www.maledatimes.com ** ጴጥሮስ ይችን ሰዓት! - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

** ጴጥሮስ ይችን ሰዓት!

By   /   May 2, 2013  /   Comments Off on ** ጴጥሮስ ይችን ሰዓት!

    Print       Email
0 0
Read Time:17 Minute, 50 Second

** ጴጥሮስ ይችን ሰዓት!

“አዬ፣ ምነው እመ ብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
እስከመቼ ድረስ እንዲህ፣ መቀነትሽን ታጠብቂባት?
ልቦናሽን ታዞሪባት?
ፈተናዋን፣ ሰቀቀኗን፣ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
አላንቺ እኮ ማንም የላት…”
.
.

የኑሮ የሕይወቱን ዳፋ፣ ከፍ ዝቁን… ውጥንቅጡን፣
ከደጅ ቆሜ ስታዘብ፣ — ከቦታዬ ተተክዬ…
….ስቃኘው ዙሪያ ገባውን፣
ቀልቤን፥ እጀማው መሀል ጥዬ…
ስሳቀቅ፣ በጣር ስማቅቅ፣ በሰቀቀን ስኮማሸሽ፤

አገር በቀል ፋሽስት ወርሮሽ፣ አገር በቀል… ናጅ፣ አቆርቋዥ፣
አገር በቀል ሽፍታ ጠምዶሽ፣ አገር በቀል… እሾህ፣ መዝማዥ፣
ስር ሰድዶ ሲያስጨንቅሽ ባይ…
…አገር በቀሉ መከራሽ፤
ለወንዝ አፈራሽ ሰቆቃሽ፣ — አላይ ስትሺ – አጥባቂ፣
ለወንዝ አፈራሽ ውጋትሽ፣ — ነቃይ ስትሺ – ሰባቂ፣
ለወንዝ አፈራሽ ቁስልሽ፣ — አጃይ ስትሺ – ሰቅሳቂ፣
ለወንዝ አፈራሽ ክፍተትሽ፣ — ደፋኝ ስትሺ – ቦርቃቂ፣
….ሲቸርሽ ሳይ ስመለከት፥
በቁጭት ስነድ’፣ ስቃትት፣

ላልረዳሽ፣ ችዬ ላልደርስሽ፣ ስጋዬ ሳይጨልም ሰንፎ፣
….ስላንቺ ወድቆ ከደጃፍ፣ ስለፍቅርሽ ተዘርግፎ፣
በፋሽስት ሴራ ተቀፍፎ፤ በጭካኔያቸው ተጠልፎ፤
ውስጥ ውስጡን በሚጮህ ‘እህህ….’፥ ውስጥ ውስጡን ስተነፍሰው፣
በማይገለጥ ብልጭታ፣… ውስጥ ውስጡን ጥርሴን ስነክሰው፣
ውስጥ ውስጡን ወገቤን ይዤ፣ ውስጥ ውስጡን ላንቺ ተክዤ፣
ችዬ ላልረዳው ስቧትር፣ በተስፋ መቁረጥ ፈዝዤ…
ውስጥ ውስጡን ብሶት አርግዤ፣ ውስጥ ውስጡን በምጥ ተይዤ፤

ስመለከተው ላይ ታቹን፣ ስቃኝ ከ… እስከ…. ውን ቆሜ፣
ከቦታዬ ላይ ተዱዬ፣ በአሳር በመከራው ዝዬ፣
በግሳንግስ ሰልፍ ታምሜ፣ በስንክሳር መአት ደክሜ፤
ግልሙትና ውስልትና፤ ሙስና፣ ግርፊያ አፈና…
….ስጋት፣ ንጥቂያ፣ ሙጭለፋ፣
እስር፣ እንግልት፣ ግድያ፤… ቅሚያ፣ ዘለፋ ዘረፋ፣
እዚህም እዚያም ተበታትኖ፣
ልጅ አዋቂ ሳይለይ ሰፍኖ፣ ወንዱን ሴቱን አብከንክኖ፤
በእህህ…. ብታዘበው፣ ታዝቤ ችዬ ብውጠው፣
ምንም ችዬ ላላመጣ!
ስጋ ሳይኖረኝ ‘ሚቀላ፣ ደም ሳይኖረኝ የሚነጣ፤

ትዝብቴን ቀኑበት መሰል፣ ከጥርሳቸው መሀል ወሸቁት፣
መንሽ መሮውን አነሱ፣ ነቃይ ጎታቹን ሰበቁ፣
…ሊመነጉሉኝ ዶለቱ፣ ሊመነጉሉኝ ታጠቁ፣
ቦታዬን ሊነቀንቁ፣ በደቦ ተነቃነቁ፤
.
.

“እና ፈርቼ እንዳልባክን፣ ሲርቀኝ የኃይልሽ ውጋገን
አንቺ ካጠገቤ አትራቂ፣ በርታ በይኝ እመ ብርሃን
ቃል ኪዳኔን እንዳልረሳት፣ እንዳልዘነጋት ኢትዮጵያን፡፡
አዎን፣ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እሸሸግበት ጥግ አጣሁ…..”
.
.
ኑሮው ንሮ፣ ጣሪያ ደርሶ፣ ‘ሚላስ ‘ሚቀመስ ቸግሮ፣
ጉልበት፣ ሰውነት ሰልሎ፣ ሆድ ባር ባር ብሎ፣ ነፍሮ፤
ጭካኔ ነግሶ ገንኖ፣… እርስ ከራስ አጨካክኖ፣
ራስ ከራስ ሲያጋድል፣ እርስበራስ ሲያበዳደል፣
ከዓለም በቃኝ ሲያቀላቅል፣… እጅን ከእግረሙቅ ሲያውል፣
ዜና ዘገባ ሲነውር፣… ማንበብ፣ መፃፍ ሲታጎሉ፣
ጥያቄ ማንሳት ሲያሳፍር፣…
ሀሳብ መግለጽ ሲያሸማቅቅ፣… ማወቅ መሰልጠን ሲያጉላሉ፣

ልጅ ተወልዶ ሲሟሽሽ፣ እናትም አብራ ስትጫጭ፣
ባል ከሚስቱ ሲበዳደል፣ እራስ ከራሱ ሲገጫጭ፣
ገሚሱ ጥፍር አብቅሎ ገላ ከገላ ሲናጭ፣
አሲድ ዱላ ሲበረቱ፣ ደም ሲያንቆረቁር፣ ሲራጭ፣
‘ሆድ ሊተረተር በከካ’፣ ላንቃ ሊሰነጠቅ በጥም፣
— በመጠጥ ውሃ ናፍቆት፣ ሲደርቅ ሲዝል ሲታመም፣
ሰውነት ሲሰልል፣ ሲቃትት፤ አካል ሲነትብ፣ ሲዘም፤
‘ለበሰበሰ እንደማዝነብ’… ያ’ፈር ቤት ሲወድቅ ከገላ፣
– ኀሰሳ-ሌላ ሲባከን፣ በእጅ ተንዶ ከለላ…
በልቶ መድገሙ ሲበርቅ፣ እንኳንስ አትርፎ መቸር፣
እንኳን ለሌላ እርጥባን፣ ለራስም ኮሮጆ ሲጠርር፣
በጠኔ እንቅልፍ ሳቢያ፣ አገር ምድሩ ሲንኳረር፥
.
.
“ያቺን ነው ኢትዮጵያ የምላት
እመ ብርሃን እረሳሻት?
ያቺን የልጅነት የምሥራች? የሕፃንነት ብሥራት
የሣቅ የፍንደቃ ዘመን፣ የምኞት የተስፋ ብፅአት
ያቺን የልጅነት እናት?
አዛኚቱ እንዴት ብለሽ፣ ጥርሶችሽን ትነክሺባት?”
*
*
*
“ሕይወቴ እምነትሽን ጸንሶ
ሥጋ ፈቃዴ ተድሶ
ለሕንፃሽ መዲና ቆሞ፣ ለክብርሽ ድባብ ምሰሶ
ሥሜን በሥምሽ ሰይሜ፣ ሆነሺኝ የእምነቴ ፋኖስ
ለዋዜማሽ – ግሸን ማርያም፣ ለክብርሽ – ደብረ ሊባኖስ
ስሮጥ፣ በወንበሩ አኖርሺኝ፣ በአንበሳው በቅዱስ ማርቆስ“
ታዲያ ዛሬ ቤቴ ሲናድ፣ ከምትሰጪኝ የብርታት ጦስ…
.
.
ምነው ያኔ ባልሰጠሽኝ፣ ቤት ለመጠሪያ፥ መጦሪያ፣
– ማረፊያ ቦታ ለቅኝት፣ መጠጊያ ሀውልት ለትዝብት፤

ትዝብቴን ቀኑበት መሰል፣ ከጥርሳቸው መሀል ወሸቁት፣
መንሽ መሮውን አነሱ፣ ነቃይ ጎታቹን ሰበቁ፣
…ሊመነጉሉኝ ዶለቱ፣ ሊመነጉሉኝ ታጠቁ፣
ቦታዬን ሊነቀንቁ፣ በደቦ ተነቃነቁ፤

.
.

ባክሽ እመ ብርሃን ይብቃሽ፣ ባክሽ ምስለ ፍቁር ወልዳ
ጽናት ስጪኝ እንድካፈል፣ የእናቴን የኢትዮጵያን ፍዳ፣
ከነከሳት መርዝ እንድቀምስ፣ ከነደደችበት እቶን
የሷን ሞት እኔ እንድሞታት፣ ገላዋ ገላዬ እንዲሆን፡፡ …..
አዎን፣ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እምፀናበት ልብ አጣሁ።”

ማስታወሻ: ይህ ግጥም የተጻፈው በባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ቆስቋሽነት (inspiration)ና በ“ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት” ተውኔት ጭብጥ መሪነት ነውና ክብሩ ሁሉ ለጋሽ ፀጋዬ ይሁን። ከላይ በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ያሉት በሙሉ ከዋናው የጋሽ ፀጋዬ ግጥም ላይ የተወሰዱ ሲሆኑ እኔ የጨመርኳቸው ከት/ተ ጥቅስ ውጭ ያሉትን ነው። የጋሽ ፀጋዬን “ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት”ን ለማንበብ ይህን ይከተሉ:
/ዮሐንስ ሞላ/

ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት
/ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን/
————
አዬ፣ ምነው እመ ብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
እስከመቼ ድረስ እንዲህ፣ መቀነትሽን ታጠብቂባት?
ልቦናሽን ታዞሪባት?
ፈተናዋን፣ ሰቀቀኗን፣ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
አላንቺእኮ ማንም የላት….
አውሮጳ እንዲሁ ትናጋዋን፣ በፋሽስታዊ ነቀርሳ
ታርሳ፣ ተምሳ፣ በስብሳ
ሂትለራዊ እባጭ ጫንቃዋን፣ እንደኮረብታ ተጭኗት
ቀና ብላ እውነት እንዳታይ፣ አንገቷን ቁልቁል ጠምዝዟት
ነፍሷን ድጦ ያስበረከካት
ሥልጡን፣ ብኩን፣ መፃጉዕ ናት፤ ….
እና ፈርቼ እንዳልባክን፣ ሲርቀኝ የኃይልሽ ውጋገን
አንቺ ካጠገቤ አትራቂ፣ በርታ በይኝ እመ ብርሃን
ቃል ኪዳኔን እንዳልረሳት፣ እንዳልዘነጋት ኢትዮጵያን፡፡
አዎን፣ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እሸሸግበት ጥግ አጣሁ
እምፀናበት ልብ አጣሁ
እማማ ኢትዮጵያን መንፈሴ፣ ተፈትቶ እንዳይከዳት ሠጋሁ …
አዋጅ፣ የምሥራች ብዬ፣ የትብት ምግቤን ገድፌ
ከእናቴ ማኅፀን አርፌ
ከአፈርዋ አጥንቴን ቀፍፌ
ደሜን ከደሟ አጠንፍፌ
ከወዟ ወዜን ቀፍፌ
በሕፃ እግሬ ድሄባት፣ በህልም አክናፌ ከንፌ
እረኝነቴን በሰብሏ፣ በምድሯ ላብ አሳልፌ
ከጫጩት እና ከጥጃ፣ ከግልገል ጋር ተቃቅፌ፤
በጋው የእረኛ አደባባይ፣ ክረምት እንደወንዙ ፍሳሽ
በገጠር የደመና ዳስ፣ በገደል ሸለቆ አዳራሽ
ከቆቅ እና ከሚዳቋ፣ ከዥግራ ጠረን ስተሸሽ
በወንዝ አፋፍ ሐረግ ዝላይ፣ መወርወር መንጠልጠል ጢሎሽ
ከፍልፈል ጋር ሩጫ ስገጥም፣ ከቀበሮ ድብብቆሽ
ከናዳ ጫፍ ሣር አጨዳ፣ ለግት ላሜ ትንሽ ግጦሽ
ለጥጃዬ የሌት ግርዶሽ
ለጥማድ በሬዎች ራት፣ ለማታቸው ትንሽ ድርቆሽ
ለግልገሌ ካውሬ ከለል
እማሳው ሥር ጎጆ መትከል
ለፀሐይ የሾላ ጠለል፣ ለዝናብ የገሳ ጠለል
ውሎ የንብ ቀፎ ማሰስ፣ ያበባ እምቡጥ ሲፈነዳ
የግጦሽ ሣር ሲለመልም፣ ሲሰማሩ ሰደድ ሜዳ
አዝመራው ጣል ከንበል ሲል፣ ከብቱ ለሆራ ሲነዳ
ፈረስ ግልቢያ ስሸመጥጥ፣ ከወፎች ዜማ ስቀዳ
ልቤ በንፋስ ተንሳፎ፣ በዋሽንት ዋይታ ሲከዳ …..
ያቺን ነው ኢትዮጵያ የምላት
እመ ብርሃን እረሳሻት?
ያቺን የልጅነት የምሥራች? የሕፃንነት ብሥራት
የሣቅ የፍንደቃ ዘመን፣ የምኞት የተስፋ ብፅአት
ያቺን የልጅነት እናት?
አዛኚቱ እንዴት ብለሽ፣ ጥርሶችሽን ትነክሺባት?
ሥሜን በሥምሽ ሰይሜ፣ ባገልግሎትሽ ስዋትት
ከዜማ ቤት እቅኔ ቤት፣ ከድጓ ቤት እመጻሕፍት
ካንቺ ተቆራኝታ ዕድሌ፣ ካንቺ ተቆራኝታ ነፍሴ
ከቀፈፋ ደጀሰላም፣ ከቤተልሔም ቅዳሴ
እኰ፣ ቀፎ ዳባ ለብሶ
ቅኔ ዘርፎ ግስ ገሦ
መቅደስ አጥኖ ማኅሌት ቆሞ
በልብስ ተክህኖ አጊጦ፣ በብር አክሊል ተሸልሞ
እመ ብርሃን ያንች ጽላት፣ ነፍስ ላይ በእሳት ታትሞ
የመናኒው ያባ ተድላ፣ ረድ ሆኜ፣ አብሮኝ ታድሞ
ሕይወቴ እምነትሽን ጸንሶ
ሥጋ ፈቃዴ ተድሶ
ለሕንፃሽ መዲና ቆሞ፣ ለክብርሽ ድባብ ምሰሶ
ሥሜን በሥምሽ ሰይሜ፣ ሆነሺኝ የእምነቴ ፋኖስ
ለዋዜማሽ ግሸን ማርያም፣ ለክብርሽ ደብረ ሊባኖስ
ስሮጥ፣ በወንበሩ አኖርሺኝ፣ በአንበሳው በቅዱስ ማርቆስ
ታዲያ ዛሬ ኢትዮጵያ ስትወድቅ፣ ከምትሰጪኝ የፍርሃት ጦስ
ምነው በረኝነት እድሜ፣ ዓይኔን በጓጎጣት የሎስ
የጋኔል ጥንብ አንሳ ከንፎ፣ ወርዶ በጨለማ በርኖስ
ባክሽ እመ ብርሃን ይብቃሽ፣ ባክሽ ምስለ ፍቁር ወልዳ
ጽናት ስጪኝ እንድካፈል፣ የእናቴን የኢትዮጵያን ፍዳ፣
ከነከሳት መርዝ እንድቀምስ፣ ከነደደችበት እቶን
የሷን ሞት እኔ እንድሞታት፣ ገላዋ ገላዬ እንዲሆን፡፡ …..
አዎን፣ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እምፀናበት ልብ አጣሁ፡፡ …..
,,,,,,,,,,,,,,,, /ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን/
/ከጴጥሮስ ያቺን ሰዓት ፣ ታሪካዊ ተውኔት የተቀነጨበ/
ምንጭ፤ “ታሪካዊ ተውኔቶች” ጸጋዬ ገብረ መድኅን
አሳታሚ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ፤ 2003ዓ.ም

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on May 2, 2013
  • By:
  • Last Modified: May 2, 2013 @ 3:15 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar