www.maledatimes.com ፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አዲሱን ረቂቅ ሊፈትሽ ይገባል - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አዲሱን ረቂቅ ሊፈትሽ ይገባል

By   /   May 8, 2013  /   Comments Off on ፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አዲሱን ረቂቅ ሊፈትሽ ይገባል

    Print       Email
0 0
Read Time:10 Minute, 57 Second

/ሎሚ መጽሔት፤ ርእሰ አንቀጽ፤ ቅጽ 2 ቁጥር 52፤ ሚያዝያ 2005 ዓ.ም./

Lomi Magazine on MoFA Draft Directive01የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ ሕገ መንግሥት ‹‹መንግሥት በሃይማኖት፣ ሃይማኖት በመንግሥት ጣልቃ አይገባም›› ሲል በግልጽ መደንገጉ ይታወቃል፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት ግን ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ያፈነገጡ በርካታ ጉዳዮች ተስተውለዋል፡፡ የሩቅ ጊዜውን ክሥተት ትተን በቅርብ ከተፈጸመው የመንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ ገብነት መሀል አዲስ አበባ የግብረ ሰዶማውያን ስብሰባ ባስተናገደችበት ሰሞን የተስተዋለውን መጥቀስ ይበቃል፡፡

ታኅሣሥ 26 ቀን 2004 ዓ.ም. በአፍሪቃ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ግብረ ሰዶማውያን ስብሰባ ሊያደርጉ መኾኑን የሰሙት የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶች ስብሰባ በማድረግ ‹‹ጉባኤውን የሚያወግዝ›› መግለጫ ለመስጠት ጋዜጠኞችን በኖርዌይ ቤተ ክርስቲያን እንዲገኙ ይጠራሉ፡፡ መግለጫው ከመሰጠቱ ጥቂት ደቂቃዎች አስቀድሞ በስፍራው የተገኙት የያኔው የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የሃይማኖት አባቶችን ሰብስበው ካነጋገሩ በኋላ ግን ‹‹መግለጫው ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ›› ተብሎ የሃይማኖት አባቶችም፣ ጋዜጠኞችም በየፊናቸው ተበታተኑ፡፡ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደሚገባ ከዚህ በላይ አስረጂ አያስፈልግም፡፡

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በሃይማኖት ጉዳዮች የሚፈጠሩ ችግሮች አገራዊ ጉዳት እንዳያስከትሉ እንደሚሠራ ተገልጧል፡፡ ኾኖም ግንበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞችና በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ጉዳይ በተደጋጋሚ ጣልቃ ሲገባ ነው የሚስተዋለው፡፡

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ‹‹መንግሥት የእኛ ያልኾነውን የሃይማኖት የአሕባሽ አስተምህሮ በግድ ሊጭንብን እየሞከረ ነው›› በማለት ተቃውሞ ማሰማት ከጀመሩ አንድ ዓመት አልፏቸዋል፡፡ ችግሩ መፈጠሩ በተገለጸ ሰሞን የፈየዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ተቃውሞ ያሰሙት ወገኖች ተወካዮቻቸውን መርጠው ችግሩ በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈታ አሳሰበ፡፡ በዚሁ መሠረት የእስልምና እምነት ተከታዮች ወኪሎቻችን ናቸው ያሏቸውን 17 ሰዎች መርጠው አሳወቁ፡፡ ወኪሎች የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ዕውቅና ተሰጥቷቸው ችግራቸውን ሲያስረዱ ቆዩ፡፡ በመጨረሻ ግን የሃይማኖቱ ተከታዮች ከመረጧቸው ወኪሎች አብዛኞቹ በሽብርተኝነት ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል በሚል ሰበብ ታስረው፣ ዛሬም ድረስ የወህኒ በር ተዘግቶባቸው የፍርድ ሂደታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ ኾኖም ግን ሕዝበ ሙስሊሙ በየመስጂዱ የሚያሰማውን ተቃውሞ አሁንም ድረስ ገፍቶበታል፡፡ ታዛቢዎች ‹‹መንግሥት ከእልከኝነት መሥመር ወጥቶ ችግሮችን መፍታት ይኖርበታል›› የሚል አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ እኛም እንላለን፡- ‹‹አንድ ዓመት የዘለቀው ተቃውሞ በመንግሥት ወገን መላ ካልተሰጠው መፍትሔው ከወዴት ሊመጣ ይችላል?››

Lomi Magazine on MoFA Draft Directiveበቡሃ ላይ ቆረቆር እንዲሉ የሙስሊሞች ጥያቄ ምላሽ ባላገኘበት ኹኔታ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ከሰሞኑ ‹‹በዐዋጅ ቁጥር 691/2003 አንቀጽ 14/1/ሸ የተሰጠውን ሥልጣንና ተግባራት ለመወጣት›› በሚል ያዘጋጀው የመመሪያ ረቂቅ ዙሪያ የሃይማኖት ተቋማት መወያየት መጀመራቸው ከወዲሁ ተቃውሞን እየፈጠረ በመኾኑ ጉዳዩ በጥንቃቄና በማስተዋል እንዲመራ ማድረግ ይገባል፡፡

በመመሪያው ረቂቅ መግቢያ ላይ መመሪያውን ማዘጋጀት ያስፈለገበትን ምክንያት ሲገልጽ፡- ‹‹ለሃይማኖት ወይም እምነት ተቋማት በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠው የሃይማኖት ነጻነት፣ እኩልነትና የመደራጀት መብትን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ለማስቻልና ነጻነታቸው እንደተጠበቀ ኾኖ አሠራራቸው ከሕገ መንግሥቱና ከሌሎች የሃገሪቱ ሕጎች ጋራ በተጣጣመ ኹኔታ እንዲቀጥል ለማድረግ ነው፤›› ይላል፡፡

የሃይማኖት ወይም እምነት ተቋማት ጠባይ በመሠረቱ መንፈሳዊ፣ በየ‹‹መጽሐፋቸው›› የሚመሩ እና ከየ‹‹መጽሐፋቸው›› በሚመነጭ ሥርዐት የሚተዳደሩ መኾኑን በመግለጽ በቀረበው ረቂቅ ላይ ትችታቸውን ያቀረቡ ወገኖች ‹‹የእምነት ወይም ሃይማኖት ተቋማት አሠራራቸው ከሕገ መንግሥቱና ከሌሎች የአገሪቱ ሕጎች ጋራ በተጣጣመ ኹኔታ እንዲቀጥል ክትትልና ድጋፍ ማድረግ›› የሚለው በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ሲቪክ ተቋማት ላይ መንግሥት የሚያካሂደው ዐይነት ቁጥጥር እንዲሰፍን ለማመቻቸት መኾኑን ከወዲሁ እየገለጹ ነው፡፡ እንዲያውም ‹‹መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም›› የሚለውን በገሃድ ይጥሳል ባዮች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሕግ የተቋቋመችው በ1952 ዓ.ም በወጣው የፍት ብሔር ሕግ መኾኑን፣ የሕጉ አንቀጽ 3 ምዕራፍ 1 ቁጥር 398፡- ‹‹የኢትዮጶያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሕግ በኩል እንደ አንድ ሰው የምትቆጠር ናት›› ተብሎ መደንገጉን የገለጹ ወገኖችም ቤተ ክርስቲያኒቱ ደንቦችና መመሪያዎችን በማውጣት ራሷን ማደራጀትና መምራት እንደምትችል በሕግ መብት እንደተሰጣት፣ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ባልተሻረበት ኹኔታ ሌላ የመቆጣጠሪያ መመሪያ ማውጣቱ ተገቢ አለመኾኑን እየገለጹ ነው፡፡

ስለዚህም የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የተቀሰቀሰው ውዝግብ ሳይበርድ ሌላ ዙር አተካሮ እንዳይፈጠር የመመሪያውን ረቂቅ በጥንቃቄ ሊፈትሽ ይገባዋል እንላለን፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on May 8, 2013
  • By:
  • Last Modified: May 8, 2013 @ 7:44 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar