www.maledatimes.com “መሪ አጣን” እያሉ ማላዘን ይቁም መሪነት እና የመሪነት ወለፈንዲዎች ታደሰ ብሩ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

“መሪ አጣን” እያሉ ማላዘን ይቁም መሪነት እና የመሪነት ወለፈንዲዎች ታደሰ ብሩ

By   /   May 2, 2013  /   Comments Off on “መሪ አጣን” እያሉ ማላዘን ይቁም መሪነት እና የመሪነት ወለፈንዲዎች ታደሰ ብሩ

    Print       Email
0 0
Read Time:51 Minute, 7 Second

መግቢያ

 

ማኅበራዊ ለውጥንና እድገትን የሚመለከቱ ዓላማዎች በአንድ ወይም በጥቂት ሰዎች ጥረት የሚሳኩ አይደሉም። እነዚህ ትላልቅ ዓላማዎች እንዲሳኩ የብዙ ሰዎች የተባበረ ጥረት ያስፈልጋል። በርካታ ሰዎችን ለእንዲህ ዓይነቶቹ ግዙፍ ዓላማዎች ማነሳሳትና እና ማስተባበር ነው መሪነት (Leadership) የሚባለው።

መሪነትን በአንድ ዓረፍተ ነገር እንተረጉመው ቢባል የሚከተለውን የመሰለ ዓረፍተ ነገር እናገኛለን።

 

መሪነት፣ ሰዎች የተለሙትን ግብ ለማሳካት የሚተባበሩዓቸውን ሌሎች በርካታ ሰዎች ቀስቅሰው አሳምነው፤ አደራጅተው፣ መንገድ እያሳዩ ለተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚያነሳሱበት እና እንቅስቃሴውንም የሚያስተባብሩበት ሂደት ነው።

 

በአንዳንድ ውይይቶች “መሪነት” (Leadership) ከ መሪ (Leader) ጋር ሲደባለቅ ይስተዋላል። መሪነት ከላይ እንደተገፀው ሂደት (Process) ሲሆን መሪ ግን በዚህ ሂደት ውስጥ ያለን አንድ ወይም ጥቂት ወሳኝ ሰዎችን ይመለከታል።

ዓላማን ለማሳካት፣ ገንዘብና ቁሳቁስ የመሳሰሉ ግብዓቶችንም ማቀናጀት የሚጠይቅ ቢሆንም እንኳን ስለመሪነት ስንነጋገር ዋነኛ ትኩረታችን ሰው ላይ ነው።  ሰው ከማናቸውም ሌሎች ግብዓቶች (ለምሳሌ ገንዘብ፣ ቁሳቁስ፣ መረጃ፣ ንብረት) መወዳደር በማይችል መጠን ውስብስብ ነው። ሰውን መምራት ሌሎች ግብዓቶችን ከማስተዳደር የከበደ ሥራ ነው።

ኢትዮጵያዊያን በምናደርጋቸው ውይይቶች “ዋናው ችግራችን የመሪ እጦት ነው” የሚል ዓይነት ድምዳሜ መስማት የተለመደ ነው። አንዳንድ ሰዎች አገራችንን ከችግሮች ማውጣት ያልቻልነው በመሪ እጦት እንደሆነ በእርግጠኝነት ይናገራሉ።

በእነዚህ ክርክሮች ውስጥ የተወሰነ እውነት አለ ብለን ብንቀበል እንኳን “ለመሪ እጦትስ የዳረገን ምንድነው?” የሚለውን ተከታይ ጥያቄ ለማንሳት ድፍረት ሊኖረን ይገባል። መሪነትን የተሳካ የሚያደርገው መሪው ብቻ አይደለም። ተከታዮች (The Led or Followers) ለተሳካ መሪነት የሚያበረክቱት ድርሻ ከፍተኛ ነው። መሪ ከምንም ብቅ የሚል ክስተት ሳይሆን ከተመሪዎች የሚወጣ መሆኑና መሪም ተመሪም በአካባቢያው ሁኔታዎች (Conditions) ተጽዕኖ ውስጥ መሆናቸው እና በመካከላቸው ያለው የተግባቦት (Communication) ዓይነት የመሪነትን ጥራት በከፍተኛ ሁኔታ የሚወስን  መሆኑ በማኅበረሰባችን ውስጥ በቂ ግንዛቤ ያገኘ አይመስልም።

ይህንን ጉልህ የግንዛቤ ክፍተት በመጠኑም ቢሆን ለመሙላት ይህ አጭር ጽሁፍ መሪነትን በአራቱ ዋና ዋና ክፍሎች (Components) ለመመርመር ይሞክራል። እነዚህ የመሪነት ክፍሎች ተከታዮች፣ መሪ፣ ተግባቦት እና ሁኔታዎች ናቸው። እግረ መንገዱንም መሪነት ምን ያህል አስቸጋሪ ሥራ እንደሆነ ለማሳየት ከታወቁ የመሪነት ወለፈንዲዎች (paradoxes) ጥቂቱን ለመመልከት ይጥራል። በመጨረሻም “ስኬታማ አመራር /Effective Leadership/ እንድናገኝ ምን እናድርግ?” ለሚለው አስጨናቂ ጥያቄ አንዳንድ የውይይት መነሻ ሃሳቦችን ይሰነዝራል።

 

የጽሁፉ ዋነኛ ዓላማ የውይይት መነሻ ሐሳብ ማቅረብ በመሆኑ ብዙ ሊፃፍባቸው የሚገቡ ሃሳቦችን በአጭሩ ጠቅሶ ያልፋል።

 

ለመሪነት አራት ወሳኝ ነገሮች

መሪነት አራት ዋና ዋና አካላት አሉት – ተከታዮች፣ መሪ፣ ተግባቦት፣እና ሁኔታ። ከአራቱ አንዱ እንኳን ቢጎድል መሪነት የለም።

ተከታዮች

ማንኛውም ሰው መሪ ከመሆኑ በፊት ተመሪ ወይም ተከታይ የመሆኑ ነገር ልጅ ሳይሆኑ ወላጅ መሆን የማይቻለውን ያህል ተፈጥሮዓዊ ህግ ነው። ይህን ሃቅ “መሪ ይወለዳል እንጂ አይሠራም (አይሰለጥንም)” የሚሉ ሰዎች እንኳን ይቀበሉታል። “ለመሪነት የተወለደው” ሰው እንኳን በልጅነቱ የወላጆቹ፣ የአሳዳጊዎቹ፣ የመምህሮቹ ተከታይ ሆኖ ማደጉ  ግድ ነው።

አንዳንድ ሰዎች ለመሪነት፣ ብዙዎች ደግሞ ለተከታይነት ተፈጥረዋል የሚለው እሳቤ በተለይ በአገራችን ባይጠፋም ቀስ በቀስ እየከሰመ ያለ አስተሳሰብ ነው።

አሁን ይበልጥ ተቀባይነት እያገኘ ያለው አስተሳሰብ ተከታዮቹ ያሉት፤ ራሱን ለቡደኑ፣ ለዓላማውና ለሁኔታዎች ተስማሚ በሆኑ ባህሪያት ያነፀ፤ አና ሁኔታዎች የተመቻቹለት ማንኛውም ሰው መሪ መሆን ይችላል የሚለው እሳቤ ነው። በዚህ እሳቤ መሠረት መሪ የሚወጣው ከተከታዮች ነው።  በዘመናዊ ማኅበረሰብ ውስጥ የድርጅትም ሆነ የአገር መሪዎች መሪ ከመሆናቸው በፊት በተከታይነት ልምድ ማካበት ይኖርባቸዋል። ጥሩ መሪዎች የጥሩ ተመሪዎች ውጤት ናቸው።

በዚህ እሳቤ መሠረት ጥሩ አመራር እንዲኖር ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ – ምናልባትም ዋነኛው – የጥሩ ተከታዮች መኖር ነው። ጥሩ ተከታይ በሌለበት ጥሩ መሪ ማውጣት ከባድ ነው።

ጠንካራ ተከታዮች የአመራሩ ምሰሶ ናቸው። መሪያቸው ጠንካራ ጎኖቹን ይበልጥ እንዲያጎለብት፤ ደካማ ጎኖቹን እንዲያሻሽል ማድረግ ይችላሉ። ጠንካራ ተከታዮች መሪያቸው ብቃት ከጎደለው በጊዜ በሌላ የተሻለ ሰው እንዲተካ ማድርግ ይችላሉ። ደካማ ተከታዮች ግን ጠንካራውን መሪ ያደክማሉ።

በአንድ ድርጅት ወይም ማኅበረሰብ ውስጥ የአመራር ድክመት መኖር አለመኖሩ ለማጣራት መደረግ ከሚገባቸው ጥናቶች አንዱ ተከታዮችን መመዘን ነው። ተከታዮችም ቢሆኑ “የአመራር ችግር ገጠመን”፤  “የመሪ ያለህ ” እያሉ ከማማረራቸው በፊት “እኛ እንዴት ያለን ተከታዮች ነን” ብለው ራሳቸውን ቢጠይቁ የተሻለ መፍትሔ ለማግኘት ይረዳል።

ስኬታማ አመራር ለማስፈን የሚረዱ የተከታዮች ባህሪያት ዝርዝር ረዥም ሊሆን ቢችልም ዋና ዋናዎቹ ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል።

 

  • ድርጅታቸው የቆመለትን ዓላማ የሚያስቀድሙ፤ ለዓላማቸው መሳካት ዋጋ ለመክፈል የቆረጡ፤
  • የጋራ ውጤት የሚገኘው በጋራ ጥረት መሆኑን የተረዱ፤ ሳየሠሩ ውጤት ከመጠበቅ አባዜ የተላቀቁ፤
  • ከአድርባይነት ስሜት የተላቀቁ እና ቅነነት ያላቸው፤
  • ለመመራት ዝግጁ የሆኑ፤ መብትና ግዴታዎቻቸውን የተገነዘቡ፤ ለድርጅታዊ ህጎች ተገዥ የሆኑ፤ እና
  • ለመምራት ዝግጁ የሆኑ፤ በራሳቸው የሚተማመኑ፤ ኃላፊነት ለመውሰድ የተዘጋጁ።

መሪ

መሪ መሆን በተከታዮች የሚሰጥ እንጂ “እኔ መሪያችሁ ነኝ” ተብሎ የሚጫን ነገር አይደለም። ተከታዮች ናቸው “እከሌ መሪያችነን ነው፤ እከሊት መሪያችን ናት” በማለት እውቅና የሚሰጡት ወይም የሚሰጧት። መሪነት በምርጫ ውጤት የሚገኝ ነገርም አይደለም። በምርጫ ሊቀመንበር ወይም ፕሬዚዳንት መሆን ይቻላል። ሊቀመንበር ወይም ፕሬዚዳንት መሆን ግን መሪ መሆን ማለት አይደለም። መሪ መሆን የሚቻለው የተከታዮችን ልብ መማረክ ሲቻል ነው።

ጥሩ መሪ ለመሆን የሚያስፈልጉ ባህሪያት እጅግ በርካታ ሲሆኑ ርዕይ (ማለትም ግልጽ  የሆነ የሩቅ ጊዜ እይታ) /Vision/፣ ጥልቅ የሆነ ስሜት /Passion/፣ የማሳመን ችሎታ፣ የማደራጀት ችሎታ፣ እና የመወሰን ችሎታ ዋነኞቹ ናቸው።

ርዕይ

መሪ ከርዕዩ ሌላ የሚሰጠው ነገር የለውም። መሪ ሰዎችን የሚያግባባው፤ ተከታዮቹን የሚያነቃቃው፣  የሚያደራጀው፣ የሚታግለው በርዕዩ ነው። “አብረን ከቆምን፤ ጠንክረን ከታገልን እዚያ መልካም  ሥፍራ መድረስ እንችላለን” እያለ ምኞቱ ምኞታቸው፤ ጉጉቱ ጉጉታቸው፤ ሕልሙ ሕልማቸው እንዲሆን ማድረግ ነው የመሪ ትልቁ ሥራ። ለዚህም ነው ታላቅ መሪ ባለርዕይ /Visionary/ መሆን ይኖርበታል የሚባለው። ርዕይ የሌለው መሪ ብቁ መሪ አይደለም።

ግልጽ ላልሆነ ግብ እንኳንስ ሌሎች ሰዎችን የገዛ ራስንም ማነቃቃት ይከብዳል። ግልጽ የሆነ ርዕይ፣ ዓላማ እና ግብ መኖር የጥሩ መሪ የመጀመሪያው እና ትልቁ መለያው ነው።  ጥሩ መሪ መድረሻውን የሚያውቅና ወደ መድረሻው እየተጓዘ የቀረውን ጉዞ በተመለከተ አማራጭ መንገዶችን እያሰላሰለ የሚኖር ሰው ነው።

ጥልቅ ስሜት

ጥሩ መሪ ለዓላማው፣ ለድርጅቱ፣ ለተከታዮቹ፣ እና ለድርጅቱ ደንቦችና መመሪያች ከፍተኛ ፍቅር እና አክብሮት ያለው ሰው ሊሆን ይገባል።

በሥራ አስኪያጅ (Manager) እና በመሪ (Leader) መካከል ያለው ትልቁ ልዩነት የዚህ ስሜት ጥልቀት ነው። ማኔጀሮችም ቢሆኑ ድርጅታቸውን፣ ሠራተኞቻቸውን ይወዳሉ ሕይወታቸውን ግን አይሰውላቸውም። ጥሩ መሪ ግን ለዓላማው፣ ለድርጅቱና ለተከታዮቹ ሕይወቱን ይሰጣል፤ ከእነዚህ የሚበልጥበት ነገር የለውም። ጥሩ መሪ የድርጅቱን ደንቦችና መመሪያዎች ከሚያዙት በላይ ይከውናል፤ ደንብ ከሚከለክላቸው ነገሮችም ደንቡ ከሚያዘው በላይ ራሱን ይገድባል። መሪ የመሪነት ሥራውን የሚከውነው ጥልቅ በሆነ የኃላፊነት መንፈስና ፍቅር ነው።

 

የማሳመን ችሎታ

መሪ ከፍተኛ የሆነ የማሳመን ችሎታ ሊኖረው ይገባል።

ሰዎችን ለማሳመን ከሁሉ አስቀድሞ ጥሩ አድማጭ መሆን ይገባል። ጥሩ መሪዎች ከፍተኛ ድርሻ ያለው የሥራ ጊዜዓቸውን ለማዳመጥ ይመድባሉ። ተከታዮች አስተያየታቸውና አቤቱታቸውን የሚያዳምጥ መሪ ይፈልጋሉ። ጥያቄዓቸው መፍትሄ ባይኖረው እንኳን በመደመጣቸው ሊረ ኩ ይችላሉ። ለዓላማቸው መሳካት፤ ለድርጅታቸው ጥንካሬ የሚያቀርቧቸው አስተያየቶች እንዲሰሙላቸው ይፈልጋሉ። የማያዳምጥ መሪ ተከታዮችን ያጣል፤ ቢናገርም የሚሰማው አይኖርም።

ጥሩ መሪ ጥሩ መረጃ አጠናቃሪ መሆን ይኖርበታል። መረጃዎችን ከተለያዩ  ምንጮች መሰብሰብ እና መተንተን የመሪው የግል ኃላፊነት ነው። አጠገቡ ያሉ ሰዎች የነገሩት ሁሉ እውነት እንደሆነ ወስዶ  ውሳኔ የሚሰጥ መሪ ጥሩ መሪ አይደለም።

ጥሩ መሪ ጥሩ ተናጋሪ መሆን ይጠበቅበታል። መሪ አንደበተ ርቱዕ ለመሆን መጣር አለበት። የመሪነት ሥራዎች በአብዛኛው የሚከናወኑት በሰው ከሰው ግኑኝነቶች በመሆኑ ተናግሮ ማሳመን የማይችል መሪ ጥሩ መሪ ሊባል አይችልም፡

ስለሆነም መሪ ከፍተኛ የሆነ የማሳመን ችሎታ ሊኖረው ይገባል ሲባል 1ኛ ጥሩ አድማጭ፣ 2ኛ ጥሩ መረጃ አጠናቃሪ፣ እና 3ኛ ጥሩ ተናጋሪ መሆን አለበት ማለት ነው።

 

የማደራጀት ችሎታ

መሪ ተከታዮችን ማወቅ እና እንደ ዝንባሌያቸውና ችሎታቸው መመደብ ይኖርበታል። መሪ ሥ.ራና ሰውን የማቀናጀት ጥበብ ሊኖረው ይገባል።

አንድ መሪ የአንድ ድርጅት የጥንካሬ መሠረቶች (1ኛ) ድርጅታዊ መዋቅር፣ (2ኛ) ድርጅታዊ ባህል እና (3ኛ) ግብዓቶች (በተለይም ሰው) መሆናቸው ያውቃል፤ እነዚህን የጥንካሬ መሠረቶችን ለማጥበቅ ይጥራል።

ብልህ መሪ ስትራቴጂያዊ ግብን ለመምታት ተስማሚ ድርጅታዊ መዋቅር መኖሩ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ ያውቃል። በዚህም መሠረት ድርጅቱ ተልዕኮውን ለማሳካት በሚያመቸው መንገድ መደራጀቱ ያረጋግጣል። ድርጅታዊ መዋቅር ከእዝ ሰንሰለት ባሻገር በደንቦች፣ በመመሪያዎች፣ በኃላፊነት ዝርዝሮች መታገዝ እንዳለበት ያውቃል።

ጠንካራ መሪ፣ ዲሲፕሊን የድርጅታዊ ባህል መሠረት መሆኑ ያውቃል። ጠንካራ መሪ፣ በጠንካራ ዲሲፕሊን ያልተገነባ ድርጅት ያለመውን ማሳካት እንደሚቸግረው ይገነዘባል። ስለሆነም ጠንካራ ዲሲፕሊን የድርጅቱ ባህል እንዲኖር ይጥራል።

ጥሩ መሪ የድርጅት ትልቁ ሃብት አባላቱ መሆናቸው ስለሚረዳ የአባላት ብቃት ለማጎልበት ይጥራል፤ የአባላትን ተሳትፎ ለማጎልበት መድረኮችን ያመቻቻል።

ልዩነቶች ጠፍተው ሁሉም አንድ አይነት እንዳይሆን፤ በተቃራኒው ደግሞ  ልዩነቶች ሰፍተው ድርጅቱ እንዳይበጣበጥ በቅራኔዎች አፈታት ጥበብ የተካነ መሆን ይኖርበታል።

 

የመወሰን ችሎታ

የተዋጣለት መሪ ተገቢው ውሳኔ በተገቢው ወቅት መስጠት የሚችል መሆን ይኖርበታል። የዘገየ ውሳኔ ጥሩ እንዳልሆነ ሁሉ የተቻኮለ ውሳኔን ከፍተኛ ጉዳት የሚያመጣ ሊሆን ይችላል። ውሳኔዎች በመረጃ መደገፍ ቢኖርባቸውም መረጃዎች ተሟልተው በማይገኙበት ወቅት ስሜትን ማዳመጥ (intuition) ተገቢ ሊሆን ይችላል።

የተዋጣለት መሪ ለውሳኔ አሰጣጥ የሚረዱ ቴክኒኮችን ማወቅ ይጠበቅበታል።

ስኬታማ ተግባቦት

ስኬታማ ተግባቦት /Effective Communication/ መሪዎች በተከታዮቻቸው፤ ተከታዮች በመሪያቸው እና ሁለቱም ወገኖች በድርጅታቸው ላይ እምነት እንዲጥሉ የሚረዳ ቁልፍ ነገር ነው። ስኬታማ አመራር መስጠት የሚቻለው ስኬታማ ተግባቦት ሲኖር ነው። የተግባቦቱ ዓይነትና አፈፃፀም በመሪና በተከታዮቹ መካከል ያለው ግኑኝነት እንዲጠናከር አሊያም እንዲበላሽ ያደርጋል።

ስኬታማ ተግባቦትን በተመለከተ ሁለት ነገሮች አጽንዖት ሊሰጣቸው ይገባል – የሥራ ዘገባዎች፣ እና የሰው ለሰው ግኑኝነት።

 

የሥራ ዘገባዎች

ስኬታማ አመራር እንዲኖር መረጃዎች ለመሪው መድረስ አለባቸው። በድርጅት ውስጥ ወቅታዊ /periodic/ እና ወቅት የማይጠብቁ ሪፓርቶች መኖር አለባቸው። የቃልም ሆነ የጽሁፍ ዘገባዎች (ሪፓርቶች) በሃቅ ላይ የተመሠረቱ መሆን አለባቸው።

እቅድና በጀት እጅግ አስፈላጊ የመረጃ ዓይነቶች ናቸው፤ ለስኬታማ አመራርም ወሳኝ ናቸው።

ጥሩ አመራር የታወቀ እዝ ሊኖረው ይገባል። በድርጅት ውስጥ የታወቀ  የሥራ ድልድል ሊኖር ይገባል። በተለይ እያንዳንዱ ሰው ለማን ሪፓርት እንደሚያደርግ፤ በምን ያህል ጊዜ እና በምን ሁኔታ ሪፓርት ማድረግ እንዳለበት ሊታወቅ ይገባል።

ሰዋዊ ግኑኝቶች

ሰዋዊ ግኑኝነቶች ለመሪዎች በጣም አስፈላጊ ናቸው። ትህትና የተሞላባቸው አነጋገሮችን መልመድ ለመሪዎች በጣም ይጠቅማል።

ለምሳሌ

  • መሪ ስህተት በሠራ ጊዜ “ስህተት ሠርቻለሁ፤ አጥፍቻልሁ። የምቀጣውን እቀበላለሁ” ቢል ያምርበታል።
  • ተከታዮች ጥሩ በሠሩ ጊዜም “በጣም ጥሩ ሠርተሃል/ሠርተሻል” ቢል ትልቅ ማበረታቻ ነው።
  • ከውሳኔ በፊትም “በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አስተያየት አለህ/አለሽ?” ብሎ  መጠየቅ ከብዙ ቅስቀሳ በላይ የአባላትን ተሳትፎ የሚያበረታታ ልማድ ነው።
  • “አመሰግናለሁ” ሊለመድ እና ሊዘውተር የሚገባ ቃል ነው።

ሁኔታ

በአንድ ሁኔታ ውጤታማ የነበረ የአመራር ስልት በሌላ ሁኔታም ይሠራል ማለት አይደለም።  ሁኔታዎች ሲለወጡ የአመራር ስልትም መለወጥ ይኖርበታል። ሁኔታ በተመለከተ በሚከተሉት ላይ ትኩረት መሥጠት ያስፈልጋል – ጉዳዩ /Issue/ ፣ የአጣዳፊነት መጠን፣ የተከታዮች ዓይነት፣ እና ባህል።

ጉዳዩ /Issue/

የተለያዩ  ጉዳዮች የተለያዩ የአመራር ዓይነቶች ይፈልጋሉ። ውትድርናና መምህርነት የተለያዩ ሥራዎች እንደመሆናቸው የሚፈልጉትም የአመራር ዓይነት ይለያያል።  ወታደራዊ አመራር የተማከለ፣ ጥብቅ እና ትዕዛዝ ላይ ያተኮረ እንዲሆን ሙያው ግድ ይላል። በአንፃሩ የአካዳሚ አመራር ብዙ ነገሮችን ለመምህራኑ የግል ውሳኔ ሊተው ይችላል። እንደዚሁም፣ የፓለቲካ ድርጅት አመራር ከቢዝነስ ኮርፓሬሽን አመራር ይለያል። የሃይማኖት ተቋማት አመራር እና መንግሥታዊ አመራር የተለያዩ ናቸው።

ከላይ በምሳሌነት የተዘረዘሩት አና የሌሎች የሥራ መስኮች አመራሮች በርካታ የጋራ ባህሪያት ያላቸው መሆኑ ቢታመንም ልዩነቶቻቸውን አሳንሶ ማየት ግን ጉዳት አለው።

በተለያዩ  የአመራር ጉዳዮች መሪዎች ተከታዮቻቸውን ለማነቃቃት የሚጠቀሙባቸው ስልቶችም በጣም የተለያዩ ናቸው። ወታደራዊ ሹመት ለወታደራዊ አመራር፤ የአካዳሚ እውቅና ለአካዳሚ ተቋማት፤ ቅድስና ለሃይማኖት ተቋማት፤ ትርፍና ቦነስ ለቢዝነስ ተቋማት መሪዎችና ተከታዮች ጥሩ ማነቃቂያዎች ሊሆኑ ይችላሉ።

ለነፃነት የቆሙ ድርጅቶ መሪዎችና ተከታዮች ያላቸው ማነቃቂያ የድርጅታቸው ርዕይ ነው፤ እሱ ደግሞ ሁሌ ፍንትው ብሎ ላይታይ ይችላል።  ለማጠቃለል፣ ጥሩ አመራር እንዲኖር ለጉዳዩ  ተስማሚ የሆነ የአመራር ስልት ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል።

 

የአጣዳፊነት መጠን

“ጊዜ” በአመራር ውስጥ እጅግ ወሳኝ የሆነ ነገር ነው። ጊዜ ካለ በእያንዳንዱ ነገር በዝርዝር ተወያይቶ ውሳኔዎች በሙሉ ድጋፍ እንዲያልፉ ማድረግ ይቻላል። ችግሩ ግን ለዚህ የሚሆን ጊዜ ሁሌ አይገኝም። ከዚህ አንፃር በተዝናና ሁኔታ እና በአጣዳፊ ሁኔታ ውስጥ ላይ የሚኖሩ አመራሮች የተለያዩ ናቸው። በተዝናና ሁኔታ ላይ አመራር አድማጭ፣ አሳታፊ፣ ምክር ጠያቂ እና ለስላሳ መሆን ይችላል። አጣዳፊ በሆነ ሁኔታ ግን እነዚህ ሁሉ የሉም። በጣም አጣዳፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ መሪ ብቻውንም ቢሆን ውሳኔ መስጠት አለበት።  ከጠላት ጋር በጦርነት ሁኔታ ውስጥ ያለን አመራር አሳታፊ አልሆንክም ብሎ መኮነን አመራሩን ማዳከም ነው።

 

የተከታዮች ዓይነት

አመራር በተከታዮች ዓይነትም ይወሰናል። ይህ ርዕሰ ጉዳይ እላይ የተነሳ በመሆኑ የተለያዩ ተከታዮች የተለያየ አመራር የሚያስፈልጋቸው መሆኑን አስታውሶ ማለፍ ይበቃል።

 

ማኅበራዊ ባህል

አመራር ከባህል ጋር በበርካታ ክሮች የተሳሰረ ነው። ለባህሉ ተስማሚ ያልሆነ አመራርና መሪ ተቀባይነት የለውም። ለምሳሌ የገጠር እና የከተማ አስተዳደሮች አንድ ዓይነት አይደሉም። የተለያዩ ሃይማኖቶች ባሉበት  አገር ውስጥ የፓለቲካ አመራር ሃይማኖቶችንም ማቻቻል ይጠበቅበታል።

 

የአመራር ወለፈንዲዎች

 

ወለፈንዲ(paradox) ተቃርኖ ነው። አንድ ነገር እና ተቃራኒው እኩል ተቀባይንት ካላቸው ወለፈንዲ ነው።  አንድ ሰው በአንድ ጊዜ አንድን ነገር አድርግም አታድርግም ከተባለ ወለፈንዲ ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለ ትዕዛዝ ተቀባይ ምን ማድረግ እንዳለበት መወሰን ይቸግረዋል፤ ማድረግ መጥፎ ነው፤ አለማድረግም መጥፎ ነው።

መሪነት በበርካታ ወለፈንዲዎች የታጀበ አስቸጋሪ ሂደት ነው። ስኬታማ መሪ ለመሆን በወለፈንዲዎች መካከል ባለ ቀጭን ክር ላይ ተዝናንቶ መቆም ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ ሁኔታ ደግሞ በወለፈንዲዎች ከተወጠረችው ክር ሥር በርካታ ሹል ምስማሮች ተሰክተዋል። መሪዎቻችን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት።

ከዚህ በታች ጥቂት የታወቁ የመሪነት ወለፈንዲዎችን እናነሳለን። በእያንዳንዱ ላይ በርካታ ገጾች ሊፃፍ የሚችል ቢሆንም እያንዳንዱን በጥቂት ዓረፍተ ነገሮች በመግለጽ እንወሰናለን።

 

ለውጥ እና ሥርዓት

ጥሩ መሪ የለውጥ ሃዋሪያ ነው። ለለውጥ ያልተነሳሳ ሰው መሪ መሆን አይችልም። ለውጥ ማለት ደግሞ ነባር ህጎችንና ልማዶችን መቃወም እና በአዳዲስ ህጎችና ልማዶች እንዲተኩ መጣር ማለት ነው። ለውጥ ማፍረስን ይጠይቃል።

መሪ ህግን አክባሪ ነው፤ ባህል አክባሪ ነው። መሪ ያላከበረው ህግ አይከበረም። ልማዶችንም ማክበር ከጥሩ መሪ የሚጠበቅ ተግባር ነው።  መሪ የሥርዓት ምንጭ ነው።

ለውጥንና ሥርዓትን በአንድ ጊዜ መጠበቅ በጣም አስቸጋሪ ወለፈንዲ ነው። በሁለቱ መካከል ክር መኖሩ እንኳን በአርጠኝነት መናገር አስቸጋሪ ነው። መሪዎች አንዴ ህግ ሲያፈርሱ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ደንቦችን ሲደነቡ የምናየው በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ በመኖራቸው ነው።

 

መምሰል እና መለየት

ጥሩ መሪ ተከታዮችን መምሰል አለበት። ተከታዮች ሲራቡ መራብ፤ ሲታረዙ መታረዝ አለበት። ተከታዮች የሚሠሩትን ሥራ እሱም መሥራት አለበት። መሪ በሁሉም ረገድ ለተከታዮቹ አርዓያ መሆን አለበት።

መሪ ከተከታዮቹ መለየት አለበት። አለበለዚያማ ምኑን መሪ ሆነው? ተከታዮቹም ቢሆኑ መሪያቸው ከእነሱ በምንም የሚለይ አለመሆኑን ሲያዩ  በመሪነት መቀበል ይቸግራቸዋል።  ሌላ ወለፈንዲ!

ውትድር ውስጥ መኮንኖችና ተራ ወታደሮች የሚመሳሰሉበት በርካታ ነገሮች ቢኖሩም የሚለያዩባቸው ነገሮች እንዲኖሩ የሚደረግበት (ለምሳሌ ምግቤት፣ መኝታ) አንዱ ምክንያት ከመጠን በላይ መመሳሰል አመራሩን ስለሚጎዳው ነው። ጥሩ አባት ልጁን ማቅረብ አለበት ሆኖም የልጁ ምርጥ ጓደኛ ለመሆን ቢሞክር ልጁንም ራሱን አይጠቅምም።

የሥራ ሰው እና የሐሳብ ሰው

ጥሩ መሪ ተግባር ላይ እንዲያተኩርና የሥራ ሰው (The Doer) እንዲሆን ይፈለጋል። “ወሬ በዛ! የተግባር ሰው አጣን” የሚሉ እሮሮዎች በብዛት ይሰማሉ። አዎ እውነት ነው መሪ የተግባር ሰው እንዲሆን ይፈለጋል።

በሌላ በኩል ደግሞ መሪ የሥራ ሰው ከሆነ ከተከታዮች በምን ተለየ? ጥሩ መሪ የሐሳብ ሰው (The Thinker) መሆን ይኖርበታል። የመሪ ዋነኛ ሥራ ርዕይ መንደፍ ነው፤ ማቀድ ነው። ቀጥሎም ርዕዩ ተግባራዊ የሚሆንበት አቅጣጫን ማሳየት፤ ማስተማር፤ ማሳወቅ ለሚሠሩ ሥራዎች የንድፈ ሐሳብ መሠረት መጣል ነው።

በተግባርና በንድፈሃሳብ መካከል ድልድይ ማበጀት ይቻላል። ከመሪዎች የሚፈለገው ግን ድልድይ ሳይሆን ሁለቱም በአንድነት ነው። ይቻላል ግን ከባድ ነው።

 

የሥልጣን ጥም እና የማገልገል ጥም

ጥሩ መሪ ኃላፊነትን ለመውሰድ የተዘጋጀ መሆን አለበት።  ኃላፊነት የማይወስድ ሰው መሪ መሆን በጭራሽ አይችልም። መሪ መሆን ማለት በከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ መገኘት ማለት ነው። ስለሆነም ጥሩ መሪ ሥልጣንን የመያዝ ፍላጎት ሊኖረው ይገባል።  ሥልጣን መያዝ ሌላውን ሰው የማዘዝ መብት ይሰጣል።

ጥሩ መሪ የሥልጣን ሳይሆን የማገልገል ጥም ሊኖረው ይገባል። ኃላፊነቶችንም መውሰድ ሳይሆን መስጠት ነው ያለበት። ኃላፊነቶችን ጠቅልሎ የሚይዝ መሪ መጥፎ መሪ ነው። ጥሩ መሪ ኃላፊነቶችን በማከፋፈል የጋራ አመራር ያሰፍናል። ጥሩ መሪ ታዛዥ ነው።  ማዘዝና መታዘዝ (የሥልጣን ጥምና የማገልገል ጥም) ተቃራኒዎች ናቸው።

 

ራስን በመሪነት ማቆየት እና ራስን ከመሪነት ማውጣት

ጥሩ መሪ ራሱን በነገሮች አናት ላይ ለማስቀመጥ ይጥራል። ሁሌም ራሱን ያስተምራል። መሪ በራሱ ላይ የሚያደርጋቸው “ኢንቬስትመቶች” ራሱን በመሪነት የሚያቆዩት ነገሮች ናቸው።

ጥሩ መሪ ራሱን ከመሪነት ለማውረድ መጣር ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ ከሱ የተሻሉ መሪዎች እንዲመጡ መንገድ ማመቻቸትና ማስተማር ይኖርበታል።

የገዛ ራሱን በነገሮች አናት ላይ አስቀምጦ እያለ እንዴት ከራሱ የበለጠ ሰው ማውጣት ይችላል? ወለፈንዲ!

 

በአንድ ጉዳይ ላይ ማትኮር እና ሁሉን ዓቀፍ እይታ

ጥሩ አመራር እና ጥሩ መሪ በአንድ አቢይ ጉዳይ ላይ ማትኮር ይኖርበታል። ያም ጉዳይ የድርጅቱ ግብና ወደዚያ ያደርሰኛል በሚለው ስትራቴጂው ላይ መሆን ይኖርበታል። በየጊዜው በሚፈጠሩ “የጎን ጉዳዮች” ትኩረቱ የሚዛባ ሰው ጥሩ መሪ መሆን አይችልም።

መሪ ሁሉን ዓቀፍ እይታ እንዲኖረው ያሻል። ጥሩ መሪ ትኩረቱ  መንገዱ ላይ ቢሆንም እንደጋሪ ፈረስ ግራና ቀኙን ላለማየት ዓይኖቹን የሸፈነ መሆን የለበትም። በየጊዜው የሚፈጠሩ እድሎችን በቸልታ የሚያሳልፍ ሰው ጥሩ መሪ መሆን አይችልም።

እይታን ዓለም–ዓቀፍ፤ ተግባሮችን ግን አካባቢ–ተኮር ማድረግ እንደ መፍትሔ ይቀርባል። ይህንን በተግባር መተርጎም ግን ቀላል ነገር አይደለም።

እሳቤ እና እርግጠኝነት

መሪው ውሳኔ  እንዲሰጥ የሚጠበቅበት በአብዛኛው ተጨባጭ መረጃዎች በሌሉበት ሁኔታ ነው። የመሪ ብቃቱ በእሳቤዎች (assumptions) ላይ ተመሥርቶ ትክክለኛ ውሳኔ በመስጠት ችሎታው ነው። መሪነት ሥነ-ጥበብ (art) ነው የሚባለው ለዚህ ነው።

የመሪ ስህተት ጉዳቱ ከፍተኛ በመሆኑ ውሳኔዎቹ ትክክለኛ ስለመሆናቸው ማስተማመኛ ሊኖር ይገባል። ተከታዮች ለውጤት ይቸኩላሉ፤ የሚያደርጉት ትንሹም አስተዋፅዖ ወደ ትልቁ ግብ የሚያደርስ የመሆኑ ማስተማመኛ ይፈልጋሉ።

በእሳቤ ላይ ተመሥርቶ ለሚሰጥ ውሳኔ ትክክለኝነት ማስተማመኛ መስጠት እንዴት መስጠት ይቻላል?  ወለፈንዲ !

 

በመሪነት ላይ ያሉ ወለፈንዲዎች እነዚህ ብቻ አይደሉም። ለአሁኑ ግን ይበቁናል። መሪነት ለዚያውም ስኬታማ መሪ መሆን በጣም ከባድ ነገር ነው። ለዚህም ነው በዓለም ዓቀፍ ደረጃም ቢሆን ብዙ ስኬታማ መሪዎች የሌሉት።

 

ስኬታማ አመራር እንዲኖረን ምን እናድርግ?

ለመሪ እጦት እኛም (ተመሪዎቹ) አስተዋጽዖ ያደረግን መሆኑ ማወቅና በራሳችን ላይ የእርምት እርምጃዎችን መውሰድ የመጀመሪያው አቢይ መፍትሄ ነው። እኛ ከልባችን እውቅና ካልሰጠናቸው ሰዎች የድርጅት ሊቀመንበር፣ ፕሬዚዳንት ወይም ፀሐፊ ስለሆኑ ብቻ መሪ አይሆኑም። ኃላፊነትን እየሰጠን ድጋፋችንን የምንነሳቸው ከሆነ ችግሩ ያለው እኛ ዘንድ ነው። ሁሉንም ነገር እነሱ እንዲያደርጉልን የምንፈልግ ከሆነ ጥያቄዓችን መሪ ሳይሆን ፈጣሪ ነው። መሪዎቻችን የቱንም ያህል ቢበረቱ ጥሩ መሪ እንጂ ፈጣሪ መሆን አይችሉም።

ሁለተኛ “መሪዎች ይወለዳሉ” በሚል ያረጀ ብሂል (ሳናውቀው ሊሆን ይችላል) ተታለን መሲህ የምንጠብቅ ከሆነ የመከራ ጊዜዓችንን እናራዝማለን። መሪነት ይለመዳል፣ እኛም እንልመደው። ለመሪነት ይሰለጠናል፤ እናም እንሰልጥን። መሪነትን ለመማር ፈቃደኞች እንሁን። “ባህር የሚያሻግር ሙሴ” ስለናፈቅን አይመጣም፤ “ሚኒሊክና ቴዊደሮስ ተመልሳችሁ ኑ” ብንላቸው ሊመጡልን አይችሉም፤ ቢችሉም ኖሮ ለዛሬው ሁኔታ ተስማሚ መሪዎች ሊሆኑ ይችሉ እንደነበር ማረጋገጫ መስጠት የሚችል የለም።

ለዛሬ ችግሮቻችን መፍትሔ መስጠት የሚችሉ መሪዎች መውጣት ያለባቸው ዛሬ እየኖረ ካለው ትውልድ ነው። ይህ ደግሞ ትኩረታችንን ወጣቱ ላይ እንደናደርግ ግድ ይለናል።  ወጣቱ ትውልድ ብዙ ፈተናዎች ያሉበት ቢሆንም እንኳን ተስፋችን እሱ ላይ ነው። ተስፋችን እውን እንዲሆን ወጣቱን ለመርዳት ጥረት እናድርግ፤ በወጣቶች ለመመራትም ዝግጁ እንሁን።

“መሪ አጣን” እያሉ ማላዘን ይቁም። ይልቁንስ (1) አሁን የተቻላቸውን ለማድርግ እየጣሩ ላሉት መሪዎች የተመቸን ተመሪዎች እንሁን፤ ለጥሪዎቻቸው ምላሽ እንስጥ፤ እንደግፋቸው (2) ራሳችንን ለመሪነት እናዘጋጅ። መሪዎች የሚወጡት ከኛው ነው። ፍልስፍና፣ ሞዴል፣ ፎርምላ ከሌሎች አገሮች መዋስ እንችላለን። መሪዎችን መዋስ ግን አንችልም፤ ቢቻልም ኖሮ (outsource ብናደርግ) አይጠቅመንም (3) ወጣቱ ላይ እምነት ይኑረን።

የትም አገር ቢሆን ስኬታማ አመራር ማግኘት ከባድ ነው። የአገራችን የአመራር ችግር ከመጠን በላይ በማግነን መዓት የወረደብን አደርጎ ማቅረብ ጉዳት አለው።  ቀላል መፍትሔ የለም ሆኖም ግን በሚገባ ካሰብንበትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ካደረግን የማንወጣው ችግር አይኖርም።

…

አስተያየት መስጠት በፈለጉ: tkersmo@gmail.com

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on May 2, 2013
  • By:
  • Last Modified: May 2, 2013 @ 11:03 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar