www.maledatimes.com የህወሃት አባላት ስብሰባ እንዲጠራ እየጠየቁ ነው! - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የህወሃት አባላት ስብሰባ እንዲጠራ እየጠየቁ ነው!

By   /   July 30, 2012  /   Comments Off on የህወሃት አባላት ስብሰባ እንዲጠራ እየጠየቁ ነው!

    Print       Email
0 0
Read Time:15 Minute, 4 Second

(ልዩ ግምገማ)
source ኢ.ኤም.ኤፍ – ከቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ድንገተኛ ህመም በኋላ ከህወሃት አካባቢ መልካም ወሬ አይሰማም። በውጭ ሲታይ አሁንም የጠነከሩ ቢመስሉም ውስጥ ውስጡን ግን መጎሻሸማቸው አልቀረም። በተለይም የህወሃት (ህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ) ሊቀ መንበር የነበረው መለስ ዜናዊ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተሽሎት ወደ ስራ እንደማይመለስ በመገለጹ፤ ከሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ይልቅ የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራላቸው ለጽ/ቤቱ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምንም ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል።

እንደደንቡ ከሆነ የህወሃት ምክትል ሊቀመንበር የሆነው አባይ ወልዱ ስብሰባውን ጠርቶ፤ በጉዳዩ ላይ ከአባላት ጋር መምከር እንደነበረበት ተገልጿል። ሆኖም ተራ አባላት የስብሰባውን መጠራት ሲጠይቁ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የህወሃት ከፍተኛ ባለስልጣናትና የደህንነት ሚንስትሩ “ለአገር ደህንነትና ጸጥታ” በሚል ምክንያት በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ዙሪያ በሚደረጉ ወይም በሚጠሩ ስብሰባዎች ዙሪያ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ላይ ናቸው። በዚህም ምክንያት የህወሃት፣ ኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ኢደህዴን ድርጅቶች በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ጋር በተገናኙ አጀንዳዎች ዙሪያ ስብሰባ እንዳያደርጉ የውስጥ መመሪያ ተሰጥቷል።

ይህም ሆኖ ግን የህወሃት አባላት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራላቸው እና የሊቀ መንበራቸው የጤና ሁኔታ እንዲብራራ እና በሞት የሚለይ ከሆነ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለመምከር ጥሪ አቅርበዋል። ይህ አይነቱ ስብሰባ ከተጠራ ከመለስ ዜናዊ የጤና ሁኔታ አልፎ የአዜብ መስፍን ጉዳይ እንዳይነሳ ስጋት አለ። አዜብ መስፍን፡ በአገር ውስጥ የደህንነት ሚንስትር በጌታቸው አሰፋ ትዕዛዝ፤ ባለቤቷን ለማስታመም ጭምር ከአገር እንዳትወጣ ተደርጋለች። ሴትዮዋ በህወሃት አስረኛ ጉባዔ ወቅት፤ ከሁለት አመት በፊት በሙሉ ድምጽ ለስራ አስፈጻሚነት ቢመርጧትም፤ በሂደት ግን በትግራይ ህዝብ ዘንድ ብዙም ተወዳጅነት ስለሌላት በስብሰባው አመራር ሆና መቅረብ ቀርቶ፤ በስብሰባው ላይ ብትገኝ ሊደርስ የሚችል ተቃውሞ እንደሚኖር ስጋት አለ።

በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ የኮሚዩኒኬሽን እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚንስትር፣ ተብሎ በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር የተሾመው የህወሃት ከፍተኛ አባል ደብረጽዮን ገብረሚካዔል ከአዜብ መስፍን ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሰዎችን እንቅስቃሴ በመሰለል ስራ ላይ መሰማራቱ ታውቋል። ደብረጽዮን ገብረሚካዔል፡ ዋና ስራው የኢህአዴግ ተቃዋሚ የሆኑ ድረ ገጾችን፣ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የማገድ ተግባር መፈጸም ሲሆን፤ የግለሰቦችን ኮምፒዩተር እና የስልክ ል ውጦችን መጥለፍ ተጨማሪ የሚንስትርነት ስራው ነው። ደብረጽዮን የሚሰልለው በህዝቡ ዘንድ ያሉትን የኢንተርኔት ግንኙነት ብቻ ሳይሆን፤ ለባለልጣናት የሚሰጡ ኮምፒዩተሮች ጭምር በግለሰቡ ቢሮ የሚስጥር እይታ ውስጥ በመሆናቸው ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጭምር በመሰለል፤ የሚያስፈራራና እርምጃ የሚያስወስድ ግለሰብ ነው።
አሁን ጫና እየተፈጠረ ያለው በቀድሞ አመራር አባላት ላይ ሆኗል። ስዩም መስፍን፣ ስብሃት ነጋ፣ አርከበ ዕቑባይ፣ አባይ ጸሃዬ ራሳቸውን ከዋና ስራ አስፈጻሚነት ያገለሉ ሰዎች ቢሆኑም፤ በጊዜያዊነት የመለስን ቦታ በመያዝ አመራር እንዲሰጡ እየተጠየቁ ነው። ሌላው ላለፉት ስድስት አመታት የክልሉ ፕሬዘዳንት የነበረው ጸጋይ በርኼ፤ በትግራይ ውስጥ የራሱን መዋቅር ዘርግቶ ስለነበር እንደጠንካራ መሪ የሚያዩት እና ብሎም በመለስ ዜናዊ ስልጣን ሊተካ እንደሚችል የሚገምቱ ሰዎች አሉ።
ጸጋይ በርኼ፡ (ሓለቃ ጸጋይ የሚሉትም አሉ)።የስብሃት ነጋን እህት ቅዱሳን ነጋ በማግባት ህወሃታዊ የጋብቻ ትሥሥር አድርጓል። በቀድሞው የክልሉ ፕሬዘዳንት አቶ ገብሩ አስራት ላይ የሰደደ ጥላቻ አለው። አቶ ገብሩ አስራት – ከመለስ ዜናዊ ጋር ተጣልቶ ከድርጅቱ ከተባረረ በኋላ፤ የትግራይ ክልል ፕሬዘዳንትነት ስልጣኑን የወሰደው ጸጋይ በርኼ ሲሆን፤ እነ ገብሩ አስራት ከቀድሞ መኖሪያቸው እንዲባረሩ እና እንዲሳደዱ አድርጓል። ግለሰቡ በአማርኛም ሆነ በትግርኛ ሲናገር ሃሳቡን ሰብሰብ አድርጎ መናገር አይችልም። እንደሌሎቹ የማሳመን ችሎታ የሌለውና ሁልጊዜም ካሸነፈው ወገን ጋር የሚሸሸጎጥ፤ በራሱ የማይተማመን ሰው በመሆኑ በታጋዩ ዘንድ የጎላ ተወዳጅነት የለውም። ለህወሃት ታማኝ ቢሆንም፤ መለስን የመተካትም ሆነ፤ ድርጅቱን ወደፊት የመምራት እድል እንደሌለው የሚገልጹት ሰዎች ያመዝናሉ።

ከዚህ ውጪ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ቴዎድሮስ ሃጎስ፣ አባዲ ዘሙ እና በየነ ምትኩ የህወሃት የበላይ አመራር እንደመሆናቸው መጠን መለስ ዜናዊን የመተካት እድል እንዳላቸው በውጭ ደረጃ የሚነገረውን ተንታኞች በተለያየ ምክንያት ውድቅ ያደርጉታል። ለምሳሌ ቴዎድሮስ አድሃኖ በግማሽ ኤርትራዊ መሆኑ፤ ቴድሮስ ሃጎስ እና በየነ ምትኩ የፖለቲካ እና የትምህርት ብቃት የሌላቸው መሆኑ እንደመሰናክል ይገለጻል። በየነ ምክሩ፡ በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንት ነው። በአስረኛው የህወሃት ጉባዔ ወቅት አርከበ እቑባይ ለስራ አስፈጻሚነት ሲመረጥ፤ ቦታውን ባለመፈለጉ ምክንያት በየነ ምክሩ እንደሟሟያ ሆኖ የገባ ሰው ነው። የክልሉ ምክትል ፕሬዘዳንት ይሁን እንጂ፤ ከትግራይ ክልል ፖሊስ ጋር በቅርብ እየሰራ ይገኛል። በህወሃት ውስጥ መሪ ለመሆን የሚያስችል ድጋፍም ሆነ ብቃት የለውም። ከነዚህ ትንታኔዎችእና ግምገማዎች በኋላ ግን ከበላይ አመራር አባላት መካከል የአንድ ሰው ስም ለብቻው እየወጣ ይገኛል – አባይ ወልዱ።

አባይ ወልዱ፡ ከቀድሞ ታጋዮች መካከል አንደኛው ነው። በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልል ፕሬዘዳንት እና የህወሃት ምክትል ሊቀመንበር እንደመሆኑ መጠን፤ መለስ ዜናዊ ከሞተ በቀጥታ የሚተካው ሰው ይሆናል። ግለሰቡ በሙስና ውስጥ ብዙም እንዳልተዘፈቀ ይነገራል። በዚህም ምክንያት ሃብት ካካበቱ የህወሃት ሰዎች ጋር ብዙም ወዳጅ አይደለም። ግለሰቡ ጥሩ የመናገር ችሎታ ያለው፤ በህዝብ አስተዳደር እና ጦር አመራር ውስጥ የተሳተፈ፤ በኢሮብ እና በአፋር አካባቢ ያሉ ሰዎች ይወዱታል። በአፅቢ ዳራ ታጋይ ሆኖ በመቆየቱ፤ በትግል ስሙ አባይ ዳራ ብለው ይጠሩታል። ባለቤቱ ትሩፋት ኪዳነማርያም በማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ የምትሰራ ሲሆን፤ የደህንነት ሰራተኛ እንደሆነች ይነገራል።
አባይ ወልዱ ከሚታወቅበት ነገር አንዱ ከሁሉም የህወሃት አባላት ጋር ተግባብቶ ለመስራት በሚያደርገው ጥረት ነው። በመሆኑም መለስ ዜናዊ ከተወገደ፤ በመለስ ዜናዊ ምክንያት ከድርጅቱ ከወጡት… ከነስዬ አብርሃ፣ ገብሩ አስራት፣ አረጋሽ አዳነ፣ ተወልደ ወልደማርያም፣ አለምሰገድ ገብረአምላክ ጋር እንደገና ለመነጋገር እና ለመደራደር ወደኋላ የማይል በመሆኑ ሌሎች የህወሃት ሰዎች በአይነ ቁራኛ የሚያዩት ሰው ነው። በዚህ ምክንያት ወደስልጣን ጫፍ ላይ እንዳይወጣ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። የግለሰቡ ችግር… ከትልቋ የኢትዮጵያ ጥቅም ይልቅ የህወሃትን ጥቅም የሚያስቀድም መሆኑ ነው። በቅርብ የሚያውቁት የህወሃት ሰዎች እንደገለጹልን ከሆነ፤ “አባይ ወልዱ ሶስት ነፍስ ቢኖረው፤ ሶስቱንም ህይወቱን ህወሃትን ለማዳን ይጠቀምበታል እንጂ፤ ኢትዮጵያን ለማዳን የሚያጠፋው ትርፍ ህይወት አይኖረውም።” ይህ ትልቅ ችግሩ ነው።

የሰሞኑ የህወሃት እና የበላይ አመራሩ ውሎ፤ እኛም ከቅርብ ሰዎች ጋር ተነጋግረን ያጠናቀርነው ዘገባ ይኸው ነበር።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on July 30, 2012
  • By:
  • Last Modified: July 30, 2012 @ 6:17 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar