www.maledatimes.com በሙስና ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡ ባለሥልጣናትና ነጋዴዎች ቁጥር 32 ደረሰ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

በሙስና ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡ ባለሥልጣናትና ነጋዴዎች ቁጥር 32 ደረሰ

By   /   May 21, 2013  /   Comments Off on በሙስና ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡ ባለሥልጣናትና ነጋዴዎች ቁጥር 32 ደረሰ

    Print       Email
0 0
Read Time:23 Minute, 11 Second

•አቶ መላኩ ፈንታ ያለመከሰስ መብታቸውን በፈቃዳቸው ተውት

•ከታሰሩ ፀሐይ ያገኙት ለአሥር ደቂቃ ብቻ መሆኑን ተናገሩ

•የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለምን እንዳልተከበረ ፌደራል ፖሊስ ምላሽ ሰጠ

የፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መረብ ጋር በመተባበር ቀረጥና ታክስ በማጭበርበር፣ አራጣ በማበደርና በመመሳጠር ሕገወጥ ዕቃዎች እንዲያልፉ ያደረጉ ተጠርጣሪዎችን ክስ በማቋረጥ፣ በተከለከለ ንግድ ፈቃድ ሲሚንቶ በማስገባት፣ የተለያዩ ዕቃዎች የጉምሩክ ሥርዓት ሳይፈጸምባቸው እንዲያልፉ በማድረግ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለው ፍርድ ቤት የቀረቡት ባለሥልጣናትና ነጋዴዎች ቁጥር 32 ደረሰ፡፡

 ከግንቦት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ግንቦት 9 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የምርመራ መዝገብ ሰባት፣ በእነ አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ የምርመራ መዝገብ 12፣ በእነ መሐመድ ኢሳ የምርመራ መዝገብ ስድስት እና በእነ ዳዊት ኢትዮጵያ የምርመራ መዝገብ ሰባት ተጠርጣሪዎች ናቸው፡፡

ባለፈው ዓርብ ከቀትር በኋላ በቀረበው የመጨረሻው የምርመራ መዝገብ የቀረቡት ተጠርጣሪዎች አቶ ዳዊት ኢትዮጵያ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የታክስ ሕግ ገዥነትና ሥጋት ሥራ አመራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ አቶ ማሞ አብዲ የታክስ አማካሪ ዳይሬክተር፣ አቶ አሸብር ተሰማ የደረቅ ወደብ የዋጋ ትመና አስተባባሪ መሆናቸው ታውቋል፡፡ አቶ ፍፁም ገብረመድኅን፣ አቶ ማሞ ኪሮስ፣ አቶ አበበልኝ ተስፋዬና አቶ ኮነ ምሕረቱ ደግሞ ነጋዴዎች ሲሆኑ፣ ከትራንዚት ድርጅት ሕገወጥ ጉዳይ አስፈጻሚዎችና ነጋዴዎች ጋር በመመሳጠርና ለሕገወጥ ተግባር በመተባበር፣ ከናዝሬት ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች እንዳይፈተሹ አድርገው በማሳለፍና የአራጣ ብድር ክስ እንዲቋረጥ በማድረግ የሙስና ወንጀል መጠርጠራቸው ታውቋል፡፡

አምስት ተጠርጣሪዎቹ ግንቦት 9 ቀን 2005 ዓ.ም. ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም፣ ሁለት ተጠርጣሪዎች ሳይቀርቡ በመቅረታቸው ተሟልተው ለግንቦት 12 ቀን 2005 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ሌላው ፍርድ ቤቱ የተመለከተው የአቶ መላኩ ፈንታ ያለመከሰስ መብት በማስረጃ መረጋገጥ አለመረጋገጡን ነው፡፡

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር ግንቦት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ምሽት ላይ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በሚኒስትር ማዕረግ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ፣ ያለመከሰስ መብት እንዳላቸው ማስረጃቸውን ለፍርድ ቤት አቅርበው ካሳዩ በኋላ፣ ‹‹ያለመከሰስ መብቴ እንዳለ እንዲታወቅልኝ እንጂ እንደ ጓደኞቼ እሆናለሁ፤›› በማለት ያለመከሰስ መብት ቢኖራቸውም በፈቃዳቸው ስለመብታቸው መከራከሩን ትተውታል፡፡

የፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአቶ መላኩ የምርመራ መዝገብ ባቀረባቸው ስድስት ተጠርጣሪዎች ላይ የጠየቀውን የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የፈቀደው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ የወንጀል ችሎት፣ የአቶ መላኩን ጉዳይ ለዓርብ ዕለት ቀጥሮ የነበረው ያለመከሰስ መብት ያላቸው ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ ሰነድ እንዲያቀርቡ በማዘዝ መሆኑ ይታወሳል፡፡

ፍርድ ቤቱ ባዘዘው መሠረት ከምክር ቤቱ የተሰጣቸውን ያለመከሰስ መብት ማረጋገጫ መታወቂያ አቅርበው፣ ለፍርድ ቤቱና ለመርማሪ ፖሊሶች በመስጠት ያለመከሰስ መብት እንዳላቸው ካረጋገጡ በኋላ፣ ምንም ማለት እንደማይፈልጉና ከጓደኞቻቸው ጋር እንደሚሆኑ ከገለጹ በኋላ መርማሪ ፖሊሶች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የአባልነት ጊዜ አምስት ዓመታት መሆኑንና አቶ መላኩ የተመረጡትም ሚያዝያ 16 ቀን 2000 ዓ.ም. እንደሆነ የተናገሩት መርማሪዎቹ፣ አምስት ዓመታቸው ሚያዝያ 15 ቀን 2005 ዓ.ም. መጠናቀቁንና አዲስ የምክር ቤት አባላት ምርጫ ተካሂዶ ውጤቱ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ሕዝቡ የመረጣቸው የሕዝብ ተወካይ የምክር ቤት አባላት እስከሚገቡ ድረስ እንጂ በአንድ የምክር ቤት መቀመጫ ሁለት ተመራጭ እንደማይኖር የተናገሩት መርማሪዎቹ፣ አቶ መላኩ ጥያቄያቸው አግባብ አለመሆኑን አውቀው ክርክራቸውን ማንሳታቸው የሚያስመሰግናቸው መሆኑን ጠቁመው፣ ሳያነሱ ቢቀሩም ጊዜው ስላለፈ እንደማያዋጣቸው ገልጸዋል፡፡

ሌላው የአቶ መላኩን ጤንነት በሚመለከት ጠበቃቸው ያቀረቡት ጥያቄ ሲሆን፣ አቶ መላኩ በአገር ውስጥ ሕክምና ሊገኝለት የማይችልና መንግሥትም የሚያውቀው በከፍተኛ ሕመም እየተሰቃዩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ መላኩ የታሰሩት ምግብ፣ መድኃኒትና ሕክምና በሌለበት ጨለማ ቤት ውስጥ መሆኑን ጠበቃው አክለው፣ መንግሥት የሕመማቸውን ሁኔታ ተረድቶና ፈቅዶ፣ ውጭ አገር እየተመላለሱ ሲታከሙ እንደነበር አውስተዋል፡፡ ሕመማቸው ለሕይወታቸው አስጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውንና የሕግ አማካሪዎቻቸውን እንዲያገኙ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቢሰጥም ሊያገናኟቸው እንዳልቻሉ ጠበቃው ተናግረዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በታሰሩበት ማዕከላዊ እስር ቤት በውጭ በር ጥበቃ ላይ ያሉ ፖሊሶች ከበላይ የተሰጠ ትዕዛዝ መሆኑን በመግለጽ ከደንበኛቸው ጋር ሊያገናኟቸው እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

የሁሉም ተጠርጣሪዎች የሕግ አማካሪ ጠበቆች እንደ አቶ መላኩ ጠበቃ ሁሉ እነሱም መከልከላቸውን፣ በጣቢያው የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ባለ ስልክ እንዲደውሉ ነግረዋቸው ሲደውሉ ‹‹መገናኘት አይቻልም›› በማለት ሊያገናኟቸው እንዳልቻሉና ለእነሱም ጥብቅ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

አቶ መላኩ ፍርድ ቤቱ ዕድል እንዲሰጣቸው ጠይቀው ሲፈቀድላቸው እንደገለጹት፣ ጠበቃቸውን የሚያገኟቸው ፍርድ ቤት በመሆኑ የመረጃ ክፍተት አለ፡፡ ሕክምና ጠይቀው አግኝተዋል፡፡ መድኃኒት ታዞላቸው በመጥፋቱ የመድኃኒት ማዘዣውን ለቤተሰብ ሰጥተው ለማስገዛት ግን አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም ቤተሰቦቻቸውን ማግኘት ባለመቻላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሁን የታሰሩበት ክፍል ጨለማ አለመሆኑንና ጠበቃቸው ጨለማ መሆኑን የገለጹት ተገናኝተው መረጃ ባለመለዋወጣቸው መሆኑን የተናገሩት አቶ መላኩ፣ ታስረው የሚገኙት ለብቻቸው በአንደ ክፍል ውስጥ ሲሆን፣ ከታሰሩበት ጊዜ አንስቶ የፀሐይ ብርሃን ያገኙት አንድ ቀን ለአሥር ደቂቃ ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ልጃቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውንና የሕግ አማካሪያቸውን ማግኘት እንዳልቻሉ አስረድተዋል፡፡ ግንቦት 9 ቀን 2005 ዓ.ም. ‹‹የሕግ አማካሪህ ይጠራሃል›› ተብለው ሲወጡ፣ የማያውቋቸው ሰዎች ማግኘታቸውን የገለጹት አቶ መላኩ፣ ‹‹ጠበቆች ነን ልንረዳህ ፈልገን ነው፤›› ሲሏቸው፣ መታወቂያቸውን ተመልክተው ሁሉንም ነገር እንደነገሯቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ያማከሯቸው ‹‹ጠበቆች ነን›› ያሉት ሰዎች ግን ፍርድ ቤት አልተገኙም፡፡ በመጨረሻም ‹‹የምክር ቤት አባል ነኝ፤ ያለመከሰስ መብት አለኝ፤ ግን እንደጓደኞቼ እሆናለሁ፤›› በማለት ንግግራቸውን አቁመዋል፡፡

የነፃ ትሬዲንግ ባለቤት የአቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር ጠበቆችም እንደ አቶ መላኩ ጠበቃ ደንበኛቸውን ማግኘት አለመቻላቸውንና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊከበር አለመቻሉን ተናግረው፣ ‹‹ከላይ የተሰጠ ትዕዛዝ ስለሆነ ማገናኘት አንችልም፤›› መባላቸውን ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም እነሱን በመጠርጠር በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ያደርጋቸው ፀረ ሙስና ኮሚሽን ስለሆነ፣ ከላይ ያሉት ‹‹እንዳይገናኙ›› የሚሉት ኃላፊዎች እንዲጠየቁላቸው ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡

የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት የአቶ ከተማ ከበደ ጠበቃ የታሸገው የደንበኛቸው ድርጅት እንዲከፈትና ሠራተኞች ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ያቀረቡት አቤቱታ ላይ መርማሪው አስተያየት እንዲሰጥበት ታዟል፡፡

ፍርድ ቤቱ ግንቦት 5 እና 6 ቀን 2005 ዓ.ም. የሰጠውን ‹‹የተጠርጣሪዎች ሕገ መንግሥታዊ መብት ይከበር›› ትዕዛዝ ለምን እንዳልተፈጸመ የማዕከላዊ እስር ቤት የእስረኞች አስተዳደር ኃላፊ ቀርበው እንዲያስረዱ ባዘዘው መሠረት፣ ኮማንደር ብርሃኑ አበበ ፍርድ ቤት ቀርበው አስረድተዋል፡፡

ኮማንደር አበበ ለፍርድ ቤቱ ምላሽ መስጠት የጀመሩት፣ የአቶ መላኩ ጠበቃ በዕለቱ ከሰጡት የተቃውሞ ቃል ‹‹ጨለማ ቤት›› ከሚለው በመነሳት ነው፡፡ ኮማንደሩ እንደተናገሩት፣ ፌደራል ፖሊስ የጨለማ ቤት የለውም፡፡ ቦታው እንደ ፌደራል ፖሊስ የሕዝብ መብት የሚከበርበት ነው፡፡ ከሕግ ባለሙያ እንደዚህ ያለ ነገር አይጠበቅም፡፡ የአቶ መላኩን ጤና በሚመለከት በታሰሩበት ጊቢ ክሊኒክ መኖሩን፣ ከፍ ካለም በሪፈራል ወደ ፖሊስ ሆስፒታል እንደሚሄዱና ከዚያ ካለፈም ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሊወሰዱ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ የራሳቸው የሕክምና ቦታም ካላቸው ተጣርቶ ሊታከሙ እንደሚችሉ ኮማንደሩ አክለዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማክበርና ማስከበር የፖሊስ ተቀዳሚ ተግባሩ መሆኑን የተናገሩት ኮማንደሩ ዜጐችን የማስከበር፣ የመጠበቅና ቅድሚያ መሰጠትም የፖሊስ ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም ሁሉም ተጠርጣሪዎች ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር እንደሚገናኙ የተናገሩት ኮማንደር ብርሃኑ፣ ጥያቄው ፍርድ ቤት የሚቀርብ ሳይሆን በአስተዳደር በኩል እነሱ ሊፈቱት የሚችሉት ቢሆንም፣ አንድም የሕግ አማካሪ አነጋግሯቸው እንደማያውቅ ገልጸዋል፡፡

ሥራው ውስብስብና በአገር ላይ የተደቀነ አገርን ሊያወድም የሚችል የሙስና ጉዳይ በመሆኑ፣ ተጠርጣሪዎቹ ከተያዙበት ግንቦት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ብርበራ የማካሄድ፣ ቃል የመቀበልና ሰነድ የመሰብሰብ የቡድን ሥራ በመሆኑና ተጠርጣሪዎቹም በቦታው ተገኝተው የሚገኘውን ንብረት በኤግዚቢት ማስመዝገብ ስለነበረባቸው፣ ቤተሰብና የሕግ አማካሪዎች ሊያገኟቸው አለመቻላቸውን አስረድተዋል፡፡ በቀጣይ ግን በማንኛውም ነገር ለመተባበር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ፍርደ ቤቱ ሁሉንም አቤቱታ አቀራቢዎችና ተከራካሪዎች ግራና ቀኝ ካዳመጠ በኋላ ትዕዛዞችን ሰጥቷል፡፡ በመጀመርያ ትዕዛዙ አቶ መላኩ ከምርጫ ቦርድ የተሰጣቸውን ያለመከሰስ መብት መታወቂያ ያቀረቡና መርማሪ ፖሊስም ምላሽ የሰጠበት ቢሆንም፣ እሳቸው መብታቸውን እንደማይፈልጉ በመግለጻቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር መሆን እንደሚፈልጉ በመግለጻቸው፣ ዓቃቤ ሕግ የጠየቀው የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መፍቀዱን ገልጿል፡፡ ቀጥሎም የፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የዜጐች መብት መከበሩን እንዲያረጋግጥ አዟል፡፡ ሌላው ደግሞ ኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት እሽግን በሚመለከት የኮሚሽኑ መርማሪ ፖሊስ ምላሹን ግንቦት 13 ቀን 2005 ዓ.ም. ይዞ እንዲቀርብ አዟል፡፡

ፍርድ ቤቱ በእነ መሐመድ ኢሳ የምርመራ መዝገብ እየቀረቡ ያሉት ስድስት ተጠርጣሪዎች ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ተመካክረው እንዲቀርቡ ቢያዝም፣ ፖሊስ ‹‹በስህተት ሳናቀርባቸው ቀርተዋል›› በማለቱ፣ ፍርድ ቤቱ ፖሊስን በማስጠንቀቅ ለግንቦት 12 ቀን 2005 ዓ.ም. እንዲያቀርብ አዟል፡፡

 REPORTER

በሙስና ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡ ባለሥልጣናትና ነጋዴዎች ቁጥር 32 ደረሰ

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on May 21, 2013
  • By:
  • Last Modified: May 21, 2013 @ 11:41 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar