www.maledatimes.com የነፃነት ጥያቄ ከልደታ ማርያም ቤተ ክርስቲያን እስከ አንዋር መስጊድ (ሀብታሙ አሰፋ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የነፃነት ጥያቄ ከልደታ ማርያም ቤተ ክርስቲያን እስከ አንዋር መስጊድ (ሀብታሙ አሰፋ)

By   /   July 29, 2012  /   Comments Off on የነፃነት ጥያቄ ከልደታ ማርያም ቤተ ክርስቲያን እስከ አንዋር መስጊድ (ሀብታሙ አሰፋ)

    Print       Email
0 0
Read Time:40 Minute, 49 Second

Lideta &Anewar mosqfor more picture please click here maledatimes pdf1 የነፃነት ጥያቄ ከልደታ ማርያም ቤተ ክርስቲያን እስከ አንዋር መስጊድ

የነፃነት ጥያቄ ከልደታ ማርያም ቤተ ክርስቲያን እስከ አንዋር መስጊድ
ሀብታሙ አሰፋ

የሙስሊሙ ህብረተሰብ ግልፅና የማያሻማ የዕምነት ነጻነት ጥያቄ አንስቷል። የአገሪቱ የበላይ ህግ በሆነውና በተግባር ስራ ላይ ውሎ በማያውቀው ህገ-መንግስት ተቀባይነት ያለው መሰረታዊ  ጥያቄ ነው። አህባሽ የተሰኘውን ባዕድ መጣሽ የሀይማኖት አስተምህሮ በግድ ሊጫንብን አይገባም፣ ለሀይማኖት መሪነት የተቀመጠው መጅሊስ (የእስልምና ጉዳዮች ም/ቤት) አይወክለንም፤ መሪዎቻችን በመስጊድ ነፃና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንምረጥ የሚል ነው።

 

ከአወልያ ተነስቶ በመላው አገሪቱና በውጭም በሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውን ይሄን ጥያቄ፤ በሀይል እመልሰዋለሁ ያለው በስልጣን ላይ ያለው የህውሃት ዘረኛ አገዛዝ፤ እንደ ትላንቱ ሁሉ በጥይት እፈታዋለሁ በጉልበት አፍነዋለሁ ብሏል። ይህን ጥያቄ ባነሱት ላይ በወሰደው እርምጃ ከአርሲ ገደብ አሳሳ እስከ አወልያ የንፁሃንን ህይወት አጥፍቷል። በሺህ የሚቆጠሩትንም አግዞ በሰንዳፋ፣ በሸዋ ሮቢትና በልዩ ልዩ እስር ቤቶች በጅምላና በተናጠል የማሰቃየት ተግባር እየፈፀመ ነው።

 

ጥያቄውን ለማሰማት በህዝበ ሙስሊሙ የተመረጡ ወኪሎችን በሙሉ ከሌሎቹ ጋር ታስረው የጭካኔ ተግባር እየተፈፀመባቸው ነው። ስርዓቱ ከዚህ ቀደም እንዳደረገው አስቀድሞ የለጠፈውን ወንጀል፤ በጭካኔ ድብደባና  ስቃይ ከፈፀመባቸው በኋላ የተነሱትንና የተናገሩትን  ፊልም አቀነባብሮ የፈጠራ ክሱ ማስረጃ ለማደራጀት  ዘመቻ መያዙን መረጃዎች አፈትልከዋል።

 

የሙስሊሙ ህብረተሰብ ድምፃችን ይሰማ ጥያቄውን እጅግ ሰለማዊ በሆነ መንገድ ማሰማቱን በመቃወምና በሌላ ዕምነት ተከታይ ወገኖቹ ጥርጣሬ እንዲፈጠር  አንዴ የአሸባሪ ተልዕኮ ለማስፈፀም የመጡ ሌላ ጊዜ በአገሪቱ በሃይል የሸሪኣ ስርዓት ሊዘረጉ በሚል የተከፈተባቸውን የሀሰት ቅስቀሳ ለመመከት እውነቱ ይሄ ነው በሚል መፅሃፍ እስከማሳተም ሔደዋል።

 

አገዛዙ ሀላፊነት በጎደለው ሁኔታ ስልጣኑን ለማቆየት እንቅስቃሴውን አደጋ አድርጎ በመቁጠር ሙስሊሙና ክርስቲያኑን ለማጋጨት ራሱ ሙሉ ለሙሉ በሚቆጣጠረው ቴሌቪዥን ሰፊ ቅስቀሳ አድርጓል። ህዝቡን እርስ በእርሱ ለማጫረስ የስልጣን እድሜውን ለማራዘም የማይመለስ ሀይል መሆኑን በተግባር አስመስክሯል። ህዝቡ አብሮ በመኖር የስርዓቱን አፋኝነት የአገዛዙን መገናኛ ብዙሃን ዋሾነት በመገንዘብ እነሱ እንደፈለጉት ሙስሊሙና ክርስቲያኑ ዕለቱን አደባባይ ወጥቶ አልተራረደም።

 

የአቶ መለስ ዘረኛ የህዋሃት አገዛዝ (መለስ ሞተም ኖረ እድሉን እስካገኘ መቀጠል የሚፈልገው ቡድን) ትላንት ክርስቲያኖችን በመደብደብ የሙስሊሞቹ ወኪል መስሎ ለመታየትና በዕምነቱ ተከታዮች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ በታቦት መውረጃ ካልጠፋ ቦታ ለመስጊድ ቦታ እየመራ ትልቅ ውጥረቶችን በየቦታው እየፈጠረ ጥርጣሬን እያስፋፋ ለመዝለቅ ሞክሯል።

 

የሙስሊሙ ጥያቄ እስልምናን የመደገፍ ወይም ያለመደገፍ ጉዳይ አይደለም። ጥያቄው የዕምነት ነፃነት ጥያቄ፣ የዲሞክራሲ ጥያቄ በመሆኑ፤ ለአማኞቹ ዕምነታቸውን የመደገፍ የማምለክ ነፃነታቸውን የማስከበር ብቻ አድርገው ሊመለከቱ ቢችሉም፤ ማንኛውም ለህግ የበላይነት የሚታገል ለአገሪቱ ሰዘላቂ ሰላም የሚያስብ ሁሉ ሊደግፈው የሚገባ የመብት ጥያቄ ነው።

 

ትላንት የሙስሊሞች አጋር ነኝ ብሎ ስልጣኑን ለማራዘም የሞከረ ስርዓት ዛሬ በተራው ተገልብጦ ደግሞ የዋልድባ መነኩሳትን መደብደቡን እንኳ ዘንግቶ፤ የክርስትና እና የክርስቲያኖች ወኪል መስሎ ለመታየት የሚፈልገው አገዛዝ በተግባር የሁለቱም አማኞች የዕምነት ነፃነት ጥያቄን የሚቃወም ሀይል ነው። ለዚህ የተወሰኑ አብነቶችን መጠቃቀሱ አይከፋም።

በአዲስ አበባ ከዛሬ ዘጠኝ  ዓመት በፊት ዛሬ በሙስሊሞች ላይ የሚከተለው የሰብአዊ መብት ረገጣ በልደታ ማርያምም ተፈፅሟል።

 

በጊዜው የልደታ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ለአቡነ ጳውሎስ አመራር አልተመቹም። የልደታን ቤተ ክርስቲያን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን ጀመሩ። ዛሬ በልደታ የምታዩት ህንፃ አንዱ ነው። ከህዝቡ የተመረጠው የሰበካ ጉባዔ አባላትና የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ በጋራ ቤተክርስቲያኑዋን ለማሳደግ፤ መንፈሳዊ አገልግሎቱን ለማሳካት፣ ጥረታቸውን ቀጠሉ። በመሀል የአቡነ ጳውሎስ ቡድን ከቤተክርስቲያኑዋ እየዘረፈ የሚወስደው ገንዘብ ላይ ቁጥጥር መዘርጋቱ፣ በተለይም እሱ የማይፈልገው ነፃ የሆነ የአመራር ስርዓትን ለመዘርጋት የሚደረገውን ጥረት  በመቃወም የቤተክርስቲያኑዋን አስተዳዳሪ ከሀላፊነት አንስቻለሁ ይላል። አዲስ ሰው ይሾማል። የቤተክርስቲያኑዋ ምዕመናን፣ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች ዲያቆናትና ካህናት ድርጊቱን ይቃወማሉ።

 

ምዕመናኑ የምንመራው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ዕምነት መሰረት ነው። ነገር ግን አቡነ ጳውሎስ አይወክሉንም። በእምነታችን ጣልቃ አትግቡ የቤተክርስቲያኑ ንብረት ለቤተክርስቲያኑዋ መዋል አለበት በሚል ተቃውሞ ያቀርባሉ።

 

ምዕመናኑ በየደረጃው ከወረዳ እስከ አቶ መለስ ቢሮ አቤት ይላሉ ሰሚ አጡ። የአቡነ ጳውሎስ ቡድን በፌዴራል ጉዳዮች በፌዴራል ፓሊስ እየተመራ ማስፈራራት፣ አንዳንድ ግለሰቦችን ማሳደድ፣ መወንጀል፣ የአሉባልታ ዘመቻ በመክፈት የቤተክርስቲያኑዋ አስተዳደርን፣ ካህናቱን እና የሰበካ ጉባኤ አባላቱን ከቦ፤ ከተቃዋሚ  ፓርቲዎች ጋር እያጣቀሱ አመጸኞች ሲሉ ወነጀሉ።እሱ አላዋጣ ሲል አንዴ ተሃድሶ ሌላ ጊዜ ጴንጤ እያሉ የአሉባልታ ዘመቻ ከፈቱ።

 

ችግሩ እያደገ ሔዶ አቡነ ጳውሎስ እሾማለሁ ምዕመናኑ የዕምነት ነፃነታችን ይከበር ራሳችንን በራሳችን ዕምነታችንን ጠብቀን እንኖራለን የሚል ሙግት ከፈቱ። መከላከያ፣ደህንነቱ፣ፓሊስና  ፍ/ቤት በእጁ የሆነው አገዛዝ የህዝቡን ቤተክርስቲያን ፍ/ቤትን በመሳሪያነት በመጠቀም ለመንጠቅ ሞከሩ። ምዕመኑን በአቋሙ ጸና።

 

የዚህ ፁሑፍ አቅራቢ በስፍራው ለዘገባ የተገኘበትን የልደታ ጉዳይ በጉልበት የተጨፈለቀበትን ህዳር 18 ቀን 1995 ዓመተ ምህርት ውሎ በመጠኑ መጠቃቀሱ አገዛዙ በሙስሊሞች ላይ የሚፈፀመውን ግፍ ትላንት በክርስቲያኖች ላይ ሲፈፀም መኖሩን ለማስታወስና የሁለቱን ዕምነት ተከታዮች ለማጋጨት የቀጠለበትን አጥፊ ቅስቀሳውን ለማስቆም የግፍ ስራቸውን ደግሞ ማስታወስ    ይጠቅመማል ብዬ አምናለሁ።

 

ህዳር 18 ቀን 1995 በልደታ ማርያም ቤተክርስቲያን ምዕመናን ህፃን አዋቂ አሮጊት ሽማግሌ ሳይሉ በቤተክርስቲያኑዋ ቅጥር ግቢ ተሰብስበው ምህላ ይዘዋል።

 

ህዳር 17 1995 ዓመተ ምህረት ማታ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አቡነ ጳውሎስ የሚመሩት ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የተባሉ ሰጡት በተባለ መግለጫ በልደታ ቤተክርስቲያን ህግና ስርዓት ሊከበር ባለመቻሉ ችግሩም ከአዲስ አበባ ፖሊስ አቅም በላይ በመሆኑ አመዐኞቹን ለመቆጣተር የፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ እንዲገባ ጠየቁ።

 

የልደታ ምዕመናንና የሰበካ ጉባኤ አባላት በወቅቱ እንደገለፁት በዚህ መግለጫ የሲኖዶስ አባላት ያልሆኑም ተገኝተዋል ብለዋል። አርብ ማለዳ በቴሌቪዥን የተሰጠውን መግለጫ በመቃወም የምዕመናኑ ተወካዮች (የሰበካ ጉባዔ ኮሚቴ አባላት) የ5500 ሰዎች ፊርማ በማሰባሰብ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን  ይገኛሉ።

ምዕመናኑን በህገ ወጥ፣ በፀረ ሰላምነት፣ በአመፀኝነት፣ ሲወነጅል ለአገርና ለህዝቡ መረጋጋት እንዳይመጣ የሚሰሩ የፖለቲካ ዓላማ አራማጆች እያለ ሲከስ የነበረው ቴሌቪዥን ለሰራው ፕሮግራም ማስተባበያ እንዲያደርግ ሲጠየቅ፤ ዜናውን የሰራው ዜና አገልግሎት ስለሆነ እኔን አይመለከተኝም ይላል። የምዕመናኑ ወኪሎች ወደ ዜና አገልግሎት ያመራሉ።

 

የምዕመናኑ ወኪሎችም ለዜና አገልግሎት  ሲኖዶሱ ሰጠው ለተባለው መግለጫ ምላሽ ለመስጠት ይጠይቃሉ። በዚህም ጉዳዩ የሀይማኖት ጉዳይ ስለሆነ የመንግስትን ጣልቃ መግባት አይጠይቅም። ሰላማዊ እንጂ አመፀኞች አይደለንም። የሀይማኖት ነፃነታችን ይከበርልን። የሚል ሀሳብ ላይ ያተኮረ ቃለ ምልልስ ሰጥተው ይመለሳሉ። ቃለ መልልሱ ሳይተላለፍ ይቀራል። በዚህ ቅር ቢሰኙም ድምፃቸውን በአገኙት የነጻ ፕሬስ ውሱን መድረክ  ማሰማት ቀጠሉ ።

አርብ ህዳር 18 ቀን 1995 ዓ.ም የልደታ ምዕመናን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አመፀኞች፣ ፀረ ሰላም ኃይሎች፣ ስልጣን ናፋቂ ተቃዋሚዎች የሚመሩት መባሉን በመቃወም፤ ጥያቄያቸውን በሰላም ለማሰማት ለምህላ ህፃን አዋቂ ሳይል ሁሉም በቤተክርስቲያኗ  ቅጥር ግቢ ይሰበሰባል። በዕለቱ በአቡነ ጳውሎስ ሲኖዶስ የፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ ይግባ በመባሉ ውጥረት ነግሷል። ልደታ ስደርስ በቤተክርስቲያኑዋ ቅጥር ምዕመናን የዕምነት ነፃነታችን ይከበር! እግዚአብሔር ያሸንፋል! መመኪያችን እግዚአብሔር ነው! የሚል መፈክር አንግበውና የእመቤታችንን ምስል፣ የስላሴን ምስል ይዘው <<አንመካም በጉልበታችን እግዚአብሔር ነው የኛ ሀይላችን>> እያሉ  ይዘምራሉ። እናቶች ያለቅሳሉ። እግዚኦታው ያስገመግማል ።

 

በዕለቱ ከእኩለ ቀን ጀምሮ የፖሊስ ኃይል በየደረጃው እየጨመረ ሔደ። ምዕመናን በሩን ዘጉ ፀሎትና ምህላ ምልጃና ልመናቸውን ቀጠሉ። ሰላማዊ ምዕመናንን አመጸኛ ብሎ ስም የለጠፈው አገዛዝ ጥያቄውን በጉልነት ለማፈን ተንቀሳቀሰ። ፖሊሶች ከሜክሲኮ አደባባይ ወደ ልደታ የሚወስደውን መንገድ ለተሽከርካሪ ዘጉ። ወደ ልደታ የሚያስገቡ መንገዶች ሁሉ ከፖሊስና ከደህንነት ተሽከርካሪዎች በስተቀር ለሌላ ተሽከርካሪዎች ዝግ ሆነ።

 

በአካባቢው የተገኙት  በርካታ የፌዴራልና የክልሉ ፖሊሶች በቤተክርስቲያኑዋ ያሉትንም ሆነ ከውጭ ያለውን በዱላ መደብደብ ያዙ ። ከውጭ የነበሩ ሰዎች የፖሊስን ድርጊት በመቃወም ወጣቶች በተቃውሞ ድንጋይ መወርወር ጀመሩ። በቤተክርስቲያኗ የሚደበደቡት ዋይታና እሪታ ቀጠለ። የቤተክርስቲኑዋ ደውል ለድረሱልን ተደወለ።የክርስቲያኖች ደም እንደ ውሃ ፈሰሰ።በፖሊስ ከተፈነከተ ጭንቅላታቸው የሚወርደው ደም ያዞራቸው በያሉበት ወደቁ።ለጸሎት የተለበሰ ነጠላ የደም ጃኖ መሰለ።ይህን የተቃወሙ ዋይታውን ሰምተው የተቆጡ ወጣቶች ከየመንደሩ ወደ ቤተክርስቲያኗ ሲሄዱ መንገዱን የዘጋውን ፖሊስን በመቃወም ድንጋይ መወርወር ጀመሩ። ከቤተክርስቲያኗ ወጥተን በአካባቢው ካሉ ሱቆች የተጠለልነውም ጉሸማ አልቀረልንም። በአጠቃላይ ሰላማዊ የሆነውን የምዕመኑን ተቃውሞ በደቂቃ ውስጥ ሽብር ነዙበት። አስለቃሽ ጭስና እሱ አልበቃ ሲል የጥይት ተኩስ ቀጠለ። በዕለቱ ማምሻውን አንድ የአካባቢው ወጣት ተገደለ።

ከልደታ ግቢ የታገቱ በመቶ የሚቆጠሩ ንፁሃን ኮልፌ ፖሊስ ማሰልጠኛ ተግዘው ተወሰዱ። ካህናት ጥምጣናቸውን እየፈቱ፣ የክህነት ልብሳቸውን እያወለቁ፣ ህፃናትና ሴቶች ወጣቶች ብቻ ሳይሆን ሽማግሌዎች ጭምር ድብደባ እንግልት እና ፀያፍ ስድብ ወረደባቸው። በባዶ እግራቸው እየተደበደቡ፣ እግር የሚወጋ ኮረት በፈሰሰበት እንዲራመዱ፣ እንደሙቀጫ እንዲንከባለሉ፣ ተዘቅዝቀው ተደፍተው የውስጥ እግራቸውን የተገረፉ ነበሩ። በጊዜው ይህን ሁሉ የዐይን እማኞችን ጠቅሰን በልደታና አካባቢዋ የተፈፀመውን ግፍ ዘግበን ነበር።

 

ከልደታና አካባቢዋ ታፍሰው ኮልፌ ተግዘው ከተደበደቡና ከተፈቱ መሃል ሙስሊሞች እንደነበሩ በጊዜው በዚያ ዘገባ አካተን ነበር። በስፍራው ከነበርን ጋዜጠኞች መካከል ዩሐንስ ወልዴ የተባለው የጦቢያ ሪፖርተር ጋዜጠኛ መሆኑን አውቀው ፖሊሶች ደብድበው ቴፕ ሪከርደሩን ነጥቀውታል።

 

በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች በፖሊስ ቆመጥ፣ የተወሰኑት ማምሻውን በጥይት ጭምር የቆሰሉ ቢሆንም በቴሌቪዥን በአመጸኞቹ ስምንት ፖሊሶች ቆሰሉ አንዱ በፅኑ የቆሰለ በመሆኑ ፖሊስ ሆስፒታል ሲተኛ ሌሎች ህክምና አግኝተው ሔደዋል ተባለ። በአመጹ የቤተክርስቲያን በርና መስኮት ሰብረዋል ሲሉ አከሉ። አስቀድሞ በቴሌቪዥን ሲቀርብ የነበረው ወንጀል ተጠናክሮ ቀጠለ።

 

በስፍራው ከጥቂት ጋዜጠኞች በተጨማሪ በጊዜው ስሙ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ የነበረው (ኢሰመጉ) ዛሬ ስሙን ተነጥቆ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) ብቻ የሆነው  የሰብዓዊ መብት ረገጣ አጣሪዎች የነበሩት ያሬድ ሀይለማርያም እና ቸርነት በስፍራው  ነበሩ። የጊዜው ኢሰመጉም በልደታ የተፈፀመውን ሰብዓዊ መብት ጥሰት አጋለጠ። ዛሬም ሰመጉ ሆኖ በሙስሊሞች ላይ የተፈፀመውን የሰብአዊ መብት ረገጣ አቤት ብሏል።

 

በወቅቱ ፖሊስ አመፅ ከማስነሳቱ በፊት ኋላ ብዙዎች እንደጠረጠሩት አስቀድሞ ለመወንጀያ ከተሰበረ የቤተክርስቲያኑ የኋላ በኩል አንድ መስኮት በስተቀር የተሰበረ አልነበረም። በጽኑ ቆሰለ የተባለው ፖሊስ የሲቪል ልብስ ለብሶ የነበረና ፌዴራሎቹ ተልእኮውን እስኪያስረዳ ጊዜ ስላልሰጡት እንደቀሩት ሰላማዊ ዜጎች ያለ ርህራሔ ሲደበድቡት በሞትና በህይወት መካከል የቀረ ነበር።

 

ኮልፌ ታፍሰው ከተወሰዱት መካከል ከቀናት በኋሏ 45 ያህል ፍ/ቤት ቀረቡ ከነዚህ ውስጥ የቤተክርስቲያኑዋ ካህናት ሰበካ ጉባኤ አባላት የሆኑ፣ ዲያቆናት፣ የሰንበት ት/ቤት አባላት ይገኙበታል።

 

የልደታ ጉዳይ በሀይል ተጨፈለቀ። ብዙዎች ታስረው ተንገላቱ። ጥቂቶችም ተሰደዱ። ከነዚህ ስደተኞች መካከል የልደታ የሰበካ ጉባኤ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ወንድሙ አዝመራ ዛሬ ድረስ በስተርጅና በግብፅ ካይሮ የስደት ህይወትን ይገፉታል።

 

በአወልያ የተነሳው ሰላማዊ ጥያቄን ከመመለስ ይልቅ አገዛዙ አንዴ አሸባሪ ሌላ ጊዜ የሸሪአ ስርዓትን በሀይል ለማቋቋም የሚጥሩ በማለት የክርስቲያን ተቆርቋሪ መስሎ ህዝቡን ለመከፋፈልና በትርምስ  የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም እየጣረ ነው።

 

አገዛዙ በአወልያ የተቀጠረውን የሰደቃና የአንድነት በዓል ለማደናቀፍ፤ የሰላም ያለህ የህግ ያለህ ያሉትን በጉልበት ጥሶ በርካቶችን ደብድቦ ጥቂቶችን ገሎ በመቶ የሚቆጠሩትን አስሮ በለመደው ስልት  ለመዝለቅ ነበር። የአወልያ መዘጋት ተስፋ ያላስቆረጠው  የዕምነት ነፃነታችን ይከበር፣ ድምፃችን ይሰማ ያለው ህዝበ ሙስሊም በአንዋር ተሰባስቦ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄውን ቀጠለ። እንደ ልደታ ቤተክርስቲያን ሁሉ አንዋር መስጊድም ። ባለቆመጥና ባለመሳሪያዎቹ ቤተመቅደሱን ሁሉ እንደረመረሙት ያንኑ በመስጊድ ደገሙት። በአንዋርም የሙስሊሞች ዋይታ ሆነ። የንፁሀን ደም ፈሰሰ። ብዙዎች ተደበደቡ ሺዎች ተግዘው በሰንዳፋ በሸዋሮቢትና በማይታወቅ እስር ቤት ጭምር  በጅምላ ስቃይ ይፈፀምባቸዋል።

የታሰሩት የህዝበ ሙስሊሙ ወኪሎችና ከነሱ ጋር ተባበሩ የተባሉ  ዋና ዋና አደራጆች  እየተደበደቡ አስቀድሞ በቴሌቪዥን የተለጠፈባቸውን ወንጀል አሜን ብለው እንዲቀበሉ ድራማ መቀነባበሩ መረጃው ሾልኮ ወጥቶ  ተጋልጧል።

እነ ጄነራል ተፈራ ማሞን የህዝብ መብት ይጠበቅ ሰላሉ “ሽንታም አማሮች” እያለ ደብድቦ የጨለማ ጉዞ የሚል የድራማ ፊልም በመፃፍ ከአዲስ አበባ ዱባይ የተዘረጋ የሽብር መረብ በጣጠስኩ ማለቱ ያልበቃው ስርዓት፤ አኬልዳማ በሚል ሌላ ዙር የፊልም ድራማ አንዷለም አራጌንና እነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ፣ ውብሸት ታዬንና ሌሎችንም በአሸባሪነት ለመክሰስ ሞክሯል። ዓለም ሁሉ አልተቀበላቸውም እንጂ ህውሀቶች የነሱን የአፈና አገዛዝ የተቃወመ ሁሉ አሸባሪ ነው።

 

ዛሬም በአንድ በኩል አገዛዙ ስልጣኑን ለማራዘም ክርስቲያንና ሙስሊሙን ለማጋጨት በካድሬዎቹ ሰፊ ቅስቀሳውን አላቋረጠም። ብዙሃኑ ህዝብ የክርስቲያኑንም የሙስሊሙንም ቤተ እምነት እየደፈረ እሱ የፈለጋቸውን ሰዎች ለመጫን የንፁን ደም እንደሚያፈስ እየተገነዘበ ነው። ነገር ግን ለአጥፊዎቹ ትላንት በልደታ ማርያም የሰሩትን ግፍ  ዛሬ በአንዋር መስጊድ የበለጠ አጠናቅረው መድገመማቸውንና በዚህ መንገድ የነፃነት ጥያቄ አፍነው እርስ በእርስ በማጋጨት ሊያመልጡ እንደማይገባ መንገር ይገባል። በጋራ መተባበር የሙስሊሙን ህጋዊና የመብት ጥያቄ በየደረጃው በመደገፍ  በአገሪቱ ላይ ነፃነት እንዲመጣ የሚደረገውን ትግል ማገዝና በሚችሉት አቅም ሁሉ ይህን ስርዓት መታገል ያስፈልጋል።

ትላንት የልደታን ግፍ ነጻ ፕሬሱ በመጠኑ ለማጋለጥ ዕድል አግኝቶ ነበር።ዛሬ ፍትህ ጋዜጣ በአንዋር የተሰራውን ግፍ እንዳትዘግብ ታግዳለች።እግዱ መቼም እንደሚነሳ አይታወቅም።ስርዓቱ የበለጠ የመቆየት እድል ባገኘ ቁጥር የአፈና አገዛዙ እየጠነከረ እንጂ እየተሻሻለ እንደማይሄድ የልደታና የአንዋር መስጊድ የትላንቱ ነጻ ፕሬስና የዛሬዋ ፍትህ መጨረሻ ጉልህ ምስክር ነው።

 

ከአርሲ ገደብ አሳሳ እስከ አወልያ የንፁሃኑን ህይወት በመቅጠፍ፣ ሺዎችን በማሰር፣ በመደብደብ፣ የፈጠራ ወንጀል በመደረት፣ ትላንት የልደታ ማርያምን ምእመናን የእምነት ነፃነት ጥያቄ እንደጨፈለቁት ግን የሙስሊሙን ጥያቄ በአንዴ መጨፍለቅ አለመቻላቸውን እያየን ነው። ልደታ ማርያምን ዘግተው ቅዳሴ እንዳስተጓጎሉት አንዋርን ግን መዝጋት አልቻሉም። ይህ ህዝብ በጋራ ሲነሳ ነፃነት የማጣት ጥያቄውን በአንድ ላይ ሲያቀርብና ለዚህም አብሮ ሲታገል የዚህ የአፈና ስርዓት  ይህ የጨካኞች አገዛዝ ያከትምለታል።

 

በነገራችን ላይ የልደታ ምዕመናንን ጥያቄ በሀይል ከጨፈለቁ በኋላ አቡነ ጳውሎስ የሚመቻቸውን ሾሙ። አዳዲስ ካህናት አመጡ። አዲስ የመጡት ተሿሚዎች እዚያ የንፁሃኑን ደም በፈሰሰበት ቤተ-ክርስቲያን የህዝቡን ገንዘብ አውጥተው ለአቡነ ጳውሎስ ገፀ በረከት የወርቅ ጫማ አሰርተው አበረከቱላቸው። በጊዜው በነፃ ፕሬስ ጋዜጦች ላይ ተዘግቦ እንደቀልድ አንድ ሰሞን አወይ ጉድ ተብሎ የቀረ ነው።

 

ዛሬም የሙስሊሙ ወኪሎችን አህባሽን አንቀበልም የእምነት ነፃነታችን ይከበር ድምፃችን ይሰማ ካሉት ሽዎችን አግዞ በማሰር በመደብደብ እንዳሰቡት ምርጫውን በካድሬዎች ለመሙላት ነው። ትላንት ይሄ በልደታና በቤተክህነት አይተነዋል።

 

የክርስትናም ሆነ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች በጋራ የዋልድባም መደፈር፣ በአወልያ ተነስቶ እስከ አንዋር የቀጠለው የዕምነት ነጻነት የመብት ጥያቄ በጋራ ይመለከተናል በማለት መቀጠል አለባቸው። በዋልድባ ቅዱሱን ስፍራ አትረሱ ያሉ መነኮሳትን እየደበደበ በማሰር ፀያፍ ስድብ የሰደበ አገዛዝ ዛሬ በክርስትና ስም መነገድ አትችልም ሊባል ግድ ነው።የሚያደርገው ጸረ ሙስሊም የአፈና እንቅስቃሴና የግፍ እርምጃን ሁላችን በጋራ ልናወግዘው ወቅቱ አሁን ነው። ለመሆኑ የዋልድባ ተቆርቋሪዎች ሰሞኑን የት ገቡ? ከአዲስ አበባ አንዱ የፌስ ቡክ ወዳጄ ምነው የዋልድባ ተቆርቋሪዎች ጠፋችሁ በሙስሊም ወገኖቻችን ላይ አገዛዙ የጀመረውን ጥቃት እስኪጨርስ <<ሚዩት>> አደረጋችሁ ወይ በላቸው ብሎኛል። ትላንትም በአደባባይ እንደታየው ለዋልድባም፣ ለአወልያና በአንዋርም ጥቃት በአንድ ላይ ድምፃችንን በጋራ ማሰማት መቀጠል አለብን።

 

አገዛዙ ዕድሜ ባገኘ ቁጥር አንዱን ከአንዱን እየለየ ለመጨረስ አይመለስም።ተግባሩን በመገንዘብ የሚያወራውን ከፋፋይነት ችላ ልንለው ይገባል። ሌላው ቀርቶ የሙስሊሙ አንድነት ስላስፈራው በብሔር ስም ለመከፋፈል ላይ ታች ማለታቸውን ማስታወስና ዛሬም አብሮ በመቆም የቀረውም ህዝብ የነፃነት ጥያቄውን በመደገፍና ተጨማሪ ጥያቄዎቹንም በማንሳት ለዕምነት ነፃነት ለዜግነት ነፃነት ለህይወት ነፃነት ለንብረት ነፃነት ለህግ የበላይነት እና ለእኩልነት በጋራ መነሳት አለበት።

 

የሙስሊምና የክርስቲያኑ በአንድነት መቆም ጊዜ ሊሰጠው አይገባም። በአገርና በዜጎች የህይወትና የንብረት ነፃነት ላይ እንቅፋት የሆኑትን በጋራ ለማስወገድ የህልውና ዋስትና ነው። ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ረግጠው የገዙ ገዢዎችን ከጫንቃችን ላይ ለመጣልና ነጻነታችንን ለማግኘት አማራጭ መንገድ ነው። በአንድነት ለነፃነት መነሳት በአንድ ላይ ድምፅን ማሰማት በጋራ ሙስሊሙ  <<አላሁ ክበር! የክርስቲያኑን መብት አትንኩ>> ክርስቲያኑም <<እግዚያብሄር ታላቅ ነው ! ሙስሊም ወገኔን አትንኩ!>> ማለት የከፋፋዮችን ሴራ ያከሽፋል።

ቸር እንሰንብት።

ለአስተያየትዎ habte05@gmail.com

 

 

 

 

 

 

በአወልያ ከተገደሉት አንዱ ሙስሊሞች

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar