www.maledatimes.com የአቶ መለስ መታሰቢያ ተቋም (Foundation)! – ክፍል ሁለት ግርማ ሞገስ (girma.moges@yahoo.com) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የአቶ መለስ መታሰቢያ ተቋም (Foundation)! – ክፍል ሁለት ግርማ ሞገስ (girma.moges@yahoo.com)

By   /   May 3, 2013  /   Comments Off on የአቶ መለስ መታሰቢያ ተቋም (Foundation)! – ክፍል ሁለት ግርማ ሞገስ (girma.moges@yahoo.com)

    Print       Email
0 0
Read Time:32 Minute, 12 Second

አርብ ሚያዚያ 25 ቀን 2005 ዓመተ ምህረት (Friday, May 03, 2013) መንግስት በመፈንቀል ስልጣን የጨበጠው የትናንቱ አምባገነን መንግስቱ ኃይለማሪያም የኢትዮጵያ ህዝብ በሰላማዊ ሰልፍ አብዮቱን እንድጠብቅ አደራ ሰጥቶኛል ብሎን ነበር። ስልጣን አልለቅም ማለቱ ነበር። የአምባገነኑ መለስ አደራ መፈክሮች ቢለዋወጡም “የልማት ጠባቂ ነኝ” እያለ መሞቱ ይታወሳል። ዛሬ በስልጣን ላይ ያሉት
የአቶ መለስ ፍጡራን አምባገነኖች ደግሞ “የአቶ መለስ ራዕይ ሞግዚት” ነን ይላሉ። ሌላ ሃያ አመቶች ሊገዙን።
የትናት በስቲያው አብዮት ጠባቂ፣ የትናንቱ ልማት ጠባቂ፣ የዛሬዎቹ ደግሞ ራዕይ ጠባቂ። የአምባገኖች መተካካት በኢትዮጵያ የሚያከትመው የኢትዮጵያ ህዝብ አፉን እና እጁን አንድ አድርጎ አደባባይ በመውጣት የስልጣን ባለቤት እኔ ነኝ ሲላቸው ብቻ ነው። በሰላማዊ ትግል የመንግስት ስልጣን ባለቤት ሲሆን ብቻ ነው።
የዛሬዎቹ አምባገነኖች ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ሰጥቶናል የሚሉትን ሞግዚትነት እንዳይነጥቃቸው በኢቲቪ እና በመሳሰሉ የፕሮፓጋንዳ አውታሮች አማካኝነት የአቶ መለስን ታሪክ በአዲስ እያሻሻሉ (እያቆነጁ) ለአቶ መለስ ያለውን ፍቅር ሞቅ ለማድረግ በየቀኑ ዘመቻ ላይ ናቸው። እነ ‘ፕሮፌሰር‘ እንድሪያስ እሸቴ ሳይቀሩ ዘመቻውን ተቀላቅለዋል። አቶ መለስ፥ “አገር ወዳድ፣ የልማት ጀግና፣ ፓን-አፍሪካዊ፣ የሰላም አባት፣ ለህዝብ ፍትህ፣ ጥሩ አስተዳደር እና ዲሞክራሲ ያመጣ” ታልቅ መሪ ነበር ይላል ዘመቻው። በጥያቄዎች እና መልሶች መልክ (ፎርማት) ክፍል ሁለት በአዲስ ተሻሽሎ ለመጣው ለአቶ መለስ አዲስ ታሪክ መልስ ይሰጣል። [መልካም ንባብ!]
ክፍል ሁለት (ከአራት ክፍሎች)፥ ጥያቄዎች እና መልሶች ስለ አቶ መለስ (1ኛ) እርግጥ አቶ መለስ ‘አገር ወዳድ‘ ነበርን? እንድሪያስ እሸቴ እንደሚለው አቶ መለስ ‘የልማት ጀግና’ ነበርን?
አገር ወዳድነት እና ጀግንነት የተሳሰሩ ጉዳዮች ናቸው። የአገር ወዳድነት መለኪያ (መስፈርት) መነሻው የአገርን እና የህዝብን በላይነት፣ ጥቅም እና ደህንነት ማስቀደም ነው። አገር ወዳድ ግለሰብ ከግል ሆዱ እና ስልጣኑ (ጥቅሙ) ይልቅ ህዝብን ያስቀድማል። አገር ወዳድነት እና ጀግንነት በፖለቲካ፣ በአገር ሉዓላዊነት፣ በልማት፣ በኢኮኖሚ፣ እና በማህበራዊ መስኮች ሁሉ ይገለጻሉ። አቶ መለስ ግን አገር ወዳድም የልማት ጀግናም አልነበረም። ላብራራ!
የሱማሌ ፕሬዘዳንት የነበረው ወታደራዊው አምባገነን ሰይድ በሬ ከሶቪየት ህብረት ተሻርኮ ተዋጊ ሚግ ጀቶች እና ታንኮች አሰባሰበ። ግብጽ ደግሞ ዚያድ በሬ በኢትዮጵያ በኦጋዴን ግዛት ላይ የነበረውን የፖለቲካ እና የመሬት ምኞት ስለምታውቅ ብዙ ገንዘብ፣ የጦር አስልጣኞች እና ተዋጊዎች ለገሰችው። የግብጽ ምኞት የአባይ ወንዝ ባለቤትነት ነው። ምኞቷን ለማሳካት ግብጽ ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያን የማናጋት እና የማዳከም ፖሊሲ አራምዳለች። ስለዚህ ሰይድ በሬን ልትጠቀም ሞከረች። ያም ሆነ ይህ ሰይድ በሬ በ1969 እና 1970 ዓመተ ምህረት
የኢትዮጵያ ግዛት የሆኑትን ኦጋዴንን፣ ጅጅጋን፣ በባቡር መስመር ላይ ከደወሌ አስከ ድሬደዋ አቅራቢያ ያሉትን ከተሞች ወረረ። ድሬደዋን፣ ሐረርን እና አዋሽን ለመያዝ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ወታደራዊ ጥቃት ፈጸመ። በዚያን ጊዜ የስልጣን ምኞቱን (ጥቅሙን) በማስቀደም አቶ መለስ “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” የሚለውን ከሃዲ የፖለቲካ ታክቲክ እንደ ትክክለኛ ምክንያት በማቅረብ ሰይድ በሬን “ግፋ፣ በርታ” አለ። አገር ወዳድ ይህን አያደርግም። አገር ወዳድ ምን እንደሚያደርግ ከታሪካችን አንድ ምሳሌ ልስጥ!
ከፍ ብለን እንደተመለከትነው ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ ያላት የመሬት እና የውሃ በላይነት ምኞት ቀደም ብሎም
የነበረ በመሆኑ ሁኔታዎች በፈቀዱላት ጊዜ ሁሉ ምኞቷን ተፈጻሚ ከማድረግ ተቆጥባ አታውቅም። ስለዚህ
ሽፍታው ካሳ (በኋላ ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ) በዘመነ መሳፍንት የኢትዮጵያ እንደራሴ በነበሩት የራስ ዐሊ እናት
እቴጌ መነን ላይ ሸፍተው ጫካ እንደገቡ ግብጾች የሚያስተዳድሩዋትን ሱዳንን ድንበር አልፈው ኢትዮጵያ ላይ
ዘመቱ። ሽፍታው ካሳ በአገራቸው መወረር ተቆጭተው ለጊዜው ዘመነ መሳፍንትን መዋጋታቸውን ወደጎን
በመተው በ1840 ዓመተ ምህረት ደበርቂ (Dabarqi) በተባለው ሜዳ ላይ ከግብጽ ጋር ስለመዋጋታቸው ተክለ
ፃዲቅ መኩሪያ እና ባህሩ ዘውዴ ጽፈዋል። በግልጽ እንደሚታየው ዘመኑ ይለያይ እንጂ የሽፍታው ካሳም ሆነ የአቶ
መለስ ትግል ግብ የኢትዮጵያ መንግስት ስልጣን ባለቤት መሆን ነበር። ሆኖም ግን የራሱን እና የግብጽን የፖለቲካ
ምኞት የተሸከመው ሰይድ በሬ ኢትዮጵያን ሲወር አቶ መለስ “ግፋ በርታ” በማለቱ በቀጥታ ከሰይድ በሬ ጋር
በተዘዋዋሪ ደግሞ ከግብጽ ጋር ተሻርኳል። ሽፍታው ካሳ ግን አገር ወዳድ ማድረግ የሚገባውን አድርገዋል።
ከኢትዮጵያ ድንበር ብትወጣም በኦቶማን ቱርክ ስር የነበረችው ግብጽ ዘመናዊ መሳሪያዎች ተጠቅማ ሽፍታ ካሳን
አሸንፋለች። አቶ መለስ ሰይድ በሬን ለመግጠም ቢፈልግ እንኳን የህውሃት ጦር መሰረት ትግራይ ስለነበር
ጂኦግራፊ አይፈቅድለት። ልግጠም ቢል እንኳን ሰይድ በሬ የጦር መሳሪያ በላይነት ስለነበረው አቶ መለስም እንደሽፍታ ካሳ ሊሸነፍ ይችላል። የሆነው ሆኖ የውይይታችን ዋናው መልክዕት ግን ከወራሪ ጋር መዋጋት አለመዋጋት
የሚለው ሳይሆን ለስልጣን ሲባል አገርን እና ህዝብን ክዶ ከወራሪ ጋር የፖለቲካም ሆነ ወታደራዊ ትብብር
ማድረግ ወንጀል ነው የሚለው ነው። ከወራሪ ጋር መተባበር ስልጣን ማስቀደምን እንጂ አገር ወዳድ መሆን
አይደለም ለማለት ነው።
አቶ መለስ በኢትዮጵያ መንግስት ስልጣን ላይ በነበረበትም ጊዜ ከህዝብ እና ከአገር ሉዓላዊነት ይልቅ በስልጣን
ላይ መቆየት በልጦበት የፖለቲካ ተቀናቃኞቹ ሱዳን ውስጥ እንዳይደራጁ ለማድረግ ለሱዳኑ አምባገነን አል-በሺር
የኢትዮጵያን ምዕራባዊ መሬት እየቆረሰ ጉቦ ይሰጥ እንደነበር ብዙ የተዘገበበት ጉዳይ ነው። በምላሹ አል-በሽር
የአቶ መለስ የፖለቲካ ባላንጣዎች በሱዳን እንዳይደራጁ ብቻ ሳይሆን የሚጠረጠሩትን ሳይቀር ወደ አዲስ አበባ
ሲልክ እንደነበር ብዙ ተዘግቧል። አገር ወዳድ አልነበረም አቶ መለስ።
በልማትም መስክ ቢሆን ያው ነው። ለምሳሌ በኢትዮጵያ የኤሊክትሪክ ኃይል የማመንጨትን የልማት ውጥን
እንመልከት። የልማቱ ግብ በኩራዝ እና በእንጨት መብራት ከሚኖረው ህዝባችን ውስጥ ግማሹን እንኳን
ከጨለማ ኑሮው የማውጣት እቅድ የለውም። ከሰማኒያ በመቶ በላይ የሆነው ኤሊክትሪክ ኃይል ለሱዳን፣ ለኬኒያ
እና ለጅቡቲ በመሸጥ ኪራይ መሰብሰብን እና በተገኘው ብር ስልጣን ማጠናከርን ያስቀደመ ነው ልማቱ። ስለዚህ
በልማትም መስክ አቶ መለስ አገር ወዳድ አይደለም። የኤሊክትሪክ ኃይል በማመንጨት የህዝቡን ኑሮ ፕሬዘዳንት
ፍራንክሊን ዲ ሩዝቬልት እንዴት እንደቀየረ በክፍል አንድ በሰፊው አንብበናል። አምባገነን መለስን የልማት ጀግና
ብሎ የሚያሞካሸው እንድሪያስ እሸቴ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል።
በኢኮኖሚውም መስክ አቶ መለስ ስልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊት እና ከወጣ ወዲህ የሽሮ፣ የዳቦ፣ የእንጀራ፣
የሚበላ ዘይት እና የመሳሰሉት መሰረታዊ ምግብ ነክ ሸቀጦችን ዋጋዎች በማወዳደር እና ከህዝቡ ገቢ መጠን
እድገት ማሽቆልቆል ጋር በማነፃጸር ከአቶ መለስ የፖለቲካ ደጋፊዎች በስተጠቀር ህዝቡ እንዴት እየደኸየ በመሄድ
ላይ እንደሚገኝ መተንተን ይቻላል። በአቶ መለስ ዘመን በአዲስ አበባ ምግብ ቤቶች የሚሰበሰብ ትርፍራፊ
እየተሰበሰበ “ጉርሻ” የሚል አዲስ መጠሪያ አግኝቶ መሸጥ መጀመሩ በፎርችህን ጋዜጣ ተዘግቦ አንብቢያለሁ።
በአዲስ አበባ የሚሰሩት ኮንዶምንየሞችም ቢሆኑ ለህዝብ የሚታደሉት በጉቦ መልክ ነው። ተቃዋሚ ፓርቲ የደገፈ
ዜጋ ቤቱን እንደሚያጣ በካድሬዎች እና በቀበሌ አስተዳዳሪዎች ይነገረዋል። ስለዚህ አቶ መለስ በማህበራዊም
መስክ የህዝብን የፖለቲካ ነጻነት ያስቀደመ ሰው ሳይሆን ስልጣኑን ያስቀደመ ሰው ነበር።
“ጀግና የሚያደርግህ ለራስህ (ለሆድህ ወይንም ለስልጣንህ) የምትሰራው ወይንም የምታደርገው ሳይሆን ለህዝብ
ነፃነት፣ እኩልነት፣ ብልጽግና የምትሰራው ወይንም የምታደርገው ነው” ይላል ማርቲን ሉተር ኪንግ። እንድሪያስ
እሸቴ አቶ መለስን ጀግና ማለትህ ከነማርቲን ሉተር ጋር ሳይቀር ያጋጭሃል።
(2) እርግጥ አቶ መለስ ፓን-አፍሪካዊ ነበርን?
አገርን በየጎሳው የሚበትን የጎሳ ፖለቲካ እና አገሮችን በየጎሳቸው ሳይበትን የፖለቲካ ውህደት ፈጥረው በአንድ
አህጉራዊ መንግስት ስር እንዲተዳደሩ የሚመኝ የፓን-አፍሪካ ፖለቲካ ተቃራኒዎች እንጂ ተደጋጋፊዎች አይደሉም።
ኩዋሜ ንኩሩማ ፓን-አፍሪካዊ የሚለውን እውቅና ያገኘው በቁጥር ከ50 በላይ የሆኑት የአፍሪካ አገሮች የፖለቲካ
መዋሃድ አድርገው እና አንድ መንግስት እንዲመሰርቱ በመታገሉ እንጂ የኤርትራ ነፃ አውጭ፣ የትግራይ ነፃ
አውጭ፣ በጋና ውስጥም ያሉት ጎሳዎች የየራሳቸው ነፃ አውጪዎች ወ.ዘ.ተ. እያለ ቀጥራቸው ከ50 ግድም ወደ
አንድ ሺ እና ከዚያ በላይ እንዲደርስ በመታገሉ አልነበረም።
ፓን-አፍሪካዊነት በአቶ መለስ ደም ውስጥ የለም። አቶ መለስ አገር ወዳድም አይደለም። አቶ መለስ የትግራይን
ህዝብ ከፍ ወዳለ ስልጣን መሸጋገሪያ መስፈንጠሪያ ያደርጋል እንጂ የትግራይ ህዝብ ፍቅረኛም አይደለም። የአቶ
መለስ ፍቅር ስልጣን ነው። ስለዚህ ትግል ሲጀምር ስልጣን በጎሳ ደረጃ እንጂ በአገር ደረጃ የሚያገኝ ስላልመሰለው
አቶ መለስ ጎሰኛ ሆነ። በአገር ደረጃ የስልጣን ባለቤት መሆን የሚቻል ሲመስለው ደግሞ ኢህአዴግ ምናምን የሚል
ሽፋን አጥልቆ ኢትዮጵያዊ ሆነ። በአፍሪካ ደረጃ የስልጣን ባለቤት መሆን የሚቻል ሲመስለው ደግሞ የፓን-አፍሪካ
ቆብ ያጠልቃል። ያም ሆነ ይህ የትግራይ ፍቅር አቃጥሎት ሳይሆን የጎሳ ፖለቲካን አቶ መለስ የፖለቲካ ህልውናው
መሰረት ያደርጋል። ኩዋሜ ግን አያደርግም። የእንድሪያስ እሸቴ ምስክርነት ምሁራዊ ስነምግባር ይጎድለዋል።
ለትዝብት ያህል በኢትዮጵያ ነፃነት፣ አንድነት እና ኤርትራ ጥያቄዎች ላይ ኩዋሜ እና አቶ መለስ የነበሩዋቸውን
አቅዋሞች ከታሪክ እንመልከት።(ሀ) በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ዋዜማ ኢጣልያ ኢትዮጵያን ስትወር የአቶ መለስ አያት ወይንም አባት ከወራሪው
ጣሊያን ጋር ስለመተባበራቸው የህውሃት የቀድሞ አባል የነበረው ገብረ መድህን አርአያ እና ሌሎች ጽፈዋል። ፓን
አፍሪካዊው ኩዋሜ ግን ወረራውን ተቃውሞ ነበር።
(ለ) እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1945 በንጉሰ ነገስት ኃይለስላሴ መሪነት እነ አክሊሉ ሃብተወልድ፣ እነ ሎሬንዞ እና
ሌሎች አገር ወዳድ ምሁራን በተባበሩት መንግስታት ኤርትራ ከኢጣሊያ ነፃ ወጥታ ከኢትዮጵያ እንድትቀላቀል
ፈታኝ እና እልህ አስጨራሽ የዲፕሎማሲ ትግል በሚያደርጉበት ወቅት በፓን-አፍሪካዊው ከዋሜ ንኩሩማ ይመራ
የነበረው 5ኛው ፓን-አፍሪካዊ ኮንፍረንስም ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ታሪካዊ ባለቤትነት እንዳላት መግለጫ
ለተባበሩት መንግስታት ልኮ እንደነበር ስፔንሰር, ‘Ethiopia at Bay’ መጽሐፉ ገጽ 198 ላይ ያመለክታል።
(ሐ) የአቶ መለስን አቅዋሞች እንመልከት፥
(ሐ-1) በኢትዮጵያ የመንግስት ስልጣን ሊጨብጥ ሲቃረብ (በ3 እና 5 April, 1990) በአሚሪካ ዋሽንግተን ዲሲ
ከአሜሪካዊው ሹም ከፖል ሄንዝ ጋር ያደረገው ፖለቲካዊ ጭውውት እንደሚያመለክተው ፖል ሄንዝ ኤርትራ እና
ኢትዮጵያ እንዳይለያዩ ማድረግ እንደሚቻል ሲናገር አቶ መለስ ሳይቀበል ቀርቷል። በስብሰባው ላይ አቶ ብርሃነ
ገ/ክርስቶስ፣ አቶ ስዩም መስፍን እና አቶ አሰፋ ማሞ ነበሩ። ፖል ሄንዝ እንደሞተ ዋሽንግተን ፖስት (The
Washington Post Sunday, June 5, 2011) ሰነዱን ስላተመው ከጉጉል ማግኘት ይቻላል።
(ሐ-2) የስልጣን ሽግግር ከደርግ ወደ ህውሃት በመደረግ ላይ ሳለም በሽግግሩ ወቅት የረዱት እነ ኮህን እና ካርተር
ሳይቀሩ በምስራቅ አፍሪካ ካሉት አገሮች ሁሉ ኢትዮጵያ ትልቋ አገር በመሆኗ ለኢትዮጵያ የባህር በር እንዲደራደር
ቢመክሩትም አፋቸውን እንዲዘጉ አድርጎ ኤርትራ እንድትገነጠል አድርጓል አቶ መለስ።
(3) እርግጥ አቶ መለስ የኢትዮጵያ የሰላም አባት ነበርን?
“ሰላም” ስንል “የፖለቲካ ሰላም” ማለታችን ነው። “የሰላም” መኖር አለመኖር መስፈርቱ “በአንድ አገር ውስጥ
የፖለቲካ ግጭት ሲወገድ፣ የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይኖር ሲደረግ፣ በሰላማዊ ትግል አምባገነኖችን በማስወገድ
ዘላቂ ሰላም ማምጣት ሲቻል ወይንም ጥረት ሲደረግ ነው። አቶ መለስ የኢትዮጵያን መንግስት ስልጣን
ከመጨበጡ በፊት ከደርግ ተቃዋሚዎች ህብረ ብሄር ኢ.ድ.ዩ. እና ኢሕአፓ ጋር የርስ በርስ ጦርነት አድርጓል።
የትግራይ ነፃ አውጭ ከነበረው ከቲ.ፒ.ኤል.ኤፍ ጋር በቀን ግንባር እንፈጥራለን ብሎ ከተስማማ በኋላ የድርጅቱን
አባላት ለሊት በእምነት ተኝተው እንቅልፍ ላይ ሳሉ ፈጅቷል። ከደርግ ተዋግቷል። ባጭሩ ለ17 አመቶች የእርስ
ጦርነት እንዲቀጥል እንጂ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ አድርጎ አያውቅም አቶ መለስ።
አቶ መለስ ስልጣን ላይ ከወጣም ወዲኽ የኤርትራን መገንጠል የተቃወሙ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪዎችን እና
በምርጫ 97 የህዝብ ድምጽ ይከበር ብለው ሰልፍ የወጡ ያልታጠቁ ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን በሰላማዊ መንገድ
አነጋግሮ ቅሬታቸውን መፍታት ሲችል ኢትዮጵያን በወረራ እያስተዳደረ ያለ መሪ በሚመስል አኳኋን ግንባር
ግንባራቸውን በማለት እንዲገደሉ አድርጓል። የሰላም ትግል ታጋዮችን፣ ጋዜጠኖችን በሃሰት ክስ ከማሰር አሰልሶ
አያውቅም። የአሁኑ ህዝባችን ብልህ (Smart) በመሆኑ ሰላማዊ ትግልን መረጠ እንጂ እንደ አቶ መለስ ቢሆን ኖሮ
በየአደባባዩ እና በየከተሞች መገዳደል ሊኖር ይችል እንደነበር ለአንድ አፍታም አልጠራጠርም።
ስለዚህ ለአለም፣ ለአህጉራቸው፣ ለአገራቸው እና ለማህበረሰባቸው ባበረኩቱዋቸው ሰላማዊ ትግሎች የኖቤል
“የሰላም ሽልማት” ከተሸለሙት እነ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ የደቡብ አፍሪካዊቹ ዴስማን ቱቱ እና ማንዴላ እና
ታዋኩል ካርማን (Tawakkul Karman) የሰላም አርበኞች ተርታ አቶ መለስ አይሰለፈም። ሽብርተኛ ነው መለስ።
(4) እርግጥ አቶ መለስ ለኢትዮጵያ ህዝብ ፍትህ፣ ጥሩ አስተዳደር እና ዲሞክራሲ አምጥቷልን?
ህውሃት ከሁለት ሊከፈል ግድም አቶ መለስ ጣቱን ወደነ ስዬ አብርሃ አሹሎ ቦናፓርቲዝም ነገሰ ሲል
ታስታውሳላችሁ? ብልጭ ብሎ የነበረውን ዲሞክራሲ ያጠፋ ቦናፓርቲ (ቀልባሽ አምባገነን) እራሱ አቶ መለስ
ነበር። ሽብርተኛነቱን ህጋዊ የሚያደርግ ህግ በመደንገግ፣ አፋኝ ፀር-ፕሬስ እና ፀረ-ሲቢክ ድርጅቶች አዋጅ
በማጽደቅ ብልጭ ብሎ የነበረውን ዲሞክራሲ ያጠፋው አቶ መለስ ነው። እነዚህን ህጎች በመጠቀም ለዲሞክራሲ
ግንባታ ጠቃሚ ተቋሞች እንዲጠፉ አሊያም የአምባገነናዊ ስልጣን ምሶሶዎች እንዲሆኑ ያደረገው አቶ መለስ ነው።
በዚህ ረገድ ከህዝብ ፍትህ፣ ጥሩ አስተዳደር እና ዲሞክራሲ የግል ስልጣኑን በማስቀደም የፖሊስ፣ የደህንነት፣
የምድር ጦር፣ የአየር ኃይል፣ ከከተማ እስከ ቀበሌ በተዋረድ ያሉ አስተዳደሮች፣ የፍትህ ዘርፍ፣ ቢሮክራሲው፣
ኢቲቪ ፣አዲስ ዘመን፣ ነፃ ፕረስ መሰል የህውሃት ጋዜጦች፣ ሬዲዮኖች (የእነ ሚሚ ስብሃትን ረዲዮኖች ጨምሮ)፣
በውጭ ጉዳይ ግልጋሎት ስር ያሉት ዛሬ በነ ቴዎድሮስ አድሃኖም እና በብርሃን ገብረ ክርስቶስ የሚመሩት
የኢትዮጵያ ኢምባሲዎች እና ቆንሲላዎች በሙሉ የአምባገነን መለስ የስልጣን መደገፊያ ምሶሶዎች ተደረጉ።እንዲሁም ከፍ ብለን ባስተዋልናቸው የስልጣን ምሶሶዎች ላይ የዲሞክራሲ ምሶሶዎች መሆን የሚገባቸውን
የሰራተኛ፣ የመምህራን፣ የሙያተኛ፣ የሴቶች፣ የወጣቶች ማህበራት አመራራቸውን ካድሬዎች በቀጥታ አሊያም
በተዘዋዋሪ መንገድ እንዲቆጣጠሩዋቸው በማድረግ ተጨማሪ የመንግስት ስልጣን ድጋፍ ምሶሶዎቹ እንዲሆኑ
ያደረገው አቶ መለስ ነው። የሙስሊሞች መጅሊስ እና የክርስትና መንፈሳዊ ተቋሞች ሳይቀሩ የፖለቲካ ስልጣን
ምሶሶች እንዲሆኑ አመራራቸውን የተቆጣጠረው አቶ መለስ ነው።
ስለዚህ ለፍትህ፣ ለነፃ ምርጫ፣ ለህግ የበላይነት፣ ለጥሩ አስተዳደር እና ለዲሞክራሲ ከታገሉ ሰዎች ተርታ ፍጹም
የማይሰለፍ ሰው ነው አቶ መለስ።
[ክፍል ሶስት እንገናኝ!]

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on May 3, 2013
  • By:
  • Last Modified: May 3, 2013 @ 10:26 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar