www.maledatimes.com ከሙስሊሙ ህብረተሰብ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተላለፈ መልእክት - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ከሙስሊሙ ህብረተሰብ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተላለፈ መልእክት

By   /   July 26, 2012  /   Comments Off on ከሙስሊሙ ህብረተሰብ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተላለፈ መልእክት

    Print       Email
0 0
Read Time:30 Minute, 28 Second

የተከበራችሁ መላው የሃገራችን ህዝቦች
ሰላምታችን እና መልካም ምኞታችን ከሁሉም ነገር ይቀድማል፡፡ ይህን መልእክት ለእናንተ ለወገኖቻችን እንድንፅፍ ያነሳሳን ምክንያት አንድም በሃገሪቱ በመንግስትም ሆነ በማንኛውም ዜጋ ስለሚከናወኑ ጉዳዮች መረጃ የማግኘት መብታችሁን ከማክበር ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሰሞኑን የራዲዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎቻችን ከወትሮው ለየት ያለ የጭንቅ ቀን አይነት መረጃ ማቅረብን በማዘውተራቸው አንድ ለህዝብ ግልፅ ሊሆን የሚገባ እውነታ በመኖሩ ይሄንን ሃላፊነት ለመወጣት ነው፡፡
አብዛኞቻችሁ እንደምታውቁት የሃገራችን ህገመንግስት በግልፅ ካስቀመጣቸው ድንጋጌዎች ውስጥ የሃይማኖት ነፃነትና የመንግስትንና የሃይማኖትን መለያየት ይገኝበታል፡፡ ይህ ድንጋጌ በሃገሪቱ የሚገኝ ማንኛውም ሰው በፈለገው የማመንንና ሲፈልግም በምንም አለማመንን መብት ያረጋገጠ በመሆኑ በልዩ ክብር የምንጠብቀው ነው፡፡ ነገር ግን ይህ በህገመንግስቱ ላይ በደማቅ ተፅፎ የሚገኘው ድንጋጌ በአስፈፃሚዎች አማካኝነት ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ በመምጣት እምነትህን እኔ ካልመረጥኩልህ የሚባልበት ደረጃ ላይ የተደረሰበት ክስተት ሃምሌ 2003 ተፈጠረ፡፡ የህገመንግስት ጥሰቱንም በቡራኬ ይፋ ያደረጉት የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም ሲሆኑ ጉዳዩንም ሰው በተሰበሰበበት በጊዮን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነበር፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ሸኽ አብደላ አልሃረሪ በሚባል ግለሰብ የተመሰረተና አመለካከቱ በገባባቸው ሃገሮች በሙሉ ትርምስ እና የእርስ በእረስ ፍጅት በማስከተል የሚታወቅ ‹አህባሽ› የተባለ እራሱን በእስልምና ስም ሸፍኖ የሚንቀሳቀስ አንጃ አለ፡፡ የአንጃውን ውስጠ ሚስጥር ሳይረዱት ቀርተው ይሆን ወይንም ያላወቅነው ሚስጥር በመኖሩ ክቡር ሚኒስትሩ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ‹‹ይህንን አመለካከት በሃገራችን ለማስፋፋት እንዴት ብንሰራ ይሻላል በሚል መንግስት ለረጅም ግዜ ሲመክር ቆይቷል›› ሲሉ እጅግ አሳዛኝና አስተዛዛቢ ንግግር አደረጉ፡፡ የአንጃው ተወካይና ከፍተኛ አራማጅ ከቤሩት ተጉዘው በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ በመገኘት ካደረጉት ንግግር ደግሞ ‹‹ወደኢትዮጵያ በነዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ተጋብዤ ስመጣ ነገሩን ለትንሽ ግዜ ለማሰብ ሞክሬ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን እምነት (አህባሽን) ለማስፋፋት መወሰኑ ትልቅ እርምጃ ነው›› በማለት መንግስት ሃይማኖት ሊመርጥልን እና በግልፅ የተቀመጠውን ህገመንግስታዊ ድንጋጌ በራሱ ሊንደው መነሳቱን አረዱን፡፡ እነዚህ ንግግሮች ደግሞ በደምፅ ተቀድተው ከበርካታ ህዝብ ዘንድ በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ደርሰዋል፡፡ ዛሬም ድረስ ለማንኛውም ሰው ማድመጥ ይቻላል፡፡
እስቲ አንድ ጥያቄ እንጠይቃችሁ፡፡ ለዘመናት የኖራችሁበትን እምነት መንግስት እና አስፈፃሚዎች በድንገት ተነስተው ‹‹እኛ ሌላ እምነት ለማስፋፋት አስበናልና እሱን መከተል አለባችሁ ብትባሉ ምን ይሰማችኋል? መልሳችሁስ ምን ሊሆን ይችላል? ነገሩን ከባለስልጣናቱ ጋር በፊታውራሪነት ብዙውን ግዜ ደግሞ በታዛዥነት የሚያስፈፅመው ደግሞ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን መንፈሳዊ ህይወት በመምራት መንግስት የሰጠንን የሃይማኖት ነፃነት ሳይሸራረፍ እንዲከበር ጥብቅና ሊቆም የሚገባው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) አመራሮች ናቸው፡፡ የመጅሊስ አመራሮች ከህዝብ በሚሰበሰብ ገንዘብ እየተመሩ ለካንስ አስቀድመው የዚህ አዲስ እምነት ተከታይ እና አራማጅ በመሆን በህዝብ ላይ ሸፍጥ ሲሰሩ ኖረዋልና ይህንን ዘመቻ በይፋ ማፋፋም ጀመሩ፡፡ ነገሩ በዚህም ብቻ ሳያበቃ እያንዳንዱ የመስጂድ አሰጋጅ፤ አዛን አድራጊ እንዲሁም ሰባኪያንና ቁርአን አስተማሪዎች የዚህን እምነት ቀኖና ተምረው ተግባራዊ ካላደረጉ በስራቸው መቆየት እንደማይችሉ መጅሊሱ አውጆ በሰፊ ዝግጅት እና በህዝብ በጀት የእምነት ማስቀየር የግዴታ ስልጠና በመላ ሃገሪቱ ተጀመረ፡፡ ስልጠናውን አልከታተልም የሚል ወይንም ቀኖናውን የሚነቅፍ ‹‹አክራሪ›› እና ‹‹ፅንፈኛ›› እየተባለ ይብጠለጠል ጀመር፡፡ በመጅሊሱ መተዳደሪያ መሰረት የአመራሮቹ ምርጫ በየአምስት አመት መደረግ እንዳለበት የተደነገገ ቢሆንም ላለፉት 12 አመታት ህዝበ ሙስሊሙ ምርጫ የሚባል ነገር ባላየበት ሁኔታ እርስ በእርስ እየተሷሷሙ የመጡት አመራሮች የህዝብን ዝምታ ከሞት በመቁጠር እምነት ማስቀየር ዘመቻ ከባለስልጣናት ጋር በመሆን ተያያዙት፡፡ መጅሊሱ ከዚህም አልፎ ረዳት አልባዎች የሚረዱበት፤ ቀባሪ ያጡ የሚገነዙበትና የሚቀበሩበት፤ ከመዋእለ ህፃናት እስከ ኮሌጅ ድረስ ትምህርት ቤት እና ሆስፒታል ያለውን የአወሊያን ሚሽነሪ ትምህርት ቤት 50 መምህራንና ሰራተኞችን በአንድ ቀጭን ትዕዛዝ ከስራ አሰናበተ፡፡
የተከበራችሁ የሃገራችን ዜጎች
እነዚህ ሁሉ አይን ያወጡ የህግ ጥሰቶች ሲፈፀሙ ህዝበ ሙስሊሙ በውስጡ ከመቃጠል እና ውስጥ ለውስጥ ከማጉረምረም የዘለለ
ምንም ያሳየው ነገር አልነበረም፡፡ የመብት ጥሰቱ እየጨመረ ሲመጣና የሚጥሱትም አካላት እንደመብታቸው በመቁጠር በግላጭ ህግን ሲጥሱ ከስምንት ወራት በፊት ህዝቡ በመሰባሰብ መመካከር ጀመረ፡፡ ተከታታይ ውይይቶች ከተካሄዱም በኋላ በአንድ የአርብ ስግደት ላይ ጥያቄዎቻችንን ለመንግስት በማቅረብ መልስ ማስገኘት አለብን ከሚል ስምምነት ላይ በመድረስ ለችግሮቻችን ዋና መንስኤ የሆኑና ለመንግስት የሚቀርቡ ሶስት ግልፅ ጥያቄዎች ተለዩ፡፡ እነሱም፡-
1. በስልጣን ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮች ያለምርጫ የመጡና ህዝቡን የማይወክሉ በመሆናቸው ህዝቡ በነፃ ፍላጎቱ፤ በገለልተኛ አስመራጮች እና በመስጂድ ደረጃ በሚመርጣቸው አመራሮች ይተኩልን፡፡ 2. አህባሽ የተባለው እምነት እንደ ማንኛውም እምነት እራሱን ችሎ የመንቀሳቀስ መብት ይኖረዋል እንጂ በሙስሊሙ መስጂዶችና መዋቅር ውስጥ በግድ እንዲጫን ሊደረግ አይገባውም 3. አወሊያ የህዝብ ንብረት እንደመሆኑ መጠን እራሱን በአግባቡ ማስተዳደር ለማይችለው መጅሊስ መሰጠት የሌለበት ሲሆን ህዝብ በሚመርጣቸው የቦርድ አባላት ይተዳደር የሚሉ ጥያቄዎች እና 4. ለነዚህ ጥያቄዎች መመለስ መንግስት አስፈላጊውን ትብብር ያድርግልን የሚል ነበር፡፡
እነዚህን ጥያቄዎች ለመንግስት ለማድረስና መፍትሄ ለማፈላለግ ደግሞ ህዝቡ በራሱ ፍቃድ 17 አባላት ያላቸውን ተወካዮች (ከሃገር ሽማግሌዎች፤ ከሃይማኖት ኣዋቂዎች፤ ከምሁራን እና ከሰባኪያን) አብዛኞቹ በሌሉበት በመጠቆም መረጦ ምርጫውን እንዲቀበሉ ጫና አሳደረ፡፡ ተወካዮቹም የህዝብን ጫና በመፍራት ጥቆማውን በመቀበል እና ከመላ ሃገሪቱ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የተፈረሙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የድጋፍ ፊርማዎችን በማስረጃነት በመያዝ እነዚህን ሶስት ጥያቄዎች ብቻ በመያዝ ምላሽ ለማፈላለግ ከላይ ታች ሲሉ ስምንት ወራት አለፉ፡፡ በሂደቱ ከክፍለ ከተማ እስከ የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከ ሁሉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ድረስ እነዚህን ጥያቄዎች በመተንተን በተለያየ ግዜ አቅርበዋል፡፡ ከዚህም አልፎ ቢያንስ ከሶስት ሚኒስትር መስሪያቤቶች ሚኒስትሮች ጋር ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን መፍትሄው ግን እንደታሰበው ቀላል አልሆነም፡፡ የጥያቄዎቹ ግልፅነት፤ የአቀራረባቸው ሰላማዊነትና ህገመንግስታዊነት ግን ከኢህአዴግ ምክር ቤት ጀምሮ በተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ምስክርነት አግኝቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ከሶስት ረጃጅም ቀጠሮ በኋላ ወሳኝ መልስ ይገኝበታል ተብሎ የሚጠበቅበት የካቲት 26 ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም እና ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሙሉጌታ ውለታው ጋር ከቀኑ 8 ሰአት እስከ ምሽቱ 2 ሰአት የደረሰ እጅግ ሰላማዊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን በእለቱ ከክቡራን ሚንስትሮቹ የማይጠበቅ ተግባር ተፈፀመ፡፡ ይኸውም ውይይቱ ሳይጠናቀቅ እና ተወካዮቹ ለመግሪብ ስግደት ለጥቂት ደቂቃዎች በወጡበት ቅፅበት ለሬዲዮ ፋና ‹‹የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች መልስ ማግኘታቸውንና ከተወካዮቹም ጋር መግባባት ላይ መድረሳቸውን አወጁ፡፡ ይህም ተብሎ ከፀሎት መልስ የቀጠለው ውይይት ላይ ለተወካዮቹ የተነገራቸው መልስ
1. የመጅሊስ ምርጫ ይካሄዳል ግን መቼ እንደሚካሄድ መናገር አይቻልም፡፡ ነገር ግን ምርጫውን የሚያስፈፅመው አሁን በስልጣን ላይ ያሉት አመራሮች እንጂ ገለልተኛ አስመራጭ አይቋቋም፡፡ ምርጫውም በመስጂድ ደረጃ ሳይሆን በቀበሌ ነው የሚካሄደው፡፡ 2. አህባሽን በተመለከተ ከዚህ በፊትም በግዴታ አልተሰጠም አሁንም በግዴታ አይሰጥም ስልጠናው ግን ይቀጥላል 3. አወሊያን መጅሊሱ ማስተዳደር ይቀጥላል፡፡ በቦርድ ይተዳደር የሚለው ተቀባይነት የለውም የሚሉ ነበሩ፡፡ የተከበራችሁ የሃገራችን ዜጎች
እዚህ ጋር እናንተው ልትፈርዱት የምትችሉት እውነት የትኛው ጥያቄ ይሆን በተጠየቀበት መልኩ መልስ ያገኘው? ነገሩ የእምነት ነፃነት ጉዳይ ነውና ተወካዮቹ ጥያቄዎቹ ተገቢውን መልስ አለማግኘታቸውን፡፡ ማለትም 1. የመጅሊስ ምርጫ በተቻለ ፍጥነት እና በገለልተኛ አስመራጭ አማካኝነት መካሄድ የሚኖርበት ሲሆን ጉዳዩም ሃይማኖታዊ እንጂ ፖለቲካዊ ባለመሆኑ በመስጂድ ሊካሄድ ይገባዋል 2. አህባሽ በራሱ ተቋም እንደ ሌላ እምነት ሊንቀሳቀስ ይገባዋል እንጂ በሙስሊሙ ንብረት በሚተዳደሩ የመጅሊስ መዋቅሮችና መስጂዶች ሊሰጥ አይገባውም 3. አወሊያም በህዝብ በሚመረጡ የቦርድ አባላት ይተዳደር በሚል ለጥያቄዎቹ መልስ አለማግኘቱን ነገር ግን የፌዴራል ጉዳዮች ቢያንስ በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ያደረገውን ትብብር አመስግኖ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አንድ የመንግስት እርከን እንጂ የመጨረሻ ባለመሆኑ ጥያቄዎቹን ለቀጣይ የስልጣን እርከን እንደሚየቀርብ በደብዳቤ በማሳወቅ ከፌዴራል ጉዳዮች ጋር የነበረውን ውይይት ቋጨ፡፡
ይህንንም ተከትሎ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በጉዳዩ ላይ ውይይት ለማድረግ ካላቸው ጠባብ የስራ ወቅት ላይ ቀጠሮ እንዲይዙ የሚጠይቅ ደብዳቤ አስገባ፡፡ የውይይት ቀጠሮውን በመጠባበቅ ላይ ባለበት ወቅት ድንገት ሳይታሰብ ያ ሰላማዊ የተባለና በሚዲያ ደረጃ የተወደሰ ጥያቄ እና አቅራቢው ህዝብ ህገ ወጥ፤ ለሰላማዊ አካሄድ ዝግጁነት የሌለው እየተባለ በመግለጫ መብጠልጠል ተጀመረ፡፡ ይሄ በጣም አስደንጋጭ እና ያልተጠበቀ በመሆኑ ለግዜው ግራ ቢያጋባንም ነገሩን በሰከነ መንፈስ በመገምገም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጠሮ እስኪገኝ በትዕግስት ለመጠበቅ ተወሰነ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩም ቀጠሮ መዘግየትና የአዝማሚያዎች አለማማር
ተከትሎ ምናልባት እኛው በሰራነው ወንጀል ኃጢያት ሊሆን ይችላልና አምላክ ይምረን ዘንድ ምፅዋት እንስጥ በሚል ህዝቡ ገንዘቡን እያዋጣ ለነዳያንና ለህዝብ ሰደቃ በማዘጋጀት የፀሎት ፕሮግራሞች በመላ ሃገሪቱ መካሄድ ጀመሩ፡፡ እነዚህ የሰደቃ ፕሮግራሞች ህዝብ በልቶ፤ ፀልዮ እና በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ የሚለያይባቸው እንጂ ምንም አይነት የረብሻም ሆነ የአመፅ አካሄድ ያልተስተዋለባቸው ነበሩ፡፡
ለዚህ ደግሞ በስፍራው የተገኙ የፀጥታ ሃይሎች ሳይቀሩ ሊመሰክሩ ይችላሉ፡፡ የዚሁ አካል የሆነውና በአዲስ አበባ አወሊያ ሊካሄድ የታሰበው የሰደቃ (ምፅዋት) ፕሮግራም ለሃምሌ ስምንት ተቀጥሮ የእርድ ሰንጋዎች ገብተውና የማብሰያ ቁሳቁሶች ተዘጋጅተው አርብ ለቅዳሜ ሌሊት ምግብ ለመስራትና ግቢ ለማሰናዳት ከመሰጂድ ባደሩ ምእመናን ላይ ያልታሰበና ለምን እንደተደረገ ያልታወቀ ድንገተኛ ተኩስ ተከፍቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲቆስሉ እስከአሁን የት እንደደረሱ ያልታወቁም ይገኛሉ፡፡ ቀሪዎቹን ለመክተፊያ ይጠቀሙበት የነበረውን ቢላዋ እያስያዙ በግድ በመቅረፅ ወደ እስር ቤት ወረወሯቸው፡፡
አንድ አደጋ ሲከሰት መስጂዶች አዛን ማድረግና ቤተክርስቲያኖች ደወል መደወል የተለመደ እንደመሆኑ በእለቱ በከተማው የሚገኙ በርካታ መስጂዶች አዛን አሰሙ፡፡ ይህንንም ተከትሎ በርካታ ምእመናን ወደመስጂድ ለፀሎት ሲተሙ በየአካባቢያቸው ተኩስ እየተከፈተ፤ አስለቃሽ ጭስ እየተተኮሰ እና ህዝቡ በዱላ እየተደበደበ እጅግ አሳዛኝ ሌሊት አነጋ፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን ህዝቡ ተቃውሞውን ቅዳሜ እና እሁድ የገለፀው በአንድ ግቢ ውስጥ በመወሰን የማንንም መብት ሳይነካ በሃዘንና በለቅሶ ብቻ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ በመንግሰስት መገናኛ ብዙሃን የተላለፈው ዜና ግን ህዝብን ሽምጥጥ አድርጎ የካደ እና የሚያሳዝን ሆነ፡፡ እንግዲህ ይህችን የሰደቃ ፕሮግራም ተከትሎ ነው ነገሮች ከመቅፅበት የተቀያየሩት፡፡ ሰላማዊነታቸው የተወደሰው የኮሚቴ አባላት እንደሽፍታ እየታደኑ ተይዘው ኢ ሰብአዊ የሆነ አያያዝ ስር ይገኛሉ፡፡ ሌሎች ሰባኪያንና የሃገር ሽማግሌዎችም ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ገጥሟቸዋል፡፡ ይህንን መሪር ሃዘን ለመግለፅ በአንዋር መስኪድ የተሰበሰቡ በአስር ሺዎች በሚቆጠሩ ምእመናን ላይ ነው የሰሞኑ የሚዲያ ሽፋን የሆነው የጅምላ እስራትንና ድብደባ ያስተናገደው ክስተት የተፈጠረው፡፡ ይኼኛውም እንደሌሎቹ በመስጂድ ቅጥር ግቢ በተሰባሰቡ ምእመናን ላይ የተከፈተ ጥቃት እንጂ ህዝብ ለአመፅ የተነሳሳበት አካሄድ አልነበረውም፡፡ አይኖረውምም፡፡
የተከበራችሁ የሃገራችን ዜጎች
እኛ እየጠየቅን ያለነው ግልፅ፤ ቀላል እና ንፁህ የሃማኖት መብት ጥያቄ ነው፡፡ ጥያቄዎቹ ማንም እንደፈለገው ዳግም አቡክቶ ቢጋግራቸው ሌላ ምንም ሊወጣቸው አይችሉም፡፡ ግልፅ ጥያቄአችንን በሃይል በመጠምዘዝ ፖለቲካዊ ይዘት ለማላበስ በመንግስት የሚደረገው ጥረት ምክንያቱ ባይገባንም ጥያቄአችን ንፁህ የመብት ጥያቄ ብቻ መሆኑን አሁንም ለመግለፅ አንደክምም፡፡ የፖለቲካ ጥያቄ ነው ያላቸው፤ እስላማዊ መንግስት ለማቋቋም ነው—-በሚል የሚነዙት ውሃ የማይቋጥሩ ተራ ወሬዎች ተናጋሪውን ከማቅለል ያለፈ ትርጉም የላቸውም፡፡ ይህንን ተራ አሉባልታ ለማጠናከር በሚልም ተደጋጋሚ ድራማዎችና በዘጋቢ ፊልም ስም የሚቀርቡ ውዥንብሮች ተበራክተዋል፡፡ በቀጣይም ይበልጥ ተጠናክረውና የህዝብ ለህዝብ አንድነትን ሊንዱ በሚችሉ መልኩ ተቀናብረው ሊቀርቡ እንደሚችሉ በብዙ ይጠበቃል፡፡ እኛም የሚነዙብን አሉባልታዎችን ወደ ጎን በመተው ከላይ የዘረዘርናቸውን ግልፅ ጥያቄዎቻችን እንዲመለሱ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ የታሰሩ የእምነት ወነድሞቻችን እስኪፈቱ ሰላማዊ ትግላችንን እንደምንቀጥል ስንገልፅላችሁ የጥያቄአችንን ግልፅነትና ከፖለቲካ ንፁህነት እንደከዚህ ቀደም እንድትረዱልን በመጠየቅ ነው፡፡
ይህ ለመነሻ ግንዛቤ ያህል እንዲረዳ በማሰብ የተዘጋጀ እንጂ ዝርዝር ሃሳቦችን አለመያዙን እንረዳለን፡፡ በቀጣይ ሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ እንደምንፅፍ እየገለፅን አጠቃላይ ሂደቱን በይበልጥ ለመረዳት የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው ያሳተመውን ‹‹እውነቱ ይህ ነው›› የሚለውን መፅሃፍ እንዲያነቡ እንጋብዛለን፡፡
አምላክ ሃገራችንንም ዜጎቿንም ሰላም ያድርግልን
ኢትዮሚድያ
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar