www.maledatimes.com የታሪክ ተወቃሽነቱን ከራሳችን እንጀምር ! በመንገሻ ሊበን - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የታሪክ ተወቃሽነቱን ከራሳችን እንጀምር ! በመንገሻ ሊበን

By   /   May 9, 2013  /   Comments Off on የታሪክ ተወቃሽነቱን ከራሳችን እንጀምር ! በመንገሻ ሊበን

    Print       Email
0 0
Read Time:38 Minute, 24 Second
                                                          ግልጽ መልእክት ለአገራችን የታሪክ ፀሃፊዎችና ፖለቲከኞች !
                                                                         የታሪክ ተወቃሽነቱን ከራሳችን እንጀምር !
                                                                                                 በመንገሻ ሊበን
እኛ ኢትዮጵያዊያን የአኩሪ ታሪክ ባለቤቶች እንደሆን ከልጅነት እድሜያችን ጀምሮ እየተነገረን ያደግን ህዝቦች ነን ። የሰው ልጅ መገኛ ፤የቅዱሳን አገር ፤የጀግኖች መፍለቂያ ምድር ፤ መቅደላ ፤አድዋ፤ ማይጨው ወ.ዘ.ተ የሚሉት ቃላት በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አእምሮ ውስጥ የሚያቃጭሉ የታሪክ ፀፊዎቻችን የብእር ትሩፋቶች ናቸው ። እጅግ የሚገርመው ግን ፣ የአፄ ቴድሮስ እጅና እግር ቆራጭነት ፤ የአፄ ዮሃንስ አንገት ቀንጣሽነት የአፄ ምኒልክ ጡት ዘልዛይነት እንደዚሁም የአፄ ኃይለስላሴ ፤ የኮሎኔል መንግስቱና የአቶ መለስ ዜናዊ አሰቃቂ ወንጀሎች የታሪካችን አንድ አካል መሆናቸው እየታወቀ በታሪክ ፀሃፊዎቻችን ዘንድ ግን ብዙም የሚዳሰሱ ነገሮች አለመሆናቸው ነው ።
እንደዚህ ፅሁፍ አቅራቢ እምነት ፣ መልካሙን ታሪካችን እንዴት አቅበን መጓዝ እንዳለብንና ከመጥፎ ታሪካችንም ምን ዓይነት ልምድ መቅሰም እንደሚገባን መማር የምንችለው ታሪክ ፀሃፊዎቻችን ትክክለኛውን ታሪካችንን ያለምንም መዛነፍና ወገንተኝነት በሃቀኛ ብእራቸው ሲከትቡልን ብቻ ነው ።መረረም ጣፈጠም የኛ ታሪክ የኛ የራሳችን ነውና ።
ለመንደርደሪያ ያህል ይህን ካልኩ በቀጣይነት ላነሳው ወደፈለኩት ርዕሰ ጉዳይ ላምራ።
አውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች እንደ ቅርጫ በተከፋፈሏት የጥቁሮች ምድር፣ በጀግኖች አባቶቻቸን ከፍተኛ መስዋእትነት ብቸኛዋ የነፃነት ቀንዴል የሆነችው እናት አገራችን ኢትዮጵያ፣ ካለፉት 50 እና 60 ዓመታት በተለይም ደግሞ ካለፉት 22 ዓመታት ወዲህ እያጋጠማት ያለው ህልውናዋን የሚፈታተን ኩነት የቱን ያህል ከባድና አሳሳቢ እንደሆነ ብዙዎቻችን የምንገነዘበው ነገር ይመስለኛል።
እንደ እኔ እምነት ለዚህ የአገርን ህልውና በቀጣይነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየጣለ ለሚገኘው የተወሳሰበ ችግር ተጠያቂዎቹ፣ ከ1983 በኋላ መንበረ ስልጣኑን የተቆጣጠረው የወያኔ ስርዓትና ከእርሱ በፊት የነበሩት ሁለት መንግስታት ብቻ ሳይሆኑ፣ የሃገራችን ታሪክ ፀሃፊዎች፤ ሙሉ እድሜያቸውን በተቃዋሚነት ጎራ ተሰልፈናል የሚሉ ሃይሎችና የኢትዮጵያን ችግር እንደ እጃችን መዳፍ ጠንቅቀን እናውቀዋልን እያሉ በየአደባባዩ የሚመፃደቁት ፖለቲከኞቻችን ጭምር ናቸው።
በእርግጥም እነዚሁ ሃይሎችና ተመፃዳቂ ግለሰቦች ፣ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ፣ ያልነበረን ታሪክ የነበረ አስመስሎ በማቅረብና ፣ “ታሪክ እንደፀሃፊው ነው” እንዲሉ ፣ ከሞላ ጎደል ሁሉንም ታሪካችንን (መጥፎም ይሁን ጥሩ ታሪክ ) ለፀሃፊው ወይም ለገዥው አካል በሚመች መንገድ በማቅረብ ፣ አንዳንዴም ኢምንቱን ፍፃሜ እጅግ በተጋነኑ የማንህሎኝነት ቃላት በመጀቦን ወይም ደግሞ ትውልድ ሊማርበት የሚገባውን አንኳር ፍፃሜ ምንም እንዳልተፈፀመ በማስመሰል፣ አላስፈላጊ የህይወትና የጊዜ መስዋእትነት እንድንከፍል ከማድረጋቸውም በላይ … በአገራችን ኢትዮጵያ ላይም አሳፋሪ ውድቅት እንዲከተልና ትውልድም ያለፈ ታሪኩን በሚገባ እንዳይገነዘብ የየራሳቸውን ድርሻ አበርክተዋል ብቻ ሳይሆን እስከ ዛሬም እያበረከቱ ይገኛሉ ።
ስለሆነም ታሪክን በማፋለስ ረገድ ፣ የታሪክ ተወቃሽነቱ መጀምር ያለበት፣ ይህንን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የተፈጸመ በደል ይፋ አውጥቶ በግልፅ በመወያየትና በመመካከር እንጅ፣ በተፋለሰ ታሪክ ላይ ተንተርሶ በጥፋት ላይ ጥፋት በመስራት አልያም ደግሞ የራስን ሌባ ጣት ወደ ሌላ በመቀሰርና ተጠያቂነቱን በሌሎች ላይ በመለደፍ መሆን የለበትም።
እንደሁሉም የአለም አገራት ፣ አገራችን ኢትዮጵያም በተለያዩ ፍፃሜዎች መጥፎና ደግ ኩነቶችን ያስተናገደች ምድር ናት ። ይህ ሁለት ተፃራሪ ኩነት በታሪክ መዝገብ ላይ በሚገባ ሊሰፍርና ትውልድም በጥልቀት ሊማርበት የሚገባው ነገር ይመስለኛል ። አስቀድሜ በፅሁፌ መግቢያ ላይ እንደጠቀስኩት ከመጥፎ ታሪካችን ምን ዓይነት ልምድ መቅሰም እንደሚገባንና መልካሙን ታሪካችን ደግሞ እንዴት አቅበን መጓዝ እንዳለብን መማር የምንችለው ታሪካችን ያለምንም መዛነፍና ወገንተኝነት በሃቀኛ ፀሃፊዎች ተከውኖ ሲቀርብልን ብቻ ነው። ከዚያ ውጭ ግን መነገር ያለበት ሃቀኛው ታሪካችን በግለሰቦችና የፖለቲካ ሃይሎች አስተሳሰብ ፤ ስሜትና ፍላጎት ላይ ብቻ ተመርኩዞ መፃፉን ከቀጠለ ፣ የታሪክ መፋለስ እንዳያስከትል በእጅጉ ሊያሰጋን የሚገባ ነገር ነው ።
ለመንደርደርያ ያህል አንድ አንኳር ነጥብ ላንሳ ። ይህ አንኳር ነጥብ ፣ ላለፉት 50 እና 60 ወይም ከዚያ በላይ ለሆኑ ዓመታት ፣ የህዝባችንና የፖለቲካ ሃይሎቻችንን ቀልብ በከፍተኛ ደረጃ ከሳቡት የአገራችን የፖለቲካ አጀንዳዎች መካከል አንዱ ነው። ይህ አንኳር ጉዳይ በአገራችን የታሪክ መዝገብ ላይ ያለምንም መዛነፍና ወገንተኝነት በሚገባ ሰፍሯልን…? ወይም ደግሞ ከእስካሁኑ ፍፃሜ በኋላስ ትውልድ ሊማርበት የሚገባው ሃቀኛ ታሪክ ያለወገንተኝነት እየተፃፈ ነውን…? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ይሰጥበት ዘንድ አንባቢን በአክብሮት እጋብዛለሁ ።
ሁሉም እንደሚያውቀው በአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻን ከሚይዙት አንኳር ጉዳዮች መካከል አንዱ የኤርትራ ጉዳይ ነው። ፖለቲከኞቻችንና ፀሃፊዎቻችን ይህንኑ አንኳር ጉዳይ አስመልክተው ከደርዘን በላይ የሆኑ መጣጥፎችን ለንባብ ማብቃታቸው የሚታወቅ ነገር ቢሆንም “ታሪክ እንደፀሃፊው ነው” የተሰኘው ብሂል ግን በመጣጥፎቻቸው ላይ መንፀባረቁ አልቀረም ። ለምሳሌ ያህል በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ፤ በደርግና በወያኔ ዘመነመንግስታት የኤርትራን ጉዳይ በሚመለከት በፖለቲከኞቻችንና ፀሃፊዎቻችን አማካኝነት ለንባብ የበቁ መጣጥፎችን ብንመለከት ፣ ትውልድ ሊማርበት የሚገባው ታሪካችን የቱን ያህል እየተፋለሰና ያለጥልቅ ጥናት በፀፊው ፍላጎትና ስሜት ላይ ብቻ ተንተርሶ እየተፃፈ እንደሆነ ለመገነዘብ የግድ ተመራማሪነትን አይጠይቅም ። ያም ሆነ ይህ ነገር ከማንዛዛትና አንባቢን ከማሰልቸት በቀጥታ በቀዳሚነት ላነሳው ወደፈለግኩት ርእሰ ጉዳይ እናምራ ። በዚህ ጉዳይ ላይ ሶስቱን መንግስታት ጨምሮ ፖለቲከኞቻችንና ፀሃፊዎቻችን ሲከተሉት የነበረውን አቋም በመጠቃቀስም፣ ከእውነተኛው የታሪክ ፍፃሜ አኳያ የየራሳችንን ድምዳሜ ለመስጠት እንሞክር።
እስካሁን ድረስ በግብታዊነት ስንከተላቸው ከቆዩት የታሪክ ፀፊዎቻችንና ፖለቲከኖቻችን መጣጥፍ አንፃር ከዚህ በታች የሰፈሩት እውነታዎች ለመቀበል የሚያዳግቱና እንደ እሬት የመረሩ መሆናቸው አሌ ባይባልም ፣ የኛ ታሪክ የኛ የራሳችን ነውና ለትውልድ ይበጅ ዘንድ ያለምንም መሸፋፈን መነገርና መፃፍ አለበት የሚል ፅኑ እምነት አለኝ ። ይህ የኔ ብቻ ሳይሆን የብዙዎቻችንም እምነት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ ።
በበርካታ የታሪክ ድርሳናት ላይ ከሰፈሩ መጣጥፎች መገንዘብ እንደሚቻለው ፣ የኤርትራ ጉዳይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እንደከፍተኛ አገራዊ አጀንዳ በተደራጀ መልኩ ተጋግሎ መስተጋባት የጀመረው በአጼ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ነው ። ከንጉስ ሃይለስላሴ በፊት የነበሩት የአገራችን ነገስታት (ንጉሰ ነገስታት ምኒልክን ሳይጨምር) ኢትዮጵያን አሁን በያዘችው የሉዓላዊነት ቅርፅ የማስተዳድር እድሉን ስላላገኙትና (የኢትዮጵያ ግዛት አንዴ ይጠብ ሌላ ጊዜ ደግሞ ይሰፋ እንደነበረ ልብ ይሏል) የግዛት ጠረፋቸውም በነበራቸው የሃይል ሚዛን ላይ የተመረኮዘ ስለነበረ፣ በማስገበርም ይሁን በሌላ ምክንያት (ለምሳሌ አፄ ዮሃንስ መጥቀስ ይቻላል ) አልፎ አልፎ ወደ ደጋማው የኤርትራ ግዛት ከመዝለቅ ባሻገር ኤርትራን እንደ ክፍለአገር ወይም እንደ ጠቅላይ ግዛት አሁን በያዘችው ቅርጽና ይዞታ የኔ ናት ብሎ የተነሳ አንድም የኢትዮጵያ ንጉስ በታሪክ አልተመዘገበም። ይህ ማለት ግን የባህር በር ጥያቄ አይነሳም ነበር ማለት አይደለም። የባህር በር ጥያቄው ግን አሰብና ምጽዋን ብቻ ሳይሆን ጁቡቲንና ሶማሊያንም ያካትት እንደነበር መዘንጋት ታሪክን ማፋለስ ነው ።
የግዛት ጅማሮውን አሰብና አካባቢዋን በማድረግና ወደተቀረው የኤርትራ ግዛት በፍጥነት በመዛመት ለ60 አመታት ያህል የቅኝ ግዛት ቀንበሩን በኤርትራ ህዝብ ላይ የጫነው የጣሊያው ፋሽስት ስርዓት፣ የመስፋፋት ህልሙን እውን ለማድረግ በኢትዮጵያም ላይ ተደጋጋሚ ትንኮሳዎችንና የወረራ ሙከራዎችን ማድረጉ ይታወቃል ። ነገር ግን በተለያዩ የማደናገርያ ስልቶችም ሆነ በሃይል የኢትዮጵያን ህዝብ እንደሌሎች የአፍሪካ ህዝቦች አንበርክኮና ረግጦ መግዛት እንደማይቻል ፣ በጀግኖች አያቶቻችን ብልህነት ፤ አርቆ አስተዋይነትና ከፍተኛ መስዋእትነት በታሪካዊው የአድዋ ጦርነት ላይ ሲረጋገጥ ፣ ወራሪው የባእድ ሃይል ያለውድ በግዱ ኢትዮጵያን እንደ ሉዓአላዊት አገር ተቀብሎ ከአፄ ምኒልክ ጋር የተለያዩ ስምምነቶችን ለማድረግ ተገደደ ።
ከነዚህ ስምምነቶች መካከል ተጠቃሾቹ የጣልያን ቀኝ ግዛትንና (ኤርትራን) የኢትዮጵያን ድንበር በተመለከተ በ1900 ፤ በ1902 እና በ1908 (እ.ኤ.አ) በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈረሙ የስምምነት ሰነዶች ናቸው ። በነዚህ የስምምነት ሰነዶች መሰረት ፋሽስት ጣሊያን የኢትዮጵያን ዳርድንበር በምንም አይነት መልኩ ላለመጣስና የአገሪቱንም ሉዓላዊነት ለመቀበል ስትገደድ፣ ኢትዮጵያ በፊናዋ ከጣልያን ጋር በምንም አይነት መንገድ በጠብ ላለመፈላለግ የውል ቃል ኪዳን አስራለች ።
በአድዋው ጦርነት የጣሊያውን ፋሽስት አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ወራሪ ሰራዊቱን ከአገራችን ሉዓላዊ ግዛቶች ጠራርጎ ያባረረው የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መንግስት፣ በጀግኖች አያቶቻችን የማያዳግም ምት ተደናግጦ የተበታተነውንና የመዋጋትና የመከላከል አቅሙ ከዜሮ በታች የወረደውን የፋሽስት ሰራዊት እስከ አስመራ ድረስ ዘልቆ ከምንጩ የማድረቅ…ብቃትና ሞራል ቢኖረውም ፣ ያልነበረን ታሪክ እንደገና መፍጠርና የክብር ስሙን በወራሪነት መዝገብ ላይ ማስፈር አልፈለገም ። እንዲያውም ንጉሰ ነገስታት ምኒልክ አሸናፊ ሰራዊታቸው ድንበሩን ተሻግሮ እንዳይገሰግስ መመርያ ሲያስተላልፉ “ የአገሩ ዛፍ የለው ፤ የወንዱ ባት የለው ፤ የሴቱ ጡት የለው። ከዚህ በኋላ አገሬ አይደለምና ፣ ተመለስ !! ” በማለት እንደተናገሩ እስካሁን ድረስ በእድሜ ጠገብ አያቶቻችንና አባቶቻችን የሚነገርና የሚተረክ እውነታ ነው ። ይህ ታሪካዊ ፍፃሜ የጀግኖች አያቶቻችንን ህግ አክባሪነት የሌሎችን ግዛት ያለመመኘት ጨዋነት በተጨባጭ ያሳየ ተግባር ነው። ከታሪካዊው የአድዋ ጦርነት በኋላ የተፈረሙት ሶስቱ ታሪካዊ ስምምነቶች ደግሞ የኢትዮጵያዊያኑን የአልገዛም ባይነትና የአገርን ዳርድንበር አሳልፎ ያለመስጠት አኩሪ ታሪክ ያስመሰከረ አንኳር ፍፃሜ ነው ።
ነገር ግን ስለኤርትራ ጉዳይ ቀን ከሌት የሚሰብኩን የዘመናችን ፖለቲከኞች ይህንን እውነታ በትክክለኛ ታሪክነቱ ሲያስነብቡን አልታዩም ። እንዲያውን ይባስ ብለው በወቅቱ የነበሩ ሁኔታዎችን ሸፋፍነው በማለፍና የኢትዮጵያውን ንጉሰነገስት መንግስት ህግ አክባሪነት በማጣጣል ለጀግኖች አርበኞቻችን መረብን ተሻግሮ አለመሄድ የተለያዩ ምክንያቶችን ከመፍጠር ባለፈ የወቃሽነት ጣታቸውን በአፄ ምኒልክ ላይ ሲቀስሩ ይስተዋላሉ ። የታሪክ መዝጋቢዎች ወይም ነጋሪዎች ስራ እውነተኛውን ታሪክ በተገቢው መንገድ በመዝገብ ላይ ማስፈር ሆኖ እያለ ፣ የኛዎቹ ጸሃፊዎችና ፖለቲከኞች ግን፣ ባልነበሩበትና ባልተካፈሉበት ታሪክ ውስጥ ሆነው የታሪክ ፈጻሚዎችን ስራ በማጣመምና የየራሳቸውን ትርጉም በመስጠት ፣ የምኒልክን ወደ ኤርትራ ግዛት ዘልቆ አለመግባት፣ አንዴ ከሰራዊታቸው በረሃብና በውሃ ጥም መድከም ጋር፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከመሃል አገር የሰራዊት ሃይል መሳሳት ጋር እያዛመዱ በመግለፅ ፣ እስካሁን ድረስ መፍትሄ ላልተገኘለት ውስብስብ ችግራችንና የህይወት፤ የንብረትና የግዜ ኪሳራችን የበኩላቸውን አሉታዊ አስተዋፅዖ አበርክተዋል ። ።
እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት ሌላም ታሪክ አለ ። እርሱም፣- በታሪክ ፀሃፊዎቻችን ዘንድ ብዙም የማይወሳውና አፄ ምኒልክ በአድዋው ጦርነት ወቅት በተማረኩት የኤርትራ ተወላጅ የጣልያን ወታደሮች ላይ የፈፀሙት እጅግ አሰቃቂ በደል ነው ። አፄ ምኒልክ ድል የነሷቸውን የጣልያን ምርኮኞች ሰብአዊነት በተመላበት ሁኔታ ተንከባክብው በክብር እንደሸኟቸው በታሪክ ፀሃፊዎቻችን መጣጥፎች ላይ ተደጋግሞ የተነገረን ነገር ቢሆንም … በጦርነቱ ላይ የማረኳቸውን የኤርትራ ተወላጆች ግን እንዴት እጆቻችውን እየቆረጡና በአንገታቸው ላይ እንደሚዳሊያ እያንጠለጠሉ ወደ አገራቸው ኤርትራ እንደሸኟቸው በታሪክ ጸሃፊዎቻችን ብእር ብዙም የተነገረለትና የተወሳለት ጉዳይ አይደለም ። ለምን…?
እርግጥ ነው ይህ እውነታ ለብዙ አመታት ስንጋተው ከቆየነው የተፋለሰ ታሪክ አንፃር ለብዙዎቻችን የማይዋጥና እንደ ኮሶ የመረረም ሊሆን ይችላል ። ነገር ግን ጣፈጠም መረረም የኛ ታሪክ የኛ ነውና ሁሉም ይማርበት ዘንድ በሚገባ መፃፍ አለበት ። ያም ሆነ ይህ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ጊዜ ከማባከን አሁንም ወደ ዋናው ነጥቤ ልመለስ ።
ቅድም እንዳልኩት ካለፉት 50 ወይም 60 ወይም ደግሞ ከዚያ በላይ ከሆኑ ዓመታት ጀምሮ እስከአሁን ድረስ የመላው ህዝባችንን ቀልብ በመሳብና በአገራችን የፖለቲካ አጀንዳ ውስጥም ጉልህ ድርሻ በመያዝ የሚታወቀው ርእሰ ጉዳይ ኤርትራን የሚመለከተው ክፍል ነው ።
ፋሽስቱ የጣልያን መንግስት በአድዋው ጦርነት ድል ተነስቶና በነጮች አለም አሳፋሪ የውርደት ሸማን ተከናንቦ ከድል ነሽዋ ኢትዮጵያ ጋር ሶስት የተለያዩ ስምምነቶችን ከተፈራረመ በኋላም ቢሆን የተስፋፊነት አባዜውን እርግፍ አድርጎ ለመተው አልፈለገም ። እንዲያውም ይባስ ብሎ በአድዋው ጦርነት የደረሰበትን አሳፋሪ ውርደት ለማካካስ ለረጅም አመታት የዘለቀ ሁለንተናዊ ዝግጅት ሲያደርግ ነበር የቆየው ። በዚህ የረጅም አመታት ዝግጅቱ ነው እንግዲያውስ ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ መጠነሰፊ የሆነና በከፊልም ቢሆን ስኬታማ የሆነበትን ወረራ ያካሄደው ። (በዚህ ርእሰ ጉዳይ ዙርያ ብዙ ስለተባለና ስለተነገረ…ወደ ዝርዝሩ ገብቼ በመፃፍ የአንባቢዎችን ጊዜ ማባከን አስፈላጊ አይመስለኝም።)
ያም ሆነ ይህ በዚህ ጉዳይ ላይ መጠቀስ ያለበትና በታሪክ ፀሃፊዎቻችንና ፖለቲከኞቻችን አንደበት ብዙውን ጊዜ በግልፅ የማይነገረን አንድ ነጥብ አለ ። ይሄውም የጣልያን የአምስት አመታት የቅኝ ግዛት ዘመን በማንና በምን መልኩ እንደተቋጨ ተድበስብሶ የሚፃፈው ታሪካችን ነው ። እርግጥ ነው ጀግኖች አያቶቻችንና አባቶቻችን በፋሽስቱ ጣልያን የተደፈረውን የአገራቸንን ክብር ወደ ነበረበት ለመመለስ ለአምስት አመታት ያህል ያደረጉት አኩሪ ተጋድሎ ሁሌም ሊዘከር የሚገባው ነው። ነገር ግን በፋሽት ጣልያን የተደፈረው የኢትዮጵያ ክብር ዳግም ወደ ነበረበት የተመለሰው ያለማንም እርዳታና ድጋፍ በጀግኖች አባቶቻችን ቆራጥ ተጋድሎ ብቻ ነው ብሎ መፃፍ ታሪክን ማፋለስ ነው ።
የእንግሊዝን ወረራ ለመመከት በመቅደላ አፋፍ ላይ ህይወታቸውን እንደሰዉት አጼ ቴድሮስ (በእርግጥ አፄ ቴድሮስ በራሳቸው ሽጉጥ ወይስ በጠላት ጥይት ተገደሉ የሚለው ታሪክ አወዛጋቢ ቢሆንም) ፣ ስለ ኢትዮጵያ ክብር እስትንፋሳቸውን ይሰጣሉ ተብለው ሲጠበቁ ጭራቸውን ቆልፈው በመፈርጠጥ ለንደን ላይ የታዩት የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ አሳፋሪ ታሪክና ፣ የጣልያንን ፋሽስት ጦር ከኢትዮጵያ ምድር ጠራርጎ ያወጣው የእንግሊዝ ሰራዊት ከፍተኛ ሚናም የታሪካችን አንዱ አካል በመሆኑ ፣ እንደ እሬት ቢመረንም የግድ መፃፍ አለበት። (ስለአዲስ አበባዎቹ የጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ፤ የዊንስተን ቸርችልና የኮለኔል በርኒንግሃም መንገዶች ፣ የስም አወጣጥ መነሻ ታሪክ የሚያውቀው ኢትዮጵያዊ ወጣት ስንት ነው…..? )
ከፍጻሜ ማህደሮቻችን ውስጥ ምርጥ ምርጡን ብቻ እየለቃቀሙ በታሪክ ድርሳናት ውስጥ ማስፈር ፣ ትዝብት ብቻ ሳይሆን ትውልድንም ማሳሳት ነው ። የታሪክ ድርሳን ማለት አኩሪ ፍፃሜ ብቻ የታጨቀበት መዝገብ አይደለም። ጣፋጭና መራራውም በአንድ ላይ ተቀይጦ የሰፈረበት የእውነተኛ ፍፃሜዎች ሰነድ እንጅ ። ስለዚህ ለትውልድ ይበጅ ዘንድ ያላንዳች መሸፋፈን ሁሉም መፃፍ አለበት።
ወደ መነሻ ነጥቤ ልመለስ………
በሁለተኛው የአለም ጦርነት በአክሲስ ሃይሎች ላይ የደረሰውን ሽንፈት ተከትሎ ፣የጣሊያው ፋሽስት ጦር እንደ ሊቢያና ሶማሊያ ግዛቶቹ ሁሉ ለአምስት አመታት ከገዛት ኢትዮጵያና ለ 60 አመታት ከአስተዳደራት ኤርትራ ጠቅልሎ ለመውጣት ሲገደድ ፣ ኢትዮጵያ ከስደት በተመለሱት ንጉስ ገዥነት በነፃነት ፣ ኤርትራ ደግሞ ጣልያንን አሸንፈው በመጡት እንግሊዞች ስር በሞግዚትነት መመራት ጀመሩ ። ከዚህን ጊዜ በኋላ ነው እንግዲህ የኤርትራ ጉዳይ በአገራችን የፖለቲካ አጀንዳ ውስጥ በተደራጀ መልኩ በከፍተኛ ደረጃ መራገብ የጀመረው ። ይህ ጉዳይ ከአገራችን ባሻገር አለማቀፋዊ ደረጃ እንዲይዝና ይበልጥ እንዲቀጣጠል ካደረጉት መካከል ደግሞ አፄ ኃይለስላሴና በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው የነበሩት አቶ አክሊሉ ሃብተወልድ በቀዳሚነት ቢጠቀሱም፣ ኤርትራን በሞግዚትነት ስም የተረከበው አዲሱ የእንግሊዝ አስተዳደርም ቢሆን ከራሱ የፖለቲካ ጥቅም አንፃር ጉዳዩን ይበልጥ በማቀጣጠልና አለማቀፋዊ ትኩረት በማሰጠት ረገድ የተጫወተው ሚናም በቀላሉ የሚገመት አይደለም ።ይህም የታሪካችን አንዱ አካል ነውና….ያለምንም መሸፋፈን አሁንም መፃፍ አለበት ።
                                                                                                                                                              &n bsp;                    ይቀጥላል…….
                                                                                                                                                              &n bsp;                       መንገሻ ሊበን
ማንኛውንም አስተያየት ለመቀበል የፀሃፊው የኢሜል አድራሻ ሁሌም ክፍት ነው ። mengeshalibenn@yahoo.com

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on May 9, 2013
  • By:
  • Last Modified: May 9, 2013 @ 12:17 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar