www.maledatimes.com ሑዱር ታሎ ኦይልና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስህተት ያሳዩ ሌሎች ጉዳዮች - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ሑዱር ታሎ ኦይልና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስህተት ያሳዩ ሌሎች ጉዳዮች

By   /   May 4, 2013  /   Comments Off on ሑዱር ታሎ ኦይልና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስህተት ያሳዩ ሌሎች ጉዳዮች

    Print       Email
0 0
Read Time:25 Minute, 25 Second
ሑዱር ታሎ ኦይልና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስህተት ያሳዩ ሌሎች ጉዳዮች
 

ከስድስት ዓመታት በፊት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ያቀረቡት የመከላከያ ሚኒስትር ከምክር ቤቱ አባላት የቀረቡ ጥያቄዎችን ሙሉ ለሙሉ መመለስ ተቸግረው ነበር፡፡ የችግሩ ምንጭ መልስ ማጣት አልነበረም፡፡

ለሁሉም ጥያቄዎች ምላሽ የመስጠቱ ተገቢነት ነበር ለሚኒስትሩ ጥያቄ የሆነባቸው፡፡ ምክንያቱም እንዲመልሱ የተጠየቁት በይፋ ሊነገሩ የማይችሉ ጥቂቶች ብቻ እንዲያውቋቸው የተደረጉ የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ጉዳዮችን በመሆኑ ነው፡፡ እናም፣ ‹‹እያቀረብኩ ያለሁት ሪፖርት የግብርና ሚኒስቴርን አይደለም›› በማለት ጠቅለል ባለና ቅኔያዊ በሆነ አቀራረብ የምክር ቤቱ አባላትን አስረድተዋል፡፡ ሚኒስትሩ ይህንን ማለታቸው ተገቢና በሌሎች አገሮችም ጭምር ተቀባይነት ያለው አሠራር ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በይፋ መናገሩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ኪሣራ ጭምር  ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥታቸውን የስምንት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተጠይቀው የሰጡት ምላሽ የመረጃ መጣረሶች የተንፀባረቁባቸው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን በአገሪቱ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ላይ ሊያስከትሉ የሚችል አቅም ነበራቸው ማለት ይቻላል፡፡ ከእነዚህ ፖለቲካዊ ስህተቶች አንዱን ለማስተካከልም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሲደክም ተስተውሏል፡፡

ሑዱር
የኢሕአዴግ አጋር ፓርቲ የሆነው የሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አባልና የፓርላማው ተወካይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሶማሊያ ውስጥ የተሰጠውን የሰላም ማስከበር የተመለከተ ጥያቄ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አቅርበውላቸው ነበር፡፡

የምክር ቤቱ አባል ጥያቄ በሶማሊያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ከአገሪቱ እንዲወጣ በመንግሥት በኩል አቋም ተይዟል ወይ? ይህ ከሆነ በአንፃራዊ ሰላም ላይ የምትገኘው ሶማሊያ ተመልሳ ብጥብጥ ውስጥ ትገባለች የሚል ነበር፡፡

ለማሳያነትም ሑዱር ከተባለችው የሶማሊያ አካባቢ የኢትዮጵያ ጦር መውጣት መጀመሩን ተከትሎ፣ በአልሸባብ ቁጥጥር ውስጥ በድጋሚ እየገባች ትገኛለች በማለት የመንግሥት አቋም ምን እንደሆነ እንዲያብራሩ ጠይቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ መስጠት የጀመሩት በጐረቤት አገሮች መካከል ሰላማዊ ሁኔታን ለመፍጠር ከአገሮች ጋር መተባበር፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ የታወቀችበትና ዝናን እያተረፈላት የሚገኘው የሰላም ማስከበር ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል የመንግሥታቸው አቋም መሆኑን በማስረዳት ነበር፡፡ ከዚህ አክለውም አልሸባብ ምንጊዜም የኢትዮጵያ ጠላት በመሆኑ የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ሁሌም የሚፋለመውና ለዚህም ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሑዱር ስለሆነው ሲገልጹ የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ጦር (አሚሶም) የኢትዮጵያ ሠራዊት ተልዕኮውን ካጠናቀቀ በኋላ የኢትዮጵያ ጦር ያፀዳውን አካባቢ የመረከብ ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ የተፈጠረ ነው በማለት ነበር፡፡

‹‹እንደሚታወቀው ተልዕኳችንን በመወጣት ወደ ድንበራችን በፍጥነት መመለስ ነበር ወደ ሶማሊያ ስንገባ ተቀምጦ የነበረው አካሄድ፡፡ ነገር ግን ወደ ሶማሊያ ከገባን አንድ ዓመት ሞልቶናል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ቆይታ አሚሶምን ወቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጦር በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች አልሻባብ የረባ አቅም የለውም ስለዚህ የአሚሶም ጦር ይተካና የኢትዮጵያ ጦር ይውጣ አልያም አልሸባብ ጠንከር ባለባቸው አካባቢዎች የኢትዮጵያ ጦር ቢገባ ይሻላል የሚል የኢትዮጵያን አቋም ለማስገንዘብ ቢጣርም፣ በሁለቱም አማራጮች መፍትሔ አለመሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

‹‹በየወሩ እየተገመገሙ እሺ የሚሉ ነገር ግን የማይፈጽሙ በመሆናቸውና ለመተካትም አንድ ዓመት የፈጀባቸው በመሆኑ አሁን የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ኃይል መግባት አለበት፡፡ እኛ ዝም ብለን ቁጭ ከምንል ወደ ድንበራችን መምጣት አለብን የሚል ግምገማ ሰለነበረን ነው ከሑዱር የወጣነው፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም፣ ‹‹አልሸባብ ሑዱርን ተቆጣጠረ የማባለው የጨዋታ ነገር ነው፡፡ በአካባቢው የሚረባ አልሸባብ አይደለም ያለው በአንድ ቀን የሚሮጥ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ይህ የሰጡት መልስ የኢትዮጵያ ጦር ሑዱርን ለቆ መውጣቱን በዚህ አካባቢ ደካማ ቢሆንም የአልሸባብን መኖር ያረጋገጠ ነው፡፡ በመሆኑም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት ቀደም ባሉ ሳምንታት የኢትዮጵያን ጦር ከሑዱር መውጣትና የአልሸባብ በአካባቢው መደራጀት መጀመርን አስመልክቶ የውጭ መገናኛ ብዙኀን ያሠራጩትን ዘገባ ሲያስተባብሉ የነበሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲፕሎማቶችን ጥረት መና ያስቀረ ነው፡፡

በተጨማሪም አሚሶም በሥርዓቱ አካባቢውን ሳይረከብ መውጣት ኢትዮጵያ በተለያዩ አገሮች የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ቀዳሚነትን በመውሰድ የገነባችው ስም ላይ ጥቁር ነጥብ የሚጥል መሆኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተንታኞች የሚናገሩት ነው፡፡

እነዚህ ተንታኞች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስቀመጡዋቸው ምክንያቶች ተገቢነት ያላቸው እንደሆኑ ይስማማሉ፡፡ ነገር ግን አፈጻጸሙ ችኩልነት የታየበትና ብልጥነት የጐደለበት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ አክለውም ጉዳዩ የሚመለከተው የአፍሪካ ኅብረትም ሆነ አሚሶም በግልጽና በይፋ ስለ የኢትዮጵያ ጦር መውጣት መጀመር ሳይነገራቸው ወደ ዕርምጃ መግባትና ይህንንም በይፋ በመናገር የሚመለከታቸው አካላት በሦስተኛ ወገን ወይም በመገናኛ ብዙኀን እንዲሰሙት መደረጉ፣ ትልቅ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳት እንዳለው አብራርተዋል፡፡ ለዚህም ይመስላል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በኋላ በነበሩ ሰዓታት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ኃይለ ማርያም በሑዱር ጉዳይ የፈጸሙትን ስህተት ለማረም ሲደክም የተስተዋለው፡፡

የተለያዩ ታዋቂ የውጭ ሚዲያዎች አቶ ኃይለ ማርያም በሶማሊያ ጉዳይ ላይ የተናገሩትን በደቂቃዎች ፍጥነት የዘገቡ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህንን ለማስተባበል ዓይኑን በጨው ታጥቦ ነው የዘመተው፡፡

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፍፁም የኢትዮጵያ ጦር ከሑዱር ወጥቷል አላሉም፤›› በማለት ፊት ለፊት የተጋፈጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ናቸው፡፡

እንደ ቃል አቀባዩ አቶ ኃይለ ማርያም ለፓርላማው የተናገሩት የኢትዮጵያ ጦር በፍጥነት በአሚሶም መተካት እንዳለበት ነው፡፡ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምም በተመሳሳይ ዘመቻ በመሳተፍ የኢትዮጵያ ጦር በፍጥነት መተካት አለበት በሚለው የመንግሥት አቋም ላይ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ጦር እስካሁን አለመውጣቱንና የአወጣጥ ሒደቱ የኢትዮጵያ ጦር ከተካ በኋላ በተለያዩ ምዕራፎች እንደሚሆን፣ በዚያው ሳምንት አዲስ አበባን ለጐበኙት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላምና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አስረድተዋል፡፡

ታሎ ኦይልና ሌሎች
ሌላው ከምክር ቤቱ የተነሳው ጥያቄና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የሰጡት ምላሽ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ህፀፅ የታየበት በኢትዮጵያ የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ላይ ስለተሰማራው የውጭ ኩባንያ ጉዳይ ነው፡፡

ታሎ ኦይል የተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ፣ አፍሪካ ኦይል የተባለ የካናዳ ኩባንያና ማራቶን ኦይል የተባለ ሌላ የአሜሪካ ኩባንያ የጋራ ኢንቨስትመንት ጥምረት በመመሥረት በታሎ ኦይል መሪነት የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ላይ በደቡብ ኦሞ መሰማራታቸው ይታወቃል፡፡ በታሎ ኦይል መሪነት የሚከናወነው ይህ የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች ከተደረገው ጥረት ጋር ሲነፃፀር በአጭር ጊዜ ውስጥ ተስፋ ሰጪ ፍንጮች የታዩበት ነው፡፡ ኩባንያው ከሚሳተፍበት የቢዝነስ ባህሪ አንፃር እያንዳንዷን የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ለባለአክሲዮኖች የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ የነዳጅ ፍለጋ ሒደቱን ይፋ ያደርጋል፡፡ ይህንን ተከትሎ ደግሞ የተለያዩ የውጭ እንዲሁም የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኅን ኩባንያው ያገኛቸውን ተስፋ ሰጪ ግኝቶች በተደጋጋሚ ሲዘግቡ ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የመገናኛ ብዙኅኑ የኩባንያውን እያንዳንዷን ግኝት አሰፍስፈው ይከታተላሉ፡፡

የወጡት ዘገባዎችን መሠረት በማድረግ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን መላምታቸውን እየሰጡ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ጥርት ያለ እውነት መቀመጥ አለበት ብለው ያመኑ አንድ የምክር ቤቱ አባልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንዲሰጡ፣ አልያም ነዳጅ ተገኝቶ ከሆነ ለሕዝቡ እንዲያበስሩ በማለት ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በነዳጅ ላይ ጥገኛ የሆነ ኢኮኖሚ የመፍጠር አቋም እንደሌለው በመግለጽ ምላሽ መስጠት የጀመሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ነዳጅ ቢገኝ እንኳ የአገሪቱ ኢኮኖሚን እየመሩ ያሉ ዘርፎችን በገንዘብ እንዲደግፍና የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንዲሆን ብቻ ነው የሚፈለገው በማለት ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በመቀጠል የተናገሩት ግን ከታሎ ኦይል ኩባንያ መግለጫ ጋር የሚጣረስ፣ እንዲሁም በኩባንያው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ጉዳት የማድረስ አቅም ያለው መሆኑን ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

በነዳጅ ፍለጋ ተግባር ላይ የሚሰማሩ ኩባንያዎች አንድ የነዳጅ ፍለጋ ጉድጓድ ለመቆፈር እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያወጡ፣ ቁፋሮው ከተጠናቀቀ በኋላ ነዳጁ ባይኖር የተጠቀሰው ገንዘብ ከሰረ ማለት እንደሆነ አቶ ኃይለ ማርያም ለምክር ቤቱ በሰጡት ምላሽ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ኩባንያዎቹ ለፍለጋ ተግባራቸው ቀጣይነት ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ገና ሥራውን ሲጀምሩ የተለያዩ ተስፋ ሰጪ መግለጫዎችን ለሚዲያዎች በመስጠት ባንኮች ብድር ለማግኘት እንደሚያመቻቹ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ታሎ ኦይልን አስመልክቶ የሚወጡ መረጃዎች ከዚህ ተለይተው እንደማይታዩና ሕዝቡ በዚህ መደናገር እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡

ኩባንያው የቆፈረው ገና 800 ሜትር እንደሆነ ነዳጅ ለማግኘት ግን እስከ 2,600 ሜትር መቆፈር እንደሚያስፈልግ የተናገሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ተስፋ ሰጪ ግኝቶች ቢኖሩም ነዳጅ የሚገኝበት ደረጃ ላይ እንዳልተደረሰ አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ምላሽ ተገቢ እንዳልሆነ የሚያስረዱ ባለሙያዎች የምላሻቸው ግድፈት የሚጀምረው ኩባንያው የደረሰበትን ደረጃ በማዛባት ነው ብለዋል፡፡ ኩባንያው በቅርቡ በገለጸው መሠረት በደቡብ ኦሞ እየቆፈረ ያለው የነዳጅ ፍለጋ ጉድጓድ 1,800 ሜትር መድረሱን፣ በዚህም ኃይድሮ ካርቦን የተባለ ውሁድ ማግኘቱንና ይህ ውሁድ ነዳጅ ስለመኖሩ የሚጠቁም ትልቅ ፍንጭ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኩባንያው በእንግሊዝ ስቶክ ኤክስቼንጅ ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ያለውና በአክሲዮን የተመሠረተ እንደመሆኑ መጠን የፍለጋ ሒደቱን በየጊዜው የማሳወቅ ግዴታ አለበት በማለት ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ፡፡

ስቶክ ኤክስቼንጅ በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ተግባራዊ ያልሆነ ጠቃሚ ንግድ መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያዎቹ፣ ኩባንያዎች በዚህ ገበያ ውስጥ አክሲዮኖቻቸውን በመሸጥ ለኢንቨስትመንትም ሆነ ሌሎች ለተሰማሩባቸው ቢዝነሶች የሚፈልጉትን ካፒታል የሚያገኙበት ከባንክ የተሻለ አሠራር እንደሆነ ያብራራሉ፡፡

በመሆኑም የኩባንያው ባለአክሲዮኖች የኩባንያውን እንቅስቃሴ የማወቅ መብት ያላቸው ሲሆን፣ ይህም በኩባንያው ያላቸውን ደርሻ ለመሸጥ ወይም ለማቆየት እንዲወስኑ ይረዳቸዋል፡፡ ሌሎች የኩባንያውን ድርሻ መግዛት የሚፈልጉም እንደዚሁ ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ታሎ ኦይል መረጃዎችን የሚያወጣው የቢዝነስ (የስቶክ ማርኬት ገበያ) ባህሪው ስለሚያስገድደውና ገቢም ስለሚያገኝበት ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
ይህ ባይሆን እንኳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደዚያ ብለው ከመናገር መቆጠብ ነበረባቸው፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ላይ ጉዳት የሌለው በመሆኑና ለኩባንያው ገቢ የሚያስገኝ ለነዳጅ ፍለጋው የሚጠቅም እስከሆነ ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ታሎ ኦይል እ.ኤ.አ በማርች መጨረሻ ላይ ቁፋሮውን እንደሚያጠናቅቅና የነዳጅ ፍለጋ ውጤቱ እንደሚታወቅ ከዚህ ቀደም በመግለጹ ያለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ነው በወቅቱ መረጃውን ያወጣው የሚሉት ባለሙያዎቹ፣ በደረሰበት ቁፋሮ ነዳጅ አለማግኘቱን በማሳወቁም በስቶክ ማርኬት ገበያው መጠነኛ የዋጋ ማሽቆልቆል ማስተናገዱን አስረድተዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ከታሎ ኦይል መግለጫ በፊት የወጣ ቢሆን ኖሮ በኩባንያው ስቶክ ማርኬት ላይ ተጨማሪ ጉዳት ያደርስ ነበር፡፡ በመሆኑም በዚህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ከመስጠት በፊት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶችን መመዘን ሊቀድም ይገባል ሲል መክረዋል፡፡  source ER

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on May 4, 2013
  • By:
  • Last Modified: May 4, 2013 @ 8:09 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar