www.maledatimes.com የፍትህ ጉዳይ እና እነ እስክንድር ነጋ በአብረሃ ደስታ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የፍትህ ጉዳይ እና እነ እስክንድር ነጋ በአብረሃ ደስታ

By   /   May 5, 2013  /   Comments Off on የፍትህ ጉዳይ እና እነ እስክንድር ነጋ በአብረሃ ደስታ

    Print       Email
0 0
Read Time:17 Minute, 54 Second

በነ እስክንድር ነጋ … የእስር ፍርድ ምክንያት በማድረግ ስለ ጉዳዩ አስተያየት እንድሰጥ የተለያዩ የፌስቡክ ጓደኞቼ ሲወተውቱኝ ከርመዋል (የቅርብ ጓደኞቼ ግን ዝምታን መምረጥ እንዳለብኝ መክረውኛል)። አስተያየቴን እንድገልፅ የገፋፉኝ ጓዶች በቁጥር ብዙ ቢሆኑም ምክንያታቸው ወይ ዓላማቸው ግን የተለያየ ነው።

ብዙ ግዜ አስተያየቴን እንድሰጥ ከወተወቱኝ ሰዎች አብዛኞቹ የኢህአዴግ ደጋፊዎች (በፌስቡክ በሚፅፉት መሰረት) ናቸው። ለምን በነ እስክንድር ነጋ ዙርያ አስተያየት እንድሰጥ ገፋፉኝ? እኔን “ማኖ ለማስነካት” ታስቦ ነው። እኔን “ማኖ ማስነካት” እንዴት ይቻላል? ከሰዎች ጋር በማጣላት ነው። እንዴት ማጣላት ይቻላል?
eskendernega-240
የህወሓት መሪዎች ከትግራይ ህዝብ የፖለቲካ ድጋፍ ለማግኘት የሚጠቀሙት ዋነኛ መንገድ “ሌሎች ተቃዋሚዎች ፀረ ትግራይ ናቸው፤ ዓላማቸው ትግራይን ማጥፋት ነው።” … ወዘተ የሚል የውሸትና የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ሲሆን በብሄር በተከፋፈሉ ህዝቦች አንድነት እንዳይኖርና አብረው ፀረ ገዢው ፓርቲ እንዳያምፁ ለማዳከም ሲባል እርስበርሳቸው እንዳይተማመኑና እንዲጋጩ ለማድረግ ያለመ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የህወሓት መሪዎች እስክንድር ነጋ የተባለ ጋዜጠኛ የታሰረበት ምክንያት “ፀረ ትግራይ በመሆኑና የትግራይ ህዝብ መጨፍጨፍ አለበት” ብሎ ስለፃፈ መሆኑ ያብራራሉ (የፍርድቤት ክሱ ሌላ ሊሆን ይችላል)። የዚህ ፕሮፓጋንዳ ዓላማ “ፀረ ትግራይ የሆኑ ሰዎች እያሰርን ነን፤ ስለዚህ የትግራይ ድጋፍ ያስፈልገናል” ለማለት ነው። የጥላቻ ፖለቲካ የስልጣን ዘመን ማራዘምያ ሲጠቀሙ እንዲህ ነው።

የህወሓት ደጋፊዎች እኔን በጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጥና ‘ማኖ እንድነካ’ የሚፈልጉበት ዋና ጉዳይ የዚህ የጥላቻ ፖለቲካ ስትራተጂያቸው አንድ አካል መሆኑ ነው። ጉዳዩ እንዲህ ነው። ያላቸው የስልጣን መዋቅርና የመንግስት (የግብር ከፋዮች) ሃብት ተጠቅመው (ያለ ተከራካሪ) እስክንድር ነጋ የትግራይ ህዝብ “መጨፍጨፍ” እንዳለበት መፃፉ ደጋግመው ወደ ህዝብ እንዲደርስ አድርገዋል (ወሬው እውነት ይሁን ዉሸት ሳይጣራ ማለት ነው)።

እኔ ታድያ (አሁን አሁን) ደህና ቁጥር ያላቸው (ከትግራይም ከትግራይ ዉጭም) ጓደኞች እንዳሉኝ የህወሓት ካድሬዎች ለመገንዘብ ችለዋል። እና … ስለነ እስክንድር ነጋ መታሰርና የታሰሩበት ምክንያት አስመልክቼ አስተያየት ከሰጠሁ በህፀፅ መሰረት ማኖ መንካቴ አይቀርም። ምክንያቱም የነ እስክንድር መታሰር ከተቃወምኩ ህወሓቶች “አብርሃ ከጠላቶቻችን ጋር አብረዋል፤ የትግራይ ህዝብ ለመጨፍጨፍ የተነሱ ሃይሎች ደግፈዋል” ብለው በመቀስቀስ የትግራይ “ደጋፊዎች” እንዲርቁኝ ማድረግ ይችላሉ። መታሰራቸው ከደገፍኩኝ ደግሞ ከትግራይ ዉጭ ያሉ ጓደኞቼ (የእስክንድር ነጋ ደጋፊዎች) እንዲርቁኝ ለማድረግ ነው። የቅርብ ጓደኞቼ አስተያየት ከመስጠት እንዲቆጠብ የመከሩኝም ለዚህ (አጣብቂኝ ዉስጥ እንዳልገባ) ይመስለኛል።

ከተቃዋሚዎችም በጉዳዩ የኔን አስተያየት የሚፈልጉ አሉ። በሁለት ምክንያቶች፤ (1) የኔን ቁርጥ አቋም ማወቅ የሚፈልጉ (የምር ተቃዋሚ ነው ወይስ አውቆ ነው? ታድያ ለምን እስካሁን አልታሰረም? በሚል ግራ የተጋቡ)። (2) በቅንነት እኔ ከነ እስክንድር ነጋ ጎን እንድሰለፍ (እንድ ደግፍ) የሚፈልጉ።

ለማንኛውም አስተያየቴን ለመስጠት የገፋፋኝ ነገር በፌስቡክ የተላከልኝን መልእክት እንዳልሆነ ልንገራቹ። በጉዳዩ ለመፃፍ ያስገደደኝ ነገር የህወሓት ካድሬዎች (ወይ ደጋፊዎች) እስክንድር ነጋን በተመለከተ እየበተኑት ያለ ፕሮፓጋንዳ ነው።

ስለ እስክንድር ነጋ ብዙ መረጃ የለኝም። እስንክድርን ያወኩት (በስም) ከታሰረ በኋላ ነው። በምን ጉዳይ እንደታሰረም (በሽብር ተጠርጥሮ ከሚል ዉጭ) ግልፅ አልሆነልኝም። አንዳንድ የህወሓት ደጋፊ ፌስቡከኞች (ና የደህንነት ሰዎች) ግን እስክንድር ነጋ (ላይ እንዳስቀመጥኩት) ስለ ትግራይ ህዝብ “ጨፍጫፍ” ፅፈዋል። ሌሎች የተከሰሰባቸው ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። እኔ ግን በዚህ ጉዳይ አተኩራለሁ። ምክንያቱም አስተያየት ለመስጠት ያስገደደኝ ጉዳይ ይህ ነውና።

እርግጥ ነው፣ በፍርድቤት ዉሳኔ ጣልቃ አልገባም። የኔ ጥያቄ “ይህ (ዉሳኔ የሰጠ) ፍርድቤት ገለልተኛና ነፃ ነው?” የሚል ነው። የህወሓት ካድሬዎች እንደሚነግሩን እስክንድር ነጋ የትግራይ ህዝብ “መጨፍጨፍ” እንዳለበት ፅፈዋል? ወይስ ስሙ እየጠፋ ነው? (በዚህ ጉዳይ አስተያየቶች እቀበላለሁ)።

እንደኔ ከሆነ ግን እስክንድር ነጋ “የትግራይ ህዝብ መጨፍጨፍ አለበት” ብሎ ይፅፋል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም:

አንድ

እስክንድር ነጋ የብዙ ሰው ትኩረት የሳበ ነው፤ አርቆ አሳቢ መሆን አለበት። እስክንድር ነፃነት ብሄርና ሃይማኖት እንደማይለይ የፃፈበት ሁኔታ እንዳለ ያነበብኩ ይመስለኛል። አንድ ታዋቂ ጋዜጠኛ ፀረ ህዝብ አስተያየት ይስጣል ብዬ አላምንም (የግል አስተያየት ነው፣ ምክንያቱም ሰው ፀረ ህዝብ አስተያየት ሊሰጥ ይችላል ወይ የተባለው ሁሉ ዉሸት ሊሆን ይችላል)።

ምናልባት ግን እስክንድር ፀረ ህወሓት የሆነ አስተያየት ሰጥቶ ሊሆን ይችላል። እስክንድር ህወሓት/ኢህኣዴግን የመቃወም ሙሉ መብት አለው። ለህወሓት ተቃወመ ማለት ግን የትግራይን ህዝብ ተቃወመ ማለት አይደለም። ህወሓቶች ከትግራይ ህዝብ ጋር መቀላቀል ያምራቸዋል። የሚሰሩት ስሕተት ወይ የሚፈፅሙት ግፍ ሁሉ በትግራይ ህዝብ ስም እንዲመዘገብላቸው ይፈልጋሉ። ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ እንደሆኑ አስመስለው መናገር ስለሚቀናቸው እስክንድር ፀረ ህወሓት ሲሆንባቸው ፀረ ትግራይ ኣድረገው እያቀረቡት እንዳይሆን? እኔ ራሴ ህወሓት ስቃወም የትግራይ ህዝብ የተቃወምኩ አስመስለው ያቀርቡት የለ?!!!

ሁለት

ማረጋገጫ ባይኖረንም እስክንድር (ህወሓቶች እንደሚሉት) ፀረ ትግራይ የሆነ አስተያየት ፅፈዋል እንበል (“እንበል” የሚል ቃል ይሰመርበት)።
(አንደኛ) ይሄ የኣንድ ግለሰብ አስተያየት ነው። አንድ ሰው የማሰብና የመፃፍ መብት ይሰጠው። የሰጠው አስተያየት ስሕተት ከሆነ ስሕተት መሆኑ ማሳየት ወይ ማሳመን በቂ ነው። ስሕተት ስሕተት ስለመሆኑ እርግጠኛ እያለን (ና ስሕተት መሆኑ ማሳመን እየቻልን) የሃይል እርምጃ መውሰድ ምን አስገለገ?

(ሁለተኛ) የኣንድ ሰው መብት መገደብ ያለበት የሌሎችን ሰለማዊ ሰዎች መብት በኣሉታዊ መልኩ መጋፋት ሲጀምር ነው። እኔ እስካለኝ መረጃ ድረስ እስክንድር ነጋ ሰለማዊ ሰው ነው (በሰለማዊ መንገድ የሚታገል እንጂ ጠመንጃ ይዞ ህዝብን ለመጨፍጨፍ የተነሳ ታጣቂ አይመስለኝም)። ሰለማዊ ግለሰብ እስከሆነ ድረስ በሌሎች ዜጎች ጉዳት የማድረስ ዕድሉ አነስተኛ ነው። (መጉዳት ከጀመረ ግን ያኔ ሕግ ጣልቃ ይገባል)። ፀረ ህዝብ የሆነ አስተያየት የተሰጠው በመንግስት ባለስልጣን ቢሆን ኑሮ አስተያየቱን የሰጠ ሰው ክፉኛ እንቃወመው ነበር። ምክንያቱም የመንግስት ባለስልጣን ከሆነ (ስልጣኑና ዓቅሙ ስላለው) ሊተገብረው ይችላል (በተጨማሪም የመንግስት ተጠሪ ፀረ ህዝብ አስተያየት ከሰጠ ስልጣኑ በኣግባቡ እየተወጣ እንዳልሆነ ማሳየት እንችላለን)።

(ሦስተኛ) “የእስክንድር ነጋ አስተያየት የኣንድ ግለሰብ አስተያየት ብቻ አይደለም” ካልን (ፀረ ህዝብ አስተያየት ያላቸው ብዙ ናቸው ካልን) እስክንድር ነጋን ማሳሰር መፍትሔ ይሆናል ወይ? ህዝብን የመጨፍጨፍ ሓሳብ በብዙ ሰዎች ጭንቅላት ከተመላለሰ አንድ ሰው (ወይ ብዙ ሰዎች) ወህኒ ቤት መወርወር ችግሩ ያባብሰዋል እንጂ አያቅለውም። ምክንያቱም አንድ ሰው ሲታሰር የተናገረውን ወይ የፃፈውን ሓሳብ አድማጭ ወይ አንባቢ እንዲሁም ተከታይ ያገኛል። ጉዳዩ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመራ ያደርጋል።

በፖለቲካ ሂደት “ሌላ ግዜ ልታጠቃን ስለምትችል አሁን ቀድመን እናጥቃህ” የሚል የሰፈር ዱርዬዎች ስትራተጂ አይሰራም። ኢህኣዴግ እንደ መንግስት እንዲህ ዓይነት አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች ችግራቸው (ሁኔታቸው) በማጥናት መፍትሔ ማፈላለግ እንጂ እንደ ግለሰብ ችግርን በችግር የመመለስ ተግባሩ ቢያቆም ጥሩ ነው።

ስለዚህ እስክንድር ነጋ ከተሳሳተ መሳሳቱን (በሓሳብ) ማረጋገጥ እንጂ ማሳሰር መፍትሔ ሊሆን አይችልም። አንድ ሰው ጥሩ ወይ መጥፎ አስተያየት ሊሰጥ ይችላል። ጥሩውን መጋራት (መደገፍ)፣ መጥፎውንም መንቀፍ ወይ መተቸት (መቃወም) እንጂ የሃይል እርምጃ መውሰድ “ስሕተት” የተባለውን አስተያየት ትክክል ስለ መሆኑ እየመሰከርን ያለን ያስመስልብናል። አንድን ሓሳብ ባለቤቱን (የሓሳቡ) በማሳሰር ስሕተት ማድረግ አይቻለም።

ስለዚህ ህወሓቶች ስለ ትግራይ ህዝብ የሚሰጡ አስተያየቶች (እስክንድር ነጋ ተናገረው የሚባለው ጨምሮ) ስሕተት መሆናቸው በሓሳብ ከማሳመን ይልቅ አስተያየት የሰጡትን ሰዎች ወደ ወህኒ መወርወር ለትግራይ ህዝብም ቢሆን አይጠቅምም።

It is so!!!

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on May 5, 2013
  • By:
  • Last Modified: May 5, 2013 @ 7:16 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar