www.maledatimes.com አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ — የ50 አመታት ድንቅ የዲፕሎማቲክ ስራ አለማቀፋዊ ስኬት http://minilik-salsawi.blogspot.com/2013/09/50.html - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ — የ50 አመታት ድንቅ የዲፕሎማቲክ ስራ አለማቀፋዊ ስኬት http://minilik-salsawi.blogspot.com/2013/09/50.html

By   /   September 20, 2013  /   Comments Off on አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ — የ50 አመታት ድንቅ የዲፕሎማቲክ ስራ አለማቀፋዊ ስኬት http://minilik-salsawi.blogspot.com/2013/09/50.html

    Print       Email
0 0
Read Time:29 Minute, 51 Second

‹‹ትናንት መስከረም 2 ቀን 2006 ዓ.ም. ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተቀጠርኩ 51 ዓመት ሞላኝ፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ አበባ ሲመሠረት የአንድ ዓመት የሥራ ልምድ የነበረኝ ወጣት ዲፕሎማት ነበርኩ፡፡
እ.ኤ.አ. ከግንቦት 22 እስከ 25 1963 በተካሄደው የመጀመርያው የነፃ አገሮች መሪዎችና መንግሥታት ስብሰባ ላይ ተካፋይ ነበርኩ፡፡ ሰላሳ ሁለቱ መሥራች አባቶች የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተርን ሲፈርሙ ታድሜያለሁ፡፡ በአዳራሹ የነበረውን ስሜት በግልጽ አሁንም አስታውሰዋለሁ፡፡ ተሳታፊዎቹ የነበራቸውን ደስታና የተስፈኝነት ስሜት ባሳያችሁ ደስ ይለኝ ነበር፡፡››
ይህን የተናገሩት አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ ሲሆኑ፣ ታዳሚዎቻቸው ደግሞ በአብዛኛው ከዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ከተለያዩ ኤምባሲዎች፣ የጥናትና ምርምር ተቋማት የተጋበዙ እንግዶችና የስብሰባውን አዘጋጅ ጨምሮ በተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ትምህርት እየተከታተሉ ያሉ ወጣቶች ነበሩ፡፡ በዕለተ ዓርብ መስከረም 3 ቀን 2006 ዓ.ም. ከ11 ሰዓት ጀምሮ በጎተ ኢንስቲትዩት አዳራሽ በተካሄደው ስብሰባ በአፍሪካ ኅብረትና በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይና የአፍሪካ ኅብረት ቋሚ ተወካዮች ሰብሳቢ የሆኑት አምባሳደር ቆንጂት፣ “OAU-AU 50 Year Anniversary: Origins, Achievements, Limitations and Future Role” በሚል ርዕስ ለውይይት መነሻ የሆነ ጽሑፍም አቅርበው ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ሚና
አምባሳደር ቆንጂት በአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራች ጉባዔ ላይ ከተበተኑት የመሪዎች ንግግሮች ውሰጥ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን፣ የቱኒዚያውን ቤን ቤላንና የታንዛኒያውን ጁሊየስ ኔሬሬን ንግግሮች በከፊል ያነበቡ ሲሆን፣ ለአኅጉራዊው ድርጅት ስኬት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና የቅርብ አለቃቸውና በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ከተማ ይፍሩ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በካዛብላንካና በሞንሮቪያ ቡድኖች መካከል የነበረውን ሰፊ ልዩነት ነፃ ሆና በማስታረቋ ብቻ ሳይሆን፣ አኅጉራዊው ድርጅት የተቋቋመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጓንም አምባሳደር ቆንጂት አስታውሰዋል፡፡ የካዛብላንካ ቡድን እንደ አልጄሪያ፣ ግብፅ፣ ጋናና ሞሮኮ ያሉ አገሮችን ያቀፈና የአፍሪካ ውህደት በፍጥነት እንዲመጣ ይፈልግ የነበረ ቡድን ሲሆን፣ የሞንሮቪያ ቡድን በተቃራኒ እንደ ናይጄሪያና ላይቤሪያ ያሉ አገሮችን ያቀፈ የውህደቱ ጥያቄ በሒደት መምጣት አለበት የሚል ለዘብተኛ ቡድን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አስታራቂነት ሊሳካ የቻለው የሁለቱም ቡድን አባል ባለመሆኗ መሆኑን አምባሳደር ቆንጂት ጠቁመዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ከግንቦት 2005 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 2006 ዓ.ም. ያለው አንድ ዓመት በሙሉ በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች እንደሚከበር በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ድላሚኒ ዙማ ከተገለጸ ወራት ቢያስቆጥሩም፣ በኅብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ ከዚህ የበዓል ስሜትና መንፈስ ጋር የተገናኘ ዝግጅት አልተደረገም፡፡ አምባሳደር ቆንጂት ይህን ስሜት ለመፍጠርና የኅብረቱ አጀንዳ የዜጎች አጀንዳና ትኩረት እንዲሆን ለማድረግ ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና ልትጫወት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ በትምህርት ተቋማት የሚደረጉ መሰል የውይይት መድረኮችም ከዚህ አኳያ ሊበረታቱ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
ያልተሳካ ኅብረት?
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት 25ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ሲያከብር አቶ አማረ ተክሌ “The Organization of African Unity at Twenty Five Years: Retrospect acd Prospect” በተሰኘ ሥራቸው ድርጅቱ ለአፍሪካ ሸክም እንደሆነና ለአኅጉሪቱ የውርደት መገለጫ ተደርጎ በብዙዎች እንደሚቆጠር ገልጸው ነበር፡፡ ‹‹ድርጅቱ ሁልጊዜም በደረሱና በሚታሰቡ ውድቀቶች፣ ስህተቶችና ድክመቶች ይተቻል፡፡ ዛሬ ድርጅቱ በከባድ የራስ መተማመን ቀውስ፣ በተዓማኒነትና በተፈላጊነቱ ላይ ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ በአንዳንድ ወገኖች የድርጅቱ ሚና ፍትሐዊ ላልሆኑና ሙሰኛ ለሆኑ መንግሥታት ዕውቅና ከመስጠት ያልዘለለ እንደሆነም ይታመናል፤›› ሲሉም አቶ አማረ ያክላሉ፡፡
ከላይ የገለጸውን ዓይነት ትችትና ወቀሳ የአፍሪካ ኅብረት 50ኛ ዓመቱን ሲያከብር መጠኑን ጨምሮ ካልሆነ አሁንም እየቀረበ ይገኛል፡፡ አምባሳደር ቆንጂት ግን ትችቶቹና ወቀሳዎቹ ድርጅቱ የተቋቋመበትን ዓላማ በብዛት ያገናዘቡ እንዳልሆኑ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አምስት ዋነኛ ዓላማዎች ነው የነበሩት፡፡ አንደኛው የአንድነትና የወንድምነት ስሜትን መፍጠር ነው፡፡ ሁለተኛው አኅጉራዊ የትብብር ሥርዓትን ማደራጀት ነው፡፡ ሦስተኛው የአባል አገሮችን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እንዲሁም ነፃነት መጠበቅ ነው፡፡ አራተኛው ቅኝ ግዛትን ማስወገድ ነው፡፡ አምስተኛው ደግሞ ዓለም አቀፍ ትብብር መፍጠር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ዋነኛ ዓላማው የሆነውን የነፃነትን ጥያቄ በሚገባ አሳክቷል፡፡ በአኅጉራዊ መድረክነቱም የአባል አገሮችን የጋራ አጀንዳና ትብብር ለማሳካት በርካታ ስኬታማ ሥራዎችን አሳክቷል፤›› ይላሉ፡፡
በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አፍሪካ አዳራሽ ውስጥ የሚገኘው በወንድማማቾቹ አሰፋና የማነ ሰርቀብርሃን የተሳለው የመሥራች አባቶች ሥዕል መካከል አንዱ ባዶ ነው፡፡ አምባሳደር ቆንጂት ባዶው ቦታ ላይ ሊቀመጥ የሚገባው ሥዕል የቶጎ መሪ ቢሆንም፣ አገሪቱ በስብሰባው ሰሞን መፈንቅለ መንግሥት ተፈጽሞባት ስለነበር ከምሥረታው ሒደት ውጪ መደረጓን ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹የአኅጉሩ መሪ ድርጅት ሰላምና መረጋጋትን ከማስፈን፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና ውህደት ከመፍጠር፣ መልካም አስተዳደር ከማስፈንና ሙስናን ከመዋጋት፣ መፈንቅለ መንግሥትንና የአንድ ሰውን አመራር ከማስወገድ፣ በአገሮች መካከል የሚደረግ ጦርነትንና የእርስ በርስ ጦርነትን ከማስቀረት፣ የኢኮኖሚ መላሸቅንና የብድር ጫናን ከማስወገድ፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ተፅዕኖ ሥር እንዳይወድቅ ከመከላከል አኳያ መጠነ ሰፊ ተግዳሮቶች እንደነበሩበት ግልጽ ነው፡፡ ይሁንና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት ሠራተኞች ባለፉት አምስት አሥርት ዓመታት ነገሮችን ለመቀየር እንዴት ጠንክረው እንደሠሩና ለውጡ አዝጋሚ ቢሆንም ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት እንዳደረጉ ልነግራችሁ እወዳለሁ፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሉት እንደነበረው ‹‹አፍሪካ እየተነሳች ነው›› ዛሬ፡፡ በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው ዘርፍ በርካታ መሻሻሎች አሉ፤›› ብለዋል
የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን እንዲተካው የተደረገው አንዳንድ ድክመቶቹን ከግምት ውስጥ አስገብቶ እንደነበርም አምባሳደር ቆንጂት ያስረዳሉ፡፡ ‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሚፈጽሙ አገሮች የውስጥ ጉዳይ አይገባም ነበር፡፡ ሰፊ የተሳትፎ መሠረት ያልነበረውና የልሂቃኑን ሚና አግዝፎ የሚያይ ነበር፡፡ ይህን ለማረም የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሚፈጽሙ አገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ሊገባ የሚችልበት የሕግ መሠረት ተቀርጿል፡፡ እርግጥ በተግባር ላይ እስካሁን አልዋለም፡፡ በሊቢያ የደረሰውን ሁሉም ያውቀዋል፡፡ ኅብረቱ ከስህተቱ የተማረ በመሆኑ መሰል ችግሮች ዳግም አይፈጠሩም፡፡ ሕዝባዊ ተሳትፎም የኅብረቱ አንዱ ዋነኛ መርህ ሆኗል፡፡ ኅብረቱ ከልሂቃን ሚና ይልቅ ተቋማዊ አደረጃጀቱ ላይ እንዲቆምም ተደርጓል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
አፍሪካ ኅብረት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ለውጥ ዘላቂነት ላይ የሚያተኩሩ እንደ ኔፓድና የአፍሪካ የአቻ ለአቻ ግምገማ ፕሮግራሞችን መቅረፁም ለአምባሳደር ቆንጂት እንደ ስኬት የሚቆጠር ነው፡፡ ሰላምና መረጋጋትን በአፍሪካ አውድ ለማምጣትም በተቀየረው የአፍሪካ የሰላምና ደኅንነት ‹‹አርክቴክቸር›› ሥር ያሉት የሰላምና ደኅንነት ካውንስል፣ የአፍሪካ በተጠንቀቅ የቆመ ኃይል፣ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት፣ የሽማግሌዎች ቡድንና የሰላም ፈንድ ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት ላይ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡ በአኅጉሪቱ የሚገኙት ስምንት አካባቢያዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦችም ከነችግራቸው አዎንታዊ ለውጥ እያመጡ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በተለይ በአፍሪካ ኅብረት የሚመሩ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮዎች ውጤታማ መሆን፣ በአጠቃላይ በአፍሪካ የግጭት ቁጥር መቀነስ፣ የኔፓድ ውጤታማ ሥራ፣ አፍሪካ በአንድ ድምፅ መናገር መጀመሯ፣ ከቀረው ዓለም ጋር የተጠናከረ የሁለትዮሽ ግንኙነት በመፍጠር፣ በተለይ ከቻይና፣ ከህንድ፣ ከኮሪያና ከቱርክ ጋር የተፈጠረው ጠንካራ ግንኙነት፣ የአፍሪካ መንግሥታት ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ያላቸው ቁርጠኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩ የመጪውን ጊዜ ተስፋ ከተግዳሮቶቹ በላይ እንዲያዩት እንዳደረጋቸው አምባሳደር ቆንጂት አስገንዝበዋል፡፡
ድኅረ ጋዳፊ አፍሪካ ኅብረት
አምባሳደር ቆንጂት አገራቸውን በዲፕሎማትነት ባገለገሉባት 51 ዓመታት ትልቁ ፈተና ከቀድሞው የሊቢያ ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊ ጋር አብሮ መሥራት እንደነበር የገለጹበት መንገድ ብዙዎቹን ተሳታፊዎች ፈገግ ያሰኘ ነበር፡፡ ‹‹አሁን ሥራ ሲሰጠኝ ተግባሬ ሥራውን በጊዜ ማጠናቀቅ ብቻ ነው፡፡ ጋዳፊ እያለ ሥራዬን ከጨረስኩ በኋላ ያለኝ ሌላው ጭንቀት ጋዳፊ ሥራውን እንዳያበላሸው እንዴት መከላከል ይቻላል የሚል ነበር፡፡››
ጋዳፊ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት እንዲቀየር ከፍተኛ ተነሳሽነት እንደነበራቸው ያስታወሱት አምባሳደር ቆንጂት፣ ይህ ማለት ግን ከግለሰባዊ የሥልጣን ፍላጎት የዘለለ እውነተኛ አፍሪካዊ ስሜት ነበራቸው ማለት እንዳልሆነ አስገንዝበዋል፡፡ በሎከርቢው የአውሮፕላን አደጋ የተነሳ ሊቢያ ላይ ተጥሎ የነበረው ጫና እንዲነሳ ከዓረብ ሊግ አስቀድሞ አፍሪካ ኅብረት በመጠየቁ ደስተኛ የሆኑት ጋዳፊ፣ ዓረቦችን አኩርፈው የአፍሪካውያንን አንድነት ማቀንቀን መጀመራቸውን አምባሳደር ቆንጂት ያስረዳሉ፡፡
‹‹የአፍሪካ ኅብረት ገና ሲመሠረት መቀመጫው ወደ ትሪፖሊ መሄድ አለበት አሉ፡፡ ቻርተሩ ሲፀድቅም ስለ ዋና መቀመጫ የሚያወሳው አንቀጽ 24 እንዳይፀድቅ በእጅ አዙርም ቢሆን ተፅዕኖ ያሳደሩት ጋዳፊ ነበሩ፡፡ ቻርተሩ ከፀደቀም በኋላ በየዓመቱ ቢያንስ አንድ የማሻሻያ ሐሳብ ይዘው ይቀርቡ ነበር፡፡ ለማሻሻያ ሐሳቡ ድጋፍና ድምፅ የሚሰጡ አገሮችን በገንዘብ ለመግዛት ያላደረጉት ጥረት የለም፡፡ ደግነቱ ማሻሻያ ሐሳቦቹ በ2/3ኛ ድምፅ ድጋፍ መፅደቅ ስለነበረባቸው ያን ያህል ድምፅ መግዛት አልቻሉም፡፡ ነገር ግን በማሻሻያ ሐሳቦቹ ላይ ይደረጉ የነበሩ ውይይቶችና አንዳንድ ጭቅጭቆች የኅብረቱን ውድ የሥራ ጊዜያት አባክነዋል፡፡ አሁን ያ ችግር የለም፡፡ ከጋዳፊ ሞት በኋላ የአፍሪካ ኅብረት በሚገባ እየሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡
አፍሪካ ኅብረትና መጪው ጊዜ
ብሩህ መጪ ጊዜን ለማረጋገጥ ኅብረቱ በዋነኛነት በገንዘብ ራሱን ሊችል፣ ተቋማዊ አቅሙን ሊያዳብር፣ የሰላምና የፀጥታ ተግዳሮቶችን በሚገባ ሊወጣ፣ በአባል አገሮቹ መካከል በተለያዩ ምክንያቶች ያሉትን የመከፋፈል አደጋዎች ሊያስወግድ፣ በአካባቢያዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦች መካከል ያለውን ተደራራቢ አባልነትን ሊያስወግድ፣ ደካማውን ኢኮኖሚያዊና የመሠረተ ልማት ውህደት ማጠናከር የሚገባው መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደር ቆንጂት፣ ወጣቱ ትውልድ ሰላማዊ፣ የበለፀገችና የተባበረች አፍሪካን ለማረጋገጥ የተሻለ ጊዜ ላይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
‹‹51 ዓመታት በሠራሁት ሥራና ለአገሬ ብሎም ለአኅጉሩ ባደረግኩት አስተዋጽኦ እኮራለሁ፡፡ የግል ሕይወቴንና የቤተሰቦቼን ፍላጎት መስዋዕት አድርጌ ነው በሥራው ላይ ይኼን ያህል ዓመታት የቆየሁት፡፡ የጎደሉ ነገሮች ነገ ይሞላሉ፡፡ እኔ በቅርቡ ጡረታ እወጣለሁ፡፡ ወደ ኋላ ተመልሼ ሥራዎቼን ሳያቸው እርካታ ነው የሚሰማኝ እንጂ ፀፀት የለኝም፡፡ ሁሉም አፍሪካዊ የኅብረቱን ሥራ ለማገዝና ለመለወጥ ሚና እንዳለው ሊገነዘብ ይገባል፡፡ እዚህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ተመራማሪዎች አላችሁ፡፡ የኅብረቱን ሥራ የሚያቃኑ በርካታ የምርምር ሥራዎች መሥራት ትችላላችሁ፡፡ ከእኔ የምትፈልጉት ዕርዳታ ካለ ቢሮዬ ምንጊዜም ክፍት ነው፡፡ እባካችሁ ባገኛችሁት አጋጣሚ አፍሪካ ኅብረትን አጀንዳ አድርጉት፤›› የሚለው የአምባሳደር ቆንጂት ምክር ነበር፡፡
‹‹ከጋዳፊ ሞት በኋላ አፍሪካ ኅብረት በሚገባ እየሠራ ነው›› አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስአምባሳደር ቆንጂት በውይይት መድረኩ ላይ በርካታ ጥያቄዎች የቀረቡላቸው ሲሆን፣ ኅብረቱ ራሱን በገንዘብ ሊችል የሚችልበት መንገድን በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ኅብረቱ ከአባላት የሚያገኘው ገቢ በመጨመሩ አሁን 50 በመቶ ራሱን መቻሉን ጠቅሰው፣ ድርሻውን ለመጨመር ኮሚቴ ተቋቁሞ የተለያዩ የገቢ መሰብሰቢያ ፕሮግራሞች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከብራዚል ኤምባሲ ተወክሎ ስብሰባው ላይ የተገኘ አንድ ወጣት አፍሪካ ከላቲን አሜሪካ ጋር ያላት የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዴት ስኬታማ ሊሆን እንዳልቻለ ላቀረበው ጥያቄ፣ አምባሳደር ቆንጂት የግንኙነት ክፍተትና ቸልተኝነት በላቲን አሜሪካ ዘንድ መስተዋሉን ገልጸው ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
አንድ ጠያቂ አፍሪካ ኅብረትን ከፍሪካ አንድነት ድርጅት ጋር ከማነፃፀር ለምን ከአውሮፓ ኅብረት ጋር እንደማይነፃፀር ለቀረበው ጥያቄ፣ አምባሳደር ቆንጂት በሰጡት መልስ ሁለቱ ተቋማት ካላቸው የታሪክ፣ የፖለቲካና የስኬት ተሞክሮ አኳያ ለንፅፅር ለማቅረብ እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡
ሕዝባዊ ተሳትፎን በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄም፣ ኅብረቱ ራሱን ለሕዝባዊ ተሳትፎ ክፍት በማድረግ ተወዳዳሪ የሌለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተደራራቢ የአካባቢ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ አባልነትም ከውጤታማነትና ከታማኝነት አኳያ ትልቅ ችግር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የዲሞክራሲ ግንባታን በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄ በሒደት ዘላቂ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በአፍሪካ ለመገንባት እየተሠራ ያለው ሥራ አበረታች መሆኑን ጠቁመው፣ መጪው 50 ዓመት ካለፈው 50 ዓመት ፈጽሞ የተለየ እንደሚሆንም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2014 እስከ 2017 የሚቆየው የኅብረቱ ስትራቴጂካዊ ዕቅድና አጀንዳ 2063 የተሰኘው የአፍሪካ ኅብረት ታላቁ ራዕይ ዲሞክራሲ የተረጋገጠባትና ኢኮኖሚው በተፋጠነ ሁኔታ የሚያድግባት አፍሪካን እንደሚፈጥርም ተስፋ አድርገዋል፡፡
http://minilik-salsawi.blogspot.com/2013/09/50.html

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on September 20, 2013
  • By:
  • Last Modified: November 6, 2013 @ 7:48 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar