www.maledatimes.com የሙስናው አስር ምስጢር! (ማረ በላዎቹ ርስ-በርስ ተበላሉ!) በሰሎሞን ተሰማ ጂ. - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የሙስናው አስር ምስጢር! (ማረ በላዎቹ ርስ-በርስ ተበላሉ!) በሰሎሞን ተሰማ ጂ.

By   /   May 21, 2013  /   Comments Off on የሙስናው አስር ምስጢር! (ማረ በላዎቹ ርስ-በርስ ተበላሉ!) በሰሎሞን ተሰማ ጂ.

    Print       Email
0 0
Read Time:35 Minute, 4 Second

        Email: solomontessemag@gmail.com

 ለብዙዎች “ሙስና” የሚለው ቃል በ1989 ዓ.ም ወዲህ የተፈጠረ ሃይለ-ቃል ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን አይደለም፡፡ ቃሉ ግዕዝ ነው፡፡ ትርጉሙም፣“ጥፋት” ማለት ነው፡፡ በአማረኛም የኖረ ሕዝባዊ ግጥም/አባባል አለ፤ እንዲህ የሚል ነው፡፡     “የከንሯ ለዛ፣ የጉንጯ ሙስና፤
         “ዐርብ ሮብ ያስክዳል፣ እንኳን ዐሙስንና፡፡” ይላል –
አዝማሪም፡፡ በዚህ አገባብም መሠረት “ሙስና” የሚለው ቃል ትርጉም “ፈራሹ፣ ረጋፊው-መልኳ፣ ውበቷ እንዳጠፋ ገፋፋኝ” ለማለትና ለማሳበብ ነው የፈለገው (ደስታ ተክለ ወልድ፣ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፣ 1962 ዓ.ም፣ ገጽ-822)፡፡
በቅርቡ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሃላፊዎችን ሰብስበው በ2006 ዓ.ም የበጀት ዓመት፣ አንድ መቶ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ እንሰበስባለን” እያሉ ይዝቱ የነበሩት አቶ መላኩ ፈንታና አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ፣ በዚህ የብር ጮማና የንዋይ ብርንዶ ውስጥ ተቀምጠው የተጣለባቸውን ኃላፊነትና ታማኝነት ቢዘነጉት ምን ያስደንቃል? ኧረ! ጨርሶ በኢትዮጵያ ብር አንገበያይም ብለው፣ በአሜሪካን ዶላርና በእንግሊዝ ፓውንድ ወይም በስዊዝ ፍራንክ ብቻ እንጠቀም ቢሉ ምን ያስገርማል? (ጥፋቱን ሙሉ ለሙሉ እነርሱ ላይ ማላከኩ ተገቢም፤ ትክክልም አይደለም፡፡ እና የማነው? በወቅቱ የእርምት ርምጃ ያልወሰደባቸው አካል ነዋ!፡፡)
በርእሴ ላይ ንዑስ-ርእስ አድርጌ የተጠቀምኩበት ሌላው ነጥብ “ማረ በላዎች” የሚለው ሃረግ ነው፡፡ ሆን ብዬ ነው፡፡ “ሙሰኞች” የሚለውን ቃል ለመጠቀምም ሆነ ለማለት ቀፈፌሽን ስለያዘኝ ነው፡፡ የዘመኑ አላዋቂ ባለስልጣኖችና የእነርሱን ቃል እንደገደል ማሚቶ የሚደግሙት ሎሌዎቻቸው እንደፈለጋቸው ይበሉት እንጂ፣ “ሙሰኞች” የሚል የግዕዝም ሆነ የዐማረኛ አገባብ የለም፡፡ “ሙሰኞች” ማለት ራሱ “ሙሰኝነት” ነው፡፡ ስለሆነም፣ በአማረኛዬ እንዳልሞስን በማሰብ “ማረ በላዎች” የሚለውን የራሴን ሃረግ መርጫለሁ፡፡ ቃሉ፣ የደስታ ተክለ ወልድ መዝገበ ቃላት (በገጽ-804 ላይ) እንደሚፈታው ከሆነ የሚከተለውን ትርጉም አለው፤ “ማረ በላ” ማለት ይላሉ፣ “ጠጉራም፣ ጥፍራም፣ ነጭና ጥቁር፣ ዐጪር ቁመት ያለው አውሬ ነው፣ ማር የሚበላ አውሬ” ማለት ነው ሲሉም ይገልፁታል፡፡ “ቀይ ማር የሚበላ የቆላ ጉንዳንም” ማለት ነው ሲሉ ይገልጹታል፡፡ “ጉንዳን”ም ተባለ “ዐጪር ቁመት ያለው አውሬ” ለምንነጋገርበት ረእሰ-ጉዳይ ገላጭና ተስማሚ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ስለሆነም፣ ተጠቅሜበታለሁ፡፡ ያልደከሙበትን የሚወስዱና የሚዘርፉ ሁሉ፣ “ገፊ-ማረ በላዎች” ናቸው፡፡
ሙስናና ማረ በላነት በኢትዮጵያ የኖረ ተግባር ነው፡፡ ስሙን እየቀያየረ “ሙስና” የሚለው የዐማረኛ ቃል ከመሆኑ በፊት የተለያየ ስያሜ ነበረው፡፡ በነገሥታቱ ዘመን “እጅ-መንሻ” ወይም “መተያያ” እየተባለ ይታወቅ ነበር፡፡ በዘመነ ደርግ ደግሞ “ብዝበዛና ምዝበራ” የሚል ትርጉም ተሰጥቶት ሲንከባለል ከቆየ በኋላ፣ በ1975 ዓ.ም ገደማ “ጉቦ” የሚል ታርጋ ተለጥፎበት በ1976 ዓ.ም “የሠርቶ አደሩ ቁጥጥር ኮሚቴ” የሚባል የአሁኑ “የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን” የመንፈስ አባት በዐዋጅ ተቋቋመ፡፡ ወያኔ/ኢህአዲግ አዲስ አበባን እንደተቆጣጠረ ሰሞንም የዛሬው “ሙስና” ደርግ ያወጣለትን “ጉቦ” የሚል ስሙን እንደያዘ ነበር፡፡ በነሐሴ 2/1983 ዓ.ም አቶ አሰፋ ደስታ የተባሉት የከፍተኛ 13፣ ቀበሌ 10 “የሰላምና መረጋጋት ኮሚቴ ሊቀመንበር” አንዲት አደጋ ካደረሰች ተሸከርካሪ ሹፌር ላይ ሃምሳ (50.00) የኢትዮጵያ ብር “ጉቦ” የተቀበሉትን የቀበሌው ሰላምና መረጋጋት አባላት አሳፍሰው፣ አሳስረዋቸው እንደነበር አዲስ ዘመን ዘገባ ያወሳል (ገጽ-1)፡፡
የወያኔ/ኢህአዲግ ታጋዮችና ተጋዳላዮች በ1984 እና በ1985 ዓ.ም በየመንግሥት መሥሪያ ቤቱም እየሄዱ “የደርግ/ኢሠፓ አባላት” ናቸው ብለው የጠረጠሯቸውን ሰዎች ከሥራ ለማባረር ይጠቀሙበት የነበረው የስም ማጥፊያና ከሥራ ማስወገጃ አጀንዳቸው፣ “ያላግባብ የሕዝብ ሃብት የዘረፉ” የሚለው ነበር፡፡ (ያኔ፣ የሕዝብ ሀብት ዘረፉ ይባሉ የነበሩትና በወያኔ/ኢሕአዲግ አባላት ይባረሩ የነበሩት “ደርግ/ኢሠፓዎች ቢበዛ ሠላሳ ሺህ ብር ቪላ ቤት የሠሩ፣ ወይም ደግሞ ባለሦስት ክፍል ዛኒጋባ የቀለሱት “ሚስኪኖች” ነበሩ፡፡) ዛሬ ታሪኩ ተቀይሯል፡፡ ከባለአምስት ፎቅ ሕንፃ በታች ያለው ሹም ካለ “ፋራና ፈዛዛ” ብቻ ነው፡፡
በጥቅምት 14 ቀን 1989 ዓ.ም “አቶ ታምራት ላይኔ ከመከላከያ ሚኒስትርነቱና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነቱም ሲወገድ፣” የጠቅላይ ሚኒስትር መለሰ ዜናዊ ጽ/ቤት የሰጠው መግለጫ እንደሚለው ከሆነ፣ “አቶ ታምራት በምግባረ-ብልሹነት ተወወግዷል” ነው፡፡ “ጥይት ያላንበረከከውን ታጋይ፣ ስኳር አንበረከከውም!” ተብሎ ነበር (አዲስ ዘመን፣ ጥቅምት 15/1989 ዓ.ም፣ ገጽ-1)፡፡ ከወራት በኋላ፣ አቶ ታምራትና ወይዘሮ ሻዲያ ሀሰን ከነግብረ-አበሮቻቸው ተከሰው ፍርድ ቤት ሲቀርቡም፣ የተከሰሱበት ወንጀል “ያላግባብ ሃብት በማጋበስ” የሚል ነበር፡፡ በዚሁ ወንጀልም መሠረት፣ አቶ ታምራት ላይኔ በ14 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ወሰነበት ተባለ፡፡ (“ተባለ” የምለው ሆን ብዬ ነው፡፡) አቶ ታምራት እስሩን ሳይጨርስ በ2000 ዓ.ም (በቅንጅት ታሳሪዎች ግርግርና በነፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ ተለማማጭነት ተፈታ፡፡ በቅርቡ ደግሞ ሪፖርተር ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ፣ በስዊዝ ባንክ አስቀምጦት የነበረው ከ5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለኢትዮጵያ መንግሥት ተመልሷል፡፡
ከላይ እንደገለጽኩት፣ በታኅሣሥ ወር 1989 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ አቶ መለሰ ዜናዊና የገመናኛ ብዙኃኖቻቸው “ሙስና” የሚለውን ቃል ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀም ጀመሩ፡፡ “ሙስና” እና “የፀረ-ሙስና ኮሚሽን” የሚባሉት ቃላት ሕግ ተረቆላቸው፣ ጽሕፈት ቤት ከፍተው፣ “ኮሚሽነርም” የሚባል ሹም ታውቆላቸው መቀፍደድና ማስቀፍደድ ተከተለ፡፡ “ሙስና ሰበብ በቁጥጥር ስር” መዋል የተጀመረው በግንቦት 16/1993 ዓ.ም ነው፡፡ ለማቋቋም የሚያስችለው ውይይት በግንቦት 10/1993 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተካሂዶ፣ ሳምንት ሳይሞላው በግንቦት 16/1993 ዓ.ም ሕግ ሆኖ ፀደቀ፡፡ ወቅቱ በጥድፊያ የተሞላና “የሕወሀት/ወያኔ ስንጠቃ በመቐሌና በሂልት አዲስ አበባ በይፋ የታወቀበት ጊዜ ነበር፡፡ ወያኔ ለሁለት መከፈሉም አርግጥ ነበር፡፡ ይሄንን ሕግ ከሚያረቁትም ሰዎች መካከል የዛሬው የገቢዎችና ጉምሩክ አቃቤ ሕግ አቶ እሸቱ ወልደ ሰንበት ነበረበት፡፡ መቀሌና ባህር ዳር ላይ ምቹ ሆቴሎችን ይዘው “የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና” ሕጉን ማርቀቅ ጀመሩ፡፡(አቶ እሸቱ በ1999 ዓ.ም እንደነገረኝ ከሆነ፣ ሕጉ ባስቸኳይ የተረቀቀው በአቶ ወረደወልድ ወልዴ ትዕዛዝ ሲሆን፣ በአቶ መለሰ ዜናዊ ቀጭን መመሪያም እንደተከወነ ነግሮኛል፡፡ በዚህም መሠረት፣ ሕጉ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ተረቀቀና ወዲያው ጸደቀ፡፡ በግንቦት 19/1993 ዓ.ም የፍትሕ ሚኒስትሩና የፀረ-ሙስና ኮሚሽነሯ ወይዘሮ እንወይ ገብረ መድህን፣ “ሕዝቡ የሙስና ወንጀልን ያለፍርሃት እንዲያጋልጥ” ጥሪ ካቀረቡ በኋላ፣ “የፀረ-ሙስና ሕጉ በቂ ጥበቃ” የሚያደርግለትም መሆኑን መግለጽ ጀመሩ፡፡ ከሁለት ቀናትም በኋላ የሙስናው ቲያትር (ገቢር አንድ) መጋረጃው ተገልጦ መታየት ጀመረ፡፡
በዕለተ ዐርብ ግንቦት 21/1993 ዓ.ም፣ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን፣ “ከፍተኛ የሙስና ሴራ ውስጥ እንደሚገኙ በተጠረጠሩት ባለሥልጣነትና ነጋዴዎች ላይ ርምጃ ወሰድኩ” ሲል ለፈፈ፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ መምሪያም በበኩሉ፣ በሙስና ወንጀል ተጠርጣሪ የሆኑትን የመንግሥታዊ ተቋማት ኃላፊዎችና ነጋዴዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገለጸ፡፡ በዚህም መሠረት፣ አቶ ስየ አብርሃ (ባለስልጣን)፣ አቶ አሰፋ አብርሃ (ባለሥልጣን)፣ አቶ ምህረትአብ አብርሃ (ነጋዴ)፣ አቶ ፍስሃ አብርሃ-ነጋዴ(አራቱን ወንድማማቾች) እና አቶ ቢተው በለይን፣ አቶ ኃይሉ ለገሠን፣ አቶ ሙሉጌታ ገብረ መድህንን፣ አቶ በለጠ አለማየሁን፣ አቶ ብርሃነ ጂጆን፣ አቶ ሶፊያ ኢብራሂምን (እነዚህ ሁሉ በአንድ ወቅት ስንቱን የሚያንጰረጵሩ የወያኔ ሹማምንት ነበሩ) በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡
ከነጋዴዎቹም መካከል አቶ ምንውዬለት አጥናፉና አቶ አበባው ደስታ (የስታር ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤቶች)፣ አቶ ወርቁ መግራ፣ አቶ አበባው ገላዬ፣ አቶ አስናቀ ጀምበሬ፣ ወ/ሮ አጀብነሽ ሳምሶን፣ ወ/ሮ የሺሃረግ ዘውዴ፣ ሚ/ር ገራርድ ማይክል ሞላይን እና ሌሎችም ነበሩ፡፡ አርብ ማታ በዜና ማሰራጫዎች ተነግሮ፣ ቅዳሜና እሑድን ተራው ሕዝብ እንዲሰልቀው አደረጉት፡፡ ሰኞ፣ ግንቦት 24/1993 ዓ.ም ደግሞ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ ማክሰኞ ግንቦት 25/1993 ዓ.ም ደግሞ ኮሚሽነሯ ወ/ሮ እነወይ ገብረ መድህን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድረስ ሄደው “የፀረ-ሙስና ምንጠራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል” ተናገሩ (አዲስ ዘመን፣ ግንቦት 17፣ 18፣ 22፣ 25፣ አና 27 ቀን 1993 ዓ.ም፣ ገጽ-1 ላይ ማግኘት ይቻላል)፡፡ የአሁኑም ክስተት፣ ትዕይነተ-ቲያትር ወሙስና (ገቢር ሁለት) እንደማለት ይመስላል፡፡
በሰኔ 1/1993 ዓ.ም በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሰረተባቸው አቶ ስየ አብርሃ፣ በመሃል ዳኛዋ ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ ውሳኔ መሠረት በዋስ እንዲለቀቁ ተደረገ፡፡ በዚያው ዕለትም፣ የፌዴራል ፖሊስ የምርመራ ማስተባበሪያ ዋና ክፍል የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ጥሶ ተከሳሹን አቶ ስየ አብርሃን በድጋሚ አሠራቸው (አዲስ ዘመን፣ ሰኔ 2/1993 ዓ.ም፣ ገጽ-1 እና 5)፡፡ ይህንኑ የአቶ ስየ አብርሃንና የፌዴራል ፖሊስን ግብግብ ተከትሎ በተፈጠረው ውዝግብ የተነሳ፣ በወቅቱ የፍትሕ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ወረደወልድ ወልዴ ተከሰው በሁለት ዓመታት “የፈተና ጊዜ ገደብ” ፍርድ ተጣለባቸው፡፡ ጉዳዩ ከከፍተኛው ፍርድ ቤት አልፎም ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ ተወስዶ ነበር፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ከብቶ ነበር፡፡ በሰኔ 16/1993 ዓ.ም ኮሚሽነሯ ወ/ሮ እንይ በመገናኛ ብዙኃን ቀርበው (አይናቸውን በጨው አጥበው) እንዲህ አሉ፤ “መንግሥት ባለፉት ሰባት ዓመታት ውሰጥ ሙስናን መዋጋት ሁኔታዎችን ሲያመቻች መቆየቱን” ገልጸው ሲያበቁ፣ “በሙስና ወንጀል የተጠረጠረና የተያዘ ሰው፣ የዋስትና መብት የለውም፤” አሉ፡፡ “ምክንያቱም፣” አሉ ኮሚሽነሯ፣ “ምክንያቱም፣ ተጠርጣሪው የዋስትና መብቱ ከተከበረለት፣ ተጠርጣሪው ሊያመልጥ ስለሚችል ነው፤” ሲሉ አከሉበት፡፡
 አስከትለውም፣ “በሙስና የተከሰሰ ሰው የዋስትና መብት እዳይኖረው የሚከለክል ሕግ መረቀቁንና በቅርብም ሥራ ላይ ይውላል፤” ሲሉ ነበር ያለባበሱት (አዲስ ዘመን፣ ሰኔ 17/1993 ዓ.ም፣ ገጽ-1)፡፡
የአሁኖቹም ተጠርጣሪዎችና የታሰሩበት ዕለት፣ የፍርድ ቤት አቀራረባቸው፣ እንዲሁም ተከሳሾቹ እያሰሙት ያለው አቤቱታ በ1993 ዓ.ም አቶ ስየ አብርሃና ባለቤታቸው እንዲሁም ሦስት ወንሞቻቸው ያሰሙት ከነበረው እምብዛም ልዩነት የለውም፡፡ (ቀንቀሎ ስልቻ፤ ስልቻም ቀንቀሎ ነው፡፡) ይሄንን አባባል ይበልጥ የሚያጠናክረው የናዝሬት ጉምሩክ ኃላፊ የተባሉት የአቶ ተመስጌን ጉልላትን “በጋንቤላ በኩል ወደ ደቡብ/ሱዳን ሊሸሹ ሲሉ ተያዙ!” የሚለውን ዜና በሐምሌ 12/1993 ዓ.ም ከወጣው የአቶ ሳሚ ዩሱፍ አኳኋን ጋር ካስተያዩት ነው፡፡ በወቅቱ አቶ ሳሚ በርካታ ብርና ዶላር ይዘው በሶማሊያ በኩል አድርገው ጂቡቲ ከገቡ በኋላ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ ገልጾ ነበር፡፡ የአቶ ሳሚ ዩሱፍ ወንጀል እጅግ አስደንጋጭ ነበር፡፡ (ልክ የሌ/ኮሎኔል ሃይማኖት 61 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ሰነድ ይዛ ልታሸሽ ስትል ያዝናት እንደሚለው ዜና፣ የአቶ ሳሚም ወንጀል ለሰሚውም የሚቀፍ ነበር፡፡) አቶ ሳሚ ቤሳ-ቢስቲን ሳይኖረው/ሳያሲዝ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 22 ሚሊዮን ብር በሕገወጥ መንገድ ከተበደረ በኋላ፣ (ያን ጊዜ፣ “የስኳር ድጋፍ ሰጪ” ከሚባለው ተቋም) “156,000 ኩንታል ስኳር ያለጨረታ ገዝቶ አየር-ባየር ከሸጠ በኋላ ዕዳውንም ሳይመልስ በሶማሊያ በኩል ሊኮበልል ሲል ተያዘ፤” የሚል ነበር (አዲስ ዘመን፣ ሐምሌ 12/1993 ዓ.ም፣ ገጽ-1)፡፡ ዛሬም፣ አቶ ተመስገን የሚኮበልሉበት አቅጣጫ ተቀየረ እንጂ ኩብለላን ነው የመረጡት፡፡ ከሕግ ፊት ሸሽተው እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡
እና፣ አቶ ሳሚ ዩሱፍም ሆኑ አቶ ተመስጌን ጉልላት ከምንድነው የሸሹት? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ በቀጥታ ወደ መልሱ ከመግባቴ በፊት፣ በግንቦት 4/2005 የወጣው ሪፖርተር ጋዜጣን ሳነብ ያገኘሁትን መረጃ ላካፍላችሁ፡፡ እንዲህ ይላል፤ “እነዚህ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት ላለፉት ሦስት ዓመታት ክትትልና ምርመራ ሲደረግባቸው እንደነበረ የታወቀ ሲሆን፣ ከመያዛቸው ሁለት ቀናት በፊት በመቀሌ ከተማ ከሙስና ጋር በተያያዘ ጠንከር ያለ ውይይት መደረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህ ስብሰባም በኋላ ጥንቃቄ በተሞላበት እንቅስቃሴ” ማረ በላዎቹን በቁጥጥር ሥር ማዋል ተችሏል” -ይላል (ገጽ-37)፡፡ ትልቁ ቁምነገር ያለው የተሰመረበት ንዑስ ዐረፍተ ነገር ላይ ነው፡፡ በፌዴራል መንግሥቱ ዋና ከተማ የሚደረጉ ስብሰባዎችም ሆኑ ውይይቶች “ፍሬ-ከርስኪ” እንደሆኑና የመቀሌቹ ስብሰባዎችና ውይይቶች ግን “መሬት ጠብ የማይሉ” እንደሆኑ ያሳብቃል፡፡ በርግጥም ይህ ለምን ተደረገ ብሎ መመርመር ያስፈልጋል፡፡
የመቀሌዎቹ፣ በ1993 ዓ.ም በእነአቶ ስየ አብርሃም ላይ የእስር ትዕዛዙን የወሰኑት ከዚያው ከመቀሌ ነበር፡፡ አዲስ አበባ በወቅቱ ምቹ አልነበረችም፡፡ ከሚያዝያ 3-7/1993 ዓ.ም ድረስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አመጽና፣ አመጹንም ተከትሎ የነበረው ዝርፊያና ግድያ፤ እንዲሁም የደሕንነትና ኢምግሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ክንፈ ገብረ መድኅን በግንቦት 4/1993 ዓ.ም በመኮንኖች ክበብ መገደል (ወዘተርፈ) አዲስ አበባን የማትታመን ሥፍራ አድርጓት ነበር፡፡ ምርጦቹ ሕወሀቶች መቀሌ ላይ ተሰብስበው፣ “የአቦይ አብረሃ ልጆችና ግብረ-አበሮቻቸው ይታሰሩ!” ቢሉ አያስደንቅም ነበር፡፡ ምክንያቱም፣ ከአዲስ አበባ ይልቅ “መቐለይ” ለሕወሀት ምቹ የቁጥጥር ዞን ስለሆነች ነው፡፡ አዲስ አበባ ላይ ስንቱ የእህት ድርጅት አባል ስለላና ብሰሳ እንደሚያደርግባቸው ስለሚያውቁም ነው መቐለይን የመረጡት (በተለይ ብአዴን)፡፡ ታዲያ “አሁን፣ በ2005 ዓ.ም ሚያዝያ ማለቂያና በግንቦት ልደታ ዋዜማስ መቀሌ ላይ ተሰብስቦ መወሰንን ምን ይሉታል?” የምትሉ እንደማትጠፉ እርግጠኛ ነኝ፡፡ አሁንም ቢሆን፣ አዲስ አበባ ውስጥ ሕዝቡ ባለፈው የቀበሌና የወረዳ/ክፍለ ከተማ ምርጫ እንደታየው ከሆነ ለወያኔ/ኢሕአዲግ ያለውን ስሜት በግልጽ አሳይቷል፡፡” ስለዚህም፣ ከፍተኛው ያገር ገዳይ መቐለይ ላይ ሸብ-ረብ ተደረገ፡፡
ሌላም ምክንያት አለው፡፡ የፌዴራል ዋና ኦዲተርን ሪፖርት ተከትሎ “ውስጣዊ ሴራዎች/Ineternal Conspirencies) መካሄደ ላይ ነበሩ፡፡ በ116 የፌደራል መንግሥቱ ተቋማት ውስጥ በተደረገው የኦዲት ምርመራ መሠረት፣ በ84 መ/ቤቶች ከ5.2 ሚሊዮን ብር በላይ ያልተወራረደ የጥሬ ገንዘብ ውዝፍ ተገኝቷል፡፡ ይህንን ገንዘብ ደግሞ በየመሥሪያ ቤቱ የአስተዳደርና ፋይናንስ ዋና መምሪያ ኃላፊዎች ሆነው እንዳሻቸው የሚያደርጉት የሕወሀት/ወያኔ አባላት ናቸው፡፡ ሰንደቅ ጋዜጣ በሚያዝያ 23/2005 ዓ.ም እንደዘገበው ከሆነ ደግሞ ችግሩ በይብጥ የሚጎላው በመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ ነው፡፡ 3.2 ቢሊዮን ብሩ ደብዛው የጠፋው በዚሁ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ምናልባትም ደግሞ ከፍተኛዎቹን የጦር መኮንኖች የሚያነካካ ነው፡፡ ብዙዎቹ፣ በማረ በላነት ይታማሉ፡፡ በአንደ በጀት አመት ግን ይኼንን ያህል ገንዘብ ተመዝብሮ አያውቅም፡፡ ምናልባትም፣ አቶ መለሰ ዜናዊ ታመሙ (ሞቱ) የሚል የተምታታ ዘገባ በነበረበት የሰኔ/2004 ማለቂያ ላይ በስልጣናቸን አንቀጥልም በሚል ተስፋ-መቁረጥ ውስጥ የነበሩ አመራሮች ካቅማቸው በላይ አሽሽተዋል፡፡ ይሄንን ደግሞ የብአዴን መሪዎች በሚገባ አውቀውታል፡፡ ማወቃችንንም ያወቅነው በ11ኛው የኢሕአዲግ ጉባኤ ወቅት የአቶ በረከት ስምኦንንና የአቶ አዲሱ ለገሠን ቀና-ቀና ማለት አብጠርጥረን ስላየነው ነው፡፡
በዋናው ኦዲተር ሪፖርት አማካኝነት የብአዴን ሰዎች ራት ለመሆን የተዘጋጁት ሕወሀቶች ከጊ ጋር ሩጫ ጀመሩ፡፡ መቀሌ ላይ መሽገው ሁለት አባላቶቻቸውን “መናጆ” አድርገው በርካታ የብአዴን አባላትን ባላቸው የደሕንነትና የፀጥታ ዕዝ ሰንሰለት ተጠቅመው በቁጥጥር ሥር አዋሉት፡፡ እራት ሊያደርጋቸው ያሰበውን ብአዴንን፣ ሀሪፍ ምሳ አደረጉት፡፡ ብዘዎቹ የብዐዴን ሰዎች ሲታሰሩ “ችግር ይፈጥሩ ይሆናል የተባሉትም የፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ብርሀነ ኃይሉ፣ ሐሙስ ተወካዮች ምክር ቤቱ የሕግና ፍትሕ ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርታቸውን ከቀረቡ በኋላ ከኃላፊነታቸው መታገዳቸውን አወቁት፡፡  ይህንንም ለማድረግ መቐለይ ላይ መሽጎ የነበረው “የትግራይ ሪፐብሊካን ፓርቲ” አመራር፣ የደሕነትና የፀጥታ ኃላፊዎችን ማዘዙ ብቻ በቂው እንደነበረ አልተጠራጠረም፡፡ በዕለተ አርብ፣ ግንቦት 2/2005 ዓ.ም መጋረጃው ተገልጦ “የሙስናው ወንጀልም ጉዳይ” ለሕዝቡ በሰበር-ዜናነት ተነገረው፡፡ (ሕዝቡ ግን የሚገርም ምላሽ ነበር የሰጠው፡፡ የፕሪሜር ሊጉና የሰውለሰው ድራማ ሲያልቅባቸው ጊዜ፣ “የሙስና ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ” የሚል ድራማ ሊያሳዩን ይፈልጋሉን? ሲል ተዘባበተባቸው፡፡ (ጎበዝ፣ ቸር እንሰንብት!)
በሳምናታዊው የአዲስጉዳይ መጽሔት ቅጽ 7፣ ቁ. 164 ላይ፤ በግንቦት 10 ቀን 2005 ዓ.ም (ገጽ 22-3) የወጣ ነው::
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on May 21, 2013
  • By:
  • Last Modified: May 21, 2013 @ 4:24 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar