www.maledatimes.com ባላገሯ በአሜሪካ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  LINKS  >  ባላገሯ በአሜሪካ

ባላገሯ በአሜሪካ

“ኦርጋኒኬን” ይደረስ ለትነበብ እስከዚያ እንደምን ሰነበትሽ? ሙሊያው ሸጋ ነው ባልንጀራዬ? ክረምቱ እንዴት ነው በይ?! መሬቱስ ዘር ሰጠ ምነ?! እመ በስልክ እንዳወጋችኝ “ክረምቱ ከባድ ነው፣ ለገበያም አላመቼ… ምንሜናስ ምንሜናስ” ብላኛለች፡፡ ይሁን እስቲ… ጫን ያለው እንዳይመጣ ከጌታ መማከር ነው ጎኔ!! “ጎኔ” ስልሽ ምን ፍክ አለኝ፡፡ ሙት ወቃሽ አያርገኝና የታታ እናት – ቅድመ አይትሽ ፍክ ይሉሻል፡፡ “ጎኔ፣ ጎኔ፣ ጎኔ…. ዶቅዬውን ፈትል ኩታ ንሽማ ስጭኝ፤ “ጎኔ፣ ጎኔ፣ ጎኔ…. ከማድጋው ጥሩ ውሃ አቀብይኝ” ሲሉሽ ወደ ጓሮ ከመዝለቃቸው ፊት “እማማ አንዳንዱዜ አንቺ እየጠራሽኝ እየመሰለኝ አሁንም ቅድምም ተምባትት…ሚያስፈልግሽን ታሁኑ ንገሪኝ” ምትይው ፍክ ይልሻል? “ላልመታዘዝ ነው መነ?” ስልሽ “ዋ! ምንሜናው ቢጠራኝስ…አንዳንድዜ እኮ የጠራችኝ መስሎኝ ጓሮ ሮጬ ስኸድ ʼአልጠራሁሽምʼ ትለኛለች፡፡ ስንት ቀን የማሪያም ብቅልን እየፈጨሁ ነው አልኩኝ” አልሽኝ፡፡ ተናፍቆቴ የተነሳ ጨዋታችን ፍክ እያለኝ ይሄንንም፣ ያንንም አልሁሽ እማየል? ይኼ አገር መችም እያስደመመኝ ይገኛል፡፡ ጨዋታችን ግን ታንችናኔ አይልፍ፡፡ አብባሌ እመዋን ተነገርሻት…በቃ አገር ተበላሸ!!! ከ20 ዐመት በላይ በአውራ ጣቴ ላይ ቆንጥጬ ይዣት የነበረች “ኦርጋኒክ፣ እጣ ፋንታያን” መንግዬ ጣልኳት፡፡ ፍክ ይልሽ እንደሁ እንጃ!! ከጉበን ዲሞ ስንጫዎት እሾህ ይሁን ስንጥር አውራጣቴ ላይ የገባው? እመ እንኳን በማበለቻ ጨርቅ ተኩሳ ደሜን አስቁማ ስንባጩን ነቅሳ ያወጣችልኝ? ግን ጨርሶ አልወጥቶም ኑሯል – አውራ ጣቴ ላይ የዳሞትን ተራራ መስሎ ከእኔ ጋር ስንት ዓመት ተጓዘ፡፡ እግዜርን የሚጠራ ሰውና አገር ምን ይሆናል፡፡ የእግዜር ሞት ታልሆነ ከሞት አፋፍ ፈልቅቀው የሚያወጡ የሰርቶ ማሳያዎች አገር – ኧሯዋ!!!! አውራጣቴን ፈትሸው ካዩ ኋላ… “ማይረባ ነው፣ ያለቦታው ነው የተቀመጠ፣ እግዜር ለሰው ልጅ ከሰጠው ሙሉ አካል ውጪ ትራፊ የሰው ስራ ነው” ሲሉኝ ይሁን ማለት!! በሌላ ቀጠሮ ሶስት ዶክተር፡፡ ከሃያ በላይ የህክምና ጓዶች ተሰባጥረው የ5ደቂቃ ቀዶ ጥገና አደረጉልኝ፡፡ እኔ ግን ወዴትኛው አለም ደርሼ እንደመጣሁ እንጃ፡፡ የእንግላል ከተኛሁበት ስነቃ… ከራስ ጸጉራቸው እስከ መላ አካላቸው…ሰማያዊ ለብሰው፣ ዙሪያዬን ቆመው ሳይ መላእክት ከበው እያጫወቱኝ ነው እንጂ ከአንዲት ኢትዬጵያዊት እግር ላይ ተቀብሮ የኖረ የባህር ዛፍ ይሁን፣ የአጋም እሾህ ስንባጭ ነቅሰው ያወጡ አልመስልሽ አለኝ፡፡ እንደ ጀብዱ “እንኳን ደስ አለሽ ..ቀዶ ጥገናሽ በተሳካ ተጠናቋል” እያሉ ፈገግታ ሰጡኝ፡፡ የድሮ የስምንተኛ ክፍል የአማርኛ መማሪያ መጽሐፍ ላይ ”ሽልንጌን” እንዳለችው ፍራፍሬ ሻጭ ጉብል እኔም..በፍጥነት “እሾሄን” እንደማለት…ቃጣኝ፡፡ “የወጣው ምንድን ነው አሳዩኝ” ማለት!! ሞሳ ሙዳይ ከመሰለች ብልቂያጥ ውስጥ የትንሽ ጣቴን አንጓ የምትመስል ነገር ናት፡፡ ከውስጡዋም ጫፏ ጠቆር ያለች እጅግ እንስ ያለች ስንጥር፣ እሾህ ምትመስል ወይንም ባለ አንድ ብር ወረቀት ላይ የተጋደመ ቀይ መስመር አለ አየል? እሷን ምትመስል ነገር ጋደም ብላልሻለች፡፡ “ምንድን ናት፣ ምንድን ናት” ብዬ መጮህ እንደለመድኩት በግምት “ይሄ ነው” እንዲሉኝ፡፡ ለሌላ ቀን ቀጠሮ ሰጥተውኝ ተሰነባበትን ከመለያየታችን ፊት.. የምክር መዓት አዥጎደጎዱልኝ፡፡ መስንበቻዬን የማጠልቀው ጫማ፣ ምርኩዝ፣ ለአደጋ ጊዜ ይሄን አድርጊ፣ እንመጣለን፣ እንደውላለን ብለው ሸካክፈውኝ ወደ ቤቴ ገባሁልሽ፡፡ ባልንጀሮቼ ሊፈቅዱኝ ሲመጡልሽ አያወናብዱኝ መሰለሽ፡፡ ተሆነ በላይ ምን ማረግ ነኝ ብዬ መጠጠቴን አንስቻለሁ፡፡ ”መላም አልሰራሽ አሉኝ፡፡ “ምነ?” ስላቸው አያቶችሽ “የአገሬን አፈር ባዕድ ይዞት አይሄድም” ብለው እግር ያሳጠባሉ፡፡ አንደኛውን አንቺ ይዘሽ መጥተሸ፣ ወስደሽ አስረከብሽ፡፡ አያቶችሽ እኮ መለኞች ናቸው – እጣ ፋንታሽን፣ አኬርሽን፡፡ …ከቅድመ፣ ከድህረ፣ ከቀዶ ጥገና በኋላ ባህሪሽን፣ አኳኋንሽ፣ መላ ሁኔታሽን እንዴት አገኘሽው፣ የተለወጠ ነገር የለም?” ሲሉኝ አስቆዘመኝ፡፡ አንዲቷ ባልንጀራዬ ያለችኝ ግን ዝም ብዬ የማልፈው ነገር ሁኖ አላገኘሁትም፡፡ “እንዴት ነሽ?” ብላ ብትለኝ፡፡ አኳኋኔን ነገርኋት፡፡ “በቃ አሜሪካ አለፈላት ኦርጋኒክ የኢትዬጵያ የዕፅዋት ተክል አገኘች፡፡ ያቆጠቆጠ የደረሰ፣ አፈር ማስ ማስ አድርገው መትከል ብቻ.. ተዚያ በዕውቅ ያሳጥሩታል፣ በቅርቡ የአሜሪካ አዲስ የዛፍ ግኝት ነው ብለው ይመዘገባል፡፡ ባለስልጣናቱም መግለጫ በመግለጫ ያደርጉናል፡፡ ፍቱን መድሃኒት ይሰሩና ኋላ ላይ እጅጃቸውን እናያለን፡፡ ከእጃችን የተቆረጠ መሆኑን ሳይነግሩን፡፡” አትልልሽም፡፡ “ከጎጃም እስከ አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ፣ አሜሪካ ድረስ ተጉዤ አምጥቼ ማስረከቤ ይታወቅልኝ” ስትይ ለሆስፒታሉ አቤት በይ፡፡ ግልባጭ ለዩናይትድ ስቴትስ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አስገቢ ብላኝ አረፈች፡፡ ባልንጀሮቼ ፈውሴን ከማወደስ ይልቅ አኳኋናቸው …ዋዘኞች አልመሰሉሽም? ለጊዜው መዝለል ይሳነኛል እንጂ እኔስ እንዴት ቡረቃ ላይ እንዳለሁ…. እልሻለሁ ጎኔ፡፡ ይሄ የምታይው ፎቶ የእንስሳት ሆስፒታል ነው – የውሻና የድመት፡፡ ታማሚው ውሻ(ድመት)የሰው ያህል ተከብረው በሆስፒታሉ ውስጥ ከባለቤቶቻቸው ጋር ወጣ ገባ ሲሉ ሳይ ኮስማናው፣ ጠውላጋው ጀርባውና ግንባሩ በዱላ የቆሳሰለው የአያ ቢሻው ጉበን ስር ተጋድሞ ሚውለው ውሻ ፍክ አለኝ፡፡ “አሁን ውሻና ድመት ቁም ነገር ነው?” አትበይንጂ የዚህ አገር ድመትና ውሻ ጉዳይ በቀጣይ ማወጋሽ ነኝ፡፡ በአለም ያገናኘን ጓዴ፡፡


Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

* Copy This Password *

* Type Or Paste Password Here *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar