www.maledatimes.com የኢትዮ ምህዳር ጋዜጠኞች ለመጪው ረቡዕ ተጠሩ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የኢትዮ ምህዳር ጋዜጠኞች ለመጪው ረቡዕ ተጠሩ

By   /   October 23, 2013  /   Comments Off on የኢትዮ ምህዳር ጋዜጠኞች ለመጪው ረቡዕ ተጠሩ

    Print       Email
0 0
Read Time:9 Minute, 37 Second
 
በዘሪሁን ሙሉጌታ
ከሀገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱና አንጋፋ የሆነው የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ላይ የ300 ሺህ ብር የስም ማጥፋት ክስ ከመሠረተ በኋላ ባለፈው ሰኞ ፍ/ቤት የቀረቡት የኢትዮ ምህዳር ጋዜጠኞችና ባለቤቶች ለመጪው ረቡዕ ተቀጠሩ። ዩኒቨርሲቲው የጋዜጣው ዘገባ መልካም ስሙና ዝናው መጉደፉን አመልክቶ ጋዜጣው በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የተሰጠው ፈቃድ እንዲሰረዝም ጠይቋል።
ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በክስ መዝገብ ቁጥር U.R/02/0839/06 መስከረም 15 ቀን 2006 ዓ.ም ባቀረበው የፍትሐብሔር ክስ ላይ ሰኔ 19 ቀን 2005 ዓ.ም በጋዜጣ ቁጥር 24 በገፅ 1 እና 10 ላይ የወጣው ዘገባ የዩኒቨርሲቲውን መልካም ስምና ዝና የሚያጠፋ በመሆኑ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነትን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ 590/2000 መሠረት ክሱን መስርቷል።
በጋዜጣው ላይ የቀረበው ክስ ሰኔ 19 ቀን 2005 ዓ.ም ‘‘የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት አባል በሙስና ወንጀል እጅ ከፍንጅ ተያዙ’’ በማለት በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከፍተኛ የማኔጅመንት አባልና ባልደረባቸው ገንዘብ ሲቀባበሉ በፀረ-ሙስና ኮሚሽን እና በብሔራዊ ደህንነት እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን መግለፁ፤ እንዲሁም በኮሌጁ ውስጥ ብልሹ አሰራር እንዳለ እና ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን የብቃት ማረጋገጫ (ሲ.ኦ.ሲ) ያልተፈተኑ የጤና ባለሙያዎች ተቀጥረው እየሰሩ በመሆናቸው ይህ ብልሹ አሰራር እንዲወገድ ማለቱ፣ በተጨማሪም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዋጅ ላይም ሆነ በዩኒቨርሲቲው ሴኔት ሌጅስሌሽን የበላይ ኃላፊዎች እንጂ የማኔጅመንት አባላት የሌሉ ቢሆንም የማኔጅመንት አባላት እንዳሉ በማስመሰል የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችን ስምና ዝና አጥፍቷል። ያለ ዩኒቨርሲቲው ፈቃድ የዩኒቨርሲቲውን ሎጎ ወይም መለያ ምልክት አውጥተዋል። በዩኒቨርሲቲው የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያልተፈፀመን ህገ-ወጥ ቅጥር እንደተፈፀመ አድርገዋል የተሳሳተ ዘገባ አትመዋል። ይህንንም እንዲያስተካክሉ ተጠይቀው ለማረም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ክሱ መቅረቡን አትቷል።
ተከሳሾቹ በፈፀሙት ድርጊት በአዋጅ ቁጥር 590/200 የተከሳሾችን ተጠያቂነት በሚመለከት በአንቀፅ 41 እና በተከታዩ ቁጥሮች የመገናኛ ብዙኃኑ ድርጅት ከ2ኛና 3ኛ ተከሳሾች ጋር በተደራራቢነት የሚከሰስ በመሆኑና በመገናኛ ብዙኃኑ አማካኝነት ለሚደርስ ስም ማጥፋት ጉዳት እያንዳንዳቸው እስከ 100,000.00 (አንድ መቶ ሺህ) ብር የሕሊና ጉዳት ካሳ ሊያስወስን ስለሚችል የጋዜጣው ተቋም፣ ስራ አስኪያጁና ዋና አዘጋጁ እያንዳንዳቸው መቶ ሺህ በድምሩ 300 ሺህ የሞራል ካሳ እንዲከፍሉኝ ሲል ዩኒቨርሲቲው ክስ አቅርቧል።
በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ተከሳሾች የሞራል ካሳ እንዲከፍሉ ከተወሰነባቸው በኋላ ያወጡት የተሳሳተ ዘገባ በማረም ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ሲል በክስ አቤቱታው ላይ ጨምሮ አመልክቷል።
የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ እና የሁለንታ ህትመትና ማስታወቂያ ኃ.የተ.የግ.ማህበር ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ሚሊዮን ደግነው በቀረበባቸው ክስ መሠረት ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2006 ዓ.ም ሐዋሳ በመሄድ ፍ/ቤት በመቅረብ  በጠበቃቸው በአቶ ተማም አባቡልጉ በኩል ተፅፎ የቀረበውን መቃወሚያቸውን አሰምተዋል።
ተከሳሾቹም ባቀረቡት ምላሽ የጣሱት ህግ አለመኖሩና ስም ጠቅሰው ያጎደፉት ስምና ዝና እንደሌለ አመልክተዋል። በተጨማሪም የስም ማጥፋቱ ነገር ተፈፀመበት ባሉት ተመሳሳይ ጋዜጣ ላይ እርማት እንዲወጣላቸው በጠየቁት መሠረት በጋዜጣው ቅፅ ቁጥር 27 ረቡዕ ሐምሌ 10 ቀን 2005 እትም ላይ ማረሚያው መውጣቱን በዚህም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2049 ኃላፊነታቸው መወገዱን እንዲሁም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 33(3) እና 244(2)(L) መሠረት ማረሚያው ከወጣ በኋላ ይህንን ክስ ማቅረብ እንደማይችሉ ጠቅሰው መቃወሚያቸውን አሰምተዋል።
በተጨማሪም ለክሱ መነሻ የሆነው ጉዳይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚታተም የንግድ ድርጅት በሆነና በፌዴራሉ መንግስት ስር በተመዘገበ ጋዜጣ የተፈፀመ ስለሆነ ይህንን ጉዳይ አይቶ የመወሰን ሥልጣን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 22(2) እና በአዋጅ 25/88 መሠረት የፌዴራሉ ፍ/ቤት በመሆኑ የሐዋሳ ከፍተኛ ፍ/ቤት ክሱን የማየት ስልጣን እንደሌለውም ጠቅሰው ተከራክረዋል።
ችሎቱም ጉዳዩን ከተመለከተ በኋላ ፍ/ቤቱ ስልጣን አለው፣ የለውም የሚለውን ጉዳይ ለማየ ለጥቅምት 20 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት የሰኞ ዕለት ውሎውን አጠናቋል።
ኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ በሁለንታ ህትመት እና ማስታወቂያ ኃ.የተ.የተ.የግል. ማህበር በየሳምንቱ ማክሰኞ ለንባብ የምትበቃ ጋዜጣ ስትሆን ከተመሰረተች አንድ አመት አስቆጥራች። የጋዜጣዋ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ጋዜጣዋ ከተመሰረተች በኋላ ይህ ክስ ሲቀርብበት ለሁለተኛ ጊዜ ነው።n

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on October 23, 2013
  • By:
  • Last Modified: October 23, 2013 @ 9:54 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar