www.maledatimes.com ፖለቲካችንና የኃይለማርያም ነገር -የግል ዕይታ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ፖለቲካችንና የኃይለማርያም ነገር -የግል ዕይታ

By   /   May 2, 2013  /   Comments Off on ፖለቲካችንና የኃይለማርያም ነገር -የግል ዕይታ

    Print       Email
0 0
Read Time:26 Minute, 18 Second

=~=~=~=~=~=~=~=~=~=~=pro meles haile
የሀገሪቱ ፖለቲካ አሁን የሚገኝበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው:: በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ህዝቡና የፖለቲካ ኤሊቱ በዚህ አይነት መልክ የተከፋፈለበትና እንደዚሁም የለውጥ ፍላጎት ጣሪያ የነካበት ጊዜ የሚገኝ አይመስለኝም::በአንድ በኩል እያደር የመንግስት ቅቡልነት ከሚገባው በታች እያዘቀዘቀ ነው:: በሌላ በኩል የህዝቡም ዘርፈ ብዙ ብሶትና የለውጥ ናፍቆት በኃይለማሪያም መንግስት ተቀባይነት ላይ በአሉታዊ መልኩ ተጽዕኖውን አሳርፎበታል::

ከኢህአዴግ ዙሪያ ውጭ ያለው ከባቢ ሁኔታም የሚያበረታታ አይነት አይደለም::ተቃዋሚዎች ከመብዛታቸውም በላይ በሀገር ውስጥም ውጭም ያሉት በበርካታ ሸንተረሮች የተከፋፈሉ ናቸው::አስማሚ ኃይል የላቸውም:: እርስ በእርስ አይደማመጡም:: ሁሉም በሚባል ደረጃ ለትንንሽና ግማሽ ድሎች እራሳቸውን አጭተው እየተንቀሳቀሱ ነው:: የበለጠ ተስሚነት የማግኘት ውድድርና ፍትጊያ ላይ ናቸው::ስለዚህም በእነርሱ ብቃት በኩል እንዲመጣ የሚታሰበው ተስፋ ዝቅተኛ ነው:: ላም አለኝ በሰማይ!

ከዚህ ይልቅ በሀገሪቱ ህዝቦችና በኢህአዴግ ግንኙነት ዙሪያ በርካታ ምላሽ የሚፈልጉ ጉዳዮች አፍጠው ወጥተዋል::ለዚህ ፖለቲካዊ ምላሽ ለመስጠትም ሆነ በይደር ለማዘግየት ወይም በተደጋጋሚ እንደተደረገው ትኩረት ለማስቀየርም የሚያስችል ብቃት አልተገኘም:: መለስ ሰዎቻቸውን(ተተኪዎቻቸውን) በዚህ አይነት ክህሎት አላሰለጠኑም:: ስለዚህም የኢህአዴግ/ህወሀት ባቡር በከፍተኛ ፍጥነት ከህዝብ ባቡር ጋር ለመጋጨት እየተንደረደረ ነው:: ውጥረቱ ምንም እንኳን ለበርካታ አመታት የተገነባም ቢሆን ለማስተንፈስ መላ ይፈልጋል:: ማሰብ ይጠይቃል:: ኃይለማርያምም፤ ሌሎችም፤ በተለይ የህወሐት አንጋፋ ሰዎች፤ ይህ ከግለሰብ አቅም በላይ እንደሆነ ዘግይቶም ቢሆን ይገባቸዋል ወይም አንዳንዶቹ ሁኔታዎች እንደገባቸው ይመሰክራሉ:: ነገር ግን á‹« የመለስ የአማካይነት ጉልበትና በጥንቃቄ የተደረደሩትን ተጻራሪ ጥቅሞች፤ ግጭቶች፤ ምንነት፤ ባህሪያትና ሊያመጡ የሚችሉትን ተጽዕኖ ማወቅ ብቻ ሳይሆን በደንብ ‘መብላትም’ ይፈልጋል:: ይህን ያደረገ የኢህአዴግም የህወሀትም መሪ መኖሩን እጠራጠራለሁ:: ይህ ክህሎት ያለው ግለሰብ ውይም ቡድን ምናልባትም ቦታ አላገኘም ይሆናል::ወይም ደግሞ ይህንን ከመጋረጃ ጀርባ ሆኖ ለመፈጸም እያቀደ ሊሆን ይችላል:: በነዚህ የውስጥ ችግሮች ምክኒያት ኢህአዴግና ሕወሀት እራሳቸውን ለማፍረስ ተቀባብለው ተቀምጠዋል::

ሁለተኛውም ከዚህ ጋር በጽኑ የተያያዘ ነው:: ውጫዊ ግፊቱን መቋቋም የሚያስችል አቅም አጥቷል:: ይህ አደገኛ ሁኔታ ላይ አድርሶታል:: አሁን በተለያዩ የአውሮፓና የአሜሪካ ከተሞች የሚደርሱባቸው ግማሽና ሙሉ ሽንፈቶች በዋነኛነት እንደ አንድና ወጥ የሚያስተባብር በመጥፋቱ ምክኒያት እየተከሰተ ያለ ነው:: መናበብ እንዳልተቻለ ይታያል:: ከወትሮው የተለየና ጠንካራ የተቃዋሚዎች እንቅስቃሴ መኖሩ ግልጽ ነው:: ነገርግን ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንዲህ አይነቱን ጥንካሬ መመከት ችለው ታይተዋል::ቴዎድሮስ አድሃኖምም የውጭ ጉዳዩን መስሪያቤት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን ያህል አላወቁትም ይሆናል:: ወይም ደግሞ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አይነት ጥልቅ የፖለቲካ አመራር የሚፈልግ ተቋም የሚሆን አይነት የግል ስብዕና የላቸውም ይሆናል:: ይህ በርግጥም ከዚህ በፊት ካላቸው የቴክኒካል ዘርፍ ብቃት ጋር አያይዞ በማየት ብቻ አይደለም:: በዲፕሎማሲው ስራ ሳይንሳዊው ቴክኒክ የጤና ጥበቃውን ያህል ቦታ የለውም:: ይበልጡኑ የፖለቲካ ጥልቀትና የአመራር ጥበብን ይፈልጋል:: በተለይ ደግሞ በእንደዚህ አይነቱ የኢህአዴግ/ህወሀት ሰኔና ሰኞ::

በዚህ ላይ በሀገር ውስጥ የስልጣን እርከንም ኃይለማርያምና ካብኔያቸው የ’ባለራዕዩን’ ያህል መቆጣጣር አቅቷቸዋል:: ለምሳሌ የቤንሻንጉሉና ሌሎች ቀውሶች እየተፋፋመ ላለው ተቃውሞ የበለጠ ድጋፍ ሰጥቷል:: የአለም አቀፍ ድርጅቶችም ድምጻቸውን ክፍ አድርገው ጥሪ ማድረግ ጀምረዋል:: ይህንን አጠቃላይ ሁኔታ አንብቦ ምላሽ መስጠት መቻል በኢህአዴግ ስነልቦና ሽንፈት ነው:: ስለዚህ ተመራጩ አካሄድ ‘ማስቀየስ’ ነው:: የፖለቲካውን የትኩረት አቅጣጫ ማስቀየር:: ከዚህ አንጻር የከሸፉ የትኩረት ማስቀየሪያዎች በርካታ ከመሆናቸው የተነሳ መስራቱም ያጠራጥራል::ለዚህ ሲባልም በደንብ የተገነባ ብቸኛ ጠንካራ ምክኒያት እስካሁን የለም:: ምናልባት የታሰሩ ሰዎችን መፍታት አንድ አማራጭ ሊሆን ይችላል:: ያም ሆኖ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የታሰሩት የህዝብ ትኩረት ያለባቸው ግለሰቦች/ርዕዮት እስክንድር በቀለ ገርባ የመሳሰሉት/ ተደራድሮ ለመፈታት ምንም አይነት ተነሳሽነት አላሳዩም:: ውብሸት ተደራድሯል ተብሏል:: ነገር ግን የህዝብ ትኩረት በእርሱ ላይ ለመገንባት የተደረገው ሙከራ ከሽፏል:: ስለዚህም እሱን ለመልቀቅ የሚያመንቱትም ውጥረት ስለማይቀንስላቸው ነው::

ይህ በእንዲህ እያለ ዋነኞቹ ሀገራዊ ጥያቄዎች ማለትም የሰባአዊ መብቶች ጥሰትና ግጭቶች፤ እያደር ወደኋላ የተጓዘው/የሚጓዘው የህግ የበላይነትና የዲሞክራሲ ጭላንጭል፤ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ እገዳውና አፈናው፤ በፖለቲካና ሲቭክ ድርጅቶችና አባላቶቻቸው ላይ የሚደረገው ዕቀባ እንግልትና ማጎሳቆል፤ የጸረ ሽብር ሕጉና ሌሎች በርካታ ያልተወራላቸው ህጎች፤ እየተጠናከረ ያለው ግልጽ አድሎ ዘረኝነትና ሙስና*፤ በሀይማኖት ተቋማት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት፤ በተለይም የኑሮ ውድነት፤ እንደዚሁም የከተማና የገጠር ስራ አጥነትና የኢኮኖሚ ነክ ተግዳሮቶች፤ ሌሎችም ተደማምረው የህዝቡን አጠቃላይ ብሶት ክፍ አድርገውታል::

በዚህ ሁኔታ የኃይለማርያም መንግስት ለአንድ አይነት አላማና በሀገር አቀፍ ራዕይ ዙሪያ የሀገሪቱን ሀዝቦች ማስተባበር እንደተሳነው ግልጽ እየሆነ ነው:: ይህ ምን ይዞ ይመጣል የሚለው ገና ያልተፈታ ጥያቄ ነው::ያለው ሲስተም ህወሐት ያለምንም ተቀናቃኝ ለጥያቄዎች ሁሉ መልስ እንዲሰጥ ተደርጎ ነው የተገነባው:: አሁን ያ አቅም ህወሐትም ውስጥ ካለው ሃይል ይልቅ እጅግ ዝቅ ያለ ግንዛቤ ባለው ሀይል እጅ ገብቷል የሚል ስሞታ አለ:: ይህ ደግሞ ሄዶ ሄዶ ለወሳኝ የህዝብ ጥያቄዎች ያለተገባ በተን/button/ በመጫን ችግሮቹን ማባባሱ አይቀርም:: እንደዚሁም ራሱን የማጥፋት ሂደቱን በከፍተኛ ሁኔታ ሊያፋጥን ይችላል::::

ተወደደም ተጠላም ኢህአዴግም፤ ሕወሀትም የመለስን ያህል ተጽዕኖ የሚያሳርፍ መሪ ማጣቱ ብቻ ሳይሆን መናፈቁ ግልጽ እየሆነ ነው::መለስ ባያሳምን እንኳን ለጊዜውም ቢሆን አብዛኛውን ቀለም ቀመስ ኤሊትና ዲፕሎማቶች ሊያጠራጥር የሚችል ቃለመጠይቅ በመስጠት፤ ፖለቲካዊ ውጥረቶችን በተደጋጋሚ የማብረድ ዕውቀት ተክኖት ቆይቷል::

ይህን ክፍተት በመታዘብ ይመስላል ወዳጄ ኪሩቤል/Kirubel Teshome/ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኃይለማሪያም ደሳለኝ ለተከማቹ የህዝብ ጥያቄዎች ለሀገር ውስጥና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን መቼ መልስ መስጠት እንደሚጀምር ጠይቆ ነበር::በርግጥም ኪሩቤልና ሌሎች ወዳጆች በቃለ ምልልሱ ከኢህአዴግ ባህሪይ አንጻር አዲስ ሃሳብና ግንዛቤ ወይም ሂስ መዋጥ እንደማይኖር ጠንቅቀው ይረዳሉ ብዬ አምናለሁ:: ይሁንና ኃይለማሪያምና እሱን የሚያሾረው/ሩት የመጋረጃ ውስጥ መሪ/ዎች ከሀገር ውስጥ ይልቅ ለውጭ መገናኛ ብዙሃን መልስ መስጠትን በቅድሚያ ተያይዘውታል:: እስካሁን የተናጠል የቃለመጠይቅ ዕድል ለአልጄዚራና ለፍራንስ 24 ቴሌብዥኖች ሰጥተዋል:: ኢትዮጵያን በሚመለከት ወይም በሀገር ውስጥ ጉዳዮች የፕሬስ ኮንፈረንስ ገና አልተሰጠም:: እንዲያም ሆኖ በግሌ የኃይለማሪያምን የማሳመን ብቃት ከምጠብቀውም በታች ዝቅተኛ ሆኖ አግኝቼዋለሁ::

በተለይ ለአንድ የፍራንስ ቫሃን ካት(ፍራንስ 24) ቴሌብዥን ጥያቄ የሰጠው መልስ አስተዛዛቢ ነበር:: ጥያቄው የኬንያውን ፕሬዝዳንታዊ ተመራጭ እሁሩ በአለም አቀፉ ፍርድ ቤት መጠርጠርና ክስ ሊመሰረትበት መሆኑን በተመለከተ ምን ይሰማሃል? የሚል ነበር::ኃይለማሪያም ‘ኬንያውያን ከመረጡት ከወንጀል ነጻ ሊደረግ ይገባል’ የሚል ዓይነት አንደምታ ያለው መልስ ሰጠ::

በአለም አቀፉ ፍርድ ቤት ላይ በርካታ የሞራል፤ የአግባብነት፤ ወጥ ያልሆነ የህግ የበላይነት አስራር፤ የተፈጻሚነት ወሰን ትኩረትና ሌሎችም በምክኒያት የተደገፉ ጥያቄዎች ማንሳት ይቻላል::ተገቢም ነው:: ለምሳሌ የዩስ አሜሪካና የእስራኤል መንግስታትና ባለስልጣናቱ በማናለብኝነት የሚፈጽሟቸውን ጉዳዮችና ሰቆቃዎችና ወንጀሎች የተጠያቂነት ብርሃን አለማግኘታቸውን መጥቀስ ተገቢ ነው:: ጥቂት ብሄርተኛና የአይዲዎሎጂ ልዩነት ያላቸው መሪዎች እንድሚያደርጉትም ይህን ሁኔታ በማንሳትም ለመከላከል ያህል ምላሽ መስጠት ይቻላል:: ያም ሆኖ በመሰረቱ ወይም በመርህ ደረጃ ችግሩ በህግ መዳኘቱ ተገቢ እንደሆነ አምኖና ለይስሙላም ቢሆን በህግ የበላይነት ላይ ቁርጠኝነት አሳይቶ መሆን ነበረበት::

ከዚህ ሌላ ከኬንያ የህግ ተቋማት አቅም በላይ ስላልሆነና የኬንያ የፍትህ ተቋማትን ሉዓላዊነት ይጫናል ብሎም ለመከራከር መከራከርም ይቻላል::ኃይለማርያም ይህን አላደረገም::ይባስ ብሎ የርዕዮት የቅርቡን አለም አቀፍ ሽልማትና የመንግስቱን ምላሽ በተመለከተ ሲጠየቅ ከርዕስ ወጥቶ ሲጠፋ ይስተዋላል:: ይህም ከወዲሁ የመለስን አለም አቀፍ ተቀባይነትና ምናልባትም ‘አሳማኝነት’ በኩረጃ እንደማይገኝ አመላካች ሆኗል::

ይህ መሪ ማጣት/መለስን ናፍቆት/ከድርጅቱ ከኢህአዴግ/ህወሀት ክበብ ችግርነት ወጥቶ የሀገሪቱም መሆኑ አይቀርም:: ለጊዜው የተረጋጋ የመሰለው ስልጣን ክፍተት ማሳየቱ እንደማይቀር ቀድሞውኑ ብዙዎቻችን ተሰምቶን ነበር::ያም ሆኖ አሁን አዲስ ሁኔታ በመሰራት ላይ ነው:: የህዝብ ሁለንተናዊ ብሶት አይሏል:: ኃይለማርያምና ካቢኔውም ቁልፎቹን አላወቋቸውም:: ይህ ባለበት ሁኔታ ሲቀጥልም ሆነ ያልተገባ ቁልፍ ሲጫኑም አደጋ አለው::ይህ ስጋት በአንድ በኩል የተቃዋሚው የውስጥ ችግሮች በሌላ በኩል ለጊዜው በተለይ ከኢህአዴግ/ህወሐት ውጭ ባሉ የፖለቲካ ኃይሎች ግፊት እንደማይከሰት ሙሉ እርግጠኛነት እንዲሰማን አድርጎን ቆይቷል::

አሁን ይህን እምነት እንደገና ማየት ተገቢ ነው:: ተቃዋሚዎች ራሳቸው በገነቡት አካሄድ ስርዓቱን የመጣል ብርታትና ቁመና ግን እስከዛሬም አልገነቡም:: ከዚህ ይልቅ በሁለት ምክኒያት ይህ ስርዓት ውድቀቱን እያጠናከረ ይገኛል:: አንደኛው የህዝቡ ሁለንተናዊ ብሶት ነው:: ሁለተኛው የመለስን ቁመናና የኃይል ክምችት የመሸከም አቅም ያለውና /የተሽክመ ግለሰብ ወይም ወጥና የሚናበብ ቡድን በመጥፋቱ ነው:: ስርዓቱም አውቆም ይሁን ሳያውቅ ለዚህ አይነት ግለሰብና ቡድን ብቻ የተሰራ ነው::

ምናልባት ይህንን ግልጽ ለማድረግ ያህል ከዚህ የሚከተለውን ማየት ያሻል:: መለስ በዘመናዊ የኢትዮጵያ የመንግስትነት ታሪክ (በተለይም ከቅርቡ የሪፐብሊክነት ታሪክ አንጻር) የመንግስትን ኃይል ከእንግዲህ በማይደገም መልክ በፈላጭ ቆራጭነት ተቆጣጥሮት ነበር::ይህን እድል ኃይለማርያም ይቅርና የትኛውም የህውሀት አንጋፋ መሪ ሊያገኘው የማይችለው በቀላሉ የማይደገም የታሪክ ክፍል ነው:: የ1993ቱን የህወሐት ክፍፍል ተከትሎና 1997ቱን የምርጫ ውጤት አስታኮ መለስ በብቸኝነት የተለያዩ የመንግስትም የፓርቲም ቁልፍ ስልጣንና ኃይል ያለተቀናቃኝ አደላዳይና አስማሚ ሆኖ ብቅ አለ::

የተፋጠጡ ፍላጎቶች ያላቸውን ግለሰቦች ለግል ስልጣን ማስጠበቂያነት ሚዛን ሳይዛባ ደርድሮ ዳማ ይጫወት ነበር:: እኒህ የዳማ ጠጠሮች/ቆርኪዎች/ እርስ በርስ መጠባበቃቸውና ፍጥጫቸው እንደቀጠለ ነው:: ከውስጥ አስማሚ ኃይል የመውጣቱ ነገር ያበቃለት ይመስላል:: የኃይለማርያምን ብቃትና ተቀባይነት ከውስጥም ቢሆን ገና አልረጋም:: ቀድሞውኑ በስመ መለስ ምርጫ እንጂ አስማሚ ሆኖ አይደለም::መለስ ደግሞ ብቃት ያለው ሰው እንዲተካኝ ብሎ አስቦ አያውቅም:: እንዲያውም ደካማ ነገር ግን ‘ብቁ መሳይ’ ፈልጎ ነው የሚያስቀምጠው::ሳይታሰብ ግን ኃይለማርያም የዕድል ዛር ቆመችለት:: ተተኪ ተብሏልና እሱን ከማስቀመጥ ውጭ ለጊዜውም ቢሆን ምርጫ አልነበረም::

አሁን አደጋው እነዚህ በተቃርኖ የተደረደሩት ኃይላት በውስጥ ያላቸው ፍጥጫና ግጭት ከፍ ሊል ይችል እንደሆነ ነው::የፓርቲው ዲስፕሊን ቀስ በቀስም ቢሆን ቀንሷል:: በአደባባይ ሳይቀር ምልክቶች መታየት ጀምረዋል:: ለምሳሌ የቅርቡ የተወካዮች ምክርቤት ስብሰባን እንደአስረጂ መውሰድ ይቻላል:: መቀሌ ላይ በቅርቡ ህወሐት ወደ ስብሰባ የተመለሰውም የቀድሞውን ተጽዕኖ መፍጠር እንዳልቻሉ በመገንዘባቸው ነው ተብሏል::

የሚንደረደረው የህዝብ ሁለንተናዊ ብሶትና የኢህአዴግ/ህወሐት ራስ አጥፊ ድክመቶች አስፈሪ ናቸው:: ከሁሉ በላይ የሚያስፈራው ደግሞ የኢህአዴግና የመንግስት አመራርም ሆነ በተቃራኒው ያሉት ፖለቲከኞች ይህን የለውጥ ፍላጎት ለህዝብና ለሀገሪቱ ጥቅም እንዴት መምራት እንደሚችሉ አለማወቃቸው ብቻ ሳይሆን ዝግጅት አለማድረጋቸውም ጭምር ነው:: አድርገውም እንደሆን አላሳመኑንም::የኃይለማርያም መንግስት ፈተናም ይህን በትክክል ተረድቶ በሚወጥነው ብልሃት ላይ ይወሰናል:: ይህ ካልሆነ ህወሐት የመጨረሻዎቹን ሙከራዎች ወደማድረግ ይንቀሳቀሳል::ምናልባትም ደብረጽዮን ለዚህ ስራ ሊታጭ ይችላል::ጨረስኩ:: በቸር ያቆየን!

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on May 2, 2013
  • By:
  • Last Modified: May 2, 2013 @ 2:40 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar