምንም ተጨባጭ ነገር አይወጣቸውም፤ የተለያዩ ቡድኖች፣ በትጥቅ ትግል ውስጥ ነን ከሚሉ ጀምሮ በሰላማዊ የፖሊቲካ ትግል ተወስነናል የሚሉና በተገኘው በማናቸውም መንገድ ወያኔ/ኢሕአዴግን እንታገላለን የሚሉ ሁሉ በኢሳት መድረክ እንዳገኙ ይታያል፤ ኢሳት የራሱ የፖሊቲካ እምነት የለውም፤ ወይም ሁሉንም የፖሊቲካ እምነቶች ይደግፋል ማለት ይቻል እንደሆነ አላውቅም፤ ዝም ብሎ እምነት የሌለው መድረክ ነው እንዳይባል ወያኔን ተቃዋሚነቱ ጎልቶ የወጣ ነው፤ ኢሳት የጸዳ የዴሞክራሲ መድረክ ነው ከተባለ ጸረ-ዴሞክራሲ አቅዋም ያላቸውን፣ ወያኔንም ጨምሮ ማስተናገድ የሚኖርበት ይመስለኛል፤ ይህ ግን ጎልቶ እየታየ አይደለም።

ዋናው የዴሞክራሲ ችግር ዴሞክራሲ መሆኑ የታወቀ ነው፤ ዋናው የነጻነት ችግር ነጻነት ነው፤ ዴሞክራሲንና ነጻነትን አልፈልግም የሚል ሰው የለም፤ በቅርቡ ከወጣው የመርስዔ ኀዘን ትዝታዬ የሚል መጽሐፍ ውስጥ አንድ እንቊ የሆነ ነገር አገኘሁ፤ እንደተጻፈ ልጥቀሰው፡-

በአእላፍ ሰገድ ኢያሱ ዘመን፣ በ1672 ዓ.ም. ጥቅምት 10 ቀን የሃይማኖት ጉባኤ ቆሞ ነበርና የቅብዓቶች አፈ ጉባኤ አባ አካለ ክርስቶስና የተዋሕዶዎች አፈ ጉባኤ አባ ኒቆላዎስ በየበኩላቸው ከመጻሕፍት እየጠቀሱ በንጉሡ ፊት በብዙ ተከራከሩ፡፡ በክርክሩም ላይ አባ አካለ ክርስቶስ ተረትቶ ጳጳሱና እጨጌው አወገዙት፡፡ ንጉሡ አእላፍ ሰገድ ዮሐንስም የተዋሕዶዎችን መርታት የቅብዓቶችን መረታት አይተው ‹‹ከበረ ሥጋ በተዋሕዶ›› ተብሎ ዐዋጅ እንዲነገር አደረጉ፡፡ እርሳቸው ራሳቸው ግን የግል እምነታቸውን ሲገልጡ ‹‹እኔ ራሴ በተረቺዎቹ በኩል ነኝ›› ብለው ተናገሩ ይባላል፡፡

አእላፍ ሰገድ ኢያሱ ከሦስት መቶ ሠላሳ ዓመታት በፊት ሦስት ቁም-ነገሮችን ያስተማረናል፤ አንደኛ ፍትሕ-ርትዕ ከሥልጣን ነጻ መሆኑን የሁለት ወገኖችን ክርክር አዳምጦ፣ የጳጳሱንና የእጨጌውን በውግዘት የተገለጸ ውሳኔ ተቀበለ፤ ሁለተኛ የግል እምነት ከዳኝነት ነጻ መሆኑን ሲያሳይ አሸናፊው ተዋሕዶ መሆኑን አወጀ፤ ሦስተኛ ሃይማኖት የግል መሆኑን ለማሳየት ‹‹እኔ ራሴ በተረቺዎቹ በኩል ነኝ፤›› በማለት የራሱን እምነት አሳወቀ፤ እነዚህ ሁሉ ቁም-ነገሮች ከሽፈው ዛሬ፣ በሚያዝያ 2005 ዓ.ም. ከሦስት መቶ ሠላሳ ሦስት ዓመታት በኋላ ከባድ ችግሮቻችን ሆነው ለተዋሕዶውም ለእስላሙም ተደንቅረውብናል! ይህ ባለህበት ሂድ! አይደለም፤ ቀኝ-ኋላ ዙር! ነው።

ከላይ ዋናው የዴሞክራሲ ቸግር ዴሞክራሲ፣ ዋናው የነጻነት ችግር ነጻነት መሆኑን ገልጬ ነበር፤ ከሦስት መቶ ዓመታት በፊት በአጼ አእላፍ ሰገድ ኢያሱ ዘመን የተወሰነም ቢሆን የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነትና ነጻነት በመኖሩ በአደባባይ በሙሉ ነጻነት ክርክር ተደርጎ አሸናፊና ተሸናፊ በይፋ ተለዩ፤ ዛሬ ግን ያንን ያህል የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነትና ነጻነት ስለሌለ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ተሰንጥቃለች፤ የኢትዮጵያ እስልምናም የመሰንጠቅ አደጋ እያንዣበበበት በመሆኑ እንዳይሰነጠቅ አጥብቆ እየታገለ ነው።

ከዴሞክራሲና ከነጻነት የሚወለደው ችግር በውይይትና በክርክር፣ በሕጋዊ ሥርዓትና በሕግ ልዕልና ይፈታል፤ በአምባ-ገነን አገዛዝ ያለው አፈና ነው፤ ነገር ግን ዴሞክራሲንና ነጻነትን የሚያፍኑ አምባ-ገነኖችና ሎሌዎቻቸው ሁሉ አፈናቸውን የሚያከናውኑት በዴሞክራሲና በነጻነት ስም ነው፤ በደቡብ አፍሪካ አፓርቴይድ መሠረት የነበረው ለነጮቹና ለጥቁሮቹ ለየብቻ ዴሞክራሲና ነጻነት ይበጃል በሚል ነበር፤ ማነው ይበጃል ብሎ የሚወስነው? ሲባል መልሱ ነጮቹ ናቸው ነው፤ ነጮቹ በዴሞክራሲና በነጻነት ለነጮች ብቻ ሳይሆን ለጥቁሮችም ይወስናሉ! ኢትዮጵያም ውስጥ እነአሜሪካ ባርከው የተቀበሉት ክልል-በዘር ከተመሠረተ ሃያ ዓመታት አለፉ፤ ውጤቱ እያቆጠቆጠ ነው፤ ዴሞክራሲንና ነጻነትን እየደፈጠጠ ነው፤ ኢትዮጵያም እየደበዘዘች ነው፤ ከዚህ የአንድ አገር ውርደት የሚጠቀሙት በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው፤ እነዚህም ሰዎች ቢሆኑ ለሢሶ ዕድሜያቸው አንኳን አይጠቀሙም፤ ለልጆች የሚተላለፍ ጥቅምም አይኖራቸውም፤ ከኢትዮጵያ ውጭ እንደልብ ተንደላቅቀው የሚኖሩበት አገርም መኖሩ ያጠራጥራል፤ ዛሬ እየተጠቀሙ እንዳሉት ነገም እንጠቀማለን ብለው ማሰባቸው ቂልነት ነው፤ ነገ ራሱን የቻለ ጣጣ ይዞ ይመጣል።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on May 1, 2013
  • By:
  • Last Modified: May 1, 2013 @ 10:32 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar